አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ሩጫ በአዲስ አበባና በክልሎች ተካሄደ

ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን (ማርች 8) ምክንያት በማድረግ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ሩጫ ባለፈው እሑድ የካቲት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በመላ አገሪቱ ተካሂዷል፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ቁጥራቸው ከ650,000 በላይ ተሳታፊዎች በሩጫው መታደማቸውም ታውቋል፡፡

በአገሪቱ በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ የመጀመርያ መሆኑ የሚነገርለት ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታው ከተጀመረ ዘንድሮ ስድስተኛ ዓመቱ ላይ ይገኛል፡፡ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገውና ‹‹ጊዜ የለንም እንሮጣለን፡፡ ለሕዳሴ ግድባችን እንቆጥባለን›› በሚል መሪ ቃል የተከናወነ የሩጫ ውድድር ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡

በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ባለፈው እሑድ በተካሄደው የሩጫ ውድድር ከ650,000 በላይ ተሳታፊዎች ዕድሜና ጾታ ሳይገድባቸው ተሳትፈውበታል፡፡ የፕሮግራሙ አንድ አካል የሆነው የአዲስ አበባው የሩጫ ውድድርም መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ የተከናወነ ሲሆን፣ ከ90,000 በላይ ነዋሪዎች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡

የታላቱ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በመገኘት ሩጫውን አስጀምረዋል፡፡ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት መላ ኢትዮጵያውያንን ከጫፍ ጫፍ ያስተሳሰረው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዕውን ሊሆን የሚችለው ይህን የመሰለ ሕዝባዊ ተሳትፎ ሲታከልበት እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡