ይናገራል ፎቶ!

ፀጉርን በመብላት ሱስ የተያዘች ሴት 

ፀጉርን በመብላት ሱስ የተያዘች ሴት የ38 ዓመት ሴት፣ ከሆዷ 15 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያለው ጥቅልል የፀጉር ኳስ እንደወጣላት የዘ ኢንዲፔንደንት ዘገባ ያመለክታል፡፡ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስና በሆድ ማበጥ ለወራት ስትቸገር ወደ ሆስፒታል ሄደች፡፡ በዚህ ሕመሟ ምክንያት 15 ፓውንድም ክብደት ቀንሳ ነበር፡፡ ሆስፒታል ስትደርስ በአፋጣኝ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላት ከሆድ ዕቃዋ የፀጉር ኳሱ ሊወጣላት ችሏል፡፡

* * *

ስለዮጋ ፍልስፍና የተናገረው በፀረ ሽብር ሕግ ታሰረ

ፌስቲቫል ላይ ከዮጋ ጀርባ ስላለው ፍልስፍና የተናገረው ሩሲያዊው የዮጋ መምህር ዲሜትሪ ዮጌይ ለእስር ተዳርጓል፡፡ ግለሰቡ የታሰረው ሕገወጥ የሚሲዮናዊ እንቅስቃሴ በማድረግ በሚል ነው፡፡ ግለሰቡ ሊታሰር የቻለው በቅዱስ ፒተርስበርግ ፌስቲቫል ላይ የዮጋን ፍልስፍና እየተናገረ አባላትን ለመመልመል ሲሞክር እንደነበር ስለተጠቆመበት ነበር፡፡

***

የትምህርት ማጠቃለያን በራፕ

አንድ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ሲጠናቀቅ መምህራን የዕለቱን ትምህርት በማጠቃለያ መልክ (Wrap ups) ያቀርባሉ፡፡ ነገር ግን የኤድዋርድስ ትምህርት ቤት ስምንተኛ ክፍል  መምህር የሆነው የ31 ዓመቱ ዳቪድ ያንሲ ግን ለተማሪዎች የዕለቱን ትምህርት የሚያጠቃልለው በራፕ እንደሆነ ኤንቢሲ ዘግቧል፡፡