የሳምንቱ ገጠመኝ

በትክክል ባላስታውሰውም የዛሬ ሃያ ሁለት ዓመት ገደማ ይመስለኛል የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት አንድ ስብሰባ ላይ ተካፍዬ ነበር፡፡ በወቅቱ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ የንግድ ውድድርን አስመልክቶ አንድ ንግግር አድርገው ነበር፡፡ ወቅቱ አገሪቱ ከዕዝ ኢኮኖሚ ተላቃ ወደ ነፃ ገበያ የገባችበት በመሆኑ በርካታ አነስተኛ የንግድ ድርጅቶች እየተቋቋሙ ነበር፡፡ በጊዜው እንደ ዛሬ ትልልቅ የንግድ ድርጅቶች፣ ሆቴሎች፣ ባንኮች፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ወዘተ የሚታሰቡ አልነበሩም፡፡ ገንዘብ ያለው ሁሉ እየተነሳ ከተማውን በአንዴ ካፌ በካፌ ወይም ስቴሽነሪ በስቴሽነሪ ያደርግ ስለነበር ለዚያ ከዕዝ ኢኮኖሚ ተንከባሎ ለመጣ ኅብረተሰብ ብርቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነጋዴ በተመሳሳይ ቢዝነስ ውስጥ ሲገባ ደግሞ ተያይዞ የመውደቅ ሥጋት ነበር፡፡

ይህንን ሥጋት የተገነዘቡት የወቅቱ የንግድ ምከር ቤት ፕሬዚዳንት ነጋዴዎች ሥራዎቻቸውን በተለያዩ መስኮች እንዲያደርጉ፣ ይልቁንም ሁሉም ተንጋግቶ አንድ ሥራ ውስጥ ገብቶ ለኪሳራ ከሚዳርግ አንዱ የሌለውን ሌላው እያቀረበ፣ አንዱ ያለውን ሌላው ሳይሻማው ጤናማ የንግድ ሥርዓት መፈጠር እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡ በምሳሌነትም አንድ ጉዳይ ያነሳሉ፡፡ እሳቸው  በወቅቱ እንዳሉት የዕርዳታ ስንዴ እንኳ ሲሰጥ የእኛ ሰው አጠቃቀም አስገራሚ ነው፡፡ ስንዴውን አንዱ ከቆላው ሁሉም መንደሩን ቆሎ በቆሎ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ ይልቅ ቂጣ፣ ቆሎ፣ ንፍሮ፣ ቂንጬ፣ ወዘተ ቢደረግ ኖሮ ጎረቤቶች ከአንድ ዓይነት የእህል ዘር የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን ይቃመሱ ነበር፡፡ ንግዱም እንዲህ ቢሆን ጥሩ ነው በማለት ነበር ማሳሰቢያ የሰጡት፡፡

እኔ ይህንን ጉዳይ ከሃያ ዓመታት በኋላ ያነሳሁት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ንግድ ጤናማ ነው የሚባለው ውድድሩ ፍትሐዊና በሥርዓት ሲመራ ነው፡፡ በእርግጥ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ምርቶች በአንድ አካባቢ በበርካታ ነጋዴዎች ቢቀርቡ ምንም ችግር አይኖርም፡፡ ሸማቹም ሆነ ሻጩ በተመሳሳይና ተቀባይነት ባለው ዋጋ እየተገበያዩ ንግዱ ይቀላጠፋል፡፡ ነገር ግን ገንዘብ የሚይዙ፣ ከወቅት ጋር የሚገናኙና ከፍተኛ ጥረት የሚፈልጉ ግብይቶች ግን ጥንቃቄ ያሻቸዋል፡፡ አንድ አካባቢ ላይ በርካታ ምግብ ቤቶችና መጠጥ ቤቶች ሊኖሩ የሚችሉት በአካባቢው ካለው የሰው እንቅስቃሴ ጋር ተመዛዝኖ ነው፡፡ አንበሳ አውቶቡስ ወይም ታክሲዎች ተገልጋይ የሌለበት መስመር ላይ እንደማይመላለሱት ሁሉ፣ ጥቂት ተገልጋዮችን ታሳቢ ያደረገ ቢዝነስ መጠኑም በዚያው ልክ መሆን ይኖርበታል፡፡

አንዳንድ የከተማውን ሕንፃዎች ስትጎበኙ የምለው ይገባችኋል፡፡ ብዙዎቹ የሕንፃ ውስጥ ሱቆች ዋጋቸው አይቀመስም፡፡ በዚህ የተነሳ ጎብኚ የላቸውም፡፡ ብራንድ ዕቃ የያዙ ካልሆኑ በስተቀር ፈላጊ እንደሌላቸው ይታወቃል፡፡ ሸማቹ የሕንፃ ኪራይ ለመክፈል ለምን ራሱን ያስቸግራል? ብዙዎቹ ውድ ካፌዎች ካሉበት የሚያም ሕንፃና አገልግሎት ከሚሰጡበት ዕቃ ውጪ ከሌሎች ካፌዎች የተሻለ መስተንግዶ የላቸውም፡፡ ዋጋቸው ግን የእጥፍ እጥፍ ነው፡፡ መደዳውን ተከፍተው የባለሀብቶችን መምጣት ሲጠባበቁ ከሚውሉ ተላላፊ ደንበኞች (Walking Customers) ቢያስተናግዱ ይመረጥ ነበ፡፡ ‘የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል’ እንደሚባለው እንደ ባቡር ፉርጎ መደዳውን ሆነው ሲያዛጉ ይውላሉ፡፡

አንድ ስሙን መጥቀስ የማልፈልገው ሕንፃ ውስጥ አንድ ታዋቂ ሰው ሬስቶራንት ከፍቷል፡፡ የሬስቶራንቱ ሜኖ ሲታይ ዋጋው ጉድ ያሰኛል፡፡ ለምሳሌ ጥብስ 180 ብር፣ ቅቅል 180 ብር፣ ክትፎ 290 ብር፣ ሽሮ 135 ብር፣ አንድ ሊትር ውኃ 25 ብር፣ ቢራ 40 ብር፣ ወዘተ ተደርድሯል፡፡ የታዘዘው ምግብ ሲመጣ ግማሽ ዋጋ አያወጣም፡፡ አስታውሳለሁ አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ፣ አንድ ክትፎ አዘጋጅቶ ለተስተናጋጅ ለማቅረብ ከ25 ብር አይበልጥም ብለው ነበር፡፡ ግዴለም ዛሬ ባለው ዋጋ 80 ብር ይፍጅ፡፡ 290 ብር መሸጥ ምን አመጣው? የሕንፃ ኪራይ፡፡ እሱም ይሁን፡፡ በዚህ ሥሌት መሠረት ከሄድን ዋጋን ተመጣጣኝ አድርጎ ብዙ ደንበኞች መሳብ ይሻላል? ወይስ ባዶ ንግድ ቤት ታቅፎ መዋል? ነፃ ገበያ ብሎ ዝም ማለት ይኼኔ ነው፡፡

አሁን ደግሞ ከተማውን አይታችኋል? አዲሱ ፋሽን የመኪና ንግድ ነው፡፡ መንገድ ዳር ያለ የተዘጋ ግቢ እየተከፋፈተ ከአሮጌ እስከ እጅግ ውድ ዘመናዊ መኪኖች ለገበያ ቀርበዋል፡፡ ከዱባይ ላያቸው ላይ ያለው የኩባንያ ማስታወቂያ ጽሑፍ ቀለም ሳይጠፋ አገሪቱን ያጥለቀለቁት አሮጌ (Second Hand) መኪኖች፣ የውስጥ ለውስጥ የመንደር መተላለፊያዎችን ሳይቀር ዘግተው የገዥ ያለህ እያሉ ይጠብቃሉ፡፡ እጅግ ምርጥ የሆኑ መርሰዲሶች፣ ሐዩንዳዮች፣ ኒሳን ፓትሮሎች፣ ወዘተ ያማሩ ግቢዎች ይዘው ያስጎመጃሉ፡፡ የከተማው ነጋዴ በሙሉ በመኪና ንግድ ውስጥ የገባ ይመስል ፉክክሩ ተጧጡፏል፡፡ ዋጋ ሲጠየቅ ግን አይቀመስም፡፡ የተወዳዳሪነት መንፈስ ሳይሆን የአድማ ንግድ ይመስላል፡፡ ለነገሩ ዱባይ በ30 ብር ሒሳብ የተገዛ ዕቃ አዲስ አበባ 700 ብር ለሽያጭ በሚቀርብበት ወቅት ገዢና ሸማች እንዴት ይገናኙ? ነው ወይስ ‘አገር ሲደኸይ ሁሉም ነጋዴ ይሆናል’ እያልን እንተራረብ? አጃኢብ ነው፡፡

የንግድ ውድድርና ሥነ ምግባር አንድ ላይ የሚሄዱ ናቸው፡፡ ነገር ግን ንግዱ በሙሉ የደላላ ምርኮኛ ሆኖ ምግብ ቢወደድ፣ የአልባሳት ዋጋ አልቀመስ ቢል፣ በአነስተኛ ዋጋ አገር ውስጥ የገቡ ተሽከርካሪዎች ዋጋቸው ቢቆለል፣ አከራይ እንደፈለገው ተከራይ ላይ ዋጋ ቢጨምር ጠያቂና ተጠያቂ እስከሌሉ ድረስ ምን ይደረጋል? ነፃ ገበያ ነው እየተባለ በአድማ ንግድ ጥቂቶች እየከበሩ ብዙኃን ሲደኸዩ ተጠያቂነት ከሌለ ምን ይባላል? በሰው ሠራሽ የዋጋ ግሽበት አገር እያመሰቃቀሉ መኖርስ እስከ መቼ ይቀጥላል? ነፃ ገበያ ሲባል እኮ መረን መለቀቅ አልነበረም፡፡ አሁን ግን እየታየ ያለው በስመ ነፃ ገበያ ነፃ ዘረፋ ነው፡፡ ዘረፋውን የሚመራው ደግሞ የደላላ ግብረ ኃይል ነው፡፡ ይኼንን ማን ያስተባብላል? (አብነት ሙላቱ፣ ከቦሌ)