ፍሬ ከናፍር

‹‹በኔ እምነት መሠረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ ዓድዋው ያለ ጦርነት የለም፡፡ በእልቂቱ በኩል 25,000 ሰዎች በአንድ ቀን ጀምበር የሞቱበትና የቆሰሉበት ነው፡፡ ፖለቲካና ታሪክ አበቃ፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ታላላቅ የተወላጆች ኃይል መነሳቱ ታወቀ፡፡ የአፍሪካ ተወላጆች ታሪክ ተለወጠ፡፡ ጥቁሩ ዓለም በኤሮፓውያን ላይ ሲያምፅና ሲያሸንፍ የመጀመሪያው መሆኑ ነው፡፡››

ጆርጅ በርክለይ እ.ኤ.አ. በ1902 በጻፈው ‹‹ዘ ካምፔይን ኦፍ ዓድዋ ኤንድ ዘ ራይዝ ኦፍ ምኒልክ›› (The Campaign of Adowa and the Rise of Menelik) መጽሐፍ ላይ፣ ኢትዮጵያ ከ121 ዓመታት በፊት በዓድዋ በኢጣሊያ ሠራዊት ላይ የተቀዳጀችው ድል አስመልክቶ የጻፈው፡፡ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. (ማርች 1 ቀን 1896) በዳግማዊ ምኒልክ ጠቅላይ አዝማችነት የዘመተው የኢትዮጵያ ሠራዊት በጄኔራል ኦሬስቴ ባራቴሪ በሚመራው የኢጣሊያ ኃይል ላይ በዓድዋ አንፀባራዊ ድል አግኝቷል፡፡ በርክለይ በመጽሐፉ የኢትዮጵያን ልዕልና ከአውሮፓ አንፃር የገለጸበትም እንዲህ ይነበባል፡፡ ‹‹ሐበሾች አደገኛ ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል፡፡ የኛ ዓለም ገና ቶር እና ኦዲዮን በሚባሉ አማልክት ሲያመልክ በነበረበት ጊዜ ሐበሾች የክርስትናን ሃይማኖት የተቀበሉ ናቸው፡፡ . . . አሁን የሁሉንም ፍላጎት ዓድዋ ዘጋው. . .፡፡››