የሳምንቱ ገጠመኝ

በዚህች ምድር ላይ ለማንም የማይቀር ነገር ቢኖር የሞት ፅዋ ነው፡፡ በጉስቁልናም ይሁን በቅንጦት፣ በክፋትም ይሁን በደግነት፣ በፈሪነትም ይሁን በጀግንነት፣ በውሸታምነትም ይሁን በሀቀኝነት፣ ወዘተ. ውስጥ የማታ ማታ ሞት አይቀሬ ነው፡፡ ሞት ሁሉንም በእኩልነት የሚያስተናግድ የእስትንፋስ መጨረሻ ሲሆን፣ የአመጣጡ ዓይነት ግን ይለያያል፡፡ አንዳንዱን በበሽታ አሰቃይቶና አማቆ ሲወስደው፣ ሌላውን ደግሞ ኮሽ ሳይል መጥቶ ይዞት ይነጉዳል፡፡ በጦር ሜዳም ሆነ በሰላማዊ ሥፍራ ሞት አለ፡፡ ቀን ያዩት ምሽት ላይ ይሰናበታል፡፡ በአጠቃላይ ‹‹ሞት አደላዳዩ›› መምጫው አይታወቅም፡፡ ለማንም አይቀርም፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ‹‹ቀብሬን አሳምረው›› ከማለት ‹‹አሟሟቴን አሳምረው›› ማለት ይሻላል፡፡

ይህንን ገጠመኝ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ስለሞት ትንተና ለመስጠት አይደለም፡፡ ነገር ግን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ታላቁ የነፃነት አርበኛ ፊደል ካስትሮ ጉዳይ ነው፡፡ በዘጠና ዓመታቸው በሞት የተለዩንን ካስትሮ የአሜሪካና ሌሎች የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች በሚያስተጋቡት የተንሸዋረረ ዘገባ ሳይሆን፣ ራሳቸውን ከቅኝ ገዥ ምዕራባውያን ጭቆና ለማላቀቅ ከታገሉ የታዳጊ አገሮች ሕዝቦችና በተለይ ደግሞ ከአስከፊውና ከወራዳው የአፓርታይድ ሥርዓት አገዛዝ ለመላቀቅ ከታገሉት ደቡብ አፍሪካውያን ወገኖቻችን ምልከታ አንፃር ነው የምናስባቸው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ተስፋፊው የሶማሊያ መንግሥት ኦጋዴንን ጨምሮ እስከ ናዝሬት (አዳማ) ድረስ መሬታችንን ለመቀማት ወረራ በፈጸመ ጊዜ እኚህ የተባረኩ ሰው ያደረጉልንን ድጋፍ መቼም ቢሆን አንረሳውም፡፡

በ1969 ዓ.ም. የሶማሊያ መደበኛ ሠራዊትና ሰርጎ ገብ ኃይል በምድር መጠናቸው ከፍተኛ በሆኑ ዘመናዊ መሣሪያዎች ማለትም መድፎች፣ ታንኮችና የተለያዩ ተተኳሾች፣ ከአየር በዘመናዊ ሚግ የጦር ጄቶችና ሔሊኮፕተሮች በመታገዝ በምሥራቅ 700 ኪሎ ሜትር፣ በደቡብ 300 ኪሎ ሜትር አገራችን ውስጥ ጠልቆ ገብቶ ነበር፡፡ በወቅቱ ዜጎቻችንን እየጨፈጨፈ ወረራ የፈጸመው ኃይል ለአገሪቱ ህልውና አደጋ በመሆኑ፣ አገሪቱ በንጉሡ ዘመን ለአሜሪካ በከፈለችው ገንዘብ የተገዛ መሣሪያ እንዲላክ ሲጠየቅ በጂሚ ካርተር ይመራ የነበረው የአሜሪካ መንግሥት አሻፈረኝ ይላል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የሶማሊያ ወራሪ ሠራዊት ሐረርና ድሬዳዋን ለመያዝ ተቃርቧል፡፡ ጅጅጋን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል፡፡ ከጣሊያን ወረራ በኋላ እጅግ በጣም አደገኛ የህልውና ሥጋት የገጠማት ኢትዮጵያ፣ የዕርዳታ እጅ የተዘረጋላት ከኩባ ነበር፡፡ ዕድሜ ለፊደል ካስትሮ 15 ሺሕ ወታደሮቻቸውንና የሕክምና ባለሙያዎችን በመላክ፣ ወረራውን ከመመከት ታልፎ በወራሪው ኃይል ላይ ፍፁም የሆነ ድል ለመቀዳጀት አስችለውናል፡፡ መቼም ቢሆን ታሪክ ፈጽሞ የማይዘነጋው የሁለቱ አገሮች ትስስር ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቀጠለ፡፡

ኩባን ስናስብ ፊደልን፣ ፊደልን ስናስብ ኩባን በፍፁም መለየት የማንችለው ለዚህ ነው፡፡ የምዕራባውያኑ ሐሰተኛ ሚዲያዎች ፊደል ካስትሮ በሕልፈት ከተለዩ ጀምሮ ሊነግሩን የሚሞክሩት በሙሉ ውሸት ነው፡፡ አፍሪካውያን በተለይ ኢትዮጵያ፣ አንጎላ፣ አልጄሪያ፣ ሞዛምቢክ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ወዘተ. ለፊደል ትልቅ አክብሮት አላቸው፡፡ የላቲን አሜሪካ አገሮች በሙሉ ፊደልን እንደ አባት ነው የሚያዩዋቸው፡፡ ዝነኛው የእግር ኳስ ጠቢብ አርጀንቲናዊው ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና፣ ‹‹ሁለተኛው አባቴን ነው ያጣሁት፤›› ብሏል፡፡ በአውሮፓና በአሜሪካ ከቀኝ ክንፍ ተስፈንጣሪዎችና ከእነሱ አራጋቢ ሚዲያዎች በስተቀር በጣም ሚዛናዊና የሐዘን ድባብ ያላቸው ድምፆች ነው የተሰሙት፡፡ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ ‹‹ፊደል ካስትሮ የሚዳኙት በታሪክ እንጂ በእኛ አይደለም፤›› ሲሉ፣ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዲኦ፣ ‹‹ፊደል ካስትሮ የተለዩ መሪ ነበሩ፤›› ብለዋል፡፡ የምዕራቡ ሚዲያ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ገለጻ ለማጣጣል ቢሞክርም፣ እሳቸው ግን በቃላቸው ፀንተዋል፡፡

የሃያኛውን ክፍለ ዘመን የዓለም ገጽታ ከቀየሩ በጣም ጥቂት ሰዎች ተርታ በግንባር ቀደምነት የሚሠለፉት ፊደል፣ በአገራቸው ማኅበራዊ ፍትሕ በማንገሥ ይታወቃሉ፡፡ ማንም ኩባዊ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ዩኒቨርሲቲ እስኪያጠናቅቅ ድረስ ያለምንም ሐሳብ በነፃ ይማራል፡፡ የጤና አገልግሎት በነፃ ነው፡፡ የሠርቶ አደሩን መደብ በመፍጠር በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ፈጥረዋል፡፡ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ በመጣሉ እንጂ፣ ኩባ ዛሬ በዓለም ላይ ብቸኛዋ በፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ባለፀጋዎች የተፈጠሩባት አገር ትሆን ነበር፡፡ ጥቁር፣ ጠይምና ነጭ ኩባውያን ያለምንም ዓይነት መድልኦ በእኩልነት የሚኖሩባት አገር ኩባ ናት፡፡ ዕድሜ ለካስትሮና ለትግል ጓዶቻቸው፡፡ በምሥራቅ አውሮፓ የተልከሰከሰው የሶሻሊዝም ሥርዓት በተግባር የታየው በኩባ ነው፡፡ የአሜሪካን ጡንቻ የተቋቋመ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ልጆችን በሰብዓዊ ፍጡርነታቸው ብቻ የሚያስተናግድ ሥርዓት ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን ሥርዓት በዓለም ላይ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ሻምፒዮን ነኝ የምትለው አሜሪካ አላሳየችንም፡፡ ጥቁሮች በነጭ ፖሊሶች እንደ አውሬ የሚገደሉባት አሜሪካ ሚዲያዎች ግን ይዋሻሉ፡፡

ይህንና ሌሎች መሰል ጉዳዮችን ከቢጤዎቼ ጋር ስንነጋገር የሁላችንም መንፈስ ተቀራራቢ ነበር፡፡ በተለይ የአሜሪካና የሌሎች ምዕራባውያን አገሮች ሚዲያዎች ዘገባዎች ላይ ተግባብተናል፡፡ እነሱ ሊግቱን የፈለጉት የምናውቀውን ጥሬ ሀቅ በማዛባት ሲሆን፣ እኛ ደግሞ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ፈጽሞ እንደማንወናበድ ነው፡፡ ፊደልና ኩባ ለኢትዮጵያ አገራችን የዋሉትን ውለታ በእነዚህ አስመሳዮችና አታላዮች እንኳን ልንዘነጋው፣ መቼም መቼም ቢሆን ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተቀባበለ ይኖራል፡፡ ሌሎች አፍሪካውያን ወንሞቻችንና እህቶቻችንም አይዘነጉትም፡፡ እኛ ግን በጦርነት ከከፈሉልን መስዋዕትነት በተጨማሪ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ልጆቻችንን በሕክምና፣ በምሕንድስና፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ ወዘተ. በነፃ አስተምረው ለወግ ለማዕረግ ስላበቁልን ዝንተ ዓለም እናመሰግናቸዋለን፡፡ ቪቫ ካስትሮ! ቪቫ ኩባ! እንላለን፡፡ ‹‹ሞት አይቀርም ስም አይቀበርም›› በማለት ጀግናችንን እንሰናበታለን፡፡

(ማስተዋል አድማሱ፣ ከጃንሜዳ)