አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

የሴቶች ጥቃት አሳሳቢ ሆኗል

 

የሴቶች አጀንዳ በለውጥና ትራንስፎርሜሽን ፓኬጅ ውስጥ ተካቶ በተግባር የሚታዩ ለውጦች ቢመዘገቡም፣ የሴቶች ጥቃት አሁንም አሳሳቢ መሆኑን የኢትዮጵያ የሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (ኢሴማቅ)ዳይሬክተር አስታወቁ፡፡

ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ መጋቢት 4 ቀን 2009 ዓ.ም. የተካሄደውን አገር አቀፍ የውይይት መድረክ አስመልክተው ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ሳባ ገብረመድኅን እንደገለጹት፣ ጥቃቱን በሚፈጽሙ ሰዎች ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ በቂ ካልሆነ ‹‹ምን የተሻለ አካሄድ ሊኖር ይገባል›› ተብሎ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባ የተፈፀመው [በ16 ዓመት ታዳጊ ላይ የተፈጸመው ግድያ] መታየቱ ጥቃት እንዳለና እንደዚህ ዓይነቱ ጥቃት እንደተራ መታለፍ እንደሌለበት ያሳያል ብለዋል፡፡

ከጥቃቱም ባሻገር የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ በጣም ዝቅተኛ ሲሆን፣ በውሳኔ  ሰጪነት ያላቸውም ድርሻ በጣም አነስተኛና 13 በመቶ ያህል ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሴቶች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ይህም ለሴቶች የድጋፍ ዕርምጃዎች ሳይታከሉ ወደ ውሳኔ ሰጪነት ለማምጣት ያስችላል ብለዋል፡፡

የሴቶች ኢኮኖሚ በተለይም የመሬት አጠቃቀም መብቶቻቸው ያልተረጋገጡባቸው ቦታዎች እንዳሉ፣ እንደነዚህ ዓይነት መብቶቻቸውንም ለማስከበር ጠንካራና አስገዳጅ አሠራሮች መዘርጋት እንዳለባቸው ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

ኢሴማቅ፣ ከአውሮፓ ኅብረት የሲቪክ ሶሳይቲ ፈንድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ባካሄደው በዚሁ የውይይት መድረክ፣ በአገራችን የሥርዓት ጾታ ያለበት ሁኔታ፣ የሴቶችን እኩልነት መብት ለማረጋገጥ መከናወን ያለባቸው ሥራዎችና በሴቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች የሚጋፈጧቸው ተግዳሮቶች ላይ ያተኮሩ ልዩ ልዩ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶች ግንዛቤና ንቅናቄ ቡድን መሪ፣ ወ/ሮ ማህደር ቢተው ‹‹የሴቶች የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ፓኬጅ›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሑፍ፣ የሴቶች ጥቃት አሳሳቢ የሆነው ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በዚህ ዙሪያ በየፊናቸው ማከናወን የሚገባቸውን ተግባር ባለመሥራታቸው ነው ብለዋል፡፡

በሴቶች ላይ የሚታየው የቤት ውስጥ የሥራ ጫና እስካልተቀነሰ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸው ያድጋል ማለት ዘበት እንደሆነም አክለዋል፡፡

እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት የሕፃናት ማቆያዎችን እንዲያዘጋጅ መታቀዱን ወ/ሮ ማህደር ገልጸው፣ በዚህም መሠረት የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴርን ለሌሎች አርአያ ለማድረግ ያስጀመረው የሕፃናት ማቆያ በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የሴቶችን ኢንተርፕራይዞች ከአነስተኛ ወደ መካከለኛና ከዚያም ወደ ከፍተኛ ለማሸጋገር የሚሰጠው ድጋፍ ውስንነት እንዳለበት፣ የማምረቻና መሸጫ ቦታዎችና በቂ መሠረተ ልማቶች እንዳልተስፋፉና የቁጠባ ባህሉ በአግባቡ እንዳላደገ፣ የኢኮኖሚ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች ቀረጻ፣ ትግበራ፣ ክትትልና ድጋፍ ሴቶችን አሳታፊ የማድረጉ እንቅስቃሴ በብዙ ዘርፎች ችግሮች እንደገጠመው ታይቷል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ106ኛ ጊዜ በአገራችን ደግሞ ለ41ኛ ጊዜ የተከበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መሪ ቃል ‹‹ተግባራዊ ለውጥ ለሴቶች እኩልነት መረጋገጥ›› የሚል ነው፡፡ መሪ ቃሉ የሥርዓተ ጾታ  እኩልነትን ለማስፈንና ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በተግባር መረባረብ የሁሉም ኅብረተሰብ ድርሻ መሆኑን የሚያስገነዝብና የባለ ድርሻ አካላት ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል  እንዳለበት የሚያመላክት ነው፡፡