አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

ፌርማታ

 

በ1950ዎቹ መጀመርያ ጫማ አስጠራጊ አዲስ አበቤዎች በፒያሳ ሲኒማ ኢትዮጵያ አካባቢ 

‹‹የተጠበሰ እንቁላል››

የሆቴልን ነገር ሆቴል ያነሣዋል፡፡ አንድ አሜሪካዊና አንድ ኢትዮጵያዊ ወደ አንድ ሆቴል ገብተው አሜሪካዊው የተጠበሰ እንቁላል፣ ኢትዮጵያዊው ደግሞ የተጠበሰ ዶሮ አዝዘው እየተመገቡ እንዳሉ ኢትዮጵያዊው የቀረበለትን ዶሮ አጥንት ሲቆረጣጥም የተመለከተው አሜሪካዊ በኢትዮጵያዊው ለማፌዝ ‹‹ለውሾቹ ምን ተረፋቸው›› ብሎ ሲጠይቀው ኢትዮጵያዊው ፈጠን ብሎ ‹‹የተጠበሰ እንቁላል›› ብሎ መለሰለት፡፡

በዚያው ዓመት ሌላ አንድ ሰባኪ መጣና ‹‹በነፋሱ ውስጥ አንድ ሆነው የሚኖሩ ሦስት አማልክት አሉ፡፡ እጅግ የከበረችና ሰፊ የሆነች ሚስትም እህትም የምትሆን እናት አለቻቸው›› ብሎ ተናገረ፡፡

ይሄን ጊዜ ሁሉም ደስ አላቸው ‹‹አማልክቱ ሦስት መሆናቸው በኃጢአታችን ላይ እንዲከራከሩ ስለሚያደርጋቸው ጥሩ ነው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ የተከበረች እናታቸው ለእኛ ምስኪን ኃጢአተኞች ትከራከርልናለች›› በማለት አሰቡ፡፡

ይሁን እንጂ እስከዛሬ ድረስ የኪላፊስ ከተማ ነዋሪዎች አምላክ ብዙ ነው፣ አንድ ነው፣ የለም አንድም ሦስትም ነው እያሉ ከመከራከራቸው በተጨማሪ ስለተከበረችው የአማልክት እናትም እየተነታረኩ ነው፡፡

  • ካህሊል ጂብራን ‹‹የጥበብ መንገድ›› (1998)

* * *

‹‹እንግሊዝ ጨው ስግተው››

ልጃቸው ቁልፍ የዋጠባቸው ሴት በፍጥነት ወደ ሐኪም ቤት ይዘው ይሔዱና ለዶክተሩ ችግሩን ይነግሩታል፡፡ ዶክተሩም ቁልፉን ለማውጣት ተኝቶ ቀዶ ሕክምና እንደሚደረግለት ሲነግራቸው እናት በመናደድ ተነሥተው ልጃቸውን ይዘው ለመሔድ ሲዘጋጁ ‹‹ወዴት ልትወስዱት ነው፤›› ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ ሴትዮዋም ‹‹የልጄን ሆድም አላስቀድድም፤ ቁልፌንም እንግሊዝ ጨው በጥብጩ ባፉ ባፉ ስግተው ይተፋታል፤›› ሲሉ መለሱለት፡፡

- ‹‹የወግ ገበታ››

* * *

‹‹አብዝተው እስካልወለዱ ድረስ…››

እንግሊዝን በመጎብኘት ላይ ያለ አንድ የየል ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር አንዱን የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ መምህር አገኘውና ስለእንግሊዝ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጠባይ ጠየቀው፡፡

‹‹ወንዶቹን እንዲያጨሱ ትፈቅዱላቸዋላችሁ? ሲል አሜሪካኑ ጠየቀ፡፡

‹‹አንፈቅድላቸውም›› ሲል እንግሊዛዊው መለሰ፡፡

‹‹መጠጥ ይጠጣሉ?››

‹‹በፍፁም አይጠጡም››

‹‹ልጃገረዶችንስ እንዲያወጡ ትፈቅዱላቸዋላችሁ?›› አሜሪካኑ ጠየቀ፡፡

‹‹ኦ ይህማ የተፈቀደ ነው›› አለ፤ እንግሊዛዊው ቀጥሎም ‹‹ይኸውም አብዝተው እስካልወለዱ ድረስ ነው›› አለው፡፡

  • አዳነ ቸኮል ‹‹የቀልዶች ማዕበል›› (2000)

* * *

የሕዝቡ ዕውቀትና ሀብት ሲያድግ የመንግሥቱ ሀብትና ሐሳብም ይሰፋል

እስቴር ሶምሎ የሚባል የጀርመን ሊቅ እንዲህ ይላል፣ እያንዳንዱ ሰው ሌላውን ሰው ሁሉ አጥቅቶ ለብቻው እንደ ፈቃዱ እንዲኖር ይወዳል፡፡ መንግሥት ግን በግዛቱ ውስጥ የሚኖሩትን ኃይለኞች ሁሉ እርስ በርሳቸው እንዲተፋፈሩ የግድ ይላቸዋል፡፡ የመንግሥት ጥረቱ ሕዝቡን ሁሉ አስማምቶ በመካከላቸው ሰላም ለማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም መንግሥት የተሻለውን ሥርዓት እያወጣ፣ ያወጣውንም ሥርዓት እንዳይፈርስበት ባለቤቱ ይጠብቃል፡፡ ሥርዓት አውጪውም ዳኛም መንግሥት ራሱ ነው፡፡ ከዳኝነቱ በቀር ሕዝቡን ከፍ ወዳለው የዕውቀትና የሀብት ደረጃ እንዲደርስ የማስተዳደሪያ ደንብ እያወጣ ባወጣውም ደንብ ሕዝቡን በሥርዓት ያስተዳድራል፡፡ ሕዝቡንም ማስተዳደር ማለት ጥንት የቆየውን የሕዝብ ጥቅም እንዳይጠፋ መጠበቅ ነው፡፡ ሌላውንም አዲስ ጥቅም አዘጋጅቶ አውጥቶ በግድ ማስፈጸም ነው፡፡ የሕዝብ ሐሳብና ሀብት ሲሰፋ መንግሥት ሐሳቡን ለማስፈጸም የበለጠ ኃይል ያገኛል፡፡

እንግዲህ እንደ ሊቁ ቃል ከሄድን ዘንድ፣ በመንግሥቱ ውስጥ የሚያድር ሕዝብ ዕውቀት የሌለውና ድሃ የሆነ እንደሆነ መንግሥቱ ኃይል ሊያገኝ አይችልም፡፡ እንኳን በውጭ አገር ሊታፈር የገዛ ሕዝቡም ቢሆን አያፍሩትም፡፡ በአገሩ ውስጥ ሽፍታ፣ ወንበዴና ሌባም ይበዛበታል፡፡ ሕዝቡ ዕውቀት ሲያድርበት ግን መንግሥት አዋቂዎች፣ ሠራተኞችንና ሹማምንቶችን ያገኛል፡፡ ሕዝቡም ሲበለፅግ መንግሥት በግብር የሚያገኘው ገንዘብ እየበዛ ይሄዳል፡፡

  • ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ‹‹መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር›› (1916)

* * *

የዘንድሮው ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ በአሜሪካ

ጨረቃ በፀሐይና በመሬት መካከል በምትሆንበት ጊዜ የሚፈጠር ድንቅ ክስተት ነው፡፡ የፀሐይ ግርዶሽ ከስንት አንዴ የሚከሰት የሥርዓተ ፀሐይ አካል ነው፡፡ በተወሰኑ ዓመታት አንዴ የሚከሰተው የፀሐይ ግርዶሽ ከፊልና ሙሉ ግርዶሽ ሆኖ ይታያል፡፡ ታዲያ የፀሐይ ግርዶሽ በሚታይበት አገር ውስጥ የሚኖሩ በነቂስ ወጥተው ለአንድ አፍታ ወደ ሰማይ ቢያንጋጥጡ አያስገርምም፡፡ ግርዶሹን የሚያዩበትን የተለየ መነፅር ዓይናቸው ላይ ሰክተው በተመስጦና በግርምት ቢያዩ ማጋነን አይሆንም፡፡

ከ99 ዓመታት በኋላ በአሜሪካ ነሐሴ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. ታይቶ በነበረው ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ አወዛጋቢው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሳይቀሩ ከእነ ቤተሰቦቻቸው በመውጣት ወደ ላይ አንጋጠው ግርዶሹን ተመልክተው ነበር፡፡ በአሜሪካ የመጀመርያው ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ የታየው ከ99 ዓመታት በፊት ነበር፡፡

ሲኤንኤን እንደዘገበው፣ ቀጣዩ የፀሐይ ግርዶሽ እ.ኤ.አ. በ2024 ይከሰታል፡፡ ግርዶሹ ሲፈጠር በተለያዩ ከተሞች በአንድ ጊዜ ጨልሞ ነበር፡፡ ከዋክብት ታይተዋል፡፡ የፀሐይ ብርሃን መጥፋትን ተከትሎ የሙቀት መጠንም ቀንሶ ነበር፡፡ ከአሬጎን ግዛት ተነስቶ ደቡብ ካሮላይና ድረስ የዘለቀውን ይህን ክስተት በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ቀጥታ ሥርጭት ማድረጉን ከፌስቡክ ድረ ገጽ ለማወቅ ተችሏል፡፡

* * *