የሳምንቱ ገጠመኝ

አንድ በጣም የምንወደው ጓደኛችን ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ውጭ አገር ለመሄድ በዝግጅት ላይ እያለ የገጠመን ጉዳይ ይህንን ገጠመኝ ለመጻፍ ተጨማሪ ምክንያት ሆኖኛል፡፡ ጓደኛችን በነሐሴ ወር 2008 ዓ.ም. ማብቂያ ሰሞን ለውጭ ጉዞ ሲሰናዳ፣ እኛ ጓደኞቹ ደግሞ ለእሱ መሸኛ እየተዘገጃጀን ነበርን፡፡ የመሸኛ ግብዣው ቅዳሜ ቀን እንዲሆን ተስማምተን ግብዣውን ለማሳመር እላይ ታች ስንል አንዲት ጓደኛችን ስልክ ደወለችልኝ፡፡ ‹‹እኛ ድግሱን ለማሳካት ፋታ አጥተናል እሱ (ጓደኛችን) ገርል ፍሬንዱን ይዞ ዱባይ ሄዶልሃል…›› ብላ ስልኩን ዘጋችው፡፡

ይህች ጓደኛችን በጣም ችኩል፣ ማመዛዘን የተሳናትና መረጃ የሌለው ወሬ ማግለብለብ ስለምትወድ ለማንኛውም ብዬ ሌላው ጓደኛችን ዘንድ ደወልኩ፡፡ ያቺ ችኩል የነገረችኝን ቃል በቃል ምንም ሳላስቀር ስነግረው ከት ብሎ ሳቀ፡፡ ‹‹ምን ሆነሃል?›› ስለው፣ ‹‹የእሷን ነገር እያወቅከው? እሱ እኮ አጠገቤ ነው ያለው፤›› ሲለኝ፣ ‹‹ቶሎ አገናኘኝ፤›› አልኩት፡፡ ጓደኛችን በጣም በተረጋጋ ድምፅ፣ ‹‹አይዞህ አለሁ፡፡ እንኳን ዱባይ ቃሊቲም አልሄደኩም፤›› አለኝ፡፡ ይህች ሴት ከየት አምጥታ ነው የምታወራው ብዬ በስጨት ስል፣ ‹‹ጓደኞቿ ምን ታወራ ይሆን ብለው የነገሯትን ነው አገሩን እያዳረሰችው ያለችው፤›› ብሎ ሲስቅ እኔ ግን ተናደድኩ፡፡

ውዱ ጓደኛችንን በሚገባ ደግሰንና ሸልመን ከሸኘነው ከቀናት በኋላ ያቺን ወሬኛ ጓደኛችንን ስልክ ደውዬላት ለምሣ ቀጠርኳት፡፡ እሷም አላሳፈረችኝም የምሣ ግብዣዬን ተቀብላ መጣች፡፡ ምሣችንን በልተን ቡናችንን ፉት እያልን ሳለ፣ ‹‹ለምንድነው ያልተጣራ ወሬ የምታወሪው? ያኔ እኮ በጣም አናደሽኝ ነበር፡፡ ሁልጊዜ ያልተጣራ ወሬ ሲነሳ ያንቺ ስም ጎልቶ ይወሳል፡፡ ይኼ እኮ ለሕይወትሽ ጥሩ አይደለም፡፡ ጋብቻ ለመመሥረትም አዳጋች ይሆንብሻል፡፡ አንቺን የመሰለች ቆንጆ ሴት በፍፁም ስምሽ በዚህ ሊነሳ አይገባም…›› እያልኩ ምክር ቢጤ አቀረብኩላት፡፡ እሷም እንደመተከዝ ብላ፣ ‹‹የእኔን ደካማ ጎን እየተጠቀሙ ላልተገባ ነገር የሚያጋልጡኝ የገዛ ጓደኞቼ ናቸው፤›› ብላ ስቅስቅ ብላ አለቀሰች፡፡ በጣም አሳዘነችኝ፡፡

የዚያን ቀን ብዙ መክሬያት ካባበልኳት በኋላ በሰላም ተለያየን፡፡ ለወራት በደግም በክፉም ተገናኝተን አናውቅም፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የአንድ ወዳጄ የሆቴል ምርቃት ላይ ለመታደም እሄዳለሁ፡፡ አዲሱን ውብ ሆቴል ለመመረቅ ከተገኙ በርካታ ሰዎች መካከል ያቺ ሴት አንዷ ነበረች፡፡ የማውቃቸው ሰዎች መሀል ገብቼ እየበላንና እየጠጣን ሳለ ያቺ ጉደኛ፣ ‹‹አንዴ እፈልግሃለሁ፤›› ብላኝ ስትጠራኝ ተነስቼ ወደሷ አመራሁ፡፡ እንደነገሩ ሰላምታ ካቀረበችልኝ በኋላ፣ ‹‹ባለፈው ጊዜ ዝም ብዬ ሰማሁህ እንጂ በጣም ተቀይሜሃለሁ፡፡ እኔን እንዴት ወሬኛ ትለኛለህ?›› ብላ ቱግ አለችብኝ፡፡ በፍፁም ያልጠበቅኩት ስለነበር በጣም ደነገጥኩ፡፡ ‹‹ከወራት በኋላ እንዲህ እንድትናገሪ ያደረገሽ ምንድነው?›› ስላት፣ ‹‹በኋላ ያንተን ጉዳይ ሳጣራ እንደሰማሁት አንተ የእኔ ጠላት ነህ፤›› ብላ አረፈችው፡፡ ይህችን ዝም ከማለት ሌላ ምን ይባላል? የቆመችበት ትቻት ሄድኩኝ፡፡

በሁለተኛው ቀን ስልኬ ሲጮህ ከኪሴ ሳወጣው ይህቺው ጉደኛ ናት፡፡ ‹‹ምን ነበረ?›› ስላት፣ ‹‹ይቅርታ ለጥፋቴ፡፡ በስህተት ነው የዚያን ቀን ያልሆነ ነገር የተናገርኩህ፡፡ ጠላቴ አንተ ሳትሆን … (የሰው ስም ጠራች) ነው፡፡ ለተፈጠረው ሁሉ ይቅርታ እጠይቃለሁ…›› እያለች ሳለ፣ ‹‹አሁን ደግሞ ማን ነግሮሽ ነው?›› በማለት ጥያቄ እንደ ዘበት ጣል አደረግኩባት፡፡ ለእኔም ሆነ ለሰሚ ግራ የሚያጋባ መልስ ሰጠችኝ፡፡ ‹‹ማንም ሳይሆን የነገረኝ ራዕይ አይቼ ነው …›› እያለች ስትቀበጣጥር እንደ ዕብድ ከጣራ በላይ እየጮህኩ ሳቄን መቆጣጠር አቃተኝ፡፡ ለምን ያህል ደቂቃዎች እንደዚህ እንደሆንኩ ባላውቅም ወደ አቅሌ ስመለስ አንድ ነገር ገባኝ፡፡ ወሬ፣ ሐሜት፣ አሉባልታ፣ ወዘተ የሚወዱ ሰዎች የአዕምሮ ችግር ሳይኖርባቸው አይቀርም፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች ሲያጋጥሙን ቢቻል አማኑኤል ሆስፒታል ካልሆነም ፀበል እንዲሄዱ ብንረዳቸው ተገቢ መሰለኝ፡፡

(አዲሱ ፋንታሁን፣ ከሪቼ)