አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ጊፍት ሪል ስቴት በውጣ ውረዶች ውስጥ አልፎ የገነባቸውን ቤቶች ለደንበኞች አስረከበ

ጊፍት ሪል ስቴት በብዙ ውጣ ውረዶች ያለፈባቸው የመሪ ሎቄ ሳይት (መንደር ቁጥር ሁለት) ቤቶች ግንባታ አጠናቆ ለደንበኞቹ አስረከበ፡፡

 ጊፍት ሪል ስቴት በ1998 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር በየካ ክፍለ ከተማ በሦስት ቦታዎች 16.3 ሔክታር መሬት ተረክቦ ወደ ግንባታ ገብቷል፡፡ ቅዳሜ ግንቦት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በተገኙበት የተመረቀው ፕሮጀክት በዘጠኝ ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ከ350 በላይ ቪላ ቤቶችና አፓርትመንቶችን ያቀፈ ነው፡፡

ለዚህ ፕሮጀክትም 850 ሚሊዮን ብር ወጪ ወጥቶበታል ተብሏል፡፡ ይኼ ፕሮጀክት በወሰን ማካለልና በተለያዩ ሌሎች ችግሮች ምክንያት የዘገየ በመሆኑ፣ ደንበኞች በተለያዩ ጊዜያት ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡

ጊፍት ሪል ስቴት ለምረቃ በዓሉ ባሳተመው መጽሔት ላይ ሐሳባቸውን በግልጽ ከተናገሩ ደንበኞች መካከል አቶ መላኩ ታደሰ (ኢንጂነር) እና አቶ ዳንኤል ክብረት (ዲያቆን) ይገኙበታል፡፡

አቶ መላኩ ከጊፍት ሪል ስቴት ቤት የገዙት በቅናሽ ሒሳቡ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በድርጅቱ ተቀጥሬ እሠራ ስለነበር አቶ ገብረየስ ኢጋታ ለድርጅቱ መልካም ሥራ ሠርተሃል በማለት ዕድል አመቻችተውልኛል፤›› ሲሉ አቶ መላኩ ገልጸው፣ ‹‹ነገር ግን ይኼንን ዕድል በራሴ ፍላጎት ለውጬ የተሻለ ቤት ገዝቻለሁ፤›› ብለዋል፡፡

[‹‹መወደድ ዕዳ ነው››]

‹‹ይህ ጊዜ እንግዲህ በ2001 ዓ.ም. ነው፡፡ ሥራው ሳይጠናቀቅ ለመረከብ የተዋዋልኩት ከአንድ ዓመት ከስምንት ወራት በኋላ ነበር፡፡ ለነገሩ ብዙ ውሎችን በዚህ መልኩ ከደንበኞች ጋር ተፈራርመናል፡፡ አሁን ታዲያ ደንበኛ ሆኜ ስመጣ ውሉ ምን ያህል እንደሚያስቆጣ የገፈቱ ቀማሽ ሆኜ አይቸዋለሁ፤›› ሲሉ የግንባታውን መዘግየት አስረድተዋል፡፡

ዲያቆን ዳንኤል ከጊፍት ሪል ስቴት መኖሪያ ቤት የገዙ ደንበኞች ያቋቋሙት ማኅበር ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ዳንኤል ለሪፖርተር እንደገለጹት አሁንም ቢሆን መንገድ፣ የኤሌክትሪክና የውኃ አቅርቦት የሚቀሩ ሥራዎች ናቸው፡፡ ‹‹የድንበር መከለልና የባለቤትነት ካርታ ሥራም ቀሪ ሥራዎች ናቸው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ዲያቆን ዳንኤል ጊፍት ሪል ስቴትን የመረጡት እዚያ የሚሠራ ወዳጃቸው በሰጣቸው መረጃ ነው፡፡ ‹‹ዕቅዱንና ቦታው ከባለቤቴ ጋር ካየነው በኋላ ወደነዋል፡፡ ቤቱም በ18 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡ እኛ ግን በ22 ወራት ውስጥ እንዲሆንልን ሐሳብ አቅርበናል፡፡ ፈቃዱን ለማግኘት ብዙ ጊዜ ፈጅቶ ነበር፡፡ አስደናቂው ነገር አራት ወር ለመጨመር አይቻልም ተብሎ ብዙ የተወዛገብንበት ጉዳይ ሰባት ዓመታት መፍጀቱ ነው፤›› ሲሉ የፕሮጀክቱን በእጅጉ መዘግየት አስረድተዋል፡፡

የጊፍት ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ገብረየስ ኢጋታ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ ግንባታው መዘግየቱን አልካዱም፡፡

‹‹ጊፍት ሪል ስቴት የመኖሪያ መንደሮች ግንባታ አልጋ በአልጋ በሆነ ጉዞ ዕውን የሆነ አይደለም፡፡ እጅግ ፈታኝና የድርጅቱን ህልውና አደጋ ላይ ጭምር የጣሉ፣ ደንበኞችንም ለሥጋት የዳረጉ ክስተቶችን አስተናግዷል፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ገብረየስ፣ ‹‹ይኼም ከተወሰኑ የውስጥ ችግሮች ጋር ተዳምሮ ለመኖሪያ ቤቶች ርክክብና ለመንደር ምረቃው መዘግየት ምክንያት ሆኗል፤›› ሲሉ ጉዳዩን አብራርተዋል፡፡

‹‹በተዋረድ በሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ መዋቅሮች ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች በፈጠሩት ውስብስብ ችግር ድርጅቱ ለዓመታት አስተዳደራዊ አገልግሎት እንዳያገኝ ተከልክሎ ቆይቷል፡፡ ጊፍት ይህ ዕርምጃ በብዙ መልኩ ቢጎዳውም ከደንበኞች ጋር የገባውን ቃል ለማክበር ግን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ጊዜ በገፋ ቁጥር የሚገጥመውን ኪሳራ በእህት ኩባንያዎች ድጎማ ለመቋቋም እየሞከረ ችግሩን ለመፍታት አስተዳደራዊና ሕጋዊ መፍትሔዎችን ሲጠቀም ቆይቷል፡፡ በተዋረድ አቤቱታውን ያጤኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሚሰጡት ቋሚና ጊዜያዊ መፍትሔ እየተበረታታን እስካሁን በመዝለቅ፣ ይኼን መንደር አስመርቀን ለደንበኞች የገባነውን ውል ማክበር ችለናል፤›› ሲሉ አቶ ገብረየስ፣ እልህ አስጨራሹን ውጣ ውረድ አልፈው ለደንበኞች ቤቱን ለማስረከብ መቻሉን አመልክተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሙላቱ በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የሪል ስቴት ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች የሚውል ቤት በማቅረብ በኩል ያለውን ክፍተት በመሙላት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ ምንጭ በመሆንና ምቹ የመኖሪያ አካባቢ በመፍጠር ረገድ መልካም ጅምር እንዳለው ገልጸዋል፡፡

‹‹ወደፊትም ሕጋዊ አሠራሩን ጠብቀው የሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶችን መንግሥት በተለያዩ ሁኔታ መደገፉን የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ነገር ግን አሁንም በዘርፉ የሚታዩ ሕገወጥና በምንም ሁኔታ ተቀባይነት የሌላቸው ተግባራት እየተስተዋሉ ስለሆነ፣ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት የዕርምት ዕርምጃ ሊወስዱ ይገባል፤›› በማለት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ አሳስበዋል፡፡

‹‹በተለይም አንዳንዶች ከደንበኞቻቸው ጋር ከጊዜ፣ ከጥራትና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የገቡትን ቃልና ውለታ ካለማክበር ጀምሮ፣ ከደንበኞቻቸው የሰበሰቡትን ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ እስካለማዋል የሚደርሱ ሕገወጥ ተግባራት መፈጸማቸው የአደባባይ ሚስጢር ነው፤›› በማለት የገለጹት ፕሬዚዳንት ሙላቱ፣ ‹‹እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች ጥሪታቸውን አራግፈው ነገ ቤት ይኖረኛል በሚል ተስፋ ገንዘባቸውን ከፍለው ለሚጠባበቁ ዜጎች ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አገርም የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡ ትክክለኛ ሥራ በሚሠሩ ኩባንያዎችም ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖም ቀላል አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሙላቱ በማጠቃለያቸው፣ ‹‹ጊፍት ሪል ስቴት ምንም እንኳን በቤቶቹ ግንባታ ላይ የመዘግየት ችግሮች ቢያጋጥሙትም፣ የተከሰቱ ችግሮችን መፍትሔ በመስጠት ሥራውን አጠናቆ ለባለቤቶቹ ለማስረከብ መዘጋጀቱ የሚያበረታታ ነው፤›› በማለት አክለዋል፡፡

ጊፍት ሪል ስቴት 2008 በጀት ዓመት በመንደር አንድ የገነባቸውን ቤቶች ለደንበኞቹ ማስተላለፉን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡