አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

የክልሎቹ ሕግጋት መንግሥታት አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ከመፍጠር አንፃር

በውብሸት ሙላት

የክልል ሕገ መንግሥት ከፌዴራሉ ጋር ሁልጊዜም ስምምነት ሊኖረው ይገባል፡፡ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ለሚያስቀምጣቸው ግቦች አስተዋጽኦ የሚያደርግ እንጂ የሚያፈርስ ወይንም የሚቃረን መሆን የለበትም፡፡ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በመደብ ወዘተ. ከፍተኛ ልዩነትና ብዝኃነት ያለበት አገር ቢሆንም እንኳን ልዩነቱን በመጠበቅ አገራዊ ስሜትን አንድነትንና አርበኝነትን የሚያጠናክር ተግባር እንጂ ተጻራሪውን መፈጸም የለበትም፡፡ የፌዴራል ሥርዓት አንዱ በረከት በልዩነት ውስጥ አንድነትን በመፍጠር አብሮ መኖር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የክልል ሕገ መንግሥት በወሰናቸው ውስጥ የሚንጸባረቁ ባህሎችን፣ እሴቶችንና ሌሎች መለያ ባህርያትን ከግምት ያስገቡ መሆን አለባቸው፡፡ በመሆኑም የክልል ሕገ መንግሥት አንድም የክልላዊ እሴቶች ማስጠበቂያ በመሆን በተጨማሪም ለአገራዊ ግብና አንድነትን አስተዋጽኦ የማድረግ ድርብ ኃላፊነት አለባቸው ማለት ይቻላል፡፡

የዚህ ጽሑፍ ትኩረት የክልሎቹ ሕግጋት መንግሥታት መግቢያቸውን ልዑላዊ የሥልጣን ባልተቤቶች ወይንም በክልል ጉዳይ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ የሆኑትን የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም የክልል የሥራ ቋንቋዎችን በመፈተሽ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመፍጠር አገራዊ ግብ ላይ ሊኖራቸው የሚችለውን አንድምታ ማመላከት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በክልል ደረጃ የሚኖራቸውን መብት ባለመርሳት ነው፡፡

መግቢያ

የሁሉንም ክልሎች ሕግጋት መንግሥታት መግቢያ የተመለከተ ሰው የሚያጤናቸው ሁለት ቁም ነገሮች አሉ፡፡ እነሱም የቀደመውን ታሪክ መውቀስና ወደፊት ስለሚኖረው አገራዊ ተስፋ ናቸው፡፡ ያለፈውን ታሪክ ከመውቀስ አንፃር የአገላለጹ ድምጸት ይለያያል፡፡ የሐረር ዓመተ ምሕረቱን ሳይቀር በመጥቀስ የደረሰበትን በደልና የከፈለውን መስዋዕት ይዘክራል፡፡ ኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሊያ በጠንካራ ድምጸት የቀድሞውን በደል ኮንነዋል፡፡ የተወሰኑት ደግሞ ስላደረጉት የጀግንነት ተጋድሎ አስረግጠው ገልጸዋል፡፡ የክልላቸውም መዝሙር ይህንኑ ማንፀባረቅ እንዳለበት ደንግገዋል፡፡ በተወሰነ መልኩ ደግሞ በተለሳለሰ መልኩ ያስቀመጡት የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የጋምቤላ ክልሎች ናቸው፡፡ የአማራ ክልል ደግሞ በቀደሙት ሥርዓቶች የተፈጸሙት የብሔር ጭቆናዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንደጎዳው ያትታል፡፡ ከዚህ አንፃር የክልሎቹም ይሁኑ የፌዴራሉ ሕግጋት መንግሥታት ኢትዮጵያን ለመገንባት የተከተሉት መስመር የቀደመውን ሥርዓት በደሎችና እንከኖችን በማውገዝ ዳግም እንዳይመለሱ ቃል በመግባት እንጂ ቀድሞ የነበረውን አንድ ሊያደርገን የሚችል የኢትዮጵያዊነት መገለጫዎች ወይንም ማንነት መሠረት በማድረግ አይደለም፡፡

ሌላው የክልሎቹ ሕግጋት መንግሥታት ያስቀመጧቸው ግቦች የተፋጠነ ልማት፣ ዴሞክራሲ፣ ሰላምና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት በመመሥረት ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር አብሮ መኖርን ነው፡፡

የሕዝብ ወሳኝነት ወይንም ክልላዊ ሉዓላዊነት

በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ስምንት መሠረት ሉዓላዊ የሥልጣን ባልተቤቶች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው፡፡ የሕገ መንግሥቱም ባልተቤቶችም እነሱው ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከፍተኛው የሥልጣን አካል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ይህ ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚወከልበት ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ መግቢያና አንቀጽ ስምንት አኳያ ከሰማንያ የማያንሱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሉዓላዊ ሆነው ሳለ የእነዚህ ቡድኖች የሚወከሉበት ምክር ቤት ግን ከፍተኛው የሥልጣን አካልን አይጋሩም፡፡ ከፍተኛው የሥልጣን አካልና ሉዓላዊ የሥልጣን ባልተቤት የተጣጣመ አይደለም፡፡

ከፌዴራሉ ሕገ መንግሥት በትይዩ የክልሎቹ ሕግጋት መንግሥታትም በግዛታቸው ውስጥ ‹‹ወሳኝ›› ወይንም ‹‹ሉዓላዊ›› የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለይተው አስቀምጠዋል፡፡ ከዚህ አንፃር በክልል እንዴት እንደተገለጹ እንመልከት፡፡

የክልሎቹን ሁኔታ ስናጤን ሦስት ዓይነት አካሄዶችን እናስተውላለን፡፡ የመጀመሪያው፣ በክልሎቹ የሚገኙ ሕዝቦች በሙሉ ወሳኝ ወይንም ሉዓላዊ  የሥልጣን ባለቤት የሆኑባቸው አሉ፡፡ የአማራ፣ የደቡብ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የጋምቤላ ክልሎች በዚህ ቡድን ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡  የብሔር ልዩነት ሳይኖር ሁሉም እኩል ወሳኝ በመሆናቸው የተወሰነ ቡድንን ብቻ ሉዓላዊ አለማድረጋቸውን እንረዳለን፡፡ በእርግጥ የእነዚህ ክልሎች ሕግጋት መንግሥታትም ቢሆኑ ብሔርን እንደ ቡድን በመውሰድ  መብት ከመስጠት አንፃር  ዕውቅና  የቸሩት ‹‹ነባር›› ለሚሏቸው ብቻ ነው፡፡ 

ሁለተኛው በሕገ መንግሥታቸው ውስጥ ሁለትና ከዚያ በላይ ነባር ብሔሮች እንዳሉ ዕውቅና ሰጥተው ነገር ግን ክልላዊ ከፍተኛ የሥልጣን ባለቤትነትን ለአንድ ብሔር ብቻ የሰጡ ናቸው፡፡ በዚህ ምድብ ውስጥ የትግራይ፣ የአፋርና የሐረሪ ሕግጋት መንግሥታት ይካተታሉ፡፡ እነዚህ ሕግጋት መንግሥታት ክልሎቹን እንደ አንድ ሉዓላዊ አገር በመውሰድ በውስጣቸው የሚገኙትን ሌሎች ብሔረሰቦች እንደ አናሳ የቆጠሩ ይመስላሉ፡፡ በመሆኑም፣ ምንም እንኳን በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ማንኛውም ብሔረሰብ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትን ቢጋሩም ከክልል ላይ ግን የተገለሉ አሉ፡፡

ሦስተኛው ምድብ ደግሞ በሕገ መንግሥታቸው ዕውቅና በመስጠትም ይሁን ከፍተኛ የሥልጣን ባለቤት በማድረግ ለአንድ ብሔር ብቻ ዕውቅና የሰጡ ናቸው፡፡ በዚህ ምድብ ሥር የሚካተቱት የኢትዮጵያ ሶማሊያና ኦሮሚያ ናቸው፡፡ በክልሎቹ ውስጥ ሌላ ነባር የሚባል ብሔረሰብ መኖሩን ከመጀመሪያውም ዕውቅና አልሰጡም፡፡

ከላይ የቀረበው በክልል ጉዳይ ውስጥ የበላይ የሥልጣን ባለቤት መሆንን የተለያየ አገላለጽን የተከተሉ ሕግጋት መንግሥታት ቢኖሩም፣ በሌሎች ሕግጋት መልሰው ልዩነት የፈጠሩ ክልሎች አሉ፡፡ ሦስት ክልሎች ለከተማ ምክር ቤት አባልነት በመሥፈርትነት ያወጧቸውን የምርጫ ሕግጋት አስረጂ በማድረግ እንመልከት፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 55 በመቶ የከተማው ምክር ቤት ለክልሉ ነባር ሕዝቦች የተተወ ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልል ደግሞ 50 በመቶ ለከተማው ኦሮሞ፣ 20 በመቶ ለገጠር ገዳዎች ተቀምጧል፡፡ ቀድሞ 30 በመቶ ለከተማው አምስት በመቶ ለገጠር ገዳዎች የነበረውን በመጨመር፡፡ በደቡብ ክልል ደግሞ በልዩ ወረዳና ዞኖች ውስጥ ለሚገኙ ከተሞች ለነባር ሕዝቦቹ 30 በመቶ ተቀምጧል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የበርታ ሕዝብ የክልሉ ነባር ያልሆኑ ብሔረሰቦች ክልሉን በመወከል በምርጫ መሳተፍ የለባቸውም በማለቱ ምክንያት የተነሳው ክርክር በተመለከተ በሰጠው ውሳኔ መሠረት ማንኛውም ሰው የሚወዳደርበትን ምክር ቤት የሥራ ቋንቋ ካወቀ መወዳደር እንደሚችል ወስኗል፡፡ ለፌዴራሉ ምክር ቤትና የክልሉ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ለሆኑት ለአማራ፣ ለደቡብ፣ ለጋምቤላ፣ ለቤኒሻንጉል/ጉሙዝ ክልሎች ምክር ቤት የሚወዳደር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አማርኛ ቋንቋን መቻል ቅድመ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን አማርኛ ከቻለ ከውድድር ሊከለከል አይገባም ማለት ነው፡፡ የክልሉ ምክር ቤት የሥራ ቋንቋም አማርኛ ያልሆኑት ትግራይ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ሐረርና የኢትዮጵያ ሶማሊያም ለውድድር አስፈላጊው እነዚህን ቋንቋዎች መቻል እንጂ የብሔር ልዩነት አይደለም ማለት ነው፡፡ በዚህ መንገድ አብዝኃኛው ሰው የተወሰኑ ቋንቋዎችን ብቻ በማወቅ አንድነትን ለማጠናከር ይረዳል ማለት ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከላይ የተጠቀሱት ሕጎች ሕገ መንግሥታዊነታቸውም ይሁን ከውሳኔው ጋር አብሮ መሄዳቸው ሊፈተሽ ይገባዋል፡፡

እነዚህ ክልሎች ሕጎቹን ሲያወጡ እንደ ፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ውሳኔ እንኳን የሚወዳደሩበትን ምክር ቤት የሥራ ቋንቋ ማወቅ አለማወቅ እንደ መሥፈርት አልወሰዱትም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ክልሎች በውስጣቸው ስላሉ ጉዳዮች ‹‹ሉዓላዊ›› ስለሆኑ ይመስላል፡፡ ተግዳሮቱ ግን ክልሎች የምርጫ ሕግ የማውጣት ሥልጣን ቀድሞውንስ አላቸው ወይ የሚለው ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 51(15) መሠረት የምርጫና የፖለቲካ መብቶችን በተመለከተ ሕግ የማውጣት ሥልጣን የተሰጠው ለፌዴራል መንግሥት ነው፡፡ ክልሎቹ የምርጫ ዓይነቶችን በየሕገ መንግሥታቸው ወስነዋል፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ አርዕስት ያላቸውን አዋጆች በማውጣት ስለምርጫ ጉዳይም እግረ መንገዳቸውን እንዲይዙ አድርገዋል፡፡ የከተማውን ምክር ቤት የሥራ ቋንቋ እስከቻሉ ድረስ በብሔር አፋር፣ አማራ፣ ወላይታ፣ ሲዳማ ቢሆኑ ባይሆኑም መወዳደር እየቻሉ እነዚህ ሕግጋት ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔና ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 እና 38 አኳያ አብሮ የመሄዳቸው ነገር ፍተሻ ያስፈልገዋል፡፡

በእርግጥ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱም ውሳኔ የብሔረሰቦችን መብት ከሚገባው በላይ ያጣበበ ስለሆነ ሌላ ሳንካ የፈጠረ ይመስላል፡፡ ለቀበሌ፣ ለወረዳና ለብሔረሰብ ምክር ቤቶች ለመወዳደር የሚፈልግ ሰው የምክር ቤቱን ቋንቋ ማወቅ ግድ ነው ካለ የአማራ ክልልን እንደ ምሳሌ ብናይ ከአዊ፣ ከዋግኽምራ፣ ከኦሮሞ አስተዳደር ዞኖችና ከአርጎባ ልዩ ወረዳ ለፌዴራልና ለክልሉ ምክር ቤት የሚወዳደር ማንኛውም ዕጩ አማርኛ መቻል ያለበት ሲሆን፣ ለዞኖቹ፣ ለወረዳዎችና ለቀበሌ ምክር ቤቶች ለመወዳደር ደግሞ አዊኛ፣ ኻምርኛ፣ ኦሮሞኛና አርጎብኛን ማወቅ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ በጋምቤላ ደግሞ ለክልሉና ለፌዴራሉ ምክር ቤቶች አኙዋውም፣ ኑዌሩም፣ መዣንግሩም፣ ኡፖውም ኮሞውም አማርኛ ማወቅ ግድ ሲሆን፣ ለብሔረሰብ ዞኖቹ (ለአኙዋ፣ ኑዌርና መዣንግር) የእነዚህን ብሔረሰቦች ቋንቋዎች ማወቅ ግድ ነው፡፡ ኡፖና ኮሞዎች የራሳቸው ዞን ስለሌላቸው ባሉት ውስጥ መሳተፍ ከፈለጉ ከሦስቱ አንዱን መቻል አለባቸው ማለት ነው፡፡ የምክር ቤቶቹን የሥራ ቋንቋ ባለማወቅ ከምርጫ ውጭ ማድረግ ለሁሉም ቋንቋዎች የተሰጠውን ሕገ መንግሥታዊ ዋስትናና የብሔረሰቦችን ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት ጋር የሚመጣጠን አይደለም፤ የሚስማማ መሆኑም አጠያያቂ ነው፡፡ ስለሆነም ክልሎቹ ያወጧቸው ሕግጋትም ይሁኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሰጠው ውሳኔ የብሔረሰቦችን መብት በማስጠበቅ ኢትዮጵያዊነትን ወይንም አንድነትን ለመፍጠር አጋዥነቱ አጠያያቂ ነው፡፡

የክልሎች የሥራ ቋንቋ ምርጫ

የቀደሙት የኢትዮጵያ ሥርዓቶች አማርኛ ብቻ ብሔራዊ ቋንቋ መሆኑ ሳያንስ ሌሎች ቋንቋዎች፣ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ላይ አደረሰ የተባለውን ችግር ሁሉ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት የጸደቀበት ቃለ ጉባኤ ላይ  ተዘርዝሯል፡፡ ችግሮቹን ለመቅረፍ የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ለሁሉም ቋንቋዎች እኩል መንግሥታዊ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ክልሎችም የራሳቸውን የሥራ ቋንቋ መወሰን እንደሚችሉ ገልጿል፡፡ በራስ ቋንቋ የመናገርና የመጻፍ እንዲሁም ቋንቋውን የማሳደግ መብትን አጎናጽፏል፡፡

በመሆኑም ክልላዊ የሥራ ቋንቋዎችም የትግራይ ክልል ትግርኛን፣ አፋር ክልል አፋርኛን ለአርጎባ ብሔረሰብና ቋንቋ ዕውቅና በመስጠት፣ የአማራ ክልል አማርኛን በተጨማሪም በልዩ ዞኖችና ወረዳ ደረጃ አዊኛ፣ ህምጥኛ፣ ኦሮምኛና አርጎብኛ፣ የኦሮሚያ ክልል ኦሮምኛን፣ የሐረሪ ክልል ሐረሪኛና ኦሮምኛን፣ የኢትዮጵያ ሶማሊያ ክልል ሶማሊኛን፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አማርኛን ተግባራዊነቱ ላይ የተወሰነ ችግር ቢኖርም አምስቱም ነባር ብሔረሰቦች ማለትም የበርታ(ሩጣንኛ)፣ ጉምዝ ጉምዝኛ፣ ሺናሻ ሺናሽኛ በልዩ ዞንና ማኦና ኮሞ በልዩ ወረዳ ደረጃ ማኦኛና ኮሞኛን፣ ጋምቤላ ክልል የክልሉን የሥራ ቋንቋ አማርኛ በማደረግ ከአምስቱ ነባር ብሔረሰቦች ለሦስቱ ልዩ ዞን በመፍቀድ ኑዌር፣ አኙዋና መዠንግር በቋንቋቸው እንዲጠቀሙ፣ ደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች ደግሞ የክልሉን አማርኛ በማድረግ ዞንና ልዩ ወረዳ ላላቸው በራሳቸው ቋንቋ እንዲናገሩና እንዲጽፉ ሕገ መንግሥታዊ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም የአዲስ አበባ የድሬዳዋ አማርኛ ሆኗል፡፡

ከዚህ አንፃር ከአሃዳዊ የመንግሥት አወቃቀር በተለየ መልኩ የፌዴራል ሥርዓት ለልዩነት ብዙ ሥፍራ መኖሩን ያጤኗል፡፡ ለሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሙሉ በእኩልነት መልስ መስጠት ባይቻልም ከቀደሙት ሥርዓታት አንፃር በእጅጉ የተሻለ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ25 የአፍ መፍቻ ቋንቋ ባላነሰ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ይሰጣል፡፡

የቋንቋ መብት በአብዛኛው የሚመለከተው የመንግሥት ተቋማት የሚጠቀሙበትን/አገልግሎት የሚሰጡበትን ቋንቋ ምርጫ የተመለከተ ነው፡፡ አንድም ቋንቋቸው የመንግሥት የሥራ ቋንቋ ያልሆነላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ቋንቋቸው ሲጠፋ እነሱም እንዳይጠፉ ሥነ ልሳናዊ ታጋሽነትን በማስፈን፣ የቋንቋ ማጥፋት ድርጊት እንዳይፈጸም መከላከል ሲሆን፣ በሌላ መልኩ ደግሞ መንግሥት እንደነዚህ ዓይነቶቹን ቋንቋዎች ለትምህርት ቤት፣ ለፍርድ ቤትና ለሌሎች መንግሥታዊ ግልጋሎቶች መግባቢያ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡

በፍርድ ቤት መጠቀምን በተመለከተ እነዚህ ማኅበረሰቦች የሚገኙት በአንድ በተለየ አካባቢ ሆኖ የራሳቸው አስተዳደራዊ ክልል ማለትም ወረዳ፣ ዞን ውስጥ ፍርድ ቤት ካላቸው በቋንቋቸው መዳኘትና ሕጎቹም እንዲተረጎምላቸው ማለት ሲሆን፣ ጉዳዩ የወንጀል ከሆነና የተከሰሱትም በሌላ አካባቢና ቋንቋ ከሆነ በነፃ የትርጉም አገልግሎት ማግኘት ማለት እንጂ በእኔው ቋንቋ የሚናገር ዓቃቤ ሕግ ካልከሰሰኝ፣ ክሱም በቋንቋዬ ካልሆነ፣ ዳኞቹም የእኔን ቋንቋ ተናጋሪ ካልሆኑ አልዳኝም፤ መብቴ ተጥሷል ማለትን ፈጽሞ አይዝም፡፡ ሥነ ልሳናዊ ትዕግሥት ይሄን ያህል እንዲታገስ አይጠበቅም፡፡ ፍትሐዊ የፍርድ ሒደት የሚጠይቀው በነፃ አስተርጓሚ ማግኘትን  ነው፡፡

ሥነ ልሳናዊ ሰብዓዊ መብትን በተመለከተ መንግሥት የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ በግል ሕይወትም ይሁን በየትም ቦታ በየትኛውም ቋንቋ መነጋገር፣ መጻጻፍ ወዘተ. ላይ መንግሥት ምንም ዓይነት ጣልቃ መግባት የለበትም፡፡ ጥንተ ፍጥረቷ ሐሳብን በነፃ ከመግለጽ ጋር መሆኗን ያጤኗል፡፡ በጥንት ዘመን በብዙ አገሮች በአንድ ብሔር አንድ አገር (Nation-State) ለመመሥረት ሲባል አያሌ ዘግናኝ ግፎች ተፈጽመዋል፡፡ ለምሳሌ በፈረንሳይ ከፈረንሳይኛ ውጭ ሲናገር የተገኘ ምላሱ ይቆረጥ ነበር፡፡

በተጨማሪም መንግሥት እነዚህ መብቶች ሲጣሱ የማስከበር ግዴታ አለበት፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ከአማርኛ ቋንቋ ውጪ ሲናገሩ ‹‹የወፍ ቋንቋ››፣ እንደ አፍ መፍቻ ቋንቋ ተናጋሪ አቀላጥፎ ሳይናገሩ ቢቀሩ ‹‹ገመድ አፍ›› እያሉ ማጥላላትን እንዲሁም ብሔርን መሠረት ያደረገ የጥላቻ ንግግርን ወንጀል በማድረግና ሌሎች ዕርምጃዎችን በመውሰድ ግዴታውን መወጣት አለበት፡፡ በተለይ ሁለተኛውን ግዴታ አለመወጣት እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ የሚኖራቸው ጥላቻ እንዲጨምርና አለማወቅን/አለመማርን ወደመምረጥ እንዲያዘነብሉ ስለሚያደርግ ውጤቱ በፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ተቀጣሪና ተወዳዳሪ እንዳይሆኑም ጭምር ያደርጋል፡፡ ይሄንን ግዴታ በተመለከተ ማንኛውም ሰው በቋንቋው ምክንያት ልዩነት ወይም መድልኦ እንዳይደረግበት በሕገ መንግሥቱና በተለያዩ ሕጎች ተደንግጓል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ግዴታዎች በአብዛኛው ቡድንን ከመጠበቅ ይልቅ ወደ ግለሰቦች መብት ያደሉ ናቸው፡፡

ሌላው የመንግሥት ግዴታ ቋንቋው ሊያድግ የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸትና መጣርን ይመለከታል፡፡ ይህን በተመለከተ መንግሥት ላይ ግዴታ የሚጥለው  የሕገ መንግሥት አንቀጽ 90(1) ይመስላል፡፡ ይህም ለጠጥ አድርገን በመተርጎም ቋንቋ የባህል አካል እንደሆነ በመውሰድ መንግሥት ባህሎች በእኩልነት እንዲጎለብቱ የመርዳት ኃላፊነት አለበት የሚለው ብቻ ነው፡፡ ይሄንን የመንግሥት ግዴታን በተመለከተ የሕገ መንግሥት አጽዳቂ ጉባዔያተኞቹ ስለ አንቀጽ 5 ሲወያዩ የአንቀጹ አካል እንዲሆን ቢጠይቁም ስለመብትና ግዴታ በሚደነግገው ክፍል ይካተታል በሚል ምላሽ ታልፏል፡፡ ከዚያ ሕገ መንግሥቱም ለጠቅላላው አለፈው፡፡ ስለሆነም የፖሊሲ አቅጣጫ ከማስቀመጥ በዘለለ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ የተቀመጠ ግዴታን አናገኝም፡፡ ይህ ሁኔታ በእርግጥ እንደማንኛውም የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶች በየጊዜው እያደገ የሚሄድ፣ አቅም የቻለውን ያህል ተጨባጭ ዕርምጃ በመውሰድ የሚወጡት እንጂ በአንዴ የሚፈጸም አለመሆኑን ልብ ማለት ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ የቅማንት ቋንቋ እንዲያድግ፣ ተወላጆቹም በዚሁ ቋንቋ የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን እንዲማሩ ለማድረግ ቢፈለግ የመንግሥት ግዴታ የሚሆነው ፊደል መቅረጽ፣ መዝገበ ቃላት፣ ሌሎች መጽሐፍት ማሰናዳት፣ መምህራን ማሠልጠንና የመሳሰሉት ተግባራት ሲሆኑ፣ እነዚህ ደግሞ በአንድ ጀምበር የሚፈጸሙ ስላልሆኑ መንግሥት በአንድ ጊዜ ግዴታውን ሊወጣ አይችልም፡፡ ይህ ግዴታና መብት ከግለሰብ ይልቅ አትኩሮቱ ወደ ቡድን ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሐረሪ ክልል ቋንቋውን ለማሳደግና ወጥ የሆነ የአጠቃቀም ሥርዓት እንዲኖረው ዳጎስ ያለ መጽሐፍ በማዘጋጀት ሕግ አድርጎ አጽድቆታል፡፡ ፊደላት መርጧል፣ ሞክሼ ሆሄያት የሚባሉት ምን ዓይነት ድምጾችን መወከል እንዳለባቸው ደንግጓል፡፡ አዳዲስ ቃላት ከተፈጠሩ በኋላ ሥራ ላይ ከመዋላቸው በፊት ማለፍ ያለባቸውን ሒደት ይዘረዝራል፡፡ መዝገበ ቃላቱንም አካትቶ ይዟል፡፡  

ስለ ቋንቋ አጠቃቀም ሲነሳ አብሮ የሚነሳው አጨቃጫቂ የመብት ጉዳይ የፊደል/የሆሄያት መረጣን የሚመለከት ነው፡፡ ምንም እንኳን ማንኛውም ብሔር በራሱ ቋንቋ የመናገርና የመጻፍ መብት እንዳላቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ሰነዶች ዕውቅና ቢሰጡም፣ እንደ ሩሲያ ያሉት ግን ማንኛውም ብሔር ከሩሲያኛ ቋንቋ ፊደላት ውጭ መጠቀም እንደማይቻል የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤታቸው ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ዓላማውም የአገር አንድነትን ለማጠናከር ነው፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ስንቃኝ ቋንቋን የማሳደግ መብት እስከምን ድረስ ነው? የሚለው ጉዳይ ወሳኝ ነው፡፡ ብዙ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የላቲንኛ ፊደላትን መጠቀምን መርጠዋል፡፡ የግዕዝ ፊደላት በበቂ ሁኔታ የቋንቋዎቹን ድምፅ መወከል ስላልቻሉ፣ ላቲንኛ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ በረከት ለመቋደስ ቀላል ስለሆነ፣ የግዕዙ ሆሄያት ድምጽን ወደ ንባብ በትክክል ለመቀየር ስለማያስችሉ ነው የሚሉ ናቸው መከራከሪያዎቹ፡፡ በእርግጥ ሌሎች ደግሞ አንዳንድ የግዕዝ ፊደላትን ለድምጾቹ ወካይ እንዲሆኑ ማድረግ ሲቻል (ለምሳሌ መቀሌ መቐሌ እንደሆነው ማለት ነው፡፡ ‹‹ቐ›› በግዕዝ ውስጥ የሌለች መሆኗን ልብ ይሏል፡፡) ለአማርኛ ካላቸው ጥላቻ የመነጨ ብቻ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ከልብ ካዘኑ እንባ አይገድም›› ነበር ነው የክርክሩ ማጠንጠኛ፡፡ በተጨማሪም የአማርኛ ፊደልን አንዴ ካወቁ ለመጻፍ መቅለሉ፣ እንዲሁም አናባቢ ፊደል መጻፍን ስለማይፈልግ ኢኮኖሚያዊ መሆኑም ሌላው ፋይዳው ነው፡፡ በመሆኑም ተማሪዎች የተለያዩ ፊደላትን በማጥናት እንዲቸገሩ ያደርጋል፡፡ ለአማርኛ የሚኖረውን ጥላቻ እንዲጨምር ማበረታቻ ይሆናል፤ ስለዚህ የአገር አንድነት ላይ ጥላውን ማጥላቱ አይቀሬ ነው፣ እንደማንኛውም መብት ገደብ ቢኖረው ጥሩ ነው የሚሉም ምሁራን አሉ፡፡

በኢትዮጵያ የፊደል መረጣን በተመለከተ አንዳንድ ምሁራኖች ብዙ ያልታሰበበት፣ ለአገር አንድነት የማይጠቅም፣ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን በላቲን አጻጻፍና አነባበብ፣ ለእንግሊዝኛና አማርኛ ደግሞ ሌላ ዓይነት ፊደላትና አነባበብ መለማመድ ለሕፃናት ከባድ ነው፡፡ ውጤታማ እንዳይሆን ያደርጋል የሚሉም አሉ፡፡ 

ለማጠቃለል በክልል ደረጃም ቢሆን እንኳን ሕገ መንግሥት ክልላዊ የፖለቲካ ፍላጎት አመላካች የፖለቲካ ፍኖተ ካርታን የሚያሳይ ሰነድ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የሕግ ሰነድም ነው፡፡ እንደ ሕግ ሰነድነቱ ጥበብ በተሞላበት መንገድ ይቀረጻል፣ ይለካል፣ ይጠበቃል፣ እንከኑም በየጊዜው እየተነቀሰ በመውጣት ይሻሻላል፡፡ ይሁን እንጂ ፖለቲካዊ ሁኔታው ሲቀየር ሕጉም ስለሚሻሻል የሲቪልና የፖለቲካ ሕይወት ዓቢይ መመርያ ነው፡፡ ክልላዊ የፖለቲካ ፍላጎት ሲቀየር አብሮ ሕገ መንግሥቱም መለወጡ አይቀሬ ነው፡፡

የክልሎቻችን ሕግጋት መንግሥታት እንደ ግብ አንድነትን ከማምጣት ይልቅ ወደቀደመ በደልና ታሪክ ያዘነበለ ነው፡፡ በክልል ደረጃም ወሳኝ ወይንም ሉዓላዊ እንደሆነ የተወሰኑ ብሔሮችን ብቻ የመረጡ ቢኖሩም፣ ልዩነት ያላደረጉት የተወሰኑት ክልሎችም ቢሆኑ በሌሎች ሕግ መልሰው አግላይ የሆነና ሕገ መንግሥታዊነታቸው አጠያያቂ የሆኑ አሠራሮችን ተከትለዋል፡፡ የቋንቋ አጠቃቀም ቢሆን አንድነትን ሊያመጣ የሚችልበትን መንገድ ማሰቡ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመገንባቱን ሒደት ይደግፋል፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡