አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጉዳይ ፍርድ ቤት ተጠርቶ ተጠየቀ

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ ጉዳይ ተጨማሪ ማስረጃ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ፣ በአግባቡ ለምን እንዳልፈጸመ ማክሰኞ ጥር 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ኃላፊዎች ቀርበው ተጠየቀ፡፡

የእነ አቶ መላኩ ፈንታን የክስ መዝገብ ቁጥር 14/356 በመመርመር ላይ የሚገኘው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት፣ በመዝገቡ ላይ ተገቢውን ፍትሕ ለመስጠት በአራት ተከሳሾች ድርጅቶች ላይ ባለሥልጣኑ ማስረጃ እንዲልክለት በተደጋጋሚ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

የአቶ ነጋ ገብረ እግዝአብሔር ድርጅት ነፃ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ የአቶ ከተማ ከበደ ድርጅት ኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ የአቶ ገብረ ሥላሴ ገብሬ ድርጅት ኮሜት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና አቶ ጌቱ ገለቴ በሥራ አስኪያጅነት የሚመሩት ጌትአስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ናቸው፡፡

ድርጅቶቹ ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ ከሚሌ እስከ አቃቂ ቃሊቲ ላጋር ጉምሩክ የፍተሻ ቦታዎች ድረስ የተመረጡ ዕቃዎችን ሲያጓጉዙ፣ ተገቢውን ግብር መክፈላቸውን ወይም ካልከፈሉ በመንግሥትና ሕዝብ ገቢ ላይ ያደረሱትን ጉዳት ገልጾ እንዲልክ ነበር ትዕዛዝ የተላለፈለት፡፡

ፍርድ ቤቱ በላከው ትዕዛዝ መሠረት ባለሥልጣኑ ኅዳር 15 ቀን 2009 ዓ.ም አራቱም ድርጅቶች የተሰጣቸውን የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር፣ በሚሌ ጉምሩክ በኩል በተደረገው ማጣራትና ፍተሻ ተስተናግዶ የተገኘ የጉምሩክ ዲክላራሲዮን መረጃ በሲስተም ውስጥ እንዳልተገኘ ጠቅሶ ምላሽ ሰጥቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤቱ በድጋሚ በሰጠው ትዕዛዝ እንደገና ተፈትሾና አጣርቶ ተገቢው ምላሽ እንዲልክለት ሲጠይቅ፣ ባለሥልጣኑ በሁሉም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ድርጅቶቹ ለበርካታ ዓመታት የከፈሉትን የቀረጥና የግብር ክፍያዎችን እየመረመረ መሆኑንና የጨረሱትን አያይዞ ምላሽ በመስጠት፣ ለቀሪዎቹ ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል፡፡

ተከሳሾቹ በተደጋጋሚ ባቀረቡት ተቃውሞ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አካቶ ያላቀረበውን ፍርድ ቤቱ በተጨማሪ ማስረጃነት መጠየቅ እንደሌለበት፣ ችግሩ አለ ቢባል ባልተከራከሩበት ጉዳይ እንዴት ብይን ሊሰጥ እንደሚችል፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነው ቢባል እንኳን በግልጽ የተጠየቀው ከሚሌ እስከ መዳረሻ ባሉ ፍተሻ ቦታዎች፣ በተደረገ የጭነት ልክ ቀረጥና ታክስ መክፈል አለመክፈሉን አረጋግጦ እንዲልክ እንጂ፣ ለበርካታ ዓመታት የሠሩበትን አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በመጨረሻ ባስተላለፈው ትዕዛዝ የተቋሙ ኃላፊ ቀርበው እንዲያስረዱ በማለቱ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነብዩ ሳሙኤል ቀርበው አስረድተዋል፡፡

በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት ለምን እንዳላኩ ተጠይቀው፣ የተረዱት በፍርድ ቤት እንደተነገራቸው ሳይሆን አጠቃላይ እንቅስቃሴውን እንደመሰላቸው ገልጸው በቀጣይ በትዕዛዙ መሠረት እንደሚፈጸም አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ባለሥልጣኑ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት በስምንት ቀናት ውስጥ ምላሽ እንደሚሰጥ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ በመዝገቡ ላይ ብይን ለመስጠት ለጥር 15 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡