አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

የወላጅና ልጅ ግንኙነት እስከምን?

በወላጆችና በልጆች መካከል የሚኖር መልካም ግንኙነትና ግልጽነት ለልጆች ሁለንተናዊ ዕድገት መሠረት ነው፡፡ ልጆች ምን እንደሚፈልጉ፣ ምን እንደሚያስደስታቸው ማወቅ ከወላጆች ይጠበቃል፡፡ ስሜቶቻቸውንና ፍላጎቶቻቸውን በግልጽ እንዲናገሩም ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ልጆቻቸውን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ሊቀርጿቸው ይገባል፡፡ ሆኖም ልማድ፣ አመለካከትና ኑሮን ለማሸነፍ የሚደረግ ትግል በሚፈጥረው ተፅዕኖ ሳቢያ ልጆች ከትምህርት ሲስተጓጎሉ፣ ለሱስና ለወሲብ ጥቃት ሲጋለጡ፣ ጉዳያቸውን ሁሉ ሚስጥር አድርገው የሚደርሱባቸውን ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጥቃት ሲያስተናግዱ ይስተዋላሉ፡፡

ከቤተሰባቸው ጋር ጥሩ ግንኙነትና ግልጽነት ኖሯቸውም ቤተሰባቸውን በመፍራትና በማፈር ጉዳያቸውን በተለይ ከፆታ ግንኙነት ጋር ያለውን ግልጥልጥ አድርገው ለቤተሰቦቻቸው መንገርን የማይደፍሩ፣ በአንፃሩ ደግሞ የጓደኛ ያህል ተቀራርበው የሚወያዩ ቤተሰቦችም አሉ፡፡

የአሥረኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ነው፡፡ የአሥረኛ ክፍልን ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ከመውሰዷ አስቀድሞ እሷና ጓደኞቿ ከሌሎች ጓደኛሞች ቡድን ጋር ፀብ ይገጥማሉ፡፡ ፀቡም ከፆታዊ ግንኙነት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ በቡድን ፀቡ ራሷን መከላከል በመቻሏ ጉዳት ባይደርስባትም ጩቤ ተሰንዝሮባት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

አሁን በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚዲያ ኦፊሰር በመሆን የምታገለግለው ወጣት እንደምትለው፣ በብቸኝነት ካሳደገቻት እናቷ ጋር በአብዛኛው እንደተለመደው የወላጅና የልጅ ዓይነት ሳይሆን የጓደኛ ያህል ግልጽነት ቢኖራትም ይህንን ፀብ አልተናገረችም ነበር፡፡ የአሥረኛ ክፍል ፈተና እስከምትወስድም የተጣላቻቸው ቡድኖች ጉዳት ያደርሱብኛል በሚል በሥጋት ውስጥ ብታሳልፍም ለእናቷ ጉዳዩን ደብቃለች፡፡

ለአሥረኛ ክፍል ተፈትና ውጤት ሲመጣ ግን ሁኔታዎች ተለወጡ፡፡ ኬሚስትሪ ‹‹ቢ›› ስታመጣ፣ ሌሎቹን በሙሉ ኤ አስመዘገበች፡፡ በዚህ ጊዜ ቀድሞውንም ፀብ የነበራቸው ልጆች ቤት ድረስ እየመጡ የስድብ ጥቃት ጀመሩ፡፡ ጉዳዩን ለእናቷ ማሳወቅ እንዳለባትም ተረዳች፡፡

እሷ እንደምትለው፣ ለእናቷ በመንገሯና እናቷ ጣልቃ በመግባቷ የአካባቢው ሰዎችና የፍትህ አካላት ተጨምረውበት ነገሩ በይቅርታ ተቋጭቷል፡፡ ሆኖም እናቷ ሥጋት ስለገባት አዲስ አበባ ልካት ቀሪውን ትምህርቷን በአዳሪ ትምህርት ቤት አጠናቃለች፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለች ከወንድ ጋር ስላላት የፆታ ግንኙነት ለእናቷ የነገረችበትን ሁኔታ ሁሌም እንደምታስታውሰው ትናገራለች፡፡ ‹‹ዩኒቨርሲቲ ስማር አይቼው የወደድኩት ልጅ ነበር፡፡ ደስ ስለሚለኝ ለክፌውም አውቃለሁ፡፡ ለእናቴ ደውዬም ስለሁኔታው ነገርኳት፡፡ ተዋወቂው ነበር ያለችኝ›› ትላለች፡፡ ከጓደኛዋ ጋር ቀጠሮ ሲኖራትም የትና በምን ሰዓት እንደሆነ ለእናቷ ታሳውቅ ነበር፡፡

እናቷ ከልጅነቷ ጀምሮ የዘረጋችላት ነገሮችን በግልጽ የመነጋገር ሥርዓት፣ ለሕይወቷ መቃናት ወሳኝ እንደነበር በመግለጽም፣ ወላጆች ልጆቻቸው በተለይ አፈቀርን፣ ተፈቀርን ወይም በፍቅር ጥያቄ የሚያስቸግረን ሰው አለ ብለው ለወላጅ ሲናገሩ ከልማድና ካለመረዳት በመነጨ ስሜት ከመቆጣት፣ እንደነውር አድርገውም ልጆቻቸውን ከማስደንገጥ ቢቆጠቡ መልካም ነው ትላለች፡፡

ወላጆች የተቻላቸውን ያህል ግልጽ ሆነውም ልጆች ጉዳያቸውን ድብቅ የሚያደርጉበት ጊዜ ይከሰታል፡፡ አንዳንዴም ይህ ድብቅነት በአጭሩ ሊቀጭ የሚችል ችግርን ችላ አስብሎ እስከሞት ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል፡፡

16 ዓመቷን ጥቅምት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ጓደኞቿና ቤተሰቦቿ በተሰበሰቡበት ያከበረችው ኖሃሚን ጥላሁን የአሥረኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን ለመፈተን የወራት ጊዜ ያህል ሲቀራት ነበር የካቲት 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀኑ አሥር ሰዓት ገደማ ሜክሲኮ አካባቢ በስለት ተወግታ ሕይወቷ ያለፈው፡፡

የአንድ ዓመት ከስድስት ወር ሕፃን ሳለች አባቷ መሞቱንና ሕይወቷ እስካለፈበት ድረስ በብቸኝነት እንዳሳደገቻት የምትናገረው የኖሃሚን እናት ወ/ሮ ወይንሸት ወዳጆ፣ ‹‹ልጄ ደረሰች፡፡ አሁን ቀና ብያለሁ ስል ልጄ ባልጠበቅኩት ሁኔታ በሞት ተነጥቃለች፤›› ትላለች፡፡

ወ/ሮ ወይንሸት እንደምትለው፣ ሟች ኖሃሚን ረጋ ያለች ዝምተኛ ልጅ ነበረች፡፡ በመሆኑም በተለይ ዕድሜዋ ከፍ ሲል የወንድ ጓደኛ እንዳላት፣ የምትቸገረው ነገር እንዳለ በማለት ብዙ ጊዜ ትጠይቃት ነበር፡፡ ሆኖም ልጇ ‘ምን ይኖራል ብለሽ ነው?’ ከማለት ውጭ ይደርስባት የነበረ ተፅዕኖ ካለ እንኳን ነግራት እንደማታውቅ ትናገራለች፡፡

ከፍርሃቷ የተነሳም ለልደቷ የጠራቻቸውን ጓደኞች ቤት ለማስገባት ፈርታ እንደነበር፣ ይህንንም በማወቋ ጓደኞቿ እንዲገቡ ማድረጓን ታስታውሳች፡፡ ‹‹ዝም ማለቷ ገሏታል፡፡ ካለፈች በኋላ ከተማሪዎች ብዙ ነገር ሰምቻለሁ፡፡ ቀድሜ ባውቅ ነገሮችን መፍታት እችል ነበር ብዬ እየተቆጨሁ ነው›› ስትል የእንባ ዘለላዎች በጉንጮቿ ላይ እየወረዱ ነበር፡፡

ብዙ ጊዜ ሴቶች ጥቃት ሲደርስባቸው ስለጥቃቱ ተወርቶ ለዚህ ጥቃት ምክንያት ስለሆኑ ነገሮች ሲነሳ ብዙዎች ምክንያት የሚያነሱትን ሲያወግዙ ይሰማሉ፡፡ በተለይ ሞት ተከስቶ ከሆነ ገዳይ ፍርዱን እንዲያገኝ ከመረባረብ ውጭ ሴቶች ለጥቃት እንዳይጋለጡ ምን እንሥራ? የወላጆችና የልጆች ግንኙነት ምን መሆን አለበት? ልጆች በትምህርት ቤት ባላቸው ቆይታ ስለሚገጥሟቸው አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ጉዳዮች እንዴት ግንዛቤ እንፍጠር? በትምህርት ቤት ውስጥ መደበኛውን ትምህርት ከመማር ባለፈ ስለሕይወት ክህሎት እንዴት እናስርፅ የሚሉት እምብዛም ሲወሱ አይሰማም፡፡ በመሆኑም ታዳጊ ሕፃናትም ሆኑ ወጣቶች ከልጅነታቸው ጀምሮ ኃላፊነት ሊሰማቸው ሲገባ ለሱስ፣ ላልተፈለገ የወሲብ ጥቃት ሲጋለጡ ከትምህርታቸው ሲስተጓጎሉ ብሎም በእከሌ ተገደዱ ሲባል ይሰማል፡፡ ይህ እንዳይሆን ግን በወላጅና በልጆች መካከል ያለ መልካም ግብቡነትና ግልጽነት የልጆችን ሁለንተናዊ ሕይወት ለማሳካት መሠረት እንደሆነ የቦስተን ሕፃናት ሆስፒታል በ2013 ያሳተመው ጆርናል ያሳያል፡፡

‹‹ለልጆቻችን የተቃና ሕይወት መሠረት ለመጣል እኛ ያለፍንበት የበዛ ፍርሃትና ድብብቆሽ ወይም ጓዳ መደበቅ ጊዜ አልፎበታል›› የሚሉት የሦስት ልጆች አባት አቶ ቴዎድሮስ፣ ጥሩ አዳማጭ ሆነው ከልጆቻቸው ጋር በግልጽ እንደሚወያዩ ይናገራሉ፡፡

በቤተሰብና በልጆች መካከል ያለው ግንኙነት እየቀነሰ፣ መደበኛውን ትምህርት የሚወስደው ጊዜ እየበዛ፣ ወላጆችም የቤተሰብ ፍላጎት ለመሙላት እየተሯሯጡ ባሉበት ጊዜ፣ ልጆች ከወላጅ ይልቅ ጓደኞቻቸውንና ውጭ የሚያዩትን እንደሚመስሉ በማስታወስ፣ በራሳቸው በኩል ልጆቻቸውን እንደጓደኛ በማድረግ ከትምህርት ባለፈ ስለፆታ ግንኙነትና በአፍላ ዕድሜ ስለሚከሰቱ ባህሪያት በግልጽ እንደሚወያዩ ይገልጻሉ፡፡

‹‹የልጆች ባህሪ ድንገት ይለወጣል፡፡ ትላንት ጥያቄ ስትጠይቂው የነበረው ልጅሽ ዛሬ ላይ ሊቆጣሽ ይችላል፡፡ በመሆኑም ቁጣውን ምን አመጣው? ቤት ውስጥ ምን ተፈጥሮ ነበር? ትምህርት ቤትስ? የዕድሜው ጉዳይ ነው ወይስ ሌላ? ብሎ ወላጅ የልጁን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መከታተል አለበት›› ሲሉም ይመክራሉ፡፡

ቤት ውስጥ ቁጣ የሚበዛባቸው ልጆች ፈሪና ድብቅ እንደሚሆኑ በማስታወስም ወላጆች በተለይም ልጆቻቸው ለአቅመ ሔዋን ሲደርሱ የሚያሳዩዋቸውን ባህሪዎች በመከታተል በግልጽና በትዕግሥት ሊያዳምጧቸውና ሊረዷቸው ይገባል ይላሉ፡፡

ወላጆች በሕይወት ዘመናቸው ክፉውንም ሆነ ደጉን ብሎም የማኅበረሰብ ተፅዕኖን አልፈው ልጆች ለመውለድና ለማሳደግ እስከበቁ ድረስ፣ ልጆቻቸው በአካልም ሆነ በአዕምሮ እንዲበለፅጉ ከልምዳቸው እያካፈሉ ሊያንጿቸው ይገባል ሲሉም ያክላሉ፡፡

የሰው ልጅ ፈጣን ዕድገት የሚያሳይባቸውና የቤተሰብን እገዛ የሚፈልግበት ወቅቶች አሉ፡፡ በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና መምህሩ አቶ እስጢፋኖስ አበራ እንደሚሉት፣ እስከ ሁለት ዓመት ያለው አካላዊ ዕድገት የተፋጠነ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ እንደ ልጆቹ ሁኔታ ከዘጠኝ እስከ 13 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ አካላዊ ዕድገት መፋጠን ይጀምራል፡፡

ሕፃናት ወደ ትምህርት ከመሄዳቸው በፊት ያለው ጊዜ ባህሪያቸውን ለመቅረጽ ወሳኝ ነው፡፡ ከአሥር ዓመት በታች ያሉ ሕፃናትም ትምህርት ቤት ቢውሉም ለወላጆቻቸው ቅርብ ስለሆኑ ወቅቱ ባህሪያቸውን ለማነፅ ያስችላል፡፡ እየጎረመሱ ሲሄዱ ወደጓደኛ የማድላት ወይም ራሴን እችላለሁ የሚል ስሜት ስለሚኖራቸው ከወላጅ የመነጠልና የውጭውን አካል የመቅረብ ዝንባሌ ይኖራቸዋል፡፡ ሆኖም ከስር ጀምሮ ጤናማ ግንኙነት የፈጠሩ ወላጆች የጎላ መለያየት አይገጥማቸውም፡፡ ልጆች ከተፈጥሮአዊ ዕድገት ጋር ተያይዞ ራሴን አውቃለሁ የሚል ስሜት ቢመጣባቸውም ከስር ጀምሮ የተቀረጹበት አስተዳደግ ስለሚኖር በልጆች ላይ ድብቅነቱ አይጎላም፡፡

ቸልተኛ የሚባሉና ከልጆቻቸው ጋር ብዙም ቀረቤታ የሌላቸው፣ አምባገነንና ልጆችን ከማቅረብና ከማወያየት ይልቅ በጉልበት ሥነ ሥርዓት ለማስያዝ ጫና የሚያደርጉና ልጆቻቸውን በነፃነት (ዲሞክራት) ሆነው የሚያሳድጉ የወላጅ ዓይነት መኖራቸው የልጆቹንም የባህሪ ስብጥር እንደአስተዳደጋቸው ያደርገዋል፡፡

ዴሞክራት በሆኑ ቤተሰቦች ውስጥ ያደጉ ልጆችም ባብዛኛው ችግራቸውን በግልጽ የሚናገሩና በራሳቸው መቆም የሚችሉ ናቸው፡፡ ወደአገራችን ሲመጣ ግን ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት ማሳደግ እንዳለባቸው እምብዛም አያውቁም፡፡ በመሆኑም በአብዛኛው በልጆችና በወላጆች መካከል ክፍተቶች ይስተዋላሉ፡፡

እንደ አቶ እስጢፋኖስ፣ በትምህርት ቤቶች አካባቢ ከትምህርት አቀባበልና ከፆታዊ ግንኙነት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ክፍተቶችም ከወላጅ አስተዳደግ የሚመነጩ ናቸው፡፡

በሥነ ልቦና ፍልስፍና፣ በልጆች አስተዳደግ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ስምንት ዓመታት ወሳኝ ናቸው፡፡ ባህሪና አመለካከት ተቀርፆ የሚያልቀውም በእነዚህ ዕድሜ ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው የማሰማመርና የመቀባባት ያህል ነው፡፡

ልጆች እስከ ስምንት ዓመታቸው በባህሪ ሳይታነጹ ቀርተው፣ ከጎረመሱ በኋላ የሚያሳዩትን ባህሪ በምን መልኩ ማረቅ ይቻላል የሚለው ሊነሳ ይችላል፡፡ አቶ እስጢፋኖስ እንደሚሉት፣ ወላጆች በጉርምስና ጊዜ ሳይሆን እስከ ስምንት ዓመት ባለው ዕድሜ ውስጥ ሥራቸውን መሥራት እንደሚገባቸው ይመክራሉ፡፡ ሆኖም ወላጆች እዚህ ላይ ያላቸው ግንዛቤ በቂ ስላልሆነ ይህንን አያደርጉትም፡፡

ልጆችና ወላጆች አብረው የሚቀመጡበት ሳይሆን የሚለያዩበት ጊዜ ይበልጣል፡፡ ሆኖም በቤት ውስጥ ቢያንስ ለእራት አብሮ መቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ከልጆች ጋር ስለውሏቸው ለማውራት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡ ሆኖም በእንደዚህ ዓይነት መድረክ ልጆች ስለማፍቀርና መፈቀር ሲያነሱ እንደነውር ቆጥረው የሚያስደነግጡ ቤተሰቦች አሉ፡፡

ለአቅመ አዳምና ሔዋን የደረሱ ልጆች ቢያፈቅሩ፣ ቢፈቀሩ፣ ያፈቀራትን/ውን ባታገኝ/ባያገኝና ይህን ሁኔታ ወላጆች ከልጆቻቸው ወይም ከሌሎች ሰዎች ቢሰሙ ምን ዓይነት ምላሽ ሊኖራቸው ይገባል ስንል ለአቶ እስጢፋኖስ ጥያቄ አንስተን ነበር፡፡

ከአሥር ዓመት ጀምሮ በሴቶች የጡት ማጎጥጎጥ፣ በመራቢያ አካላት ስፍራ ፀጉር ማብቀል የዳሌ መስፋት ሲጀምሩ፣ በወንዶች ደግሞ የድምፅ መጎርነን፣ ጡንቻ የማውጣትና በሰውነት ላይ ፀጉር መታየት ይጀምራል፡፡ እነዚህ ክስተቶች የሆርሞን ለውጥ ስለሚያመጡ የተለየ አስተሳሰብና አመለካከት ይመጣል፡፡ ይህ ሴቶች ወደ ወንዶች ወንዶችም ወደ ሴቶች እንዲመለከቱ ያደርጋል፡፡ ማፍቀርና መፈቀርም ይፈጠራል፡፡

ልጆች ስለነዚህ ክስተቶች አውቀውና ዝግጁ ሆነው ቢያድጉ ቢያፈቅሩም፣ ቢፈቀሩም የፍቅር ጥያቄ ቢቀርብላቸውም አይደነግጡም፡፡ እንዴት መወጣት እንደሚችሉም ያውቃሉ፡፡ ከልጅነታቸው ያልተቀረፁት ደግሞ ወዳልተፈለገ ዕርምጃ ይገባሉ፡፡ ስለሆነም ወላጆች ልጆቻቸው ተፈጥሯዊ ክስተቶች ሲያጋጥማቸው ከመጮህና ከመቆጣት ይልቅ ሊመክሯቸው ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ልጆች ችግራቸውን ይደብቃሉ ያፍናሉ፡፡ ይህ የተዳፈነ ስሜትም በምክር ሊፈታ የሚችል ጉዳይን ወደ መጥፎ ይለውጠዋል፡፡

ልጆችን በግልጽ አወያይቶና ኃላፊነት እንዳለባቸው ነግሮ የማሳደጉን ሰፊ ድርሻ ወላጆች ቢወስዱም በትምህርት ቤት ውስጥ የሚኖረው ሁኔታም ወሳኝ ነው፡፡ በመሆኑም ከወላጆች ኃላፊነት ጎን ለጎን የሥርዓተ ፆታ ትምህርት በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ራሱን ችሎ መካተት አለበት ይላሉ፡፡ የውጭ አገሮች ተማሪዎችም የሥርዓተ ጾታ ትምህርትን በሥርዓተ ትምህርቱ ተካቶላቸውና የራሱ ፕሮግራም ተበጅቶለት ይማሩታል፡፡

በአገራችን ሲታይ የሥርዓተ ፆታ ትምህርት በአብዛኛው በሥነ ሕይወት ትምህርት ውስጥ ተካቶ ለተማሪዎች የሚቀርብ ቢሆንም፣ በመደበኛው ትምህርት ፈተና ለማለፍ ካልሆነ በስተቀር የሕይወት ክህሎት የሚያስጨብጥ አይደለም፡፡ ስለሆነም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

በየትምህርት ቤቶች ያሉ የሥነ ልቦና አማካሪዎች በምን መልኩ ይሠራሉ? አሉስ ወይ? ምን ያህልስ ወደ ተማሪዎች ይቀርባሉ? የሚለውም ሌላው መታየት ያለበት ነው፡፡

እንደ አቶ እስጢፋኖስ፣ የጋይዳንስና ካውንስሊንግ ሥራ ታቅዶና በቂ ባለሙያም ተመድቦለት ሙሉ ዓመቱን የሚሠራ፣ ተማሪዎች በር እስኪያንኳኩ የሚጠብቅ ሳይሆን ወደ ተማሪዎች ቀርቦ መሥራት አለበት፡፡