​ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዶፒንግ በሚገኝባቸው አትሌቶች ላይ የዕድሜ ልክ ዕገዳ እንደሚጥል አስታወቀ

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዶፒንግ (አበረታች ንጥረ ነገር) በሚገኝባቸው አትሌቶች ላይ የዕድሜ ልክ ዕገዳ እንደሚጥል አስታወቀ፡፡ ከፌዴሬሽኑ ዕውቅና ውጭ በየትኛውም አገር ተወዳድረው የችግሩ ሰለባ በሚሆኑ አትሌቶች አገሪቱ ተጠያቂ እንደማትሆን ጭምር ገልጿል፡፡

በቅርቡ ወደ ኃላፊነት የመጣው የብሔራዊ ፌደሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ረቡዕ ታኅሣሥ 19 ቀን 2009 ዓ.ም. በብሔራዊ ሆቴል በሰጠው መግለጫ፣ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) የፀረ አበረታች ኤጀንሲ (ዋዳ) ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአምስት የዓለም አገሮች የሰጠውን ማስጠንቀቂያ መነሻ በማድረግ የመፍትሔ አማራጭ ያለውን በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ የዓለም አቀፍ ፀረ አበረታች ንጥረ ነገሮች ኤጀንሲ (ዋዳ) በስድስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ላይ ምርመራ እንዲደረግባቸው ትዕዛዝ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡

ይህንኑ የዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች ንጥረ ነገሮች ኤጀንሲ (ዋዳ) ያስተላለፈውን ትዕዛዝ መነሻ በማድረግ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በተለይ በአበረታች ንጥረ ነገሮች በሚጠረጠሩ አትሌቶች ላይ በሚወስዳቸው አምስት የውሳኔ ሐሳቦች ላይ ማብራሪያም ሰጥቷል፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በተገኘበት በተሰጠው ማብራሪያ መሠረት፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ዶፒንግ በሚገኝባቸው አትሌቶች ምንም ዓይነት ድርድርም ሆነ ይቅርታ አይኖረውም፡፡ ለእውነተኛና ንፁህ አትሌቶች መብትም በማንኛውም ሁኔታ እስከ መጨረሻው እንደሚቆም፣ ይህ የአቋም መግለጫ በፌዴሬሽኑ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ከአበረታች ንጥረ ነገሮችና ድርጊቶች ጋር ተያይዞ ከሚነሱ አትሌቶች፣ ማናጀሮችና አሠልጣኞች ጋር አብሮ እንደማይሠራም አስታውቋል፡፡

አዲሱን የፀረ አበረታች እንቅስቃሴን ትኩረት በምርመራ ላይ በማተኮር፣ ከብሔራዊ የፀረ ዶፒንግ ጽሕፈት ቤት ጋር አብሮ በመቀናጀት እ.ኤ.አ. ከ2017 ጀምሮ 200 ናሙናዎችን በመውሰድ ምርመራ ለማሠራት ስለማቀዱም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ በዚህ መሠረት ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንና ከዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) የዕገዳ ቅጣት በተጨማሪ የአገሪቱ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 526 መሠረት በማድረግ ከአበረታች ንጥረ ነገሮች ጋር ተያይዞ ወንጀል የሠራ ማንኛውም አካል በኢትዮጵያ ሕግ ተጠያቂ እንደሚሆንም ፌዴሬሽኑ ገልጿል፡፡

በመግለጫው እንደተገለጸው ከሆነ፣ አንቀጽ 526 ዶፒንግን አስመልክቶ ሲያብራራ ማንም ሰው በተፈጥሮና በሥልጠና የተገኘው የአካል ብቃት በጊዜያዊ መልክ በይበልጥ እንዲጨምር በማድረግ በስፖርቱ ውድድር ጊዜ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ የበላይነት ለማግኘት የሚረዱ በሕግ የተከለከሉና ጎጂ የሆኑ ሰው ሠራሽ ነገሮችን ያመረተ፣ ወደ አገር ውስጥ ያስገባ፣ በባለሙያነት ያዘዘና ያከፋፈለ፣ እንዲሁም ቀደም ሲል በተጠቀሱት ነገሮች በሕገወጥ መንገድ የተጠቀመ፣ ወይም ሌላ ሰው እንዲጠቀምባቸው ያደረገ እንደሆነ በቀላል እስራት ይቀጣል፡፡ መቀጮው ወይም ድርጊቱ ከባድ ጉዳት ባስከተለ ጊዜ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ማስቀመጡን በዝርዝር አስረድቷል፡፡

ፌዴሬሽኑ በተጨማሪም ከዚሁ ከአበረታች ንጥረ ነገሮች ጋር ተያይዞ በአይኤኤኤፍ አራት ዓመት ዕገዳ ከተጣለበትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባል ከሆነ  እስከመጨረሻው ዕገዳ እንደሚጣልበት ጨምሮ አስታውቋል፡፡