የ40/60 ጉዳይ ከምን እስከ ምን?

 

 እንደሚታወቀው  የ40/60 ቤቶች ፕሮግራም ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለዕድለኞች  ይደርሳል የሚል ዕቅድ ነበር፡፡  ይሁንና በአሁኑ ወቅት ሦስት ዓመት  አለፈው፡፡ ከ160 ሺሕ በላይ ተመዝጋቢዎች ውስጥ ለአንድም ግለሰብ ቤቱ አልቆ አልተሰጠም፡፡  ሁልጊዜ  ሲነገር የምንሰማው 1,200 ቤቶች የዛሬ ወር ይተላለፋሉ፣ በቀጣዩ ጊዜ ለዕድለኞች ዕጣ ይወጣል፣ ወዘተ እየተባለ  ሲነገር ቆይቷል፡፡ ግን አንድም ቤት ዕጣው ሳይወጣ ይኸው እዚህ ደርሰናል፡፡

በእኔ ግምት ተመዝጋቢዎች  በመንግሥት ላይ ተስፋ የቆረጡበት  ትልቁ  ምክንያትም ይኼው ይመስለኛል፡፡   በአሁኑ ወቅት በርካታ ሰዎች  የመንግሥት ሠራተኛው ሳይቀር ተበድሮ፣ ያፈራውን ንብረት ሸጦ፣ እንዲሁም  ቅሪቱን አንጠፍጥፎ፣ ገንዘቡን ያወጣው የቤት ፕሮግራሙ አፋጣኝ  መፍትሔ ይሰጠኛል ብሎ በማሰብ ነበር፡፡ ለዚህ ሲል ተቻኩሎ ተመዝግቧል፡፡ ይሁንና ‹‹ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም›› ሆኗል ነገሩ፡፡ 

በወቅቱ ሕዝቡ ያዋጣው ገንዘብ ለሌላ ጉዳይ ቢውል መለስተኛ ቅሪት  ያፈራ ነበር፡፡ ታዲያ መንግሥታችን ሰው በዝምታ እየታዘበው እንደሆነ  እንዴት አላስተዋለም?

 እኔ በበኩሌ በአሁኑ ወቅት  ለመንግሥትም፣ በሥራው ላይ  ለሚገኙ ባለሙያዎችም የደረሱትን ቤቶች ለማስረከብ ምቹ ወቅት ነው ብዬ  አስባለሁ፡፡ ኃይሉን ሁሉ ተጠቅሞ  ብዙ ቤት መሥራት የሚችልበት ጊዜም ነው፡፡   በሁለተኛው  የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን  በአዲስ አበባ ብቻ 350,000 ቤቶች  ይገነባሉ የተባለው  መቼ ነው የሚሳካው?   በጀቱስ ለምን አይለቀቅም? ይኼስ አንዱ ‹‹የመልካም አስተዳደር ችግር›› እንደሆነ ከመንግሥት የተወሰረ ይሆን?  እኔን የሚያሳዝነኝ ና ግር የሚያሰኘኝ መልካምና ቅን  አማካሪዎች የሉትም? እንድል የሚገፋፋኝ ይኸው ችግር ነው፡፡ ይሠራል ይባላል፣ ግን ለሰው አይደስርም፡፡

በእኔ እምነት በቤት ፕሮግራም  ውስጥ ያለን ሰዎች፣ እንደሚገባን ባለመሥራታችን   ምክንያት ሕዝብ  በዝምታ  እየታዘበና  እየተቸን  ነው፡፡  በከተማው ያለው የቤት  ኪራይ  ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሆኑ  ሃይ  ባይም ያለው ስለማይመስል የኋላ ኋላ የሀብታምና የጭሰኛ ግጭት ተፈጥሮ  ወደማያባራበት አዝማሚያ እንዳያመራ  እፈራለሁ፡፡  ስለሆነም  የሚመለከተው  አካል  ወደ ማንም እጁን  ሳይቀስር  በቀን፣ በወርና  በዕሩብ ዓመት  በእዚህ  ዘርፍ  ምን ሠርቼ  የከተማውን  ሕዝብ   ቀልብ  መሳብ ይገባኛል ብሎ  ማጤን  አለበት፡፡ ካልሆነ ግን  አደጋው  በሁላችንም  ላይ መሆኑን  አንዘንጋ    እላለሁ፡፡  ቸር ያሰማን፡፡

(ወልዱ በፍርዱ፣ ከአዲስ አበባ)

*  *  *

የኢትዮጵያዊነቴ ድርሻ ምኑ ላይ ነው?

የ53 ዓመት ባለፀጋ፣ የስድስት ኢትዮጵያዊያን ልጆች አሳዳጊ፣ የሁለት ማስተርስ ዲግሪና የዲፕሎማ ባለቤት ነኝ፡፡ ከአሥራ አምስት በላይ የውጭና የአገር ውስጥ ሥልጠናዎች የወሰድኩኝና ጠቃሚ የአመራር ክህሎቶች ያሉኝ፣ ለመንፈሳዊ ማንነት የተሻለ ዋጋና ክብር የምሰጥ፣ ቀናና የፍቅር ሰው መሆኔን የማምን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡

ይኼንን ጽሑፍ እንድጽፍ ያስገደደኝ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በቅንነቴ፣ በቅድስናዬና በቅን ልቦናዬ ላይ እየፈጠረብኝ ያለው ጫና ስላንገሸገሸኝና ስለበዛብኝ ለሚመለከታችሁ ባለሥልጣናት አቤቱታዬን ለማሰማት ነው፡፡

በዚህች አገሬ በምላት ምድር ለዕድሜና ለማንነቴ አስተዋጽኦ ያልነፈገችኝ አገር፣ ከእኔ ጋር ያሉ ውብና ፍቅር የሞላቸው ቤተሰቦቼ ፀሎትና ምልጃ፣ የብዙ ወዳጆቼ መልካም ምኞት፣ የአስተዳደጌ ጨዋነት፣ በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊነቴ፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነቴ፣ ከእኔ የሆነው አንዳች ሳይጎድል ቤተሰቦቼን የማኖርበት አንድ ሕጋዊ የኪራይ ቤት ወይም አንድ ኮንዶሚኒየም ወይም ጎጆ መቀለስ የሚያስችል ብጣሽ መሬት የከለከለኝን ፖለቲካ እንዲዳኝልኝ አቤቱታዬን ሳቀርብ በምሬት ነው፡፡

የመማረሬ ምክንያት

ማንነቴ ብዙዎችን እንዳውቅ ዕድል ሰጥቶኛል፡፡ ከማውቃቸው ብዙዎቹ የኪራይ ቤት በትዕዛዝ የተመቻቸላቸው፣ አነሰ ቢባል አንድ የግል ቤት ወይም ቦታ ከጎን የሚያስተዳድሩ አሊያም የበርካታ ቤቶች ባለቤት በመሆናቸው ምክንያት በኪራይ ገቢ ባለሀብቶች የሆኑ፣ እንዲሁም መሬት በመሸጥ የደረጁ መሆናቸውን አውቃለሁ፡፡ የእኔና የእነዚህ ሰዎች ልዩነት ከምናመልከው አምላክ፣ ከአንጡራ ገቢ ቁጠባ፣ ከሞራልና ከስብዕና፣ ከትምህርትና ከዕውቀት ወይም ከዜግነት እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡ የእነዚህ ሁሉ ልዩነት ከፖለቲካ ድርጅት አባልነት የተገኘ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምክንያት ልሰጠው አልቻልኩም፡፡

አኗኗሬና ትዕዝብቴ

በአዲስ አበባ ከተማ መኖር ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ስምንት የግለሰብ ቤቶችን አፈራርቄ በኪራይ ኖሬያለሁ፡፡ ስድስቱ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ሲሆኑ፣ ስድስቱም ቤቶች በትርፍነት ይዘው ከሚኖሩ ሰዎች የተከራየኋቸው ነበሩ፡፡ ሦስቱ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሲሆኑ፣ በሚስቶቻቸው የሚተዳደሩ ነበሩ፡፡ አንዱ ባለሥልጣን ሌላም ቦታ ሁለት ቤቶች እንዳሉት አውቃለሁ፡፡

 ከዚህ በመነሳት፡-

  1. እኔ የኪራይ ቤት ከመንግሥት ያጣሁት እነሱ ስለሚኖሩበት እንደሆነ አወቅሁ፤
  2. እኔ ኮንዶሚኒየም ያጣሁት እነሱ ሦስት፣ አራት፣ ወይም 10 የሚያከራዩት ቤት ስላስፈለጋቸው መሆኑን ተረዳሁ፣
  3. እኔ መሬት ያጣሁት እነሱ የሚሸጡት ወይም የሚይዙት እንዳያንሳቸው በመሳሳት እንደሆነ ገባኝ፡፡ ታዲያ ይኼን ጊዜ ኢትዮጵያዊነቴን የት ላገኘው እንደምችልና የዜግነቴ ፋይዳ ለመቼ እንደሆነ መረዳት ተሳነኝ፡፡ ጨዋነት፣ ቅንነትና ቅድስና በኢትዮጵያ ምድር ‹‹አስኮናኝ ባህል›› የተደረገ መሰለኝ፡፡

የጨነገፈው ተስፋዬ

ከዛሬ አምስት ዓመታት በፊት ለቤት ፈላጊዎች ሁሉ ዋስትና እንደሚሰጥ የተነገረለት የ10/90፣ የ20/80፣ እና የ40/60 የቤት ፕሮግራም ይፋ ሲደረግ በኢትዮጵያ የምኅረት ቀን መቅረቡን፣ ለዜጎች ንጋት መፈንጠቁን ጻፍኩ፣ አወራሁ፡፡ እኔም የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን በ40/60 ፕሮግራም ተመዝግቤ በገባሁት ውለታ መሠረት ግዴታዬን ተወጣሁ፡፡ ለግዴታዬ መወጣት ሚስጥሩ የእኔን ድካም፣ የቤተሰቦቼ መንከራተትን ለማስቀረት፣ ልጆቼ ‹የእዚህ ሰፈር ልጆች ናቸው› እንዲባሉ የነበረኝ ምኞት፣ የኢኮኖሚዬ መላሸቅ እንደሚያበቃ ተስፋ በማድረግ ነበር፡፡ አሁን ግን ተስፋዬ ወዴት እንዳለ፣ የት እንደገባ ማወቅ አቃተኝና ነው ይኼን ደብዳቤ ለመሪዎቼ እንዲደርስ የጻፍኩት፡፡

አንድ የምንሆነው የአንድ የፖለቲካ ድርጅት አባል ስንሆን ብቻ እንጂ በዚህች አገር ላይ ተወልደን፣ አድገን፣ ተምረን፣ ሰው ሆነን፣ ለአገር ባለን ጠቃሚ ራዕይና አስተዋጽኦ እንዳልሆነ የሚነገረውን ሳልሰማው ወይም ሳይገባኝ ቀርቶ ከሆነ ልመለስ፡፡ እኔ መንግሥትን የሚቃወም ሐሳብ የማራመድና አቋም በመያዝ ትግል መጀመሬ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያዊነቴ የመኖሪያ ዋስትና የማግኛው ሚስጥር ምን እንደሆነ እንዳውቅ ይፈቀድልኝ ነው ጥያቄዬ፡፡ የሁለት ዓይነት ዜጎች መኖርና የዜግነት መብትና ጥቅም ከሰዎች ማንነትና ውልደት ሳይሆን ከፖለቲካ ደብተር የሚገኝ መብት መሆኑ በይፋ ተነግሮ ከሆነ እኔ ካልሰማሁ ቢነገረኝ ወደዚያ ለመመለስ አልቸገርም፡፡ ምርጫ የግል መብቴ መስሎኝ አልመረጥኩትም ነበር፡፡ ተቃዋሚ በመሆኔም አልነበረም፡፡   

የተከበራችሁ መሪዎቼ፣ በአንድ በኩል የእከሌ ሀብት እዚህ ደርሷል፣ እከሌ አሥር ኮንዶሚኒየምና ብዙ መሬት አለው የሚለው ሐሜት አሳፋሪና አስገራሚ ሆኖ ከሚታይበት ጠረፍ አልፏል፡፡ ኮንዶሚኒየም ጠፍቷል እየተባባልን በምንተማማበት አገር፣ በቆሻሻ ክምር ዕልቂት በሚሰማበትና የበርካታ ቤተሰብ መፈናቀል በደረሰበት ወቅት በእኔ የደረሰውን ዓይነት የተስፋ መጨለም እንዴት አጣጥሞ መኖር እንደሚቻል ሳስብ አብዝቶ ያሳስበኛል፡፡ መላውና መፍትሔው ከወዴት ይሆን? እላለሁ፡፡

ማጠቃለያ

ችግሬን በትንሹ ሳስረዳ በሐዘን ነው፡፡ ጊዜዬንና ብዕሬንም በመቻቻል፣ በልማት፣ በፍቅር፣ በሙያ ትንታኔ ወይም ዕውቀት መር በሆነ ጉዳይ ላይ ቢሆን ተጠቃሚው ሁላችንም ነበርን፡፡ እኔ የብዙዎች ምሳሌ እንጂ ብቻዬንም እንዳይደለሁ ይሰማኛል፡፡ ሆኖም ግን መደረግ አለበት የምላቸውን ነጥቦች ያካተትኩበት አስተያየቴን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

  1. የ40/60 ዕጣውን ለእኔ አስቀድሙ ሳይሆን፣ እንደ ችግሩ ስፋትና ጥልቀት ቅድሚያ የሚሰጠው ቅድሚያው ይሰጠው እላለሁ፡፡ ባለሥልጣንነትና የፓርቲ አባልነት የቅድሚያ መመዘኛ አይሁን፡፡ ከፍተኛ አለመተማመን ይፈጥራልና፡፡
  2. የመኖሪያ ቤት በኪራይ የማግኘት መብት ይኑረኝ፡፡ የገቢዬ 60 በመቶ ለኪራይ በመክፈል ዕድሜዬን የፈጀሁ በመሆኔ ጥያቄውን ማንሳቴ ተገቢ መሆኑ ይሰማኛል፡፡
  3. ከዚህ ቀደም በበርካታ ልማታዊ ጉዳዮች ላይ ሐሳቤን እሰጥ እንደነበር አሁንም ችግሬን በማዳመጥ እንዳልሰነካከል ልበረታታ እላለሁ፡፡

(ከአዲስ አበባ ቤት አልባዎች አንዱ)