​ ‹‹የታሪክ ተማሪዎቻችን ያለፈውን የኢትዮጵያ ታሪክ አሻራ ጠልቀው የሚመለከቱት፣ ሪቻርድ ፓንክረስት በከፈቱት መስኮት ነው፡፡››

የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የዩኔስኮ ለሰብአዊ መብትና ዴሞክራሲ ወንበር ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ፣ ለፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትና ሪታ ፓንክረስት መታሰቢያ በተዘጋጀ መጽሔት ላይ ካሰፈሩት ቀዳሚ ቃል የተወሰደ፡፡ ማክሰኞ የካቲት 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ሥርዓተ ቀብራቸው የተፈጸመው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ከባለቤታቸው ሪታ ጋር ላከናወኑት ዘርፈ ብዙ አገልግሎት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕይወት እያሉ፣ በመሠረቱት ‹‹የኢትዮጵያ ጥናት መጽሔት-Journal of Ethiopian Studies›› በክብር ዘክሯቸዋል፡፡ ፕሮፌሰር አንድርያስ በቀዳሚ ቃላቸው ላይ የተንደረደሩት የፓንክረስት ቤተሰብን እንዲህ በመግለጽ ነው፡፡ ‹‹የፓንክረስት ስም በ20ኛው ክፍለ ዘመን በተለያዩ ዝግጅቶችና ሁነቶች በግንባር ቀደምትነት ተነስቷል፡፡ የሴቶች የመምረጥ መብት፣ የሠራተኛው መደብ መብት የማስከበርና የፀረ ፋሺስት ንቅናቄዎች፣ እንዲሁም በፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ስሙ ይታወሳል፡፡ ወደ ኢትዮጵያም ስንመጣ የፓንክረስት ቤተሰብ [እናት ሲልቪያ፣ ልጅ ሪቻርድና የልጅ ሚስት ሪታ] ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ ላይ በነበራት አይበገሬነት ተሳትፏል፡፡ ድኅረ ጦርነትም ኢትዮጵያና ኤርትራ አብረው እንዲሆኑ ብዙ ጥሯል፡፡››