የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጥፋተኛ ተባለ

የሽብር ተግባር ወንጀል ፈጽሟል በማለት የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶበት ሲከራከር የከረመው የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ጥፋተኛ ተባለ፡፡

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ተቀስቅሰው የነበሩ ግጭቶች እንዲባባሱ የሚያደርጉ መጣጥፎችን በግል ኢሜይል አድራሻውና ድረ ገጾች ላይ ሲጽፍና ሲያሠራጭ እንደነበር ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ በሰውና በሰነድ እንደ ክሱ ማስረዳቱን በመግለጽ፣ አቶ ዮናታን እንዲከላከል የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ብይን ሰጥቶ ነበር፡፡

[ዓለምን ሥጋት ላይ የጣለው የሳይበር ጥቃት]

አቶ ዮናታን በራሱ የኢሜይል አድራሻና በድረ ገጾች ያስተላለፈው ወይም የጻፈው መጣጥፍ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ተጠቅሞ መሆኑን እንዲያስረዱለት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም፣ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና ጦማሪ በፈቃዱ ኃይሉን የኤክስፐርት መከላከያ ምስክር አድርጎ መቁጠሩንና ስለመጣጥፎቹ በዝርዝር ማስረዳታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ አቶ ዮናታን ሊያስተባብል እንዳልቻለ በመግለጽ ጥፋተኛ ብሎታል፡፡ በመሆኑም የቅጣት ማክበጃና ማቅለያ በሬጅስትራር በኩል እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት ለሰኔ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡