የሳምንቱ ገጠመኝ

በቅርቡ አሉባልታን በተመለከተ አንድ ጥቅስ ማንበቤ ትዝ ይለኛል፡፡ ጥቅሱ፣ ‹‹አሉባልታ በጥላቻ በተሞሉ ሴረኞች ይፈጠራል፣ በጅሎች ይሠራጫል፣ ደደቦች ደግሞ እየተቀባበሉ የራሳቸው ያደርጉታል፤›› ይላል፡፡ ይህ በአውሮፓውያን ዘንድ በሚገባ የሚታወቅ ጥቅስ ነው፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋልና ይህንን ገጠመኝ ለመጻፍ የበለጠ ምክንያት የሆነኝ ሰሞኑን ያነበብኩት አንድ አስገራሚ ጽሑፍ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 6 ቀን 2017 ፕሮጀክት ሲንድኬት በተባለ ታዋቂ ድረ ገጽ ላይ የወጣ ጽሑፍ ርዕሱ “Free Speech and Fake News” ይላል፡፡ ይህ ፒተር ሲንገር በተባሉ የፕሪንስተንና የሜልቦርን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የተጻፈ ጽሑፍ የዘመናችንን አስፈሪነት በሚገርሙ ማስረጃዎች ይተርክልናል፡፡ በንግግር ነፃነት ስም እየተፈበረኩ የሚወጡ ሐሰተኛ ዜናዎች (አሉባልታዎች) የወደፊቱን ዓለም ምን ያህል ሊያተራምሱት እንደሚችሉ ይተነትናል፡፡ እኔ ደግሞ ከራሴ በርካታ ገጠመኞች አንፃር ይህንን አስገራሚ ጽሑፍ ሁለቴ ተወጣሁት፡፡

ፕሮፌሰር ሲንገር ባለፈው ኅዳር ወር የተካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መቃረቢያ ላይ የወጣ አንድ ሐሰተኛ ዜና፣ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ተወዳዳሪ የነበሩትን ሒላሪ ክሊንተንን በሕፃናት ላይ አስገድዶ መድፈርና የመብት ጥሰት የሚፈጽም አንድ ቡድን አለቃ አድርጓቸዋል ይላሉ፡፡ ይህ አሉባልታ በአጭር ጊዜ በማኅበራዊ ሚዲያዎችና የቀኝ ክንፍ የቶክ ሾው ፕሮግራም አዘጋጅ በሆነ ግለሰብ አማካይነት በፍጥነት ተዛመተ፡፡ በአሉባልታው መሠረት ሕፃናት በሒላሪ ክሊንተን ይገደላሉ፣ አካላቸው ይቆራረጣል፣ ይደፈራሉ፣ ወዘተ ተብሎ በቪዲዮ ተቀነባብሮ በማኅበራዊ ሚዲያ በመሠራጨቱ ከ400 ሺሕ ጊዜ በላይ ታይቷል፡፡ በዚህ ሐሰተኛ ዜና የተነሳ የብዙዎች አዕምሮ መናወጡን ጸሐፊው አትተዋል፡፡ ምንም እንኳ በምርጫ ውጤቱ ላይ የፈጠረውን ተፅዕኖ በተመለከተ የተናገሩት ባይኖርም፣ አሉባልታው ግን ግዳጁን በሚገባ በመወጣት ለዶናልድ ትራምፕ መመረጥ አመቺ ሁኔታ አልፈጠረም ማለት አይቻልም፡፡

በማኅበራዊ ድረ ገጾች ኃላፊነት በማይሰማቸው ሰዎች አማካይነት አሉባልታዎች ሲሠራጩ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት ፈፅሞ ገደብ እንዲጣልበት የማልፈልግ ቢሆንም፣ ይህንን እጅግ በጣም መሠረታዊ የሆነ የሰው ልጆች መብት የሚጋፋ አሉባልታ ማሠራጫ ሲሆን ግን ያበሳጨኛል፡፡ ጸሐፊው እንዳሉት፣ ሐሰተኛ ዜናዎች በስፋት እየተሠራጩ ሃይ የሚል የሚጠፋ ከሆነ በተለይ ኑክሌር በታጠቁ አገሮች መካከል አደጋ ይፈጠራል፡፡ መተማመንን እየሸረሸረ ለአላስፈላጊ ፍጥጫና ግጭት ይዳርጋል፡፡ ይህም ክቡር የሆነውን የሰው ልጆች ሕይወት ለአደጋ ያጋልጣል፡፡ በሐሰተኛ ዜና ምክንያት የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር በፓኪስታን ላይ የኑክሌር ማስፈራሪያ ማድረጋቸው ሲወራ፣ የፓኪስታን አቻቸው በትዊተር ገጻቸው ፓኪስታንም የኑክሌር ባለቤት መሆኗ መረሳት የለበትም ማለታቸው በፒተር ሲንገር ጽሑፍ ውስጥ ተገልጿል፡፡ ይህ ተለጥጦ ሰሜን ኮሪያን ከአሜሪካ ጋር ቢያፋጥጥ ምን ሊፈጠር ይችላል? አለመተማመን ከመቼውም ጊዜ በላይ በተንሠራፋበት በዚህ ዘመን ሐሰተኛ ዜናዎች በረቀቀ መንገድ ሲሠራጩ አገሮች ወደ ጦርነት ውስጥ አይገቡም ማለት የዋህነት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የውሸት ቪዲዮዎች በብዛት እየተሠራጩ የዋሆችን ሲያስለቅሱ፣ ለአመፅ ሲያነሳሱና የከፋ ጉዳት ሲያደርሱ በስፋት ይታያል፡፡

ይህንን እዚህ ላይ ገታ ላድርገውና ከራሴ ገጠመኝ አንዳንድ ነገሮችን ለማቅረብ ይፈቀድልኝ፡፡ የዛሬ አንድ ወር ገደማ ቢሮአችን ውስጥ በሥራ ምክንያት በጓደኞች መካከል አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ ይህንን አጋጣሚ ለመጠቀም የፈለገች አንዲት ወሬኛ ባልደረባችን የሥራ ጭቅጭቃችንን የጥቅም ግጭት አስመስላ ማስወራት ጀመረች፡፡ ሌሎች የሥራ ባልደረቦቻችን በየተራ ሲያናግሩን በሥራ የተጋጨነው ጓደኛሞች አንድ ዓይነት ነገር ነው የምንነጋገረው፡፡ እነሱ ግን ከዚህ የዘለለ የጥቅም ግጭት ውስጣችን ተፈጥሮ የደበቅነው እየመሰላቸው ዙሪያ ዙሪያውን ቢሞክሩም በመልሳችን የሥራ ፀብ ብቻ መሆኑ ይነገራቸዋል፡፡ የተቻላቸውን ያህል ጥረት ቢያደርጉም በዚያች ወሬኛ ከተነገረው ጋር የሚገጥም ነገር ያጣሉ፡፡ ሦስታችንንም አንድ ላይ አገናኝተው ካስማሙን በኋላ በወሬኛዋ የተነሳ ያባከኑትን ጊዜ እያሰቡ ተበሳጩ፡፡ አንዱ ግን ይህ ትምህርት ሊሆን እንደሚገባ ተናግሮ ወሬኛዋን ስም አወጣላት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ‹‹ካሊካ›› ትባላለች፡፡ የወሬኛዋ የዳቦ ስም ሆኖ ቀረ፡፡ ወሬን እንደወረደ ሳያጣሩ ሲሰሙት ልጅና ወላጅንም ያጋድላል፡፡

አንድ ጊዜ ልደታ ፍርድ ቤት ለጉዳይ ሄጄ የሌሎች ሰዎች ጉዳይ በችሎት እየታየ ነው፡፡ በዕለቱ የከሳሽ ምስክሮች እየተደመጡ ነው፡፡ የተጠሩት ሦስት ምስክሮች ተራ በተራ እየቀረቡ ሲመሰክሩ የሦስቱም ምስክርነት የተለያየ ነው፡፡ ተከሳሽ በከሳሽ ላይ ድብደባ ፈጽሞ የአካል ጉዳት አድርሷል ተብሎ ክስ በተመሠረተበት ጉዳይ ሦስቱም ምስክሮች ድብደባውን የገለጹበት አተያይ በጣም ይገርማል፡፡ አንዱ የያዘው ዱላ እጁ ላይ እስኪሰባበር ድረስ ጉዳት አደረሰበት ሲል፣ ሌላው በድንጋይና በጩቤ ነው ይላል፡፡ ሦስተኛዋ ምስክር በብረት ዘንግ እንዳይሆን አድርጎ ሰባበረው ትላለች፡፡ ዓቃቤ ሕግና ጠበቃ እየተገለማመጡ ማስታወሻቸውን ሲይዙና መስቀለኛ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ የሐሰት ምስክርነቱ እጅግ በጣም ያሳፍር ነበር፡፡ ከችሎቱ ስንወጣ አንድ ትልቅ ሰው የተናገሩት አይረሳኝም፡፡ ‹‹ምናለበት ተቀራራቢ ውሸት ነግረዋቸው እሱኑ ቢዘባርቁት፤›› ነበር ያሉት፡፡ ያም ሆነ ይህ ችሎቱ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ዓይን ግን ከትዝብትም በላይ ነበር፡፡ ነግ በኔ ነዋ፡፡

የአሉባልታን ጉዳይ ከማጠቃለሌ በፊት አንድ ልጨምርና እንለያይ፡፡ የምኖርበት አካባቢ የድሮ መንደር በመሆኑ ወሬ ሳንፈልግ ይመጣል፡፡ አንድ ቀን አንዱ የውጭውን በር በጣም ያንኳኳል፡፡ ልጆች ስላልነበሩ ምን መጣ ብዬ በፍጥነት ሄጄ እከፍታለሁ፡፡ በሠፈራችን የታወቀ አውደልዳይ ነው፡፡ ‹‹ምን ሆነህ ነው እንዲህ በሩን የምትደበድበው?›› ስለው፣ አንድ አስገራሚ ወሬ ሰምቶ መምጣቱን ይነግረኛል፡፡ ምን እንደሆነ ስጠይቀው፣ በሠፈራችን ታዋቂ የሆኑ ትልቅ ሰው ልጅ መጠጥ ቤት ውስጥ የአንዱን አራት ጥርሶች አውልቆ መታሰሩንና ሄጄ እንዳዋያቸው ሊነግረኝ መምጣቱን ካሳወቀኝ በኋላ ይሄዳል፡፡ ከቆይታ በኋላ ወደ አዛውንቱ ቤት ስሄድ ከወትሮ የተለየ ምንም ነገር የለም፡፡ ቆይ እስቲ ብዬ ከቤታቸው አጠገብ ያለ ኪዮስክ ያለው ሰው ዘንድ በመሄድ ስለተነገረኝ ነገር ስጠይቀው ምንም አለመስማቱን ነግሮኝ ይኼንን ያልተጣራ ወሬ እንዳረጋግጥ ይመክረኛል፡፡ እንደተባልኩት ሳጣራ እንዲህ ዓይነት ወሬ የለም፡፡ በስንት ፍለጋ ያንን አውደልዳይ አግኝቼ ወሬውን ከየት እንዳመጣው ስጠይቀው፣ ‹‹አፕሪል ዘ ፉል….›› እያለ ሲያላዝንብኝ በራሴ ተናድጄ ወደ ቤቴ ተመለስኩ፡፡ አሁን ግን ነገሮች ሁሉ ከአፕሪል ዘ ፉል በላይ ሕይወትን አደጋ ውስጥ ስለሚከቱ ራሳችንን ከሐሰተኛ ዜናዎች ወይም ወሬዎች እንጠብቅ፡፡ አሉባልታ የስንቱን ጓደኝነትና ዝምድና ያፈረሰውን ያህል አገርንም ያጠፋል፡፡

(ምናሴ ባዩ፣ ከፈረንሣይ ሌጋሲዮን)