አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጠ

  • የቀድሞ የአንድነት አመራር አቶ ዳንኤል ሺበሺ ታሰሩ

አረና ትግራይ ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አረና) ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታን ፖሊስ አስሮ እንዲያቀርብ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠው በሽብር የወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው በሰኔ ወር 2006 ዓ.ም. በቁጥጥር ከዋሉ በኋላ ክስ የተመሠረተባቸው አቶ አብርሃ፣ የሥር ፍርድ ቤት መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ከወሰነ በኋላ ዓቃቤ ሕግ ካቀረበባቸው ይግባኝ ጋር በተያያዘ ነው፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመቃወም፣ ውሳኔው የተሰጠው ያቀረበው የሰውና የሰነድ ማስረጃ በአግባቡ ሳይመረመር መሆኑን ጠቅሶ ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው የይግባኝ አቤቱታ ተቀባይነት በማግኘቱ፣ አቶ አብርሃ ደስታና አቶ ዳንኤል ሺበሺ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ብይንን ተከትሎ አቶ አብርሃና አቶ ዳንኤል ፍርድ ቤት ቀርበው የመከላከያ ምስክሮቻቸውን እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሲሰጥ ሊገኙ ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ ሌላ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡ ሰኞ ግንቦት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. አቶ ዳንኤል እጃቸው በካቴና ታስሮ በፖሊስ ታጅበው ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም፣ አቶ አብርሃ ግን ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡ አቶ ዳንኤል ለምን እንዳልቀረቡ ሲጠየቁ ምንም የሚያውቁት እንደሌለና እንዳልሰሙ አስረድተዋል፡፡

[ዘንድሮ በአራት ክፍለ ከተሞች ከፍተኛ የእሳት አደጋ መመዝገቡ ተገለጸ]

በዕለቱም ፍርድ ቤት የቀረቡትም በፖሊስ ታጅበው ከአምስት ወራት በላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈዋል ተብለው ከታሰሩበት ፖሊስ ጣቢያ መሆኑ ታውቋል፡፡ አቶ አብርሃ ባለመቅረባቸው ፖሊስ አስሮ እንዲያቀርባቸው ትዕዛዝ በመስጠት፣ አቶ ዳንኤል ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩና ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

አቶ አብርሃ ደስታ በቅርቡ የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል፡፡ ለምን ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ ሪፖርተር ጠይቋቸው ምንም የሰሙት እንደሌለና የሚገኙትም መቐለ ከተማ እንደሆነ፣ ለዓቃቤ ሕግና ለፖሊስ ያስመዘገቡት የድሮ አድራሻቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ እንደሆኑም አክለዋል፡፡