የሮያሊቲ ምንነትና ለግብር አከፋፈሉ የወጣ ሕግ አረዳድና አሠራር አስፈላጊነት

ውብሸት ሙላት

የሮያሊቲ ክፍያ ታዳሽ ካልሆነ የተፈጥሮ ሀብቶች፣ ከደንና ግዘፋዊ ሀልዎት ከሌላቸው ንብረቶች የሚገኝ ገቢን ይይዛል፡፡ ማዕድን በማውጣት፣ ነዳጅና ጋዝ በማምረት፣ ደን በመትከልና የደኑን ውጤት በመሸጥ ለሚገኘው ገቢ የመሬቱ ባለቤት አምራቾቹን የሚያስከፍለው ገቢ የሮያሊቲ ክፍያ ይባላል፡፡ በኢትዮጵያ፣ መሬት የመንግሥት በመሆኑ ከአምራቾቹ ምን ያህል የሮያሊቲ ክፍያ ማግኘት እንዳለበት የመወሰን ሥልጣን አለው፡፡ ከፍተኛ የማዕድን ሥራዎች፣ ከጋዝና ፔትሮሊየም ምርት የሚገኝው ሮያሊቲውም ሆነ አምራቾቹ የሚያገኙት ገቢ ላይ የሚጣለው ግብር በፌደራሉ መንግሥት የሮያሊቲ መጠን ወሳኝነት፣ ግብር ጣይነትና ሰብሳቢነት የሚገኘውን ገቢ የፌደራልና የክልል መንግሥታት የፌደሬሽን ምክር ቤት በሚወሰነው ቀመር መሠረት ይከፋፈላሉ፡፡ ከፍተኛ ካልሆኑ የማዕድን ሥራዎች የሚገኘው ሮያሊቲና አምራቾቹ ገቢ ላይ ከሚጣለው ግብር የሚገኘው ገቢ ደግሞ የክልሎች ነው፡፡ ከደን የሚገኝ ሮያሊቲም ሆነ የገቢ ግብርም እንዲሁ የክልሎች ነው፡፡

ሌላው የሮያሊቲ ዓይነት ከአዕምሯዊና ከሌሎች ግዘፋዊ ሀልዎት በሌላቸው ንብረቶች አማካይነት ባለቤቱ ወይም መብቱ የተላለፈለት ወይም የመጠቀም ፈቃድ የተሰጠው ሰው የሚያገኘው ክፍያ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረትም ይኸው ነው፡፡ከማዕድን፣ ከፔትሮሊየምና ጋዝ፣ ከደን ጋር በተገናኘ የሚገኘውን ሮያሊቲ አይመለከትም፡፡ በመሆኑም ለሮያሊቲ የሚሰጠው ትርጓሜ፣ የሮያሊቲ ተጠቃሚዎች ወይም ባለቤቶች፣ ሮያሊቲ ላይ የሚጣል ግብር ወይም ታክስና የመሳሰሉት ጉዳዮችን ከዚህ በመቀጠል ሲገለጹ የሚመለከቱት አዕምሯዊ ንብረትና ግዙፍነት የሌላቸውን ንብረቶች ብቻ ነው፡፡

ለዚህ ጽሑፍ ገፊ ምክንያቶቹ ሦስት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ሙዚቃ ጋር በተያዘ የቅጅና ተዛማጅ መብት ያላቸው ሮያሊቲ ክፍያ የሚባለው ገቢ የቱ እንደሆነ የሚስተዋለው የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲሁም በተወሰነ መልኩ ጭራሹንም ይህ መብት የሌላቸው ነገር ግን እንዳላቸው የሚቆጥሩ በርካታ ሰዎችን በግል ግንኙነትና በሙያ አገልግሎት ያለኝ ትዝብት ነው፡፡ ሁለተኛው፣ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የግል ድርጅቶች ከቅጅና ተዛማጅ መብት ጋር በተያያዘ ክፍያዎችን ሲፈጽሙ እንደ ሮያሊቲ በመቁጠር ግብር ቆርጠው የሚያስቀሩበት ሁኔታ አንዳንዱ የሮያሊቲ ክፍያ ያልሆነን እንደሆነ በመውሰድ፣ በሌሎች ሁኔታዎች ደግሞ በትክክል ሮያሊቲ የሚገባቸውን እንደ ሌላ ዓይነት የገቢ ምንጭ በመቁጠር በሁለቱም ሁኔታ በተሳሳተ የግብር ምጣኔ መጠቀማቸው እንዲሁም ከሥዕል ጋር የተያያዙ የጥበብ ውጤቶች ላይ የሮያሊቲ ክፍያን ያገለለ መሆኑን መረጃዎች ስለሚያሳዩ ነው፡፡ ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ በሙዚቃው ዓለም ዙሪያ ያሉ ባለሙያዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‹‹የጋራ አስተዳዳር ማኅበር›› ለማቋቋም የተለያዩ ጥረቶች በማድረግ ላይ ስለሚገኙና በተቃራኒው ይህ እንቅስቃሴ የለመዱትን የኢኮኖሚ ጥቅም በተወሰነ መልኩ የሚያስቀርባቸው አካላት የሚያደርጉት የማደናቀፍ ተግባር መጉላቱ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ጽሑፍ የሮያሊቲ ክፍያ ምንነት፣ የሮያሊቲ ክፍያ የሚያስገኙ ሥራዎችና ንብረቶች የትኞቹ እንደሆኑ በተወሰነ መልኩ ደግሞ ያልሆኑትን ሊያመላክት የሚችል ዳሰሳ ያደርጋል፡፡ በሌላ አገላለጽ ክፍያቸው ሮያሊቲ ሊባል የሚችሉት ሰዎች ያሳያል፡፡ ቀጥሎም ከግብር ጋር በተያያዘ ግብር የመጣል ሥልጣንና የግብር አሰባሰቡን የሚመለከቱ የሕግና የአተገባበር ክፍተቶች ላይ ጥቆማዎች ይቀርባል፡፡  

የሮያሊቲ ምንነት

ስለሮያሊቲ በርካታ ብያኔዎች አሉ፡፡ ለብያኔዎቹ መለያየት ሁለት ምክንያቶችን ማንሳት ይችላል፡፡ የመጀመሪያው፣ ብያኔዎቹ ታሳቢ ያደረጉት የአዕምሯዊ ንብረት ዓይነት መለያየት ነው፡፡ ከፈጠራ መብት፣ ከቅጅ፣ ከንግድ ምልክት፣ ከኢንዱስትሪ ሚስጥር ወዘተ አንፃር እንደየዘርፉ ብያኔ መሰጠቱ ነው፡፡ ከፈጠራ መብት አንፃር የተሰጠ ትርጉም ከቅጅ መብት አኳያ ሲታይ የተለየ መሆኑ ነው፡፡ የአገራችን የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ የሰጠው ትርጉም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ፣ ብያኔዎቹ በዋናነት በሕግ የሚሰጡ መሆናቸው ነው፡፡ የሕግ ትርጓሜ ደግሞ አገሮች እንደሚከተሉት የሕግ ሥርዓት፣ ሕጉ ተፈጻሚ እንዲሆን እንደመረጠው ጉዳይ፣ እንደ ሕጉ ዓላማ የሚወሰን ስለሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ ፌዴራሉ የገቢ ግብር አዋጅ (ቁጥር 979/2008)፣ የቅጅና ተዛማጅ መብት ጥበቃ ማሻሻያ አዋጅ (ቁጥር 872/2009) ለሮያሊቲ የሰጧቸው ትርጓሜዎች መለያየት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የሁለቱ ሕጎች ዓላማ የተለያየ ስለሆነ (በእርግጥ የተጣጣሙ ቢሆኑ የተሻለ ነበር) ትርጓሜያቸው እንዲለያይ አድርጎታል፡፡

ይሁን እንጂ ሁሉም ብያኔዎች ቢያንስ ሁለት ነጥቦችን ይጋራሉ፡፡ የመጀመሪያው ሮያሊቲ ክፍያ መሆኑ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ፣ የክፍያው መሠረት የሆኑት ግዘፋዊ ሀልዎት የሌላቸው ንብረቶች (በዋናነት ለአዕምሯዊ ንብረት) መሆናቸው ነው፡፡ በመሆኑም ሮያሊቲ የአዕምሯዊ ንብረትን ለመጠቀም ሲባል ለባለንብረቱ የሚፈጸም ክፍያ ነው፡፡

የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ማሻሻያ አዋጅ ሮያሊቲም እንዲህ በማለት ብያኔ ሰጥቷል፡፡ ‹‹ከንግድ ሥራ ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ ለሚውል በዚህ አዋጅ መሠረት ጥበቃ ለሚያገኝ ሥራ በተጠቃሚው አማካይነት ለባለመብቱ የሚከፈል የአገልግሎት ክፍያ ነው፡፡›› ይህ ትርጉም ቢያንስ የሚከተሉትን ቁምነገሮች  ይዟል፡፡ የመጀመሪያው ሮያሊቲ የሚከፈልበት ሥራ በአዋጁ (ቁጥር 410/1996) ጥበቃ ያገኘ መሆን አለበት፡፡ በመሆኑም አዋጁ ጥበቃ ያደረገላቸውን ሥራዎች ለይቶ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ አዋጁ ጥበቃ ያደረገላቸው ደግሞ የሥነ ጥበብ (literary)፣ የኪነ ጥበብ (artistic) እና የሳይንስ ውጤቶች የሆኑ ናቸው፡፡ እነዚህም የሚታተሙ ሥራዎች (መጽሐፍ፣ የመጽሔት፣ የጋዜጣ መጣጥፍ ወዘተ)፣ በቃል የቀረበ ሥራ (ስብከት፣ ንግግር፣ ሌክቸር)፣ የሙዚቃ ሥራ፣ ድራማ፣ ውዝዋዜ፣ የኦዲዮ ቪዥዋል ውጤቶች፣ ኪነ ሕንፃ፣ የሥነ ጥበብ ሥራዎች (ሥዕል፣ ቅብ፣ ሀውልት፣ ቅርጽ፣ ሕትመት፣ ጥልፍ፣ የፊደል ቅርጽ)፣ ሥዕላዊ መግለጫ፣ ካርታ፣ ንድፍ (sketch)፣ ባለ ሦስት ገጽታ ሥራዎች (three dimensional works)፣ የኮምፒውተር ፕሮግራምና እነዚህን የመሳሰሉት ናቸው፡፡ አዋጁ የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን የሚመለከት ስለሆነ ሥራ ተብለው ጥበቃ የሚያደርግላቸው እንዲህ ዓይነቶቹን ነው፡፡ ስለሆነም፣ የፈጠራ ውጤት (patent)፣ ኢንዱስትሪያዊ ወይም የንግድ ወይም ሳይንሳዊ መሣሪያ ለመጠቀም የሚገኝ ፈቃድ፣ የንግድ ምልክት፣ ሚስጥራዊ የንግድ ቀመር በዚህ አዋጅ እንደ ሥራ የሚቆጠሩ አይደሉም፡፡ ጥበቃ የተሰጣቸው በሌሎች አዋጆች ነው፡፡

ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ ከላይ የተገለጹት ሮያሊቲ የሚያስከፍሉት ከንግድ ሥራ ጋር በተገናኘ ጥቅም ላይ ሲውሉ ነው፡፡ የንግድ ሥራ ምን እንደሆነ ደግሞ በንግድ ሕጉ ላይ የተሰጠውን ትርጓሜ መመልከት ይገባል፡፡ አንድ ሰው ሙያዬ ብሎ ትርፍ ለማግኘት የሚያከናውነው ተግባር ሆኖ ተግባራቱም ተገልጸዋል፡፡ ስለሆነም በሕጉ የንግድ ሥራ ላልሆነ ተግባር የቅጅና የተዛማጅ መብት ጥቅም ላይ በመዋሉ ክፍያ ቢፈጸም ሮያሊቲ አይደለም ማለት ነው፡፡ ክፍያ የሚፈጽሙት ተጠቃሚዎቹ ለንግድ አገልግሎት የሚያውሉት ወይም የተጠቀሙበት መሆን አለበት፡፡

ሦስተኛው ቁምነገር ደግሞ ክፍያ የሚፈጸምለት ሰው የሥራው ባለቤት ወይም የመጠቀም መብቱ በተለያዩ መንገዶች የተላለፉለት ሰው መሆን አለበት፡፡ ሥራዎቹ በነጋዴዎች በሚሸጡበት ጊዜ የሚፈጸሙ ክፍያዎችን አያካትትም፡፡ ሥዕል ወይም ቅርጻ ቅርጽን ብንወስድ ሠዓሊው ወይም ቀራጺው ሥራውን ለነጋዴ ከሸጠ በኋላ ነጋዴው በድጋሚ ሲሸጣቸው የሚገኘው ገቢ ሮያሊቲ አይባልም፡፡ ነጋዴው የሚያገኘው ገቢ ላይ የሚጣለው ግብርም የንግድ ግብር ነው፡፡ በተወሰኑ አገሮች ግን የሥነ ጥበብ ውጤቶች ድጋሚ ሲሸጡም የሚከፍሉት ግብር የሥራው ባለቤት እንደሚከፍለው የሮያሊቲ ታክስ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ትርጉም ጠባብም ግራ አጋቢም ነው፡፡ ጠባብነቱ በቅጅና ተዛማጅ ጥበቃ አዋጁ ላይ ዕውቅና የተሰጣቸው መብቶች ከንግድ ሥራ ጋር ለተያያዘ ነገር ጥቅም ላይ ሲውል ተጠቃሚው ለባለቤቱ የሚከፍለውን ክፍያ ብቻ የሚመለከት በመሆኑ ነው፡፡ ከንግድ ሥራ ጋር ያልተገናኘ ከሆነ የሚከፈለው ክፍያ ሮያሊቲ አይደለም ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ከዚህ ውጭ በሆኑ ግንኙነቶች የሚገኝ ክፍያ ሮያሊቲ ስላልሆነ ጠባብ ነው፡፡

ግራ አጋቢነቱ ደግሞ፣ የንግድ ሥራ ማለት ምን እንደሆነ፣ በምን ዓይነት የሚፈጸሙ ተግባራት ንግድ ሥራ እንደሚባሉ ግልጽ አይደለም፡፡ ይህንን ሁኔታ ለማስረዳት የሚከተሉትን ምሳሌዎች እንውሰድ፡፡ አንድ ዘፈን በብሮድካስት ሚዲያ ቢተላለፍና ብሮድካስተሩ ለቅጅ መብት ባለቤቶቹ የሚከፍለው ክፍያ፤ አንድ ሙዚቃ ድግስ (ኮንሰርት) ሲዘጋጅ  አዘጋጁ ለቅጅ መብት ባለቤቶቹ የሚከፍለው፤ አንድ ተውኔት ለብሔር፣ ብሔረሰቦች ቀን ለሚተላለፍ ዝግጅት በመጻፉ የሚከፈለው ሁሉም ከቅጅ መብት የሚመነጩ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ናቸው፡፡ ነገር ግን የመጀመሪያዎቹን ሁለቱን ከፋዮቹ የንግድ ሥራ ለማከናወን በማሰብ ስለሚከፍሉ ሮያሊቲ ይሆናል፡፡ በሦስተኛው ምሳሌ ደግሞ ከፋዩ መንግሥት በመሆኑና ዓላማውም ንግድ ስላልሆነ ሮያሊቲ አይደለም ማለት ነው፡፡

ግራ አጋቢነቱን የሚያባብሰው ሌላው ምክንያት፣ የገቢ ግብር አዋጁ ለሮያሊቲ ከላይ ከቀረበው በሰፋ ሁኔታ ትርጓሜ መስጠቱ ነው፡፡ በአዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ 979/2008 አንቀጽ 2(20) መሠረት ሮያሊቲ የሚያስገኙ ሥራዎች ለማንኛውም ጉዳይ ቢሆን ማለትም ለንግድም ሥራም ይሁን ሌላ ምንም ዓይነት ልዩነት ወይም ገደብ ሳያበጅ የሚገኘውን ገቢ በሙሉ ያካትታል፡፡ በቅጅና ተዛማጅ መብት ጥበቃ አዋጁ ግን ከንግድ ሥራ ጋር በተገናኘ የሚከፈል እንደሆነ አይተናል፡፡ በገቢ ግብር አዋጁ መሠረት ሮያሊቲ የሚያስገኙት ሥራዎችም ከላይ ካየነው በተወሰነ መልኩ የተጨመሩ አሉ፡፡ ለአብነት በብሮድካስት ሚዲያ የሚተላለፉ ሥርጭቶችን ለመጠቀም የሚያስችል መብት ለማገኘት ሲባል የሚፈጸመው ክፍያዎችን ይጨምራል፡፡ በቅጅና ተዛማጅ መብት አዋጁ ደግሞ ይህ ተዛማጅ መብት ነው፡፡ ከተዛማጅ መብት የሚገኝ ክፍያ ደግሞ ሮያሊቲ አይባልም፡፡ የብሮድካስቲንግ መብትን በመጠቀም የሚገኝ ክፍያ ሮያሊቲ ከሆነ በተመሳሳይ መልኩ ከዋኞች (ድምፃውያን፣ ተወዛዋዦች፣ ሙዚቀኞች፣ ተዋናዮች ወዘተ) እና ድምፅ በመቅረፅ የሚያሰናዱ (sound recording producer) የሚያገኙት ክፍያ ሮያሊቲ ሊሆን ይገባው ነበር፡፡ ተዛማጅ መብት ያላቸው ከዋኞች፣ ብሮድካስተሮችና ድምፅ በመቅረጽ የሚያሰናዱት ሆነው ሳለ ከሦስቱ ውስጥ አንድኛውን ብቻ በመምረጥ ልዩነት ማድረግ መብቱን ትርጉም አልባ ያደርገዋል፡፡ ተመሳሳይ መብት ተመሳሳይ ጥበቃና ተመሳሳይ ጠቀሜታ ሊያስገኙ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በዚሁ በገቢ ግብር አዋጁ ዘፋኞችን እንደ አዝናኝ ብቻ በመቁጠር ሰውን በማዝናናት ከሚያገኙት ገቢ መክፈል ያለባቸው የታክስ መጠን አሥር ከመቶ ነው፡፡ ድምፅ በመቅረፅ የሚያሰናዱት ደግሞ በተመለከተ የተገለጸ ነገር ስለሌለ ምንአልባት የንግድ ግብር መክፈል አለባቸው ማለት ነው፡፡

በአንዳንድ አገሮች ሮያሊቲ እንደ ነገሩ ሁኔታ እንደ ቢዝነስ ገቢ ወይም እንደ ግል ገቢ ሊቆጠር ይችላል፡፡ ይህን ሁኔታ ለማብራራት መጻፍን፣ መፍጠርን ሙያቸው በማድረግ ራሳቸውም ይህንኑ ተግባር እንደ ንግድ ከወሰዱት በንግድ ሕግ የሚተዳደር ቢዝነስ ስለሚሆን የሚገኘውም ገቢ የቢዝነስ ገቢ ይሆናል፡፡ እንደ ቢዝነስ ገቢ ለመውሰድ የተለያዩ መረጃዎችን በአግባቡ መመርመር ይገባል፡፡ ካልሆነ ደግሞ ቢዝነስ አይሆንም ማለት ነው፡፡ ሥራው የተፈጠረበት ሁኔታ ወሳኝነት አለው፡፡ የቢዝነስ ገቢ ለመሆንም ላለመሆንም፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነም የተለያዩ የትርጉም፣ የአርትኦት፣ እንዲሁም ጥናትና ምርምር ለማድረግ ፈቃድ አውጥቶ የሚሠራ ሰው የሆነን ግለሰብ የሕይወት ታሪክ ለመጻፍ ከግለሰቡ ጋር ወይም ከቤተሰቦቹ ቢዋዋልና ቢጽፍ ለጻፈበት የሚከፈለው ክፍያ የቢዝነስ ገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ሥራው ወይም ሙያው ፈቃድ አውጥቶ የሚያከናውነው አካል በመሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር አንድ መጽሐፍ ቢያሳትምና አሳታሚ ድርጅት ቢያሳትምለት፣ ፕሮፌሰሩ ከአሳታሚው የሚቀበለው ክፍያ እንደ ቢዝነስ ገቢ አይወሰድም፡፡ ፕሮፌሰሩ መጽሐፍ ለመጻፍ የንግድ ፍቃድ አውጥቶ ባለመሥራቱ ወይም እንደ ንግድ ቆጥሮ የሚሠራው ባለመሆኑ ነው፡፡ እንደ ቢዝነስ ሊቆጠር የሚገባው ሥራው በተፈጠረበት ወቅት የነበረው ሁኔታ እንጂ ኋላ ላይ የሥራው ባለቤት ነጋዴ በመሆኑ አይደለም፡፡ በመሆኑም በተለያዩ ጊዜያት ድጋሚ መጽሐፉ በመታተሙ ሮያሊቲ ቢከፈል እንኳን እንደ ቢዝነስ አይቆጠርም፡፡

በኢትዮጵያ ሁኔታም የፈጠራና የቅጅ መብቶች፣ የንግድ ምልክትና ስም፣ የንግድ ሚስጥር የአንድ ቢዝነስ አካላት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የንግድ ድርጅቶች (የሽርክና ማኀበሮችም ይሁኑ ኩባንያዎች) እነዚህ ከላይ የተገለጹት የንግድ ሀብታቸው አካል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ታዋቂ ሆቴል የንግድ ምልክቱንና አሠራሩን ጭምር በማከራየት ክፍያ ሊያገኝ ይችላል፡፡ እነ ሸራተን፣ ሒልተን፣ ማሪዮት ሆቴሎች እንደሚያደርጉት ማለት ነው፡፡ ከዚህ ኪራይ የሚገኘው ገቢ ሮያሊቲ ነው፡፡ አንድ የኮምፒውተር ፕሮግራም (ሶፍትዌር) የሚያሠራ ድርጅት የቅጅ መብቱን እንዲጠቀሙ በማድረግ የሚያገኘው ገቢም ሮያሊቲ ነው፡፡

ሮያሊቲ በተለያየ መልኩ ሊከፈል ይችላል፡፡ በጥቅል ሊከፈል ይችላል፤ ሥራው ሲሸጥ ከሚገኘው ገቢ ለመካፈልም ሊሆን ይችላል፤ ሁለቱንም ያጣመረም ሊሆን ይችላል፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት አንድ የሙዚቃ አሳታሚ ድርጅት አንድ የግጥምና የዜማ ደራሲ እንዲሁም አቀናባሪ ከሆነ ባለሙያ ጋር ለአንድ አልበም የሚሆን 12 ዘፈኖች እንዲሠራለት ቢዋዋልና ለዚህ ሥራው 200,000 ብር ቢከፍለው ወይም ደግሞ ከሚገኘው ገቢ 60 በመቶ እንደሚከፍለው ቢዋዋሉ ወይም 100,000 ብር እና ከሚገኘው ገቢ 25 በመቶ ሊከፍለው ቢስማሙ እንደማለት ነው፡፡ በሦስቱም ሁኔታ የሙዚቃ አሳታሚው የሚከፍለው ሮያሊቲ ነው፡፡ እዚህ ላይ አንድ ልብ ሊባል የሚገባ ቁምነገር አለ፡፡ ይኼውም አሳታሚው ከሥራ ፈጣሪው ጋር የሚያደርጉትን ውል የሚመለከት ነው፡፡ አሳታሚው አንድን ሰው  ግጥምና ዜማ እንዲደርስለት ቀብድ በመስጠት ቢያሠራውና ሥራው ሲጠናቀቅ ቀሪ ክፍያውን ቢከፍለው፤ እንደ ውሉ ሁኔታ ክፍያው ሮያሊቲ አልበለዚያም ደመወዝ ሊሆን ይችላል፡፡ ሮያሊቲ የሚሆነው የሥራው ባለቤት ጸሐፊው ሲሆን ነው፡፡ ውሉም ይህንኑ ሲገልጽ ነው፡፡ አሳታሚው ለደራሲው ድርሰቱን ሲያዘጋጅ ለሚያስፈልጉት ወጪዎች የከፈለው ሲጀመር ገና ስላልተሠራ፣ እንዲሁም እንደ ቅጥረኛ ከተወሰደ አሳታሚው የሚከፍለው ካሳ (ደመወዝ) የቅጅ መብቱ የአሳታሚው ሊያደርገው ይችላል፡፡ በመሆኑም ሮያሊቲው አሳታሚው የሚያገኘው ገቢ ይሆናል፡፡ ደራሲው የሚከፍለውም ግብር ሮያሊቲ ላይ ተመሥርቶ አይሆንም ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ ለአሳታሚዎችም፣ ለሥራ ፈጣሪዎችም ለግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤትም እንዲሁም ለሒሳብ ባለሙያዎችም ጭምር ነው፡፡ በተለይ የሥራ ፈጣሪውና አሳታሚው (እንደ ነገሩ ሁኔታ አሳታሚው ሙዚቃ ሲሆን ድምፃዊው ሊሆን  ይችላል) ከአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት በተጨማሪ ከግብር አንፃር የሚኖረውን አንድምታ ማየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ታክስ ኦዲተሮችና የሒሳብ ባለሙያዎችም የውሉን ይዘት አንብበው የታክስ ሁኔታውን መለየት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሕግም አንድ የተቀጠረ ወይም የአገልግሎት ክፍያ የተከፈለው ሰው ለሚሠራው ሥራ የቅጅ መብቱ በመርህ ደረጃ የቀጣሪው እንጂ የተቀጣሪው አይደለም፡፡ የተቀጠረው ሰው የቅጅ መብቱ ባለቤት ለመሆን ውል ያስፈልጋቸዋል፡፡ በውሉ የቅጅ መብት ባለቤትነቱ የተቀጠረው ሰው ነው እስካልተባለ ድረስ የቀጣሪው ነው፡፡ ሮያሊቲ ክፍያ የሚመለከተውም ቀጥሮ ያሠራውን ሰው ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ ከሙዚቃ፣ ፊልምና ቴአትር ጋር በተያያዘ የቅጅና ተዛማጅ መብት ጥበቃ የማያገኙትን ብሎም የሚያገኙት ክፍያ ሮያሊቲ የማይሆነውን በአጭሩ እንመልከት፡፡ በእነዚህ ሥራዎች ውስጥ በርካታ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ፡፡ በቪዲዮ የተዘጋጁ ሙዚቃዎች፣ ፊልምና ቴአትር ሁሉም ዳይሬክተር ያስፈልጋቸዋል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ደግሞ የምስልና  የድምፅ ኤዲተር፣ የካሜራ ባለሙያ፣ የአልባሳትና የውበት አጠባበቅ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ፡፡ በቴአትር ደግሞ የመድረክ አዘጋጆች፣ የመብራትና ድምፅ አሰናጂዎች ይኖራሉ፡፡ በእነዚህ ሥራዎች ውስጥ ኪነ ጥበባዊ ፈጠራ መኖሩ የማይካድ ነው፡፡

በየትኛውም ቴአትር፣ ፊልምም ይሁን በድምፅና ምስል የተዘጋጁ ዘፈኖች (ክሊፖች) ላይ የዳይሬክተሩ ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ ሁሉንም ቢሆን ለዕይታ ወይም ለመድረክ የሚያበቃቸው ዳይሬክተሩ ነው፡፡ ዳይሬክተሩ የራሱን ፈጠራ ይጨምርበታል፡፡ ቴአትርን እንደምሳሌ ብንወስድ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን የተረጎመውን የሼክስፒርን ኦቴሎ መራሔ ተውኔት አባተ መኩሪያና ሌላ አዘጋጅ በተመሳሳይ ሁኔታ  አያዘጋጁትም፡፡ ድርሰቱን አንብበው የተረዱበት፣ ገጸ ባሕርያቱን ወደ ተዋናይ የቀየሩበት፣ ተዋናዮቹን የሚቀርፁበት መንገድ ልዩነት ይኖረዋል፡፡ የልዩነቱ ምክንያት ደግሞ ዳይሬክተሩ ተውኔቱን የተረዳበት መንገድ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ የዳይሬክተሩ ፈጠራ ነው ማለት ይቻላል፡፡

የውበትና አልባሳት ባለሙያዎችንም ብንወሰድ በዚሁ በኦቴሎ ቴአትር ላይ ተዋናዮቹ ምን ዓይነት ልብስ መልበስ እንዳለባቸው፣ ፊታቸውና ፀጉራቸው ምን መምሰል እንዳለበት ባለሙያዎቹ (costume designers) የተለያየ ዓይነት አረዳድ ብሎም የአልበሳት ምርጫ የፊትና የፀጉር አሠራር ይመርጣሉ፡፡

የመድረክ ግንባታንም ብንወስድ እንዲሁ ነው፡፡ ኦቴሎ ሲታይ መድረኩን ሎሬት አፈወርቅ ተክሌና አሁን ደግሞ ሌላ ባለሙያ በተመሳሳይ አያዘጋጁትም፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ባለሙያዎች የራሳቸው የሆነ ኪነ ጥበባዊ ፈጠራ ቢኖራቸውም፣ በቅጅና ተዛማጅ ጥበቃ አዋጁ ሥራቸው እንደ ሥነ ጥበባዊ ወይም ኪነ ጥበባዊ ሥራ ጥበቃ አልተደረገለትም፡፡ የቅጅም ይሁን የተዛማጅ መብት የላቸውም፡፡ በመሆኑም የሚያገኙት ክፍያም ሮያሊቲ አይባልም ማለት ነው፡፡

ሮያሊቲና ግብር

ግዘፋዊ ሀልዎት በሌለው ንብረት ምክንያት የሚገኝ ገቢ ምንም እንኳን የተወሰኑ ልዩ ድንጋጌዎች ቢኖሩትም፣ በጥቅሉ ሲታይ በገቢ ግብር መርሆችና ድንጋጌዎች ተገዥ ነው፡፡ የግብር ሕግን እንዲሁም ከአዕምሯዊ ንብረት የሚገኝ ገቢን (ሮያሊቲን) የሚመለከቱ ዝርዝርና ልዩ ሕጎችን ማወቅ ለባለቤቱም ይሁን ለመንግሥት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ለባለቤቱ ወይም መብቱ ለተላለፈለት ሰው የግብር ግዴታውን አውቆና አክብሮ ግዴታውን በመወጣት ከተጠያቂነት ይታደግበታል፡፡ ለመንግሥት ደግሞ ሮያሊቲ ላይ የሚጣል ግብርን በተገቢው፣ ውጤታማና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ማስተዳደር እንዲችል ይረዳል፡፡ በመሆኑም አሁን መንግሥት እየተሠራበት ያለውን ቅጥአንባሩ የጠፋበት ከሮያሊቲ ላይ የሚገኝ ገቢ ላይ የሚጣል ግብር አስተዳደርን ትኩረት በመስጠት፣ በማስጠናትና ሥርዓት በማስያዝ መንግሥታዊ ግዴታውን መወጣት እንዳለበት ጥቆማም ነው፡፡

ግብር የመጣል ሥልጣን

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት ግብር የመጣል ሥልጣን የፌደራል፣የክልልና የጋራ የሁለቱም ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱ ሲፀድቅ ያልተካተቱ (ተረስተውም ይሁን አዲስ የግብር መሠረት ሆነው) ከሆነ የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ስብሰባ ለማን መሆን እንዳለበት ይወስናሉ፡፡ ይህ ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠው ክፍፍል ነው፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ ሕገ መንግሥቱን ስንበረብር ከአዕምሯዊ ንብረት የሚገኝ ገቢ ላይ ግብር የመጣል ሥልጣን የፌደራሉም ላይ አልተገለጸም፡፡ የክልል ሥልጣንም ነው አልተባለም፡፡ በጋራ ከሚገኘውና ከሚሰበሰበውም ውስጥ የለም፡፡ በመሆኑም ተለይቶ ያልተሰጠ ግብር ወይም ታክስ ነው ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የፌደራሉንና የክልሎችን የገቢ ግብር አዋጆች በየፊናቸው ሮያሊቲ ላይ ግብር የመጣል ሥልጣን እንዳላቸው በመውሰድ ሕግ አውጥተዋል፡፡

እርግጥ እነዚህ የገቢ ግብር አዋጆች ከወጡ በኋላ የፌደሬሽንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ሮያሊቲ ላይ ግብር የመጣል ሥልጣንን ሮያሊቲ ተከፋዮቹን መሠረት በማድረግ ለፌደራል ወይም ለክልል ሊሆን የሚችልበትን ሁኔታ  ወስነዋል፡፡ ሮያሊቲ የሚከፈለው (ግዘፋዊ ሀልዎት የሌለውን ንብረት ባለቤት የሆነው) ድርጅት ከሆነ ግብር የሚጥለው የፌደራሉ መንግሥት፣ ግለሰቦች ከሆኑ ደግሞ ለክልሎች ተሰጥቷል፡፡

አዲሱ የፌደራል ገቢ ግብር አዋጅ ሮያሊቲ የሚለውን የግብር ምጣኔ፣ የከፋዮቹን ማንነትና የመሳሰሉትን ሁኔታ እንደደነገገ ተመልከተናል፡፡ የምክር ቤቶቹ ውሳኔና የአሁኑ የግብር አዋጅም ከቀድሞው ባለመለየት ሮያሊቲ ተከፋዮቹ ማንም ይሁኑ ማን ልዩነት ሳያደርግ ለፌደራሉ መንግሥት ሰጥቷል፡፡

ሮያሊቲ ላይ የሚጣለው ግብር ከተገኘው ወይም ከሚገኘው አጠቃላይ ገቢ ላይ አምስት ከመቶ ነው፡፡ እንደሌላው የንግድ ግብር ለሥራው የወጣውን ወጭ ተቀናሽ በማድረግ ከሚገኘው የተጣራ ትርፍ ላይ የሚጣል አይደለም፡፡ የአዕምሯዊ ንብረቱን ለማግኘት የወጣ ክፍያ አይታሰብም፡፡ ከዚህ ከአምስት በመቶ ክፍያ ውጭ ሌላ ግብርም አይጣልም፡፡

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባ ቁምነገር አለ፡፡ ይኼውም የአዕምሯዊ ንብረት ቢሆኑም ባይሆኑም ማንኛውንም ግዘፋዊ ሀልዎት የሌላቸውን ሀብቶች በመግዛት ወይም በመከራየት የንግድ ሥራ ለማከናወን ነጋዴዎች የሚከፍሉት የሚመለከት ሳይሆን የመብቱን ባለቤቶች ብቻ ነው፡፡ ነጋዴዎች  ለንግድ ምልክት፣ ለፈጠራ መብት (ፓተንት)፣ ለቅጅ መብት ወዘተ ባለቤቶች ለከፈሉት ክፍያ (ሮያሊቲ) የንግድ ወጭ ሆኖ ይወሰድላቸዋል፡፡ የእርጅና ቅናሽም ይታሰብላቸዋል፡፡ በመሆኑም በገቢ ግብር አዋጁ ላይ የተገለጹት አዕምሯዊ ንብረትን የሚመለከቱ የእርጅና ቅናሾች ሮያሊቲ በመክፈል ንግድ የሚነግዱትን እንጂ ክፍያ ተቀባዮችን የሚመለከት አይደለም፡፡

ከግብር ጋር በተያያዘ መነሳት ያለበት ሌላው ነጥብ ደግሞ ሮያሊቲ ላይ የሚጣለው ግብር የሚሰበሰብበት ሁኔታ ነው፡፡ የሮያሊቲ ክፍያ ፈጻሚው የንግድም ይሁን ሌላ ዓይነት ድርጅት ታክሱን ቀንሶ በማስቀረት ለግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ገቢ ማድረግ አለበት፡፡ ክፍያውን የሚፈጽመው ማንኛውም ግለሰብ (ለምሳሌ አንድ ድምፃዊ ለዜማ ደራሲ፣ አንድ ሰው ከሠዓሊው ከራሱ ሥዕል ቢገዛ) ከሆነ ሮያሊቲው ላይ ሊጣል የሚገባው ግብር መክፈል የሚገባው ተከፋዩ ሊሆን እንደሚችል የገቢ ግብር አዋጁ አንቀጽ 93(3)(ለ) ላይ ተደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ ይኼን ማስፈጸም የሚቻልበት ስልት አልተዘረጋም፡፡ 

በአጠቃላይ ሮያሊቲን በሚመለከት ወጥ ሆነ አረዳድና አተገባበር እንዲኖር በተለያዩ ሕግጋት ላይ የተቀመጡት ትርጓሜዎችን መከለስ ተገቢ ነው፡፡ በተለይ የአዕምሯዊ ንብረት መሥሪያ ቤት (የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር) ለሮያሊቲም ይሁን ለክፍያው መነሻ የሚሆኑትን መብቶች ዝርዝር ደንብ ማውጣት ይጠበቅበታል፡፡ ትርጓሜውንም ማሻሻልም እንዲሁ፡፡ የገቢ ግብሩ ደግሞ በተወሰነ መልኩ የተዛማጅ መብት ተጠቃሚዎች ላይ የሚታየውን ክፍተት በማሻሻያ ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ ላይ ቢካተት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሁን ባለው አሠራር ግብር ቀንሰው ገቢ የሚያደርጉ በርካታ ተቋማት ደግሞ የክፍያው ዓይነት ሮያሊቲ ላልሆነው (ለምሳሌ ለዘፋኞች፣ ድምፃውያኖች፣ተዋናዮች፣ ዳይሬክተሮች ወዘተ) አምስት በመቶ ብቻ ግብር መቀነሳቸው፤ የተለያዩ የኮምፒውተር ፕሮግራም (ለምሳሌ ድረ ገጽና ሌሎች ሶፍትዌሮች) በመሥራታቸው የሚያገኙት ክፍያ ሮያሊቲ በመሆኑ ሌላ ግብር ሊከፍሉ ስለማይገባ እንዲህ ዓይነት አሠራሮችን ማስተካከል የሚቻልበት ሥልጠናና ማብራሪያ ማዘጋጀት ይገባል፡፡ የኪነ ጥበብ ውጤቶች በተለያዩ ዓውደ ርዕዮችና በሌላም መንገድ ሲሸጡም ሆነ ሲስሉ ለሚከፈላቸው ክፍያ አሁን በተለያዩ ቦታዎች እንደሚደረገው ተርን ኦቨር ታክስ ሳይሆን እንደሌሎቹ አምስት በመቶ ብቻ የሚከፍሉበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡