አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወዴት ነው ያለኸው?!

በይትባረክ ምሥጋናው

የግል የባንክ ኢንዱስትሪው ኢትዮጵያ እንደ አገር እያስመዘገበች ላለችው ፈጣን ዕድገት እንደ አንድ መታያ አድርገው የሚዘክሩት በርካታ ምሁራንና የዓለም የገንዘብ ድርጅቶች እንዳሉ ከተለያዩ መጣጥፎችና መረጃዎች መመልከት ይቻላል፡፡ የእኔም ግምገማ በአብዛኛው ከእነዚህ ምሁራን ጋር ይመደባል፡፡

በእርግጥም የግል ዘርፉ ኢኮኖሚ እጅግ አመርቂ እመርታ ካሳየባቸው መስኮች መካከል የባንክ ኢንዱስትሪው ተጠቃሽ ነው፡፡ ዘርፉ በአሁኑ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎችን ክፍት በማድረግ፣ በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ዋነኛ ከሚባሉ ቀጣሪ ተቋማት መካከል ግንበር ቀደም ሆኗል፡፡ የአገሪቱ የቁጠባ ባህል እንዲዳብርና እንዲያድግ በርካታ ቅርንጫፎችን በመክፈት ተደራሽነቱን ከማረጋገጡም በላይ፣  በተለያዩ የግንዛቤ ፈጠራዎችና የውድድር መንፈስን በሚያነቃቁ ሽልማቶች አማካይነት የቁጠባ ባህል እንዲሰርፅ ከፍተኛ ሥራ አከናውኗል፡፡ በመንግሥት ባንኮች አማካይነት የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ሽፋን የማያገኙ የንግድ እንቅስቃሴዎች ብድርና የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ በማድረግ ድርጅቶቹ ቀጭጨው እንዳይቀሩ ከማድረጉም በላይ፣ እነዚህ ድርጅቶች እንዲስፋፉና በተራቸውም ተፈላጊውን አገልግሎት ለማኅበረሰቡ እንዲያቀርቡ፣ በተጓዳኝም መጠነ  ሰፊ የሆነ የሥራ ዕድል እንዲፈጠሩ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ወደፊት የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በከፍተኛ መጠን በማሳደግና በአገራችን እየተካሄደ ያለውን ልማትና ዕድገት ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ በመደገፍና የኃይል ቅርበቱን አስተማማኝ በማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ለተረጋገጠለት የታላቁ የዓባይ ግድብ ኃይል ማመንጫ፣ የግል ባንኮች ዝቅተኛ ወለድ በመክፈል ከፍተኛውን መዋጮ በማድረግ ጥቅማቸውን አሳልፈው በመስጠት የሕዝብ አጋርነታቸውን በተግባር አሳይተዋል፡፡

የግል ባንኩ ዘርፍ የአገሪቱ ልማት ብሎም ዕድገት ይበልጥ እንዲጎለብትና የዜጎች ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ሰፋፊ ዕድሎችን  በማመቻቸት መጠነ ሰፊ የሆነ ገንቢ ሚና  የመጫወቱን ያህል፣ ከዕለት ወደ ዕለት እየጠነከረ የመጣውን ውድድር መቋቋም ያቃታቸው አንዳንድ ባንኮች የአሠራር ሥልታቸውን በማዘመንና አዳዲስ አሠራርን በመቀየስ ከመወዳደር ይልቅ፣ ሕገወጥ ድርጊት በመፈጸም አንዱስትሪው ያሳየውንና ወደፊትም ለማሳየት የሚችለውን መልካም ዕድል የሚያጨነግፍ ተግባር ውስጥ በመዘፈቅ ላይ መሆናቸውን የሚጠቁሙ ድርጊቶች እየተንፀባረቁ ነው፡፡

ይህንን ተግባር በእንጭጩ ለመግታት በብሔራዊ ባንክ የባንኮች ቦርድ አባላት እስከማገድና የአንዳንድ ባንኮችን ፕሬዚዳንቶች እስከማባረረር የደረሱ አንዳንድ ጠንካራ ዕርምጃዎች የታዩ ቢሆንም፣ በተለይ ጀማሪ ባንኮች ውድድሩ የፈጠረውን ጫና በሕጋዊ ውድድር ተቋቁሞ ተፈጥሮአዊ ዕድገታቸውን ጠብቀው ከማደግ ይልቅ፣ አቋራጭ ሥልቶችን በመጠቀም ዘለቄታ የሌለው ትርፍ ማስመዝገብን እንደ መፍትሔ ይዘው እንደቀጠሉ በግላጭ እየታ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም አንድ የግል ባንክ ይህንኑ የውድቀት መንገድ በመከተል የሌለውን የውጭ ምንዛሪ እንዳለው በማስመሰልና የራሱ ያልሆኑ ደንበኞችን በማሳሳት ሌተር ኦፍ ክሬዲት በጨበጣ እንዲከፍቱ በማድረግ በኢንዱስትሪው ውስጥ የፈጠረው ሕገወጥ እንቅስቃሴ ከፍተኛ የሆነ መናጋት ከመፍጠሩም በላይ፣ የተለያዩ የውጭ አገር ባንኮች ከኢትዮጵያ ባንኮች ጋር ላለመሥራት ውሳኔ ላይ የደረሱበት፣ አንዳንድ ምርት አቅራቢ አገሮች የንግድ አታሼዎቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ልከው ከመንግሥት ጋር እስከመጋጨት የደረሱበት ሁኔታ መፈጠሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

ይህ ተግባር እንደ ቋያ እሳት በመቀጣጠል ከጥቂት ባንኮች በስተቀር አብዛኛዎቹ ባንኮች ደንበኞቻቸውን ለመከላከልና ከራሳቸው ጋር ለማቆየት ሲሉ፣ በገቡበት የግዴታ ውዴታ ጦርነት በኢንዱስትሪው ውስጥ በርካታ ጉዳቶች ተከስተዋል፡፡ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ነጋዴዎችም ለዘመናት ደክመው ከተጎዳኙዋቸው የውጭ ዕቃ አቅራቢዎቻቸው ጋር የነበራቸውን ውል እንዲያቋርጡ ተገደዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ዘግይቶም ቢሆን ተጠያቂ ባላቸው የባንክ አመራሮች ላይ ዕርምጃ ባይወስድ ኖሮ፣ ከግለሰብ ነጋዴዎች ጉዳይነት አልፎ በአገሪቱ ላይ አንዣቦ የነበረው በመልካም አፈጻጸም ላይ የተመሠረተው የውጭ ምንዛሪ እንቅስቃሴ አደጋ ላይ ይወድቅ አንደነበር ጥርጥር የለውም፡፡  

ኢንዱስትሪው ለአገሪቱ ኢኮኖሚ መሳለጥ፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ እንዲሁም ለቁጠባ ባህል ያለው ወሳኝ ሚና ይህን ያህል የገዘፈ ከሆነና ውድቀቱም የበርካቶችን ሕይወት ከማተረመስ አልፎ የአገሪቱን ንግድ ሚዛን በማዛባትና ተዓማኒነትን በመሸርሸር ከዓለም አቀፍ ባንኮች ጋር ያለውን በመልካም ግንኙነት (In Good Faith) ላይ የተመሠረተ የግብይት ሥርዓትን እንደሚንድ ከታወቀ፣ ችግሩ በአፋጣኝና ገጽታውንም ከመቀየሩ በፊት በወቅቱ መፍትሔ ሳያገኝ ለምን ቀረ የሚለው ጥያቄ የበርካቶች ራስ ምታት እንደሆነ ቀጥሏል፡፡

ከላይ የተዘረዘረው ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቼ የኢንዱስትሪውን ውድቀትና ኪሳራውን አሊያም ተስፋውን እንደ መነሻ እንድተነትን፣ ብሔራዊ ባንክም በተራው ራሱንና በሥሩ የተኮለኮሉትን ባንኮች በጥንቃቄ እንዲፈትሽ የሚያመላክት ጥያቄ እንዳጭር ያደረገኝ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንድደርስ ያስገደደኝ አሥጊ ሁኔታዎችን ለመታዘብ በመብቃቴ ነው፡፡

ዛሬ ኢንዱስትሪው በተለይም ደግሞ ትንንሽ አቅም ይዘው የተነሱት ባንኮች ካለፈው ስህተት ተምረዋል ወይ ቢባል? ከሚታየውና ከሚሰማው አኳያ የእኔ መልስ አልተማሩም ነው፡፡ ይህ ግን ጀማሪዎችም ሆኑ ነባር ባንኮች በኢንዱስትሪው ውስጥ ሕግና ሥርዓትን ጠብቀው በገበያ ሥርዓትና በውድድር የሚመሩ ባንኮችን የማይመለከት መሆኑን ግንዛንቤ እንዲወሰድልኝ በአክብሮት አሳስበለሁ፡፡

ችግሩ ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ ከችግሮቹ መካከል በተለይ ተጠቃሽ የሆነው፣ ትንንሾቹ ባንኮች ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ያለአቅሟ ውኃ ተግታ ዝሆንን ለማከል እንደተወጣጠረችው እንቁራሪት ያገኙትን ሁሉ በመሰልቀጥ ትልልቆቹን ለማከል ውጥረት ውስጥ መግባታቸው ነው፡፡ በዓመታዊ ስብሰባዎቻቸው ላይ ለባለቤቶቻቸው የሚገቡት ቃል አዙሪት እየሆነባቸው፣ ሕገወጡንም ሆነ ሕጋዊውን ሥራ እያፈራረቁ ለመተግበር አስገዳጅ ማነቆ ውስጥ ተዘፍቀዋል፡፡

ትልልቅ የሚባሉትም ባንኮች ቢሆኑ የነፃ ገበያ ሥርዓቱ በሚፈጥረው ዕድልና ውድድሩ በሚጠይቀው የአገልግሎት ጥራት ላይ ተመሥርተው በሕጋዊው የገበያ አቅም ላይ ከመወዳደር ይልቅ፣ በሕገወጥ መንገድ የሚካሄድ የውጭ ምንዛሪ ዝውውር ውስጥ እጃቸውን ሙሉ በሙሉ ዘፍቀው በባንኩ ባለቤቶች እጅ የዘንዶ ጉድጓድ እየለኩ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህንን ሕገወጥ ተግባር ሕጋዊ በማድረግም ከአንዱ ባንክ ወደ ሌላው በደላላ እየታገዙ ደንበኛን በማስኮብለል ተግባር ላይ በስፋት መሰማራታቸው አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነው፡፡ ይህንን ስል የትኞቹን ባንኮች እያነሳሁ እንደሆነ የእያንዳንዱ ባንክ ከፍተኛ አመራር ልቦናው እንደሚያውቀው እርግጠኛ ነኝ፡፡

እስካሁን እነዚህ ከላይ ያነሳኋቸው ችግሮች የየባንኮቹን ፕሬዚዳንቶች ወይም ከፍተኛ ኃላፊዎች ከሥራ እንዲሰናበቱ ከማድረግ ያለፈ ለጥፋታቸው ተመጣጣኝ ቅጣት የሚጥል አካሄድ ባለመኖሩ፣ ከፍተኛ ኃላፊዎቹ በሕገወጥ እንቅስቃሴው አማካይነት በአማላጅነትና በጥቅም ተጋሪነት በመሳተፍ የሚያግበሰብሱት ሀብት ከተሰጣቸው፣ የባንኩ ባለቤቶች የኃላፊነት አደራም ሆነ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ሊፈጠርበት ከሚችለው አደጋ በላይ የሚያጓጓ በመሆኑ ከቀደመው ስህተት ለመማርም ሆነ ቢያንስ ከባንኩ ባለቤቶች የተሰጣቸው አደራ ቢቀር እንኳን ለአገር ከመቆርቆር የሞራል የበላይነት ተራ ለመሠለፍ እንኳን ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል› የባንክ አንዱስትሪው ባህል ሆኗል፡፡

ከባንኮች ጋር የቀረበ ግንኙነት ስላለኝ በብዙ ገዳዮች ላይ ማስረጃው ባይኖረኝም፣ መረጃ ግን በተፈለገው መጠን አለኝ፡፡ በተለያዩ ባንኮች ውስጥ ዓመታዊ ስብሰባም ሆነ ዝግጅት ላይ ስለምገኝ አጋጣሚውንም ተጠቅሜ  ከተሰብሳቢውም ሆነ ከደንበኛው መረጃ መቃረም የተለመደ ተግባሬ ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ከላይ እንደጠቀስኩት በመረጃ ለማስደገፍም ሆነ ስም ለመጥራት የሚያበቃኝ ተጨባጭ ነገር ባለመኖሩ (ሕገወጥ ሥራው በአብዛኛው የሚሠራው በከፍተኛ ሚስጥር በመሆኑ) ዝምታን መርጬ ነበር፡፡ በቅርቡ ግን ወደ ቶጎ ውጫሌ በግል ጉዳዬ በመሄዴ በወሬ ደረጃ የሰማሁት በተግባር እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ችያለሁ፡፡

ቶጎ ውጫሌ በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ የምትገኝ ትንሽ መንደር ነች፡፡ ቶጎ ውጫሌ በታሪክ ፊት ስትወሳ ግን እንደ ትንሽ መንደርነቷ ጠባብ አይደለችም፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የዜጎቻችን በርካታ መስዋዕትነት ያስተናገደች፣ እጅግ ስመጥር ጀግኖችን ያፈራች፣ የኢትዮጵያውያን አልገዛም ባይነት መገለጫ ነች፡፡

ዛሬ ግን ታሪኳ ሌላ ሆኗል፡፡ ይህች ትንሽ መንደር ከአቅሟ በላይ የባንኮች መናኸሪያ ሆኖለች፡፡ ቅርንጫፍ የሌለው ባንክ የለም፡፡ የባንክ ሠራተኛን ጥመርታ ከነዋሪዎቻ ጋር ብናሰላው እያንንዳነዱ ነዋሪ ሁለት ሁለት የባንክ ባለሙያ የሚደርሰው ይመስላል፡፡  የንግድ እንቅሰቃሴዋም በአብዛኛው በኮንትሮባንድ ዕቃ፣ በሕገወጥ የውጭ ምንዛሪና በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ተመሥርቶ የሚከናወን ነው፡፡ ታዲያ ለምን ይህንን ያህል የባንኮችን ትኩረት አገኘች የሚል ጥያቄ ለሚያነሳ መልሱ ከባድ ሊመስል ይችላል፡፡ እውነታው ግን ወዲህ ነው::

ቶጎ ውጫሌ ላይ የከተመው ወፈ ሰማይ ደላላ ዓላማው እንደየልምዱ የተለያየ ቢመስልም የኮንትሮባንድ ዕቃ፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና የዕፅ ማቀባባል ሥራ ማዕከል ያደረገው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት፣ ሽያጭና ዝውውር ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ደላላ "በሙያው" የዚህ ወይም የዚያ ሥራ ደላላ ቢባልም ቀዳሚ ተግባሩ ግን በዚሁ ሕገወጥ እንቅስቃሴ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ሕጋዊ እንዲሆን ወይም እንዲታጠብ (Money Laundering) ለማድረግ የውጭ ምንዛሪ ባለቤቶቹን ከባንኮቹ ጋር ማገናኘት ነው፡፡ ባንኮቹ በሕገወጥ መንገድ የተገኘውን የውጭ ምንዛሪ በሕጋዊ መንገድ እንደተገኘ በማስመሰል ወደ ባንክ ሥርዓት ውስጥ ያገቡታል፣ ወይም ያጥቡታል፡፡

ይህ እንግዲህ በወዳጅነት ቀርቤ መረጃ ከሰጡኝ ደላሎች የተገኘ መረጃ ነው፡፡ ይህንን እንድቀበል ጠቋሚ መነሻ የሆነኝ ደግሞ አንዳንድ ትንንሽ ባንኮች ያስመዘገቡት ትርፍ እመርታ ያሳየው ከተለመደው እንቅስቃሴ ይልቅ፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ከተሰበሰበ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ላይ በመመሥረት መሆኑ ነው፡፡ የባንክ ኢንዱስትሪው ለእያንዳንዱ ባንክ ያለው የመቶኛ ድርሻ ይታወቃል፡፡ ሥሌቱ መሠረት የሚያደርገውም ባንኮቹ ባላቸው ቅርንጫፍ ብዛት፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ በነበራቸው ቆይታ፣ ባላቸው ካፒታል፣ ተቀማጭ ሒሳብና በመሳሰሉት ነው፡፡ በዚህ ሥሌት መሠረት ትልልቆቹ ባንኮች ማሰባሰብ ከቻሉት በላይ ትንንሾቹ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ማሰባሰባቸው ሕጋዊ መሠረቱ ሊመረመር ይገባዋል የሚል አቋም አለኝ፡፡

ብሔራዊ ባንክ የሕዝብ ሀብትና የደንበኞችን ቁጠባ የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ በተጓዳኝም የባለቤቶቹ ሀብትም ሲጠበቅ ማየቱ ለባንኮቹ ጤናማ እንቅስቃሴ ወሳኝ መሆኑን የሚገነዘብ ይመስለኛል፡፡ ይህ ያልተለመደና የተገኘውን ከመሰልቀጥ የመጣ ትርፍ መንስዔ መመርመር ያለበት ለዚህ ነው፡፡ ከውድቀት በኋላ በድጋሚ ለመማር ታሪክ ዕድል የማይሰጥ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሌላው ቢቀር በሕገወጥ መንገድ የተፈራው የውጭ ምንዛሪ ዜጎቻችንን በሕገወጥ መንገድ በማዛወር የተገኘ ሊሆን እንደሚችልና ይህ ደግሞ ችግሩን ከሥሩ ለመፍታት መወሰድ ከሚገባው ዕርምጃ ቀዳሚው እንደሆነ በዜግነት የምከራከርለት ጉዳይ ነው፡፡ ቀጥሎም ይህ ገንዘብ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄዱ የሽብር ፈጠራ ድርጊቶችን ለማገዝ እንደማይውል ማን ዘብ ሆኖ ሊከራከር ይችላል ብዬ እጠይቃለሁ፡፡

የባንክ ኢንዱስትሪው ዕድገት በአቅሙ የሚጎርሰውን ያህል እየጎረሰ መሆን አለበት፡፡ የግል ባንኮችም ያገኙትን እየሰለቀጡ ትርፍ ብቻ ማዕከል አድርገው የሚራመዱ ከሆነ፣ አደጋው ከባንክ ለባንክ ግብግብ (Turf War) ወደ አገራዊና ሕዝባዊ ኪሳራ ላለመሸጋገሩ መከላከያ ማቅረብ አይቻልም፡፡ ብሔራዊ ባንክም ‹በዕንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ› ውሎ አድሮ ከመከሰቱ በፊት የቁጥጥር አድማሱን አስፍቶ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡ አሥጊና የተዛቡ የውጭ ምንዛሪ እንቅስቃሴዎችም (Suspicious Transaction) በጥልቀት ይመርመሩ፡፡ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎችን በመጠቀም የተገኙ የውጭ ምንዛሪዎችን ተጠቅሞ የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አደላደል መመርያ ከሚፈቅደው ውጪ ደንበኞችን በማስተናገድ የሚከናወኑ የደንበኛን ተራ የማዛባት ተግባሮች መንስዔያቸው ሊመረመር ይገባዋል፡፡ እንደ ዜጋ ከሕገወጥ የሰውና የዕፅ ዝውውር በተገኘ የውጭ ምንዛሪ አቀባባይነት ከአቅማቸው በላይ የሚያብጡ ባንኮች ጉዳይ ትኩረት አለማግኝቱ ያሠጋኛል፡፡ መንግሥትንም ለሽብርተኝነት ሊውሉ የሚችሉ የገንዘብ ዝውውሮች ለዜጎች ደኅንነት ሲባል ሊያሳስቡት ይገባል፡፡ ኮንትሮባንድን፣ ሕገወጥ የሰውና የዕፅ ዝውውርን አልፎ ተርፎም ለሽብር ሊውሉ የሚችሉ ሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ እንቅስቃሴዎችን በመግታት፣ የሕዝብን በሰላም የመኖር መብት ለማስከበር እንዲቻል የባንኮችን ጓዳ ጎድጓዳ መንግሥትና ብሔራዊ ባንክ መፈተሽ  ይገባቸዋል፡፡ በቅርቡ በዚህ ጉዳይ ላይ በተብራራ ትንተና እመለሳለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡