የትምህርት ቤት ዩኒፎርም ስፌት ፋብሪካ ሊቋቋም ነው

በኢትዮጵያ ከችግረኛ ቤተሰቦች ተወልደው በየአቅራቢያቸው በሚገኙ የመንግሥት መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ አሥር ሺሕ ሕፃናት የትምህርት ቤት ዩኒፎርም እያዘጋጀ በነፃ የሚያቀርብ የልብስ ስፌት ፋብሪካ በ50 ሚሊዮን ብር ሊቋቋም ነው፡፡

ራዕይ ለትውልድ የበጎ አድራጎት ድርጅት፣ በባለቤትነት የሚያቋቁመውን ፋብሪካ አስመልክቶ ሰሞኑን በሸራተን አዲስ በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው፣ ግንባታው የሚከናወነው በአዲስ አበባ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ለገጣፎ አካባቢ በሚገኝ አሥር ሺሕ ሜትር ካሬ ቦታ ላይ ነው፡፡

ፋብሪካው በየዓመቱ 360 ሺሕ ዩኒፎርምና ቦርሳ የማምረት አቅም የሚኖረው ሲሆን፣ ደረጃውን የጠበቀ መጋዘን፣ የሠራተኞች መዝናኛ ክበብ፣ ሠራተኞች ሕፃናት ልጆቻቸውን የሚያቆዩባቸው ክፍል ይኖሩታል፡፡

አቶ ያሬድ ግርማ፣ የድርጅቱ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ይህንኑ አስመልክተው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፋብሪካው ውስጥ የሚገቡ ልዩ ልዩ የልብስ ስፌት መሣሪያዎችን፣ ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ደግሞ ሲሚንቶ በነፃ ለማቅረብ፣ እንዲሁም ለቁፋሮና ተዛማጅ ለሆኑ ሥራዎች ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ለመተባበር ቃል ገብተዋል፡፡

በፋብሪካው ውስጥ ተመድበው የሚሠሩትም ሥራ የሌላቸው፣ ነገር ግን ሥልጠና ቢሰጣቸው መሥራት የሚችሉ የሕፃናቱ ወላጆች ሲሆኑ፣ ሥልጠናውን ለመስጠት የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ፋብሪካው የሚያዘጋጃቸውን ዩኒፎርሞች በነፃ ከሚያገኙት መካከል ከኦሮሚያ 3,000፣ ከአማራ 2,000፣ ከአዲስ አበባ 1,500፣ ከትግራይ 1,000 ሕፃናት ይገኙባቸዋል፡፡ የቀሩትም ክልሎች እንደየተመደበላቸው መጠን ይደርሳቸዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ለግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በሽያጭ እንደሚያቀርብ፣ የሚገኘው ገቢም ለሠራተኛ ደመወዝ፣ ለፋብሪካው ሥራ ማስኬጃና ልዩ ልዩ ወጪዎች እንደሚውል ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው የሚያዘጋጃቸው ዩኒፎርሞችና ቦርሳዎች የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ እንደሚሆኑ አቶ ያሬድ ጠቁመው፣ ኅብረተሰቡ ዩኒፎርሙን በመግዛት እንዲሁም መንግሥት ከሕግ አንፃርም ሆነ ከአቅም ግንባታ አኳያ ሊሟሉ የሚገባቸውን ልዩ ልዩ ድጋፎች በማድረግ ከበጎ አድራጎት ድርጅቱ ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡