አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

የጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስትመንት የገጠሙት ፈተናዎች ምን ያስተምሩናል?

በያሲን ባህሩ

በምዕራብ የአገሪቱ ጫፍ የሚገኘው የጋምቤላ ሁሌም ክልል በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ ትኩረት እንደሳበ ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት በእርስ በርስ ግጭት፣ በጎርፍ መጥለቅለቅና በመቶ ሺዎች የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን በማስተናገዱ ስሙ ይጠቀሳል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከግብርና ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ በሚሊዮን ሔክታር የሚገመት መሬት በሊዝ ሽያጭ የተዘጋጀበት መሆኑ በትልልቆቹ መገናኛ ብዙኃን ሳይቀር ተዘግቧል፡፡

ለዚህ አባባል ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ከሦስት ዓመታት በፊት አልጄዚራ የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ‹‹ኢትዮጵያ ለሽያጭ የቀረበች መሬት›› (Ethiopia Land for Sale) በሚል ርዕስ ያስተላለፈው ዶክመንተሪ አንዱ ነው፡፡ ሲኤንኤንም ‹‹ህንድ 1.2 ቢሊዮን ሕዝቦቿን እንድትመግብ እየረዳት ያለች አፍሪካዊት አገር›› (The African Country Helping India feed 1.2 Billion People) የሚል ተቀራራቢ ዘገባ አስተናግዷል፡፡ የእንግሊዙ ዘ ጋርዲያንና ሌሎችም የጋምቤላን የመሬት ጉዳይ በስፋት ዘግበውታል፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥት አገላለጽ ‹‹ኒዮ ሊብራል›› የሚባሉት ተፅዕኖ ፈጣሪ መገናኛ ብዙኃንና ርዕዮተ ዓለም ተኮር ተቋማት (ሒውማን ራይትስዎች፣ አክላንድ ኢንስቲትዩት) ተጨማሪ መግለጫዎች አውጥተዋል፡፡ እነዚህ ከሰብዓዊ መብትና ከአካባቢ ጥበቃ ‹‹ተቆርቋሪነት› የሚመነጩ ሒሶች የተለያዩ ፍላጎቶቸን መሠረት አድርገው ቢሰነዝሩም፣ የአገር ውስጥ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የግሉ ሚዲያም ሐሳቡን በስፋት ተቀባብለውታል፡፡ መንግሥትም ‹‹በሀብታችን መጠቀም ስንጀምር በድህነት ታስረን እንድንኖር የሚመኙ ኃይሎች ይጮኻሉ፤›› ሲል ሲያጣጥለው ቆይቷል፡፡

አሁን ደግሞ የጋምቤላ መጠሪያ ሌላ ሆኗል፡፡ ከሰባትና ከስድስት ዓመታት በኋላ ብዙ የተወራላት የግብርና ኢንቨስትመንት ፍሬው ያልታየ፣ የተነገረለትን ያህል ያላመረቃ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በቢሊዮን የሚገመት የአገር ሀብት የሚመዘበርበትና የሀብት ውድመት መፈንጫ ሆኗል፡፡

ለአባባሉ ማሳያ የሚሆነው ከቀናት በፊት ሪፖርተር ጋዜጣ ‹‹ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበ ጥናት›› ማለት ያቀረበው መረጃ ነው፡፡ ይኼ 14 ገለልተኛ ባለሙያዎች እንደተሳተፉበት የተነገረለት ጥናት እንደሚያስረዳው፣ በክልሉ ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ለ623 ባለሀብቶች ከ630 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት ተላልፏል፡፡ ከዚህ ውስጥ 409 ሺሕ ሔክታር የሚደርሰው በጋምቤላ ክልል፣ ቀሪው 220 ሺሕ ሔክታር ደግሞ በፌዴራል የግብርና ኢንቨስትመንትና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ በውክልና ከወሰደው መሬት የተላለፈ ነው፡፡

ከተላለፈው መሬት ግን እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ በድምሩ ከ76.8 ሺሕ ሔክታር ያልበለጠ መሬት ብቻ መልማቱን ነው ጥናቱ ያሳየው፡፡ ለዚህ ምክንያቱም ባለሀብቶች ለልማቱ ትኩረት አለመስጠታቸው፣ አብዛኛው ባለሀብት መሬት እየወሰደ ያለው አልምቶ ራሱንና አገርን ለመጥቀም ሳይሆን በአቋራጭ የባንክ ብድር ለማግኘትና በታክስ ነፃ ለመጠቀም ነው፡፡ ይኼ በአቋራጭ የመበልፀግና የመበዝበዝ ዝንባሌ 29 ባለሀብቶች ከወሰዱ መሬትና ከተበደሩት የሕዝብ ሀብት ውጪ ‹‹የት እንዳሉም አይታወቁም›› በሚል ተወስቷል፡፡

‹‹አልሚ›› ተብዬዎች ከልማት ባንክና ሌሎች ባንኮች ከ4.96 ቢሊዮን ብር በላይ ተበድረዋል፡፡ ይሁንና ከ200 ዋነኛ ተበዳሪዎች ከሚጠበቀው በስድስት እጥፍ ያነሰ ልማት ከመታየቱ ባሻገር፣ ሙስናን መደራደር ጎልቶ የታየበት ሁኔታ አጋጥሟል፡፡ በቅርቡ ገዢው ፓርቲ ባካሄደው የ‹‹ተሃድሶ ግምገማም›› ለሥርዓቱ ቅርበት ያላቸው ነባር ታጋዮች፣ ጡረተኛ የመከላከያ መኮንኖችና የተሻረኩ ኪራይ ሰብሳቢዎች የዘረፋው ዋነኛ ተዋናይ መሆናቸውን በግልጽ አሳይቷል፡፡  

‹‹በታዳጊው ጋምቤላ ክልል›› ብዙ ያነታረከው የግብርና ኢንቨስትመንት ለአካባቢው ነዋሪዎችም ሆነ ለአገሪቱ የሚታይ ጥቅም አላስገኘም፡፡ እንዲያውም ‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል› እንዲሉ ቀማኞች መሬት መውሰዳቸው ሳያንስ በገፍ እየተበደሩ በሌላ አካባቢ ሕንፃና ቤት እየሠሩ አከራዩ፡፡ የማሽነሪ ኪራይ፣ የኮንትሮባንድ ንግድና መሰል አመቺ የአቋራጭ መንገዶች ላይ ተረባረቡ፡፡ በነገራችን ላይ ከወራት በፊት በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በመቶ ሺሕ ሔክታር መሬት ይዞ ለመከነው የካሩቱሪ (የህንድ ኩባንያ) እርሻ ልማት ውድቀትም ሰፊ ዘገባ መቅረቡን እናስታውሳለን፡፡

ይኼ ሁሉ መቀራመትና የሕዝብ ሀብት ብክነት ዘግይቶም ቢሆን መንግሥትን አሁን አባኖታል፡፡ ሁሉንም አልሚዎች በጅምላ መፈረጅ ባያዳግትም፣ አብዛኛው ‹‹ኢንቨስተር›› በኪራይ ሰብሳቢነት እየነጎደ መሆኑ ሲታይም ወዴት እየተሄደ ነው? የሚል ከፍ ያለ ጥያቄን የሚያጭር ነው፡፡ ግን ምን ይደረግ?

ጋምቤላ የእምቅ ሀብት ምድር

     3.2 ሚሊዮን ሔክታር ስፋት ያለው የጋምቤላ ምድር ከአውሮፓዊቷ ሥልጡን አገር ቤልጅየም እኩል የሚባል የቆዳ ሽፋን አለው፡፡ በዚህ ክልል ከ337 ሺሕ ያልበለጠ ሕዝብ ብቻ ሲኖር፣ ቤልጀየም ግን 12 ሚሊዮን ሕዝብ (36 እጥፍ በልጣ) እንደሚኖርባት ልብ ይሏል፡፡ ስለሆነም ጋምቤላ ከስፋቱ ጋር ሲሰላ በአማካይ በአሥር ሔክታር አንድ ሰው ብቻ የሚኖርበት ነው፡፡ ይኼም ገና ሊለማ የሚችል ሰፊና ዕምቅ መሬት ባለቤት የሆነ ክልል መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

ከክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ በተገኘ የቅርብ መረጃ መሠረት ጋምቤላ ካለው 3.2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ 2.6 ሚሊዮን የሚሆነው ለእርሻ አመቺነት አለው፡፡ ከዚህ ውስጥ 1.2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ለኢንቨስትመንት ዝግጁ የተደረገ ሲሆን፣ እስካሁን ከግማሽ ያነሰው ነው ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች በሊዝ የተሰጠው፡፡

የጋምቤላ ክልል የመሬት ሀብት ብቻ አይደለም ያለው፡፡ ይልቁንም ሌሎች የተፈጥሮ ፀጋዎቹም ለእርሻ ኢንቨስትመንት አመቺ ያደርጉታል፡፡ የጋምቤላ የዝናብ መጠን ከ800 እስከ 1,200 ሚሊ ሜትር መሆኑ አንዱ ተጠቃሽ ፀጋ ነው፡፡ ክልሉ 1.9 ቢሊዮን ሜትር ኩብ የከርሰ ምድር ውኃ ሀብት ያለው ሲሆን እንደ ባሮ፣ አኮቦ፣ ጊሌና አልዌሮ የመሳሰሉ ትልልቅ ወንዞች ባለቤትም ነው፡፡ በክልሉ ውስጥ በርካታ ጅረቶችና አነስተኛ ሐይቆች (ሙሉ፣ ታታ፣ ቡሬና አልዌሮ) ሰው ሰራሽ ሐይቆች ይገኛሉ፡፡፡ የክልሉ የውኃ ሀብት ክምችት ከእርሻም ባሻገር ለዓሳ ሀብት ልማትና ለውኃ ትራንስፖርትም ጠቀሜታ ይሰጣል፡፡

የጋምቤላ ወንዞች የዓሳ ሀብት ልማት ከፍተኛ መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እስከ 107 ዓይነት የዓሳ ዝርዎች በአካባቢው የሚገኙ ሲሆን፣ ዘርፉም ገና ያልተነካና ዕምቅ ነው፡፡ ለነገሩ የክልሉ የዓሳ ሀብት ገና ጥቅም ላይ ያልዋለ ነው፡፡ በዋነኛነት በአርብቶ አደርነት የሚተዳደረው የኑዌር ዞን ተዝቆ የማያልቅ የእንስሳት ሀብትን ይዟል፡፡

የጋምቤላ ክልል በማዕድን መስክም ትኩረት የመሳብ ዕድል ያለው ነው፡፡ ምንም እንኳን በተፈጥሮ ነዳጅና ድፍድፍ ዘይት ረገድ ያለው ይዞታ በጠራ መረጃ ታውቆ ይፋ ባይደረግም፣ ከፍተኛ የወርቅ ማዕድን የተከማቸበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በባህላዊ መንገድ ከሚወጣ ጥቂት ወርቅ በስተቀርም እምብዛም ጥቅም ላይ ያልዋለ መሆኑም ይታወቃል፡፡

ዘመናዊ ሆቴሎች፣ ሎጆችና የቱሪዝም መሠረተ ልማቶች አለመጠናከራቸው ነው እንጂ የቱሪዝም ሀብቱም የጋምቤላ ክልል ተስፋ ነው፡፡ በተለይ በዱር እንስሳት ሀብቱ በአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃነት የሚቀመጠው የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክና ዋና ከተማዋን ለሁለት ከፍሎ የሚያልፈው የባሮ ወንዝ ብዙ ትኩረት የሚስቡ ናቸው፡፡ ለዚህም ጋምቤላ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የአየር መንገድና ዋና ዋና መንገዶች ማግኘትና ሰላሟን አጠናክራ ማስጠበቅ ከቻለች ተስፋ ይኖራታል፡፡

ጋምቤላ ወጥመድ የማያጣት ቆቅ

የጋምቤላ ብሔራዊ ክልል የአችዋ፣ የኑዌር፣ የሚንጃንግ፣ የኮምፕሮኦፓ ነባር ብሔረሰቦችን ጨምሮ በርካታ የአማራ፣ የትግራይ፣ የኦሮሞ፣ የጉራጌ፣ ወዘተ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የሚኖሩበት ነው፡፡ ከዚያም አልፎ በየጊዜው ቁጥር ቢቀያየርም በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ሠፍረውበታል፡፡

ይሁንና በክልሉ በተደጋጋሚ እንደታየው ብሔር ተኮር ግጭቶች ሲቀሰቀሱ በዚህ መዘዝ የሰው ሕይወት ይጠፋል፣ ንብረት ይወድማል፡፡ እዚህ ላይ የፌዴራሉ መንግሥትም ሆነ የክልሉ መንግሥት የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርጉም ቦታው ሰፊና ድንበር ላይ የሚገኝ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከደቡብ ሱዳን በመጎራበቱ ‹‹ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል›› መሆኑ አልቀረም፡፡

አሁን በተጨባጭ እንደታየው የውጭውም ሆነ የአገር ውስጡ ጥገኛ ታዲያ ጋምቤላን ያጠመዳት ለሥውር ጥቅሙ ብቻ እንዲሆን ያደረገው አንዱ ‹‹የሰላም ዋስትና የለም›› የሚል አጉል ጨዋታ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በቅርቡ በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጣቢያ የጋምቤላ እርሻ አልሚዎች ማኅበር መሪ የተባሉ ቅሬታ አቅራቢ ብዙዎቹ እርሻ የወሰዱ የትግራይ ባለሀብቶች ያልተገባ መገፋት አጋጥሟቸዋል ሲሉ የመንግሥትን የቅርብ ጊዜ የእርምት ዕርምጃ ተችተዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚሳዩት በክልሉ የትግራይ ባለሀብቶች በርከት ብለው የገቡበት አንዱ ምክንያት ያለውን የፀጥታ ሥጋት ተጋፍጠው ለመሥራት በመድፈራቸው ነው፡፡ በተለይ ቀደም ሲል በትግሉ የተሠለፉና ከመከላከያ የተሰናበቱ ዜጎች ይኼን ፈተና (Challenge) ደፍሮ ለመቋቋም ወደኋላ እንደማይሉ ይታመናል፡፡ ይሁንና አሁን በታየው የኪራይ ሰብሳቢነት መንገድ በአቋራጭ ለመገልፀግ የሚደረግ ጥድፊያ በጊዜው ካልታረመ፣ በሶማሊያ በየመንደሩ ታንክና መድፍ ያጠመዱ የጎሳ መሪዎች ዓይነት አስቸጋሪ ጥገኞች ላለመቀፍቀፋቸው ዋስትና የለም፡፡

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ነባሩ የጋምቤላ ክልል ማኅበረሰብ በአንፃራዊነት ሕይወቱ በመቀየር ላይ ነው፡፡ በመንደር እየተሰባሰቡ ከተበታተነ ሕይወት መውጣት ከመጀመሩም ባሻገር፣ የትምህርትና የጤና ልማት ተቋዳሽ መሆን ችሏል፡፡ ለዚህም ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ክልሉ ያለው ሲሆን 34 ጤና ጣቢያዎች፣ 126 ጤና ኬላዎችና አንድ ሆስፒታል መኖሩም አብነት ናቸው፡፡ የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን ጨምሮ የመሠረተ ልማቱ መስፋፋቱም ተስፋ ሰጪ መሆኑ ሊካድ አይችልም፡፡

በግልጽ የሚታየው ጉድለት ግን አሁንም ነባሩ ማኅበረሰብ የፖለቲካው እንጂ የኢኮኖሚው ተዋናይ አልሆነም፡፡ በጋምቤላ ከተማ ከአነስተኛ ሱቅ አንስቶ ሆቴል ቤቶች፣ የአልባሳት መሸጫና ልዩ ልዩ አገልግሎቶች መስጫ ቢዝነሶች በደገኞች ነው የተያዘው፡፡ የመሬት ቅርምቱ የፈጠረው አዲስ የድለላና የኪራይ ሰብሳቢነት ትስስሩ እየፋፋ የመጣውም ከነባሩ ይልቅ በሌላኛው ማኅበረሰብ አንዳንድ ተዋናዮች መሆኑን ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡

ይኼ ሁኔታም የመንግሥት መዋቅሩን፣ የባንክ የሌብነት ተዋንያንን፣ የግብርናና የመሬት ሰጪ ሴክተሩን በጥገኛ መረብ እያስተሳሰረ ለመሆኑ የሰሞኑ ጥናት አረጋግጧል፡፡ ይኼ የተዛባ አካሄድ ደግሞ መንግሥት ያለውን ውስን ሀብት ለግብርናው መስክ መጠናከር ለማዋል ካለው ፍላጎት አንፃር ይበልጥ ለብልሽት ተጋልጧል፡፡ ልማታዊ አካሄድ እንዲቀጭጭ ከማድረጉ አንፃር ሲመዘንም፣ በአሁኑ ወቅት ጋምቤላን ወጥመድ የሆነባት ኪራይ ሰብሳቢነት መሆኑን በግልጽ ያሳያል፡፡

ጋምቤላ ሆይ ትኩረት ይገባሻል!

     ‹‹የጥቁሩ ወርቅ ምድር›› የምትባለው ጋምቤላ ቤልጂየምን የሚያክል መሬትና ሀብት ይዛ እንኳን በዓለም በአገራችንም ሳትታወቅ ኖራለች፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት በደግም በክፉም ከመጠቀሷ ባሻገር ያላት ዕምቅ አገራዊ ሀብትም ተለይቷል፡፡ ይኼን ሀብት ያለብልሽትና ውንብድና በጤነኛ መንገድ ለክልሉ ሕዝብም ሆነ ለአገሪቱ እንዲጠቅም ማድረግ የዚህ ትውልድ ድርሻ ነው፡፡ በተለይ ክልሉን ኪራይ ሰብሳቢነትና ኢፍትሐዊነት አጥለቅልቆት ያልተፈለገ ትርምስና ቀውስም እንዳይከሰት፣ ከ‹‹ብሔር ፖለቲካ››ና ከሙስና አጓጉል ጨዋታ ወጥቶ አሠራሮችን ግልጽነትና ተጠያቂነት ማላበስ፣ በመርህ ላይ የተመሠረተ ልማታዊ አካሄድን መከተል ያስፈልጋል፡፡

እንደ መፍትሔ

  • መንግሥት አሁን በጀመረው መንገድ የጋምቤላን ዕምቅ ሀብቶችና ተግዳሮቶችን በጥናት ይለይ፣ የታሰበውን አካሄድ በቁርጠኝነት ያርም፣ ያስተካክል፣
  • ያላለሙ የመሬት ባለይዞታዎች ይነጠቁ፣ የተበደሩት የሕዝብ ሀብትም በአፋጣኝ ይመለስ፣ እንዲያውም የቀረጥ ነፃና የግብር እፎይታም በሕዝብ ጥቅም ላይ ያላአግባብ የተፈጸመ ደባ ለሁሉም ማስተማሪያ በሚሆን መንገድ ይጋለጥ፣ እርምትም ይወሰድ፣
  • በልማታዊ መንገድ ተስፋ ሰጪ እንቅስቀሴ ውስጥ የገቡ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ይበረታቱ፣ ሁለንተናዊ ዋስትና የሚያገኙበት ሥርዓትም ይዘርጋላቸው፣ በተለይ በትንሽ በትልቁ ባለሀብቱን ለማማረርና ለመዝረፍ ያሰፈሰፈው ‹‹የመንግሥት ሌባ›› የሚጋለጥበት መንገድ ይበጅ፣
  • ጋምቤላ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ምድር ብቻ ሳትሆን የነባሩ ማኅበረሰብም መጠቀሚያና በእኩልነት መኖሪያ እንድትሆን በትኩረት ይሠራ፣  
  • በተለይ ከመሬት ልማት ጋር በተያያዘ በክልሉ ያለው ሀብት በመሬት ባንክ ሥርዓት ተይዞ ውጤታማ የውጭ ባለሀብቶችና ከአገር ውስጥም የተደራጁ ወጣቶችን እንዲያሳትፍ ይደረግ፣ እስካሁን የተሄደበት የተዝረከረከና የኢፍትሐዊነት አካሄድም በአስቸኳይ ይገታ፣ ይገታ፣ ይገታ፣

በመጨረሻ ሌሎች ታዳጊ ክልሎች ከጋምቤላ ሊማሩት የሚገባው የኪራይ ሰብሳቢነት መፈልፈያ ከሚሆን አደጋ ራሳቸውን ሊጠብቁ ይገባል፡፡ አፋር፣ ቤንሻንጉልና ሶማሌ ክልሎች በባለሀብትና በመንግሥት ኃላፊነት ስም የሚዘረጋን የሕዝብ ሀብትን የመበዝበዝ ዝንባሌ ሊፋለሙ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድም የፌዴራሉ መንግሥት የተጣለበት ኃላፊነት ከፍ ያለ መሆኑን ማጤን ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected].  ማግኘት ይቻላል፡፡