አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ወይስ ወጣቱን መሸንገያ?

የሚኖረው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ነው፡፡ አሥረኛ ክፍል ድረስ መደበኛ ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ በ2002 ዓ.ም. ከሌሎች 14 ጓደኞቹ ጋር በመሆን በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው በብድር ብሎኬት ማምረት ጀመሩ፡፡ የኮሌጅ ዲፕሎማ ሠርተፊኬት የነበራቸው አባትም ነበሩ፡፡ ብድር፣ የማምረቻ ቦታና ሌሎችንም ድጋፎች ማግኘት ከባድ አልነበረም፡፡ ጅማሮው ሠርተው ገቢ ለማግኘት ከፍተኛ ጉጉት ለነበራቸው ለእሱና ለጓደኞቹ ትልቅ ተስፋ ሆነ፡፡ በ40 ሺሕ ብር ብድር የተጀመረው ብሎኬት የማምረት ሥራ እያደገ ካፒታላቸው ሦስት መቶ ሺሕ ብር ደረሰ፡፡ ይህ ቢሆንም ግን ነገሮች አስቸጋሪ ነበሩ፡፡

በየጊዜው የአባላት በሐሳብ አለመስማማትና የምርታቸው ሳይነሳ መከማቸት የማኅበሩ ትልቅ ፈተና ነበር፡፡ ባለመግባባት ስድስት አባላት ብዙም ሳይጓዙ ማኅበሩን ጥለው በመውጣታቸው የቀሩት ዘጠኝ ነበሩ፡፡ የሚያመርቱትን ብሎኬት ያቀርቡ የነበረው ለገላን ኮንዶሚኒየም ሳይት ነበር፡፡ የአባላት ቁጥር መቀነስንና አለመግባባትን ተቋቁመው እየተንገዳገዱም ቢሆን መቀጠል ችለው የነበረ ቢሆንም፣ የምርታቸው ሳይነሳ መከማቸትና የማሽን መበላሸት የማኅበራቸውን ጉዞ በአጭር (በሦስት ዓመት) እንደገታው ወጣቱ ይናገራል፡፡ ‹‹የምርቱ አለመነሳት በእርግጠኝነት ባይሆንም የቤቶች ልማት ችግር እንደነበር ይሰማኛል፤›› የሚለው ወጣቱ ዛሬ የተበላሸው ማሽን ከማምረቻ ቦታቸው ላይ እንደሚገኝና በማኅበሩ የባንክ ሒሳብ ያለውም ሃያ ሺሕ ብር ብቻ እንደሆነ በቁጭትና በሐዘን ይናገራል፡፡ እሱ እንደሚለው የማኅበሩ አባላት ተበታትነዋል፣ ስደትን ቀጣይ ዕርምጃቸው ያደረጉም አሉ፡፡ በትንሽ ጀምረን ምርታችንን እናስፋፋለን፣ ገቢያችንን አሳድገን ለብዙዎች የሥራ ዕድል እንፈጥራለን የሚለው የእሱና የጓደኞቹ ዕቅድ እንዲህ ተደምድሟል፡፡ ሥራ ካቆሙ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ይህ የእነሱ ማኅበር የተለየ አጋጣሚ ሳይሆን መንግሥት የሥራ አጥነት ችግርን ለመፍታት በፈጠረው አጋጣሚ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው በተለያየ ዘርፍ የተሰማሩ የብዙ ወጣት ማኅበራት ተመሳሳይ ዕጣ ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በመጀመሪያ ደረጃ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው እንዲንቀሳቀሱ ሲደረጉ፣ ቁጥርና መደራጀት ላይ እንጂ የአባላት የሥራ ፈጠራ አቅምና ክህሎት ላይ ትኩረት አለመደረግን ለእነዚህ ኢንተርፕራይዞች ደካማነት ብሎም በአጭር መቅረት በምክንያትነት የሚያስቀምጡ አሉ፡፡

ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ እ.ኤ.አ. በ2010 የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ድህነትን በመቀነስ፣ የሥራ ዕድልን (በተለይም ለወጣቱ) በመፍጠርና ቢዝነስን በማሳደግ ረገድ ያላቸውን ሚና በሚመለከት ያሳተመው ጥናት እንደሚያስቀመጠው፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ስትራቴጂ ከፍተኛ ድጋፍና ዕርዳታ ላይ መሠረት ያደረገ መሆን የተለያዩ አሉታዊ አንድምታዎች አሉት፡፡ ይህ በኢንተርፕራይዞች የተደራጁ እውነታውን ያላገናዘበ ከፍተኛ ድጋፍ እንዲጠብቁ ሲያደርግ፣ ወደ ምርት በመግባት ሒደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ የድጋፉ ከፍተኛ መሆንም ቢዝነሶቹ በራሳቸው እንዲቆሙ ከማድረግ ይልቅ ጥገኛ እንዲሆኑ በማድረጉ፣ ቢዝነሶቹ አድገው ተወዳዳሪ ኢንተርፕራይዝ በመሆን ለኢንዱስትሪ መስፋፋት መሠረት ወደ መሆን እንዳያመሩ እውክታ ፈጥሯል፡፡

ብሎኬት ማምረት ላይ ተሰማርቶ የነበረው የወጣቱና የጓደኞቹ ማኅበር ውድቀትም፣ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከላይ ከተጠቀሱት ነገሮች ጋር የተገናኘ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ወጣቱ እንደሚለው እነሱ በተደራጁበት ወቅት አርባ የሚሆኑ ሌሎች ብሎኬት ማምረት ላይ የተሰማሩ ማኅበራት የነበሩ ቢሆንም፣ ብዙዎቹ በአጭር ቀርተው ዛሬ እየተንቀሳቀሱ ያሉት ስድስት ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህም ቢሆኑ ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ ዛሬም እየተንገዳገዱ ያሉ ናቸው፡፡

በተቃራኒው ከሁለት ዓመት በፊት ለዶሮ ዕርባታ መገናኛ አካባቢ ቦታ ላገኙ የኮሌጅ ምሩቁ ኃይሉ ወልደሰንበትና ጓደኞቹ ብድር ማግኘት ከባድ ነበር፡፡ የ100,000 ብር ብድር ለማግኘት ሃያ በመቶውን ቀድመው መቆጠብ ነበረባቸው፡፡ ሌሎች ድጋፎችንም ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፍም ነበረባቸው፡፡ በተመሳሳይ በዚህ ዓመት 210,000 ብር ብድር አግኝተው ወደ ወተትና የወተት ተዋጽኦ ምርት ለገቡት ዘለዓለም ፍቅሬና ጓደኞቹም ብድርና ሌሎች ድጋፎችን ማግኘት እጅግ አድካሚ ጉዞ ነበር፡፡ ወደ ምርት የገቡትም ከጥቂት ወራት በፊት ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ፣ መንግሥት ባለፉት ዓመታት የወጣት ሥራ አጥነትን በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች አማካይነት ለመፍታት በተንቀሳቀሰበት መንገድ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡ በዋነኝነት የሚጠይቁት አካሄዱ በትክክልም ለወጣቱ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንና ወጣቶቹ በተሰማሩባቸው ዘርፎች የተመረቱ ምርቶች ለወገንና ለአገር ልማት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ነው፡፡ በዚህ ረገድ በመገናኛ ሾላ መንገድ በተደራጁ ወጣት ማኅበራት (በተለያዩ) እየተሠሩ በተደጋጋሚ ተተክለው የተነቀሉ የብረት የመንገድ አካፋዮችን በመጥቀስ፣ በእነዚህ ኢንተርፕራይዞች የሚመረቱ ምርቶችና የሚሰጡ አገልግሎቶች ደረጃቸውን ያልጠበቁ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ በተመሳሳይ በጥቃቅንና በአነስተኛ በተደራጁ ወጣቶች ተመርተው የቀላል ባቡር መስመር እንደሚገነባበት እየታወቀ፣ ከግንባታው ጥቂት ቀደም ብሎ መገናኛ ኡራኤል መንገድ ላይ በተቀመጡ ማግሥት የተነሱ የመንገድ አካፋዮችን መጥቀስ ይቻላል ይላሉ፡፡ ‹‹ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ ወጣቱን መሸንገያ ሳይሆን ትርጉም ባለው መንገድ የወጣት የሥራ አጥነት ችግርን የሚፈታና ለአገር የሚጠቅም መሆን አለበት፤›› ሲሉ ዶ/ር የራስ ወርቅ ያሳስባሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት ለወጣቱ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ያለ እንቅስቃሴ ለአገር የማይጠቅም ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህም ለወጣቱ ሥራ ዕድል ፈጠራ እየተባለ ለልማትና ለአገር ዕድገት ጠብ የማያደርግ ዕርምጃ መጨረሻው ገደል በመሆኑ ማንም አይጠቀምም፡፡ ይህ እንዳይሆን ደግሞ በጥቃቅንና አነስተኛ የሚደራጁ ወጣቶች በሚገባ የሠለጠኑና አቅማቸው የተገነባ፣ መናኛ ነገር አምርቶ ገንዘብ ማግኘት የሚፈልጉ ሳይሆን፣ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ማምረት የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንዲሁ ለወጣት ማኅበራቱ የገንዘብና የግብዓት ድጋፍ የሚያደርግ አቅመ ቢስ የመንግሥት ተቋም ሳይሆን ማኅበራቱን ማሠልጠን፣ ማብቃት እንዲሁም የምርቶችን ጥራት መቆጣጠር የሚችል ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹የታየው ግን ቁጥጥር የሌለበት አመራረት፣ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ግብዓቶች አምርቶ ማቅረብ ነው፤›› በማለት ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ድጋፍ በመስጠት፣ ብድር በማመቻቸትና በሌላውም እንቅስቃሴ ያለው ሙስናም ሌላው ራስ ምታት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ጥናት መደምደሚያም የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ዘርፍን የሚመራው የመንግሥት ተቋም፣ በተቋምና በሰው ኃይል የተደራጀ ይሆን ዘንድ በፖሊሲ ደረጃ ነገሮች መጤን እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ዘርፉ የአደረጃጀትና የሠለጠነ ሰው ኃይል ችግር ስላለበት፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ውጤት እንደማይመራ ያስረግጣል፡፡

ባለፉት አሥር ዓመታት በመንግሥት በተደረገው በጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ ዕድል ፈጠራ እንቅስቃሴ በርካታ ችግሮች መስተዋላቸውን መንግሥትም ያምናል፡፡ የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ዘላቂ መሆን ሲገባቸው አብዛኞቹ ጊዜያዊ መሆናቸውን የሚናገሩት፣ የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ ከተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች 60 በመቶውን የያዙት ጊዜያዊዎቹ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ፡፡

በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ ድጋፍ የሚደረገው ለአምስት ዓመት እንደሆነና ከዚህ ጊዜ በኋላ ኢንተርፕራይዞቹ ወደ ሚቀጥለው ደረጃ መሸጋገር እንደሚገባቸው ስትራቴጂው ላይ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ኢንተርፕራይዞቹ መሸጋገር አይፈልጉም፡፡ ቢፈልጉም ይህን ማድረግ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ የሌላቸው ማለትም በቂ ድጋፍ ያልተደረገላቸውም አሉ፡፡

ከላይ በተጠቀሰው ጥናት ከልክ ያለፈና ኢንተርፕራይዞቹን ለጥገኝነት ያጋለጠ ድጋፍ የተባለውም ይኸው ነው፡፡ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ አነስተኝና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አለመሸጋገራቸውና ለኢንዱስትሪ መስፋፋት ምንም ጠብ የማያደርጉ የመሆናቸውን ነገር፣ ‹‹ካፒታላቸውን የሚደብቁና በድጋፍ የተሰጣቸውን ቦታ ይዘው የሚቆዩ ናቸው፤›› በማለት ይገልጹታል አቶ ዘነበ፡፡

በመጀመሪያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጠናቀቂያ ላይ ከ700 ሺሕ በላይ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የነበሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ በ2008 ዓ.ም. ወደ ታዳጊና መካከለና ደረጃ መሸጋገር የቻሉት 1,586 መሆናቸውንም አቶ ዘነበ ይናገራሉ፡፡

በሌላ በኩል በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ከፍተኛ ሙስና መኖሩ በተጨባጭ የታየባቸው አጋጣሚዎች አንድ ሁለት ብቻ ተብለው በጣት የሚቆጠሩ አይደሉም፡፡

ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ትርጉም ባለው መንገድ የሥራ አጥነት ችግርን እየፈቱ ባለመሆናቸው፣ ለኢንዱስትሪ መስፋፋትም ይህ ነው በሚባል ደረጃ እያበረከቱ አይደለም፡፡ ይልቁንም የፖለቲካ ድጋፉን በማጠናከር ለመንግሥት መጠቀሚያ እየሆኑ ነው ተብለው ይተቻሉ፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ብድርና ድጋፍ ለማግኘት ዕድል የሚያገኙ በወረዳና በመሰል አደረጃጀት የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው፣ ዕድሉን ካገኙ በኋላም ቢሆን የተለያዩ ድጋፎችን ለማግኘት የፖለቲካ ተሳትፏቸውን ቀጣይነት ማረጋገጥ የሚችሉ እንደሆኑም ይነገራል፡፡

አስተያየቶቹ ትክክል ናቸው፡፡ እውነትም መንግሥት የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ኢንቨስትመንትን ለፖለቲካ ጥቅም አውሎታል ቢባል እንኳን፣ እዚህም ላይ ራሱ የሚነሳ ጥያቄ አለ፡፡ በዚህ መንገድስ መንግሥት ድጋፍ አፈራ ወይ? የሥራ ዕድል ተፈጠረለት የተባለው ወጣትንስ ድጋፍ አገኘ ወይ?

እንደ ዶ/ር የራስ ወርቅ ያሉ ምሁራን የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ያስመዘገበው ምንም አዎንታዊ ተፅዕኖ የለም ባይሉም ትርጉም ያለው የሥራ ዕድል ለወጣቱ በመፍጠር፣ ወጣቱን የሙያ ባለቤት በማድረግ፣ አቅም በመፍጠር፣ ለአገር ዕድገትና ልማት በማበርከት፣ እንዲሁም የፖለቲካ ድጋፍ በማስገኘት ረገድ ጭምር ይህ ነው የሚባል ነገር አለመፈየዱን ያምናሉ፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ መንግሥት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ የሚውል የአሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅ ጥር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማፀደቁ ይታወቃል፡፡ ይህ ትልቅ ገንዘብስ ጠቃሚና ቆጣቢ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ እንደሚውልና መንግሥት እንዴት እዚህ ውሳኔ ላይ እንደደረሰ የሚጠይቁ ደግሞ ብዙዎች ናቸው፡፡ ካለፈው ዓመት ኅዳር ወር ጀምሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከ ታወጀበት ጊዜ ድረስ በአገሪቱ ተቀስቅሶ ከነበረው ሰፊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ፣ የወጣት ሥራ አጥነት በእጅጉ መስፋፋት እንደ አንድ ምክንያት ተነስቷል፡፡ ለዚህም ይመስላል የወጣት ሥራ አጥነትን ችግር በአፋጣኝ መፍታት ግድ ያለው መንግሥት፣ የአሥር ቢሊዮን ብር የወጣቶች የተዘዋዋሪ ብድር ፈንድ ሐሳብ ይዞ የመጣው፡፡

የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በገቢ ማስገኛ እንቅስቃሴዎች ተደራጅተው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮቻቸውን እንዲያቃልሉ፣ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ፈንዱ እንደ ተቋቋመ የአዋጁ መግቢያ ያስረዳል፡፡

የመቋቋሚያ ፈንዱ ምንጭ የፌዴራል መንግሥት የሚመድበው አሥር ቢሊዮን ብር በጀት እንደሚሆን አዋጁ ያስረዳል፡፡ ፈንዱን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሆነ፣ ነገር ግን የፈንዱ ተጠቃሚዎች አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ብድሩን የማቅረብ ሥራ እንዲሠሩ፣ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት በሌሉበት ደግሞ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ብድሩን እንዲያቀርቡ ተደንግጓል፡፡

በዚህም መሠረት የንግድ ባንክ ኃላፊነት ለክልሎች የተደለደለውን በመለየት ለሚመለከታቸው አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ማስተላለፍ፣ ተቋማቱ የተላለፈላቸውን ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ማዋላቸውን መቆጣጠር፣ ስለፈንዱ ገንዘብ አጠቃቀም ዝርዝር መግለጫ የያዘ ሪፖርት በየስድስት ወሩና በየዓመቱ የተመረመረ የፈንዱ ሒሳብን ለገንዘብና ለኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ማቅረብ ይገኙበታል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወይም እርሱ የሚመድበው ኦዲተር በየዓመቱ የፈንዱን ሒሳብ የመመርመር ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል ደግሞ የክልሉን ድርሻ  የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ትንበያዎችን መሠረት በማድረግ መደልደል፣ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመመካከር በፈንዱ ለሚሸፈኑ ፕሮጀክቶች የሚሰጥ የብድር ጣሪያ፣ የወለድ መጠን፣ የእፎይታ ጊዜና ተከፍሎ የሚያልቅበትን ጊዜ የተመለከቱ መመርያዎችን የማውጣትና የመወሰን ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

ከፈንዱ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት ከ18 እስከ 34 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ማንኛቸውም ኢትዮጵዊያን መሆናቸውን አዋጁ ያመለክታል፡፡ ከፈንዱ የክልሎች ድርሻንና ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ የሚጠበቁ ወጣቶችን የሚመለከተውን ዝርዝር መረጃ በቀጣዩ ሰንጠረዥ ላይ መመልከት ይቻላል፡፡

ከ18-34 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት ወጣቶች ብዛት በክልሎችና በከተማ መስተዳድሮችና የፈንድ ገንዘብ (ብር 10 ቢሊዮን) ድርሻ

ተ.ቁ

ክልል/ከተማ

18-34 ዕድሜ ወጣት ብዛት

ከጠቅላላ ወጣት ያለው ድርሻ (%)

ከብር 10 ቢሊዮን ያለው ድርሻ

(1)

(2)

(3)

(4=3X10 ቢሊዮን)

1

አፋር

618,827

2.06

206

2

ትግራይ

1,578,463

5.27

527

3

አማራ

8,024,773

26.79

2,679

4

የኢትዮጵያ ሶማሌ

1,806,539

6.03

603

5

ኦሮሚያ

10,314,270

34.39

3,439

6

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ

338,433

1.13

113

7

ደቡብ

5,643,731

18.82

1,882

8

ጋምቤላ

150,414

0.50

50

9

ሐረሪ

80,259

0.27

27

10

አዲስ አበባ

1,255,486

4.19

419

11

ድሬዳዋ

164,762

0.55

55

 

ጠቅላላ ድምር

29,975,958

100

10 ቢሊዮን

 

ምንጭ፡- የፌዴራል ከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ

የዚህ ዕድል ይፋ መሆንን ተከትሎ በአንዳንድ ቦታዎች ተጠቃሚ የሚሆኑ ወጣቶች ምዝገባ ቤት ለቤትና በወረዳዎች ተካሂዷል፡፡ ምንም እንኳ ከዚህ ቀደም ባይሳካም ሪፖርተር እንዳነጋገረው ወጣት ያሉ ከአሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንዱ ተጠቃሚ ለመሆን ዳግም ተመዝግበዋል፡፡ ከእሱ ጋር ብሎኬት ማምረት ላይ ተሰማርቶ የነበረ አንድ ጓደኛው ዛሬም ተደራጅቶ ለመሥራት ተስፋ የሰነቀ ቢሆንም፣ ዕድሉ የፖለቲካ ተሳትፎ ላላቸው ነው የሚሆነው ብሎ በማሰብ መመዝገብ ከንቱ ልፋት ነው ያሉም ብዙዎች መሆናቸው ይነገራል፡፡

በሌላ በኩል ይህ ትልቅ የአገር ኢንቨስትመንት ወጣቱን ለመሸንገል ሳይሆን ለአገርና ለወገን እንዲጠቅም፣ ተጠቃሚ ወጣቶች ሲመረጡ ጠንካራ መመዘኛዎች መቀመጥ እንዳለባቸው፣ ሁሉን ለማዳረስ መሞከር ሳይሆን የተጠቃሚዎች ቁጥር በሚገባ መወሰን እንዳለበትና የሙስናው ነገርም ሊታሰብበት እንደሚገባ አስተያየታቸውን የሰነዘሩ አሉ፡፡ (ምሕረት ሞገስ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጋለች)