አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

የጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስትመንት ለምን ተዳከመ?

በጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስተሮች ኅብረት ሥራ ማኅበር

የጋምቤላ ሕዝብ ወኪል የሆነው የጋምቤላ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና የፌዴራል መንግሥት ክልሉን በማልማት የክልሉ ሕዝብ የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል፣ ቆራጦች የሆኑና ራሳቸውንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልማታዊ ዜጎችና አጋሮች በክልሉ ልማት እንዲሳተፉ በይፋ ጋበዙ። ጋምቤላ ታዳጊ ክልሎች ተብለው ከሚጠሩ የአገራችን ክልሎች በጣም በዝቅተኛ ደረጃ የምትገኝ ክልል ናት። የተሻለ ምቾት፣ ብዙ ባለሀብት ከሰፈረባትና ብዙ ገንዘብ ከሚንሸራሸርባት ከመዲናችን አዲስ አበባ ጠረፍ አካባቢ ያለችው ጋምቤላ ከ780 ኪሎ ሜትር በላይ ርቃ ትገኛለች። የክልልና ፌዴራል መንግሥት ጋምቤላ ሰፊ ለም የመሬት ሀብት እንዳላት በማውሳት፣ ከመሬቷ ፍሬ አፍርተው ለገበያ በማቅረብ የሚያለሟትና የምታለማቸው ዜጎች ለማግኘት በሰፊውና በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርቧል።

አቤት! የኛ አገር ምድር! የመንግሥታችን ፖሊሲና የልማት አቅጣጫ ሰንቀን በላብ በወዛችን ጥረን ግረን አብረንሽ እናድጋለን ብለን የሞቀ ጎጇችንና ቤተሰቦቻችን ተሰነባብተን ጥሪውን የተቀበልን ጥቂት ዜጎች፣ የእርሻ ኢንቨስተሮች ለመሆን የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ ጋምቤላ ደረስን። እርሻ ከባድ የኢንቨስትመንት ዘርፍ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከተማ የለመደ ባለሀብት የማይመርጠው ዘርፍ መሆኑ ይታወቃል። ቢሆንም ከጋምቤላ ሕዝብና መንግሥት ጋር ተባብረን ለፍሬ እንበቃለን ብለን ተስፋ የሰነቅን ልማታዊ ዜጎች ከየአቅጣጫው መጥተን ጋምቤላ ተገናኘን። ጋምቤላም ቀድሞ ለደረሰ ቅድሚያ በሚል መርህ ‹‹እንኳን ደህና መጣቹሁ›› ብላ ታስተናግደን ጀመር።                                  

የጋምቤላ መሬቶች ለሜካናይዝድ እርሻ ልማት የተዘጋጁ አይደሉም። እኛ ወደ እርሻ ኢንቨስትመንት ስንገባ በከተማዋ ከሁለት ያልበለጡ ሆቴሎች፣ ከከተማዋ ወደ እርሻ ቦታ የሚወስድ መንገድ አልነበረም። ከሁሉም በላይ አስተማማኝ ያልሆነ ፀጥታ፣ የጉልበት ሠራተኛ ያለመኖር፣ ንፁህ ውኃ ያለማግኘት፣ መብራትና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ባልነበሩበት ሁኔታ ነው። ታድያ ቀድም ባለ የሕይወት ጉዟችን በሌላ ቦታ ያፈራነውን ሀብትና ንብረት አፍስሰን ክልሉን ለማልማት የደፈርን ቆራጥ ኢትዮጵያዊያን በሞፈርና በቀንበር ሳይሆን በትራክተር፣ በበሬ ጉልበት ሳይሆን በነዳጅ ኃይል፣ ሜካናይዝድ ፋርም ለመፍጠር በጋምቤላ መሬቶች ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀመርን። ይኼን ያደረግንበት ጊዜ ስለጋምቤላ መልካም ምሥል ባልነበረበት ጊዜ መሆኑ ማስታወስ ተገቢ ይመስለናል።                          

እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ሆነን ተፈጥሮን ለእርሻ ምቹ ለማድረግ ከተፈጥሮ ጋር ልማታዊ ትግል አካሄድን። መሠረተ ልማት በሌለበት የመሬት ልማት ለማከናወን፣ ሕይወት፣ አካልና ንብረት ማጣት ለልማቱ የሚከፈል ዋጋ ነበር። የመሬት ልማት ሥራውን ስትታገል ከርመህ አንድ የአገሪቱ ልማት የማይፈልግ ‹ክፉ› ወይም ‹ነገሩ ያልገባው› ሰውም ሊጎዳህ ይችላል። በመሆኑም ብዙ ዓይነት ሰው ሠራሽ የደኅንነት ችግሮች ነበሩ ይኼም ታልፏል። ለእርሻ ዝግጁ ያልሆኑ ሰፋፊ ለም መሬቶች የእርሻ ማሳ እንዲሆኑ ለማልማት የሚከናወን ተግባር እንዲሁ በጥላ ሥር ሆነህ ዕቃን በመሸጥና በመለወጥ እንደሚገኝ ሀብት ተመኝተህ የምትገባበት አይደለም። አዲስ የአየር ፀባይ፣ አዲስ መንደር፣ ብዙ ያልተጠበቀ ነገር መጋፈጥ ግድ ይላል፡፡ ቆራጥነትንም ይጠይቃል።

ከዚህ በላይ ዘር መሬት ላይ በትነህ፣ በስብሶ፣ ተመልሶ በቅሎ፣ አረም ታርሞ፣ ከነፍሳት ታድገህ፣ ታጭዶ፣ ተወቅቶ፣ ለገበያ ቀርቦ ይኼ ሁሉ ረጅም መንገድ ተጉዞ ከቀናህ የበተንከውን ትሰበስባለህ፡፡ ለፍሬ ለአምሃ ትበቃለህ። ገበያና ኢንዱስትሪ ይንቀሳቀሳሉ። እርሻና የእርሻ ሰዎች ሕይወት እንዲህ መሆኑ የገባን ዜጎች፣ የአገራችንን ፀጋ አነቃቅተን ወሳኝ የኢኮኖሚ አውታር በሆነው የእርሻ ኢንቨስትመንት ተሠማራን።                  

የጋምቤላን የልማት ጥሪ ተቀብለን በልበ ሙሉነት የሄድን ኢንቨስተሮች ሀብትና ንብረታችንን ይዘን እንጂ፣ የመንግሥት ብድር አመቻችተን እንዳልነበረ መታወቅ አለበት። ይኼ እውነታ መረሳት የሌለበት ሀቅ ነው። በተጨማሪ ኢንቨስተሩ ወደ ተሰጠው የእርሻ ቦታ ይሁን ወደ አካባቢው የሚወስድ የተሰናዳ መንገድ አይታሰብም። መደበኛ ሆነ ተንቀሳቃሽ ስልክ አልነበረም። በሥራ ላይ ውለው አቅጣጫ ስተው በመከላከያ አብሪ ጥይት እየተፈለጉ የተገኙ ኢንቨስተሮች ብዙ ናቸው። ይኼም ለአገር ልማት የተከፈለ ዋጋ ነው።

ብዙ የመሠረተ ልማትና የአቅርቦት እጥረት ባለበት አካባቢ በዘመናዊ የእርሻ መሣሪያና በሰው ኃይል ለማልማት ዘመናዊ እርሻን ዕውን ለማድረግ የታገልን ዜጎች የከፈልነው መስዋዕትነት፣ አሁን ጋምቤላ የሞቀች ከተማ እንድትሆን ብዙ መንደሮችም ሰላም እንዲሆኑ ረድቷታል ቢባል ደፍሮ ‹ውሸት› የሚል አይኖርም። እኛ የጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስተሮች የክልሉን ኢንቨስትመንት ህያው ለማድረግ የከፈልነው ዋጋ በጣም ብዙ፣ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። መንግሥት እርሻን ለማሳደግ ባለው ቁርጠኝነት በዝናብ ለሚካሄድ እርሻ ከአራት ዓመታት በኋላ በ40/60 መዋጮ ብድር ፈቀደ ተባለ፡፡ ቀድመን በሥራ ለነበርን ኢንቨስተሮች እሰየው የሚያሰኝ ነበር። ይሁን እንጂ የሰማይ ዝናብና መሬት አቀናጅቶ ወደ ምርት ለመድረስ ለሚታገለው ኢንቨስተር ግን አሁንም ዘርፉ የዕለት ተዕለት ብዙ ውጣ ውረድ ስለሚሻ ሁሌም ጥንካሬውን፣ ፅናቱንና ውሳኔውን የሚፈትን ጭንቀት አይቀሬ ነው።

መንግሥት ባለፉት ዓመታት እርሻ መር ኢኮኖሚ መምረጡና አሁንም እርሻ ተቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ ማድረጉ ተገቢ እንደሆነ በማሳ ለዋለ ሰው ማብራርያ አያስፈልገውም። እርሻ ‹ሕይወት ያለው ነገር መንከባከብ ነው›፡፡ ነገር ግን ፈጣን የቢሮክራሲ ምላሽ ካላገኘና ምላሹ የዘገየ ከሆነ ከሞት በኋላ እንደመድረስ መሆኑ መታወቅ አለበት። የቢሮክራሲው ምላሽም የምታውቁት ነው። ቢሮክራሲው ከተፈጥሮ በላይ ለእርሻ ኢንቨስተሩ ሌላው በወረቀት ላይ ያለ ፈተና ነው። ተፈጥሮንም ቢሮክራሲንም በብቃትና በተደረጀ ስንታገል ቆይተናል። አሁንም በጋምቤላ ገጠሮች ትራክተሮች፣ የእርሻ ማሽነሪዎችና የግብርና ባለሙያዎች ላይ ታች ሲሉ ይውላሉ። የአካባቢው ነዋሪዎችም የቻሉትን፣ ያጠኑትን ያህል አብረውን ይንቀሳቀሳሉ። ኢንቨስተሩም የልጆቹን ናፍቆት፣ የካፌ ጨዋታ፣ የማኪያቶና ኬክ፣ ሳውናና ጃኩዚ፣ ጥላ ሥር ተቀምጦ መዝናናት፣ ይቆይልኝ ብሎ ከፀሐይ ንዳድና ከአቧራ ጋር ታግሎ ራሱንና አገሩን የሚለውጥ ፍሬ ለማፍራት ተስፋ ሰጪ በሆነ ደረጃ ይገኛል። ኢንቨስተሩ በቆሎ፣ ጥጥ፣ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ማሾ አምርቶ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገሮች ገበያ ማቅረብ ጀምሯል። ዘግይቶ ከደረሰው የኢንቨስትመንት ብድሩንም መመለስ የጀመረ ብዙ ነው።                                  

‹ውሻው ይጮኻል ግመሉ ግን መንገዱን አላቋረጠም› እንዲሉ ስለኢንቨስተሩ ብዙ ተብሏል። የጋምቤላ መሬት ግን እትብታችን የተቀበረባት አገር መሬት ናት በሚሉ ቆራጥ ኢትዮጵያዊያን እየለማች ነው። ወሬን በወሬ ከመመለስ በተግባር የታየውን ለውጥ መናገር ይሻላል። የጋምቤላ ገጠሮች ባተሌ ወይም በእንግሊዝኛው “ቢዚ” ሆነዋል። እንደ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ክልሎች የኢኮኖሚ መነቃቃት ተፈጥሯል። በክልሉ በተፈጠረው የኢኮኖሚ መነቃቃት በሳምንት አንድ ጊዜ የነበረው የአየር መንገድ በረራ በቀን ሁለት ጊዜ ሆኗል። ሌላው የኢንቨስትመንቱ ትሩፋት ከእያንዳንዱ የጋምቤላ ቤት በዚህ ኢንቨስትመንት ምክንያት ቢያንስ አንድ የቤተሰብ አባል የድርጅት ሠራተኛ ሆኖ ተጨማሪ ገቢ ለቤተሰቡ ይፈጥራል። ከአጎራባች ክልሎች የሚመጡ ሠራተኞችም ብዙ ናቸው።                             

ኢትዮጵያዊያን የእርሻ ኢንቨስተሮች ከጋምቤላ ሕዝብ ጋር አብረው ይውላሉ፣ አብረው ያድራሉ። በዚህም ኢንቨስተሮቹ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ብዙ ዓይነት ማኅበራዊ እገዛ ያደርጋሉ። ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ የሚያበረክቱ፣ ሰፋፊ መሬቶች አርሰው፣ ዘርተውና አፍሰው ምርቱን የሚያከፋፍሉ፣ ትምህርት ቤትና የጤና ተቋም የሚገነቡ ብዙዎች ናቸው። የጋምቤላን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የተገነዘቡ የሆቴል ባለሀብቶችም አምና ባለአምስት ፎቅ ሆቴል ሠርተዋል። እኛ ግን ወደ እርሻ ስንሠማራ በጋምቤላ ሻይ ቤት ማግኘት ከባድ ነበር። አሁን ሁሉም ነገር ተለውጧል። በዚህም ደስተኞች ነን።  

ነገር ግን ክፉ ዘፈን የሚያቀነቅኑ አደገኛ ዘረኞችና የድል አጥቢያ አርበኛ የመሆን ልምድ ያላቸው ‹‹የበሬውን ምሥጋና ወሰደው ፈረሱ›› እንደሚባለው አስቸጋሪውን የልማት ሒደት ጥላሸት ቀብተው፣ ዛሬ በሌሎች መስዋዕትነት በተስተካከለው ጊዜ ብቅ ብለው ለመበልፀግ የተዘጋጁ የውስጥና የውጭ ሰዎች ከባድና አደገኛ ዘመቻ ሲያካሂዱ ሰንብተው መንግሥትንም ጭምር ለማደናገር ችለዋል። ሠራተኛ ወሬ እያወራ እያሳበቀ ሊውል አይችልም፡፡ ሥራውን ማን ይሠራለታል? ወሬኛው ግን ሥራው ወሬ ነው። የጠንካራውን ዜጋ ላብና ደም መምጠጥ ነው። ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› የሚል እንጂ ‹ሥራ ችግር ያሸንፋል› የሚል መሪ ቃል የለውም። በመሆኑም የባተሌውን ፍሬ ለመንጠቅ ወሬ ሲፈበርክ፣ ሲያስተሳስር፣ ሲያዳርስ፣ ሲጋብዝና ሲነዘንዝ ይውላል። እንዲህ ያሉት ወሬኞችና ዘረኞች ያደረጉት የማደናገር ተግባርን መተረክም ሥራችን ባይሆንም፣ እየደረሰብን ያለውን ጥቃት ለመከላከል መናገር ግድ ስላለን እውነቱን እንነግራችኋለን።

የወሬ አሎሎው የተጀመረው ‹‹የጋምቤላ መሬት እየተወረረ ነው›› በሚል ሲሆን፣ ይኼም ወሬ ‹‹የባንክ ብድር ተፈቀደ›› ሲባል ተጀመረ። ከዚያ በፊት ያሳለፍናቸው የመሬት ልማት ትግሎች ዓመታት ላይ ወሬ አልነበረም። ምክንያቱም ቁርጠኝነትና ወገናዊነት የሚጠይቅ ውሳኔ የሚያስፈልግበት ጊዜ ስለነበር። የድል አጥቢያ አርበኞቹ አስቸጋሪው የመሬት ትግል እስኪያልቅና ሌላው ዜጋ መስዋዕት እስኪሆንላቸው መጠበቅ ነበረባቸው። በሌሎች መስዋዕትነት የጋምቤላ ኢኮኖሚ ተነቃቃ። ከዚህ በኋላ ወሬው መጠናከር ነበረበት። በመሆኑም በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኃይሎች ሚዲያዎች በማስተባበር የመሬት ወረራ ወሬውን አጠናከሩት። እነዚህ ሰዎች ትኩረታቸው ኪሳቸው ነውና ከሁሉም ፀረ መንግሥትና ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በመሆን ወሬውን አራገቡት። መንግሥትም በአጀንዳው ላይ ምላሽ እስኪሰጥ ድረስ ገፉበት። ተሳካላቸው። ወደ ሁለተኛውና ወደ ላቀው ደረጃ መሻገር ነበረባቸው። በመሆኑም ወራሪ የሚሏቸው ዜጎችን ማንነት መጥቀስ ጀመሩ።  

እንደተወራው የወሬ አሎሎ ብዛትና የቅስቀሳ ስፋት ብዙ ጥቃት በደረሰብን ነበር። የጋምቤላ ሕዝብ ምሥጋና ይድረሰውና ወሬኞቹ ወደፈለጉት አቅጣጫ አልሄደም እንጂ፣  የተደገሰው ድግስ በየማሳችን የምንቀርበት ነበር። ልባሙ የክልሉ ሕዝብ ይኼን ባለማድረጉ የተቆጩት የውስጥም የውጭም ኃይሎች የወራሪዎቹ ስም ዝርዝር በሚል በኢሳት ለወዳጅም ለጠላትም ይፋ አደረጉት። አሁንም ጨዋው የጋምቤላ ሕዝብ በኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ላይ እጁን አላነሳም፡፡ ይልቁንም ተባብሮ መሥራቱን ቀጠለ። በዚህ መንገድ ያልተሳካላቸው የአገርና የእኛ ጠላቶች ወደ ቢሮክራሲው በመዞር ሌላ አቅጣጫ ጀመሩ። እርግጥ ከመጀመርያውም ራሳቸው የቢሮክራሲው አባላትና ጓዶቻቸው ያሳበቁት ወሬ እንደነበረ ባይካድም፣ ጥቂት የትግራይ ሰዎች ጋምቤላን ተከፋፍለው እንደተቀራመቱት በማስመሰል አዲስና አደገኛ ወሬ አድርገው ቢሮክራሲውን አራገቡት። በተጨማሪም ‹‹የመንግሥት ፋይናንስ እየተዘረፈ ነው›› የሚል የማደናገሪያ ግብዓትም በመጨመር ማስፋፋታቸውን ቀጠሉ። በሥራ ላይ ያለ አርሶ አደር ለእነዚህ ሁሉ ወሬ ጊዜ የለውም። ወሬው ግን እግር አውጥቶ እየተከተለን ልማታዊ ሥራችንንና መልካም አገራዊ ራዕያችንን ተፈታተነ።  

በነገራችን ላይ የተጠቀሱት ወሬዎች የተፈበረኩት ‹‹በዝናብ ለሚካሄድ እርሻ መንግሥት ብድር ፈቀደ›› ከተባለ በኋላ መሆኑን እንዳትዘነጉ። ወሬው የታሰበለትን ‹ዒላማ› እንዲመታ የሚመስል ታሪክ እንዲኖረው ለማድረግ የወሬና የድል አጥቢያ አርበኞችና መሐንዲሶች የተዋቀረ መቸት ያለው የልብ ወለድ ድርሰት ተፈጥሮለታል።

‹‹ለጥቂት የትግራይ ተወላጆች የልማት ባንክ ያለ ኮላተራል ይሰጣቸዋል፣ ለግብርና ብለው የሚወስዱት ገንዘብ አዲስ አበባ ፎቅ ይሠሩበታል፣ ሃያ ሁለት ይዝናኑበታል . . . ›› ተባለ። ይኼ ወሬ ወዳጅንም ጠላትንም ለማደናገር እስኪችል ድረስ አቅም አግኝቷል። ማስቲካ፣ ክሬም፣ ቸኮሌት ለማምጣት ያልተገባ የፋይናንስ አሠራር ይኖር ይሆን? ብሎ የጠየቀ ብሎም ያወራ ቢሮክራት ግን አልሰማንም። በዚህ ዘርፍ ስንት የውጭ ፋይናንስ አገራችን አጥታ ይሆን? ብሎ ያዘነ ተቆርቋሪ ባለሥልጣን ግን አላየንም። ለእርሻ የተደረገው በጣም አናሳ የሆነ ብድር ግን ተዘረፈ ተባለ። የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚጎዳው የትኛው ነው? ወይስ ነገሩ ዘርና ቀለም ይመርጣል? ይኼ የወሬ ደረጃ ዘመቻው የተሳካበት እርከን ነው። በመሆኑም ብድሩ ከአንድ ዓመት በላይ ቆመ። ኪሳራው በእኛ መሬት አልምተን፣ ተፈጥሮን ቀይረን፣ ልማት አይተን፣ አገር እንገነባለን ባልን ዜጎች ላይ ሆነ። አዲስ አበባን ሳይለቁ የሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶች ግን ብድርም አልቀረባቸው፣ ነገርም አልደረሰባቸውም። የባንክ ብድር እንኳንስ ኢትዮጵያዊያን የሆነውን የትግራይ ተወላጆች ህንድ፣ ቻይና፣ ፓኪስታን . . . ይወስድ የለም? በዚህ የታሪክ አጋጣሚ መጪው ትውልድ ከእኛ ከአርሶ አደሮቹ ወይስ አየር በአየር ትርፍ ከሚገኝበት ሥራ ላይ ከሚሠሩ ዜጎች ይማር?

የልማት ባንክ ተበዳሪዎች ሁሉም ኢትዮጵያዊያንና የሌሎች አገር ዜጎች ሆነው እያለ፣ ወሬኞቹና የአገሪቷ መሠረታዊ ጠላቶች በትግራይ ተወላጆች ላይ ማነጣጠራቸው የሚያተርፉባቸው ነገሮች ስላሉዋቸው ነው። አንደኛ ለሃያ አምስት ዓመታት ሲያዜሙት የነበረ ዜማ ስለሆነ በቀላሉ የአድማጭ ህሊና ይቀበለናል በሚል እሳቤ ነው። ይኼ እሳቤ በጋምቤላ ሕዝብ ህሊና ውስጥ ሠርቶ ቢሆን ኖሮ ይደርስብን የነበረው የአካልና የሕይወት ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ነው። ይኼ ተሳክቶላቸው ቢሆን ኖሮ የዜጎችን ተዘዋውረው የመሥራት መብታቸውን መገደብ ይችሉ ነበር፣ አልሆነም። የጋምቤላ ሕዝብ በየዕለቱ የምናደርገውን ጥረትና ድካም ስለሚያይ ወሬውን አልተቀበለውም። ይሁን እንጂ በሌላው ኢትዮጵያዊ ህሊና ግን የትግራይ ተወላጆች የተለየ ዕድል እየተሰጣቸው ይሆን? የሚል ጥያቄ አልፈጠረም ብለን አናስብም። ስለዚህ በቦታው በሌለ ሕዝብ ላይ የማደናገር ሥራ ተሳክቶላቸዋል የሚል ግምት አለን።  ሁለተኛው በራሱ ፈቃድ ልማቱን ለማደናቀፍ ዝግጁነት የነበረው ቢሮክራሲ ላይ የተካሄደ ዘመቻ ለወሬኞቹ ባለሙሉ ፍሬ ሆኖላቸዋል። በመሆኑም ግብርናውን ለአንድ ዓመት የሚጎዳ ብድርን የማቆም ውሳኔ ወስኖላቸዋል። በዚህም በኢንቨስተሮች ህሊናና ዝግጁነት ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት አድርሷል። ሦስተኛው ሥርዓቱን ይደግፋሉ ብለው የሚያስብዋቸውን ሰዎች በሥርዓቱ ቢሮክራቶች ጉዳት እንደሚደርሳቸው በቂ መልዕክት አስተላልፏል። ይኼ ሁሉ ግን ምቾትና ድሎት ባለበት የንግድ ሥራ ስለተሰማራን ሳይሆን፣ የትግራይ ተወላጆች በመሆናችን ብቻ የደረሰብን የተቀነባበረ ግፍ ነው።   

የወሬው አሎሎ ስለፋይናንሻል ድህነታችንም አዚሟል። ዋናው ድህነት የአስተሳሰብ ድህነት ነው። እንኳንስ መሬት ላይ በግልጽ የሚታይ ትራክተርና ሌሎች የእርሻ መሣሪያዎች በግዢና በውሰት ይዘን ሄደን፣ ሥራ ጀምረን፣ ፍሬያማ ሆነን፣ ሐሳብ ብቻ ይዞ መሄድ በቂ ነው። ድሆች ናቸው ብለው የዘፈኑብን ግን በሆቴል ስም ካገኙት ብድር አተራርፈው ወይም  በኢምፖርት ሸቀጥ ገንዘብ ያካበቱ ወገኖቻችን ናቸው። እኛ ሀብት ከመሬት ይፈጠራል ማለታችን አዲስ ሀብት ለመፍጠር በማሰባችን ነው። ወሬኞቹ ግን በተመቻቸና በሌሎች ድካምና መስዋዕትነት መኖር የኑሮ ዘይቤያቸው ያደረጉ ስለሆኑ፣ በልማታዊ ባለሀብት ላይ ስም መለጠፍ ዋና ሥራቸው ሆኗል። እኛ ቀደም ብለን ያለንን ዕውቀት፣ ጉልበትና ሀብት  በጋምቤላ በማፍሰሳችን የሚታይ የኢኮኖሚ መነቃቃት ተፈጥሯል። ለዚህ እኛን አመስግነው ወደ ራሳቸው ሥራ መግባት ሲጠበቅባቸው፣ እኛን ለመጉዳት የሆነና ያልሆነ በማውራት ሥራችን መበደል ለምን አስፈለጋቸው? ሰው የግድ ከአንድ ዘር መፈጠር የለበትም። አስገራሚው ነገር በመንግሥት ቢሮክራሲ ውስጥ ያሉ ሰዎች ይኼንን ማራገባቸው ይገርማል። የሆነ ሆኖ እኛ ድሆች አይደለንም፡፡ ድሆቹ ጥገኞቹ ናቸው። እኛ ከመሬት ልማት ጋር በመታገል ላይ ያለን ዜጎች ነን። ለልማቱ ድፍረትና ፈቃደኝነት ይኑራቸው እንጂ ለሁላችንም ይበቃናል። በማንነታችን ላይ የሚያካሂዱት ዘመቻ ግን አገር የሚበትን ስለሆነ መንግሥትም ሆነ ልባም ዜጎች ሊያቆሙት የሚገባ ድርጊት ነው። ካልሆን ግን ጉዳቱ ለሁሉም ይደርሳል!፡፡    

በወሬኞች ምክንያት የደረሰብን ጉዳት

ሀብትና ንብረታችን በማሳ ላይ እያለ ለመሰብሰብ ሳንችል እንድንቀር ሆን ተብሎ ያለበቂ ሙያዊ ምክንያት ወሬ በማብዛት ብቻ የባንክ ብድር እንዲቆም ተደርጓል፡፡ በተወሰኑ የፌዴራል ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች ያሉ ለሥርዓቱ ወገንተኝነት የሌላቸው በወፍራም ወንበር ተቀምጠው ልማቱን ሳይሆን የአልሚው ማንነት የሚገዳቸው ባለሥልጣናት፣ በደስታ እያስተናገደን የነበረውን የጋምቤላ ክልል መንግሥት እየተጫኑ በሔክታር 30 ብር የነበረውን የመሬት ግብር በአንድ ጊዜ ወደ 111 ብር ከፍ እንዲልና አቅማችን ተዳክሞ እንድንወጣ አሲረውብናል። ከፍተኛ ድጋፍ የሚሻው የኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንት ለዘርፉ የተቀመጠው የባንክ ብድር ወለድ 8.5 ብር የነበረ ሲሆን ወደ 12.5 ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል። ይህም በጋምቤላ በእርሻ የተሠማራንን ለማክሰር ታስቦ የተደረገ ቢሆንም ጦሱ ግን ለሁሉም በዘርፉ ያሉ ኢነቨስተሮች ደርሷል። ሌላው ሆን ተብሎ የመሬት መደራረብ እንዲፈጠር ተደርጓል። በዚህም ኢንቨስተሩ እርስ በርሱ እንዲጋደል ለማድረግ የታቀደ ሴራ እንጂ ሥራው ከባድ ነገር ሆኖ አይደለም። ለመሬት ልማት በሔክታር የሚፈቀድ ብድር ከዘጠኝ ሺሕ ብር ጀምሮ በተካሄዱ ተከታታይ ጥናቶች 43 ሺሕ ብር ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ ያለ ሙያዊ ጥናት ብድሩ በሔክታር በቀጥታ ወደ 11 ሺሕ ብር ድንገት እንዲወርድ ተደርጓል። ይኼም በኪሳራ እንድንወጣ ታስቦ የተደረገ እንጂ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጥናት እንኳን ለሔክታር 78 ሺሕ ብር ይፈቅዳል። በእርሻ ኢንቨስትመንት የሚሠማራ ዜጋ ከ7.5 ሚሊዮን ብር በላይ በካሽ ሊኖረው ይገባል የሚል ገዳቢና ከባድ ደንብ አስቀምጧል። ይኼም ድሆች ናቸው ከሚል እሳቤ የተነሳ የማጥቂያ ታክቲክ ነው እንጂ ለዘርፉ ዕድገት የሚጠቅም አይደለም። ለእርሻ ኢንቨስትመንት ተጨማሪ ኮላተራል እንዲቀርብ የሚደነግግ መመርያ ወጥቷል። በጣም አስገራሚው ነገር በከፍተኛ ዋጋ የለማው መሬት በመዋጮ እንዳይያዝ የሚያደርግ ደንብ ተቀርጿል። ይኼ አሠራር ከኢንቨስትመንት መሠረታዊ ባህርይ ጋር የማይገናኝ ሲሆን፣ እኛን ለማክሰር ያለሙት ወገኖች ግን ዒላማቸውን ለማሳካት ደንቡን ተግባራዊ ለማድረግ ወደ ኋላ አላሉም። ከመሬት መደራረብ እስከ ሌላኛው የቢሮክራሲ አሻጥር የፈጸሙት ሰዎች የጋምቤላ እርሻ ጉዳይ የአገር ችግር ለማስመሰል በመቻላቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተደርጓል። ይሁን እንጂ አጣሪ ኮሚቴው የወሬኞቹና የአሳባቂዎቹ ደጋፊዎች ስብስብ ሆኗል። ምክንያቱም የተጠቀመው የማጣራት ዘዴና ባለድርሻ አካላት የመፍትሔ አካል እንዲሆኑ ለማድረግ ፈቃደኛ ያለመሆን ማሳያዎቹ ናቸው። በተጨማሪ ኮሚቴው የታረሰ መሬት እንጂ የለማ መሬት በጥናቱ ለማካተት ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ መሬት ላይ ያለው ልማት አነስተኛ እንዲሆን የማድረግ ዘዴ ተጠቅሟል። ይኼም እውነተኛ የአካባቢው የልማት ሁኔታ ማሳየት አልቻለም።

በ2007 ዓ.ም የመሬት መደራረብ ችግር በሚል ሰንካላ ምክንያት የተደረበበትም ያልተደረበበትም ኢንቨስተር በጅምላ ብድሩ እንዲቆም ተደረገ። በ2008 ዓ.ም. ደግሞ ‹የባንኩ ገንዘብ እየተዘረፈ ነው› በሚል በድጋሚ ቆመ። በእነዚህ ሰንካላ ምክንያቶች የኢንቨስተሩን ልማት ሲጎዱ ከቆዩ በኋላ ጥናት እናካሂድ ብለው ተሠማሩ። ‹‹አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ›› የሚሉት ሆኗል። ተደጋጋሚ ጥቃት ካደረሱ በኋላ ዳኝነቱን ራሳቸው ይዘው ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚያሳስት ሪፖርት አቀረቡ። ይኼ ሁሉ ሴራ ግን ግብርናውን ወይስ ወሬኛውን ይጠቅማል?  ህሊና ያለውም ኃላፊነት የሚሰማውም ሰው ጉዳዩን ተመልክቶ ይፍረድ። መሬት ቆፍረን ተጨማሪ ሀብት ፈጥረን ለመኖር ያደረግነው ጥረት በማንነታችን ምክንያት ከተሰናከለ፣ በዘርፉም ላይ በአገር ሆነ ትርጉም ያለው ችግር ይፈጥራል ብለን እናምናለን። ከሁሉም በላይ ለዘረኞች የልብ ልብ ይሰጣል። ምክንያቱም በሙያተኞች እውነቱን መግለጥ እየተቻለ በጅምላ ችግር ውስጥ እንድንገባ ማድረግ የወሬኞቹና የአሳባቂዎቹ ችግር ብቻ ሳይሆን፣ የፈጻሚው አካልም ስህተት ስለሚሆን ነገሩ በጊዜው ይታረም እንላለን። ነገሩ ካልታረመ በበኩላችን እንደ ዜጎች ሠርተን የምንኖርበት ዕድል የጠበበ ሆኖ ሊሰማን ጀምሯል። ዛሬ በእኛ ላይ ነገ በሌሎች ላይ ሳይደገም ይታረም መፍትሔ ይሰጠን!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected].  ማግኘት ይቻላል፡፡