አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ዳሸን ቢራ ዓመታትን ላስቆጠረው ለትግራይ ስታዲየም ግንባታ 42 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ታላላቅ ስታዲየሞች በሁሉም የአገሪቱ ክልል ከተሞች መገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከሁሉም በፊት ግንባታው የተጀመረው የትግራይ ዘመናዊ ሁለገብ ስታዲየም ለግንባታው መዘግየት አጥጋቢ መልስ የሚሰጥ አካል ባይኖርም ከታናናሾቹ ባነሰ እንቅስቃሴ የግንባታው ሒደት በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ የዳሸን ቢራ አክሲዮን ማኅበር ለዚሁ ዓመታትን ላስቆጠረው ለትግራይ ስታዲየም ግንባታ ማጠናቀቂያ ይውል ዘንድ 42 ሚሊዮን የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል፡፡

በመቐለ ከተማ የግንባታው መሠረት ሲጣል ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት ላይ ይውላል ተብሎ ሲነገር የነበረው በ2006 ዓ.ም. የነበረ መሆኑ ግንባታውን አስመልክቶ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይሁንና ከ12 ዓመታት በላይ በግንባታ ሒደት ላይ የሚገኘው ይኼው የመቐለ ዘመናዊ ሁለገብ ስታዲየም፣ በ2006 ቀርቶ በ2009 ዓ.ም. እንኳ መጠናቀቅ አለመቻሉ በተለይም የክልሉ ተወላጆችን እያነጋገረ ይገኛል፡፡ በመዘግየቱ ምክንያት የክልሉ ተወላጆች አጥብቀው ቅሬታ ሲገልጹና ሲያነሱ የሚስተዋሉ ሲሆን፣ በክልሉ በሚደረጉ ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ተመሳሳይ ጥያቄዎችንና ቅሬታዎችን ሲያነሱ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ለዚህን ያህል ዓመታት ለስታዲየሙ ግንባታ መዘግየት በቂ ምክንያት የሚሰጥ አካል እንዳልተገኘም እየተነገረ ይገኛል፡፡

የዳሸን ቢራ አክሲዮን ማኅበር የካቲት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በመቐለ ከተማ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት በግንባታው መዘግየት ቅሬታ እየቀረበበት ለሚገኘው የትግራይ ስታዲየም ግንባታ ማጠናቀቂያ የሚለውን የገንዘብ ድጋፍ ያደረገው በክልሉ ከሚሰጠው ምርት ትርፍ ቀንሶ በማስቀረት መሆኑን አስታውቋል፡፡ ዳሸን ቢራ ከስታዲየሙ የገንዘበ ድጋፍ በተጨማሪ ለመቐለ ከተማ እግር ኳስ ክለብ 500,000 ብር ድጋፍ ማድረጉ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በዚሁ የገንዘብ ርክክብር ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የዳሸን ቢራ ፋብሪካ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ ማሩ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የዳሸን ቢራ ፋብሪካ ላለፉት 16 ዓመታት በመላ አገሪቱ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተለያዩ የማኅበራዊ ልማቶችን በመደገፍ ማኅበራዊ ግዴታውን እየተወጣ መሆኑን መናገራቸውም በመግለጫው ተካቷል፡፡

የመቐለ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤልያስ ካህሳይ በበኩላቸው፣ ዳሸን ቢራ በትግራይ ክልል በሁሉም የማኅበራዊ ዘርፍ እያበረከተ ላለው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸው በመግለጫው ተካቷል፡፡