የዕድገት አቀበት ከባድነት በተጓዡ መንገድ አመራረጥና አካሄድም ይወሰናል

በጳውሎስ ደሌ

            የዓለምን ኢኮኖሚ አሿሪነት ወደ ደቡብ እስያ እያዘነበለ ባለበት በዛሬው ጊዜ ውስጥ አገራችን ኢዱስትሪያዊ የአኮኖሚ መገንባት ግቧን የምታሳካው በምን ዓይነት ሥልት ነው? የልማታችን አካሄድ መልስ አግኝቶ አብቅቶለታል? የፖለቲካ ኢኮኖሚ ጠበብት አበክረው ሊያብላሉትና እንደ ሁኔታዎች ለውጥ የሚቃና መልስ ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም በዚሁ እምነት መሠረት ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጥቂት ነጥቦች ያቀርባል፡፡

ምዕራብም ላቀ ደቡብ ምሥራቅ ያለንበት የዓለም ኢኮኖሚ በትርፍ አጋባሽነት ሩጫ የሚመራ እንደመሆኑ፣ ነባር ጌታም ላይ ይሁን አዲስ ጌታ ላይ መጠምጠም ለጥቃት ያጋልጣል፡፡ ድህነትን ለማሸነፍና ኢንዱስትሪ ለመገንባት የሚታገል አገር ማንም ላይ ከመጣበቅ ርቆ ከሁለቱም ጎራዎች ብልህ አትራፊ የመሆን ጨዋታ ይጠበቅበታል፡፡

ይኸውም፡-

  1. የአንዱ ወይም የሌላው ታላቅ አገር አጨብጫቢ ከሚያደርግና ሉዓላዊ ጥቅምን ሊጎዳ ከሚችል አዘንባይነት መራቅ፣ እንዲሁም በፓርቲዎች መካከል የሠለጠነና የተለሳለሰ ግንኙነት እንዲፈጠር በማድረግና በሕግ ጥሰት፣ በመብት ረገጣና በመሳሰሉት ኢትዮጵያ ላይ የሚደርሱ ግድፈቶችን የሚበትኑ መልካም መሻሻሎችን በማሟላት ከሁሉም አቅጣጫ የልማትን እገዛንና የቀጥታ ኢንቨስትመንት ሳቢነትን መጨመር የዕድገት ትግልን ፈተና ለማቅለል መሠረታዊ ነው፡፡ ይኼንን ባለማድረጋችን ልማታችን ለሚቀርበት ጥቅምና ለሚገጥመው መሰናክል ከራሳችን ሌላ ማንንም ተጠያቂ ማድረግ አንችልም፡፡ በመንገድ ግንባታዎች ውስጥ የቻይኖች ተቋራጭነት ጎልቶ የሚታየው ከዚያ የሚገኝ ብድር አስገድዶን? ወይስ የራሳችንን የግንባታ አቅም ማሳደግ አቅቶን? (የታላቅ አገር ልዩ ወዳጅ ካለን ወዳጅነታችን የዕድገት በተለይም የቴክኖሎጂ ሽግግር ጥቅም መቆንጠጥ አለበት፡፡)

ኢንቨስተር መሰል ለሆኑ ሥውር አጭበርባሪዎች በማያጋልጥ ጥንቃቄ፣ የአዋጪ ቴክኖሎጂና የሙያ ሽግግርን የሚያስገኙ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ከየትኛውም ወገን በሽርክናም ሆነ በተናጠል የመሳብ አቅማችንን ማጎልበት ልዩ ትኩረት የሚሻ ተግባር ነው፡፡ በዚህ አጠቃላይ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ግን በረዥም ዘመን የተካበተ ጥበብና ልምድ ካለው ምዕራብ (ጃፓንን ጨምሮ) ጥራት ያላቸው ቴክኖሎጂዎችን በመሳብ ላይ ልዩ ጥረት ማድረግ፣ ካፒታል ወደ ሌላ አገር አሻግሮ በማሠራት ረገድ ጀማሪ የሆኑ አዲስ መጥ ኃይሎች ሰጥቶ በመረከብ ጥበብ ገና ያልተካኑ እንደመሆናቸው፣ ትርፋችን ኪሳራ እንዳይሆን ነቅቶ መጠበቅ ሁሌም መረሳት የለባቸውም፡፡

በረዥም ጊዜ ከሚከፈሉና በወሳኝ ፕሮጀክቶች ላይ ከሚውሉ ባለአነስተኛ ወለድ ብድሮች በቀር፣ ባለከፍተኛ ወለድ የአጭር ጊዜ ብድሮችን ከየትም ወገን ቢሆን መራቅ፣ እንደዚሁም፣ የውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች አዲስ የሚፈጠር ትርፋቸውን ለማስፋፊያና አዳዲስ ሥራ ላይ ለመሠማራት እንዲያውሉ በማበረታቻ ሥርዓት መገፋፋት ተዛምደው ሊሠራባቸው ይገባል፡፡

2. የራስን ውስጣዊ አቅም ከማይደርቅና ከሚሰፋ ምንጭ እንዲፈልቅ ማድረግ ለአሮጌም ይሁን ለአዲስ መጥ ኃያል ሳይሽቆጠቆጡ የዕድገትን ትግል ለመምራት አንፃራዊ ነፃነት ያስገኛል፡፡ የውስጥ አቅም በምን በምን?

በመንግሥትና በግል በኩል ያሉ ሀብት አባካኝና አጥፊ አኗኗሮችን ያጨመተ የቆጣቢነት ባህል ማዳበር፣ ይኼንንም የሚያግዝ የፖለቲካ ሥራና ባለባንኮች የአስቀማጩን ገንዘብ በብላሽ/በኪሳራ ከማስቀመጥ ያልተሻለውን የቁጠባ ወለድ መጠን ማሻሻልና ግሽበትን ማርገብ፡፡

ገና ብቅ ሲሉ ቅንጦትና መኪና ላይ ከመንጠላጠል ተቆጥቦ ገንዘብን  ማሠራትንና በአንድ ሙያና በአንድ ሥራ ላይ ሳይወሰኑ ገቢን ለማስፋት መጣጣርን የሚያዳብር፣ አንድ የተወሰነ የክፍያ ልክ አስቀምጦ እሱን ካላገኘሁኝ እያሉ ሲንገላጀጁ መዋልን የሚቀይር (የራስ ሁኔታን ሥራው የሚፈጀውን ጊዜ፣ የሥራውን ቅለትና ክብደት እያዩ መተጣጠፍን የሚያስፋፋ) አመለካከት ማስረፅ፡፡

በየደረጃው ያለን ማሠልጠኛ የሰላ የችሎታ ማፍሪያ እንዲሆን ማብቃት፡፡

የቴክኖሎጂውን ክምችትና የማዳረስ ሥርዓትን አበልፅጎ ልዩ ልዩ የሥራ አማራጮችን ማስተዋወቅ (የኢኮኖሚያችን የተሳሰረ ዕድገት ሳይዘነጋ)፣ ከሕዝብ ውስጥ የሚፈልቁ አዋጭ የሥራ ሐሳቦችንና ፈጠራዎችን ከቁጠባ ጋር በተያያዘ ሥልት ተጨባጭ እንዲሆኑ መደገፍ፣ ለልማት የሚውል እውቀትን ለማሰስ ኢንተርኔት ሁነኛ መሣሪያ መሆኑን አስቦ አገልግሎቱን ፈጣንና ርካሽ ማድረግ፡፡

ችግራችን ‹‹ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል›› የሚባለውን የሚጨምር ነውና በመንግሥትም ይሁን በግል ደረጃ አፍንጫ ሥር ያሉ ሥራዎችንም የማስተዋል ንቁነትን ማዳበር ይጠበቅብናል፡፡ አራት አምስት ቅጠል ያላቸው ባለቀለም የልጆች መጻሕፍት ከህንድ እያመጣን በመቶ ቤት ብር የምንሸጠውና የምንገዛው (እዚህ አዘጋጅቶ ባነሰ ዋጋ ገፍ የማትረፍ ዕድሉ ባልተነካበት አገር ውስጥ) የእውቀት አቅም ጠፍቶ አይደለም፡፡

በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በቴክኖሎጂ አሻጋሪነትና በውጭ ምንዛሪ መጋቢነት የሚገለጽ የልማት አርበኝነት ሙሉና እመርታዊ የሚያደርግ፣ የውስጥ ኮንትሮባንድ ጥቃትን በአብዛኛው የሚገታ ማሻሻያና ለውጥ ማድረግ፡፡

ለውጭ ሸቀጥ ባርነት የዳረገንን የውጭ ዕቃ አምላኪነትን ከማዳከምና አርበኝነትን ከማሳደግ ጋር በተያያዘ ሁኔታ፣ ለውጭም ሆነ ለውስጥም መናኛ ሥራ ፍዝ ተጠቂ ካልሆነ ሸማችነት ጋር እጅና ጓንት የሆነ የጥራት ቁጥጥርን መሠረት መጣል፣ በጥራት አምርተውም ይሁን ጥራቱ የተሟላ ዕቃ አስገብተው ለገበያ የሚያቀርቡ ወገኖችን የሚንከባከብ ሥልት መፍጠር፣ በእነዚህ መንገዶች የውስጥ ምርትን ጥራት ቀጣይ ማድረግና የውጭ መናኛ/ሐሰተኛ ሥራዎችን ወረርሽን ከአገር ውስጥ ገበያ ማባረር፡፡

ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በጥራትና በመጠን ጉድለት የማይታማ ዝና እንዲያገኙ ጠንክሮ መሥራት፣ በተለይም ወደ አሜሪካና ወደ አውሮፓ በሚላኩ ምርቶች ላይ የጥራትና የደረጃ ስኬት ሰፊ ገበያን የሚጠራ ወሳኝ የተወዳዳሪነት ብልጫ መሆኑን ከወዲሁ ማወ፡፡

እነዚህን ባካተተ የለውጥ ሒደት የአገሪቱ የውጭ ንግድ ከጉድለት ወጥቶ አትራፊ እንዲሆን ማብቃት ለምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

3. ወደበለፀጉ አገሮች ምርትን በመላክ ላይ የተንጠለጠለ ኢኮኖሚ በዓለም ገበያ ላይ በሚደርስ ቀውስና ሁሉም በሚሮጥበት የገበያ ሽሚያና በማዕቀብ ለመመታት የተጋለጠ መሆኑ አይቀርም፡፡ ከዚህ አደጋ ለመጠንቀቅ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ቅርንጫፎች እርስ በርስ ማመጋገብ፣ የኢንዱስትሪያዊ ዕድገትን ከሕዝብ የኑሮ ደረጃ ዕድገትና የፍጆታ ስፋት ጋር ማገናዘብ፣ እንዲሁም ከአካባቢ አገሮች ጋር የንግድ ትስስር መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡

4. የገንዘብ ምንዛሪ ዋጋን ዝቅ በማድረግ ወደ ውጭ የሚላክ ንግድን ማሳደግ፣ በመሸጫ ዋጋ ትንሽ ተጎድቶ ብዙ በመሸጥ ለማትረፍ ያለመ ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ አተራረፍ ውስጥ (በአብዛኛው ሁኔታ) ዋናውን ውለታ የሚሸከመው የሠራተኛ ጉልበት ርካሽነት ነው፡፡ የአገር ውስጥ ገንዘብን (ብርን) የውጭ የምንዛሪ ዋጋ ዝቅ የማድረጉ ዕርምጃ የማምረቻ ወጪን የማናር ውጤት ካስከተለ ግን ወደ ውጭ ላኪው በዝቅተኛ ዋጋ ተወዳዳሪ ለመሆን ከመቸገሩም አልፎ፣ ለሚያስገኘው ለእያንዳንዱ የውጭ ምንዛሪ የሚከፈለው ተጨማሪ የብር መጠን እውነተኛ ገቢ አይሆንለትም፡፡

በብር ምንዛሪ ዋጋ ቅነሳ ምክንያት ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎች ዋጋ ሲያሻቅብ፣ ከጥራት ጋር በተሻለ ዋጋ የሚገኙ የአገር ውስጥ አማራጮች እስከሌሉ ድረስ፣ ከውጭ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ተፅዕኖ በቆሎ ድረስ ሄዶ የዋጋ ለውጥ ማስከተሉ የማይቀርና የማያስደንቅ ነው፡፡

ስለዚህ በምንዛሪ ቅነሳ ወደ ውጭ ላኪነትንም ሆነ የአገር ውስጥ አምራችነትን ለማበረታታት ሲፈለግ ከምንዛሪ መጠን ለውጥ ያለፈ ጥንቃቄና ሥራ ያስፈልጋል፡፡ የአገር ውስጥ አምራች ከውጭ የሚገቡ የተወሰኑ የምርት ግብዓቶች ቢኖሩበት እንኳ፣ በዚያ በኩል የሚመጣ የውጭ ጭማሪን በሌሎች ማካካሻዎች ተቋቁሞ፣ በአገር ገበያ ውስጥ በዋጋና በጥራት የውጭ ዕቃዎችን የማሸነፍ አቅም እንዲያጎለብት የመርዳት መንግሥታዊ ኃላፊነት ግድ ነው፡፡ ይኼ ኃላፊነት የውጭ ንግድን ከመጥቀምም ጋር በቀጥታ የተሳሰረ ነው፡፡

የመሠረታዊ ኑሮ ፍጆታዎች ዋጋ ሰማይ እየወጣ ከሄደ ወጪ ንግዱም ርካሽ የአመራረት ወጪን ተመርኩዞ የማትረፍ ዕድሉ በዚያው ልክ ያንሳል፡፡ ኢንዱስትሪያዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማድረግ እስከታቀደ ድረስም በአጠቃላይ መሠረታዊ ኑሮ፣ በፍጆታዎች የዋጋ ግሽበት እንዳይደቆስ የሚያስችል ፖሊሲ መከተል የማይታለፍ ነው፡፡

በ1998/1999 ዓ.ም. ገበሬውን መታረቂያ በኅብረት ሥራና በመንግሥታዊ አካል በኩል በተሰቀለ ዋጋ እየገዙ ገቢው እንዲጨምር እንደተደረገ ሁሉ፣ ከዚያ ወዲህና ዛሬም የገበሬውን የድምፅ ‹‹ወገናዊነት›› እና ዋስትና እያሰቡ ‹‹ገበሬው ወደፊትም በዋጋ መውረድ እንዳይመታ የኢሕአዴግ መንግሥት ይጠብቀዋል›› ማለትና የናረ የእህል ዋጋ እንዳይቀንስ መታገል ልማትን አያዛልቅም፡፡ የናረ ኑሮ ማደግ እስከቀጠለ ድረስ ባልጋሸበ የሠራተኛ ደመወዝ ኢንዱስትሪያዊ ሸቀጥን አምርቶ በዋጋ የውጭዎቹን መወዳደር ከባድ ይሆናል፡፡

ገበሬው ያላግባብ እንዳይነጠቅ የሚጣረውን ያህል ለሸማቹም መጣር አግባብ ነው፡፡ ለዚህም ገበያ ውስጥ ጣልቃ እየገቡ ዋጋን ከመቆጣጠር ይበልጥ የግብርና የአመራረት ወጪን በሚቀንሱ ለውጦች የገበሬውን ገቢ ማሳደግ ሊተኮርበት ይገባል፡፡ ከውጭ የሚገባ አርቲፊሻል ማዳበሪያ አገር ውስጥ እንዲመረት ማድረግ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተጠቃሚነትን ከመሬት የእርከን ዘዴ ጋር ማስፋት፣ ሰው ሠራሽ የተባይ ማጥፊያ ወጪን በተፈጥሯዊ ተባይ ማጥፊያና በሥነ ሕይወታዊ ዘዴ መቀነስ፣ የምርጥ ዘር ዋጋ ውድነትን በተስፋፋ ሕዝባዊ የማባዛት መንገዶች መቀነስ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ የገበሬው ገቢ በተጀመረው ዓይነት ከዘርፈ ብዙ የሥራ እንቅስቃሴዎች ጋር መያያዙም በሆነ የምርት ዋጋ መውደቅ ምክንያት እንዳይመታና የሚያዋጣ ዋጋ እስኪያገኝ ድረስ ምርቱን ለማቆየት አቅም ይሰጠዋል፡፡ ቀልጣፋ የመንገድ ግንኙነቶችና የገበያ ጣቢያዎች መስፋፋትም የአምራችንም ሆነ የአከፋፋይ ወጪን ያቀላሉ፡፡ የአገር ውስጥ ምርቶችንም ሆነ ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦችን በማከፋፈል በኩል ያለውን በጥቂቶች መረብ የሚቃኝ የገበያ ሁኔታ ብዙ ተሳታፊ ያለበት ውድድራዊና አጭር እንዲሆን አድርጎ መግራት ለሁሉም ወገን ጥቅም ነው፡፡

ደመወዝተኛውን በተመለከተ ገና ደመወዝ ተጨመረ ሲባል (አዲስ ገንዘብ ወደ ገበያ ገብቶ ሳያጨናንቅ) ከጭማሪው እኔም ድርሻ ይገባኛል እንደ ማለት ያለ የዋጋ ጭማሪ ወዲያው በሚታይበት አገር፣ በአዋጅ ደመወዝ መጨመር ብርንና ጭማሪውን ገለባ ከማድረግ በቀር ብዙም የሚፈይድ አይደለም፡፡ በአዋጅና በአንዴ የሚደረግን ጭማሪ ትቶ በመደበኛ መንገድ መጠቀም በብዙ መልኩ የተሻለ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይበቃም፡፡ ደመወዝ መጨመር የሚባል ነገር የወረቀት ብር ቁጥርን ከመጨመር በላይ በዋናነት በአጠቃላይ በኅብረተሰብ ኑሮ መሻሻል በኩል በሚመጣ የኑሮ መቅለል የሚገለጽ ‹‹ጭማሪ››ን መቆንጠጥ ይኖርበታል፡፡

ቀደም ብሎ ስለገጠሩ እንደተጠቀሰው በከተማም ያለው ሕዝብ በአቅሙ ሊገዛው የሚችል የምግብ፣ የመጠለያ፣ የመጓጓዣ፣ የትምህርት፣ የጤና አገልግሎት፣ ወዘተ አቅርቦት መኖር አለበት፡፡ ከመንግሥት ትምህርት ቤቶችና ከጤና ተቋማት መስፋፋት ጋር አስተማማኝ አገልግሎት ከሌለ የተሻለ ነገር ፍለጋ ጥሪት ማራገፍ አይቀርም፡፡ የመጓጓዣ፣ የምግብና የመጠለያ አገልግሎት ዋጋ ለወሬም የማይመች ሆኗል፡፡ እኛ የምንለው በአንድ ጊዜ ሁሉም ችግር ካልተወገደ አይደለም፡፡ ትልቅ ችግር የሆነው ሁሉም እንደ አቅሙ ሊኖርበት የሚችልበት የኑሮ ኮሪደር ወይም እርከን፣ በተለይም ከ1998 ዓ.ም. በኋላ መናጋቱ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ውስጥ የመንገድ ዳር ሻይ ሦስት ብር፣ አንድ ሽልጦ ሁለት ብር፣ የተጠበሰ አገዳ በቆሎ ሦስት/አራት ብር ይሸጣል፡፡ በየጓዳ ጎድጓዳው ተውተፍትፎ የሚሠራ ቤት ትንሽ ችግር እንዳያቀል የባለቤቶችና የቤት ፈላጊዎች አለመመጣጠን፣ የግንባታ ፈቃዱና የግንባታው ወጪው ገትሮ ይዟል፡፡ የሙሉ ክፍያም ሆነ የዱቤ ግዢ አቅም ያለውን ዜጋ ወደ አዲስ የቤት ግንባታ በሰፊው እያሽጋገረ ውድቅዳቂውን ቤት ለደሃው መተንፈሻ ማድረግ የተሳካለት፣ ወይም በዝቅተኛ የኪራይ ቤት ፕሮጀክት ያስተናገደ ፕሮግራም የለም፡፡ የተጀመረው የጋራ ቤት ልማት በአዝጋሚነቱ ችግር ከመቆንጠር አላለፈም፡፡ አፍርሶ ግንባታ ከተማ በማዳረስ ረገድ ጥሩ ቢሆንም የቤት ችግርን ፈቺነቱ አከራካሪ ነው፡፡ ወጣም ወረደ ከማዕድ ቤት የማይሻል አንድ ክፍል ቤት ብር 1,500 ይከራያል፡፡ በዚህ ሁኔታ የባለዝቅተኛ ገቢ ኑሮ ‹‹የአስማት ኑሮ›› በሚል ቀልድ ቢገለጽ አይገርምም፡፡ ከማደሪያና ከሆድ አልፎ የመጓጓዣውን፣ የትምህርቱን፣ ወዘተ ወጪ ማሰብ ለአንዳንዱ አጉል መቀናጣት ሊመስልም ይችላል፡፡ እነዚህን የመሳሰሉት ችግሮች የልማት እጥረትና ሰው ሠራሽ ምክንያት ያላቸው ናቸው፡፡

5. ለማጠቃለል ለተጠቃቀሱት ችግሮች መፍትሔ የማግኘት ዕዳ መንግሥት ላይ ብቻ የሚጣል አይለደም፡፡ ነገር ግን በመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ ያለ የእውቀትና የብልኃት አቅም በአግባቡ አነቃንቆ መፍትሔ ላይ ማዋል ይጠበቅበታል፡፡ ይኼንን ተግባር ለማሳካትም ሕዝብ የፈቀደውና የሚሰማው መንግሥት በተከታታይ መኖሩ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይኼ ከተሟላ ተራራም ይገፋል፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡