አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

‹‹መንግሥት ስፖርቱን የሚያግዝ ከሆነ በስሙ የሚነግዱ ሕገወጦችን መስመር ሊያሲዛቸው ይገባል››

ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፣ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት

በኢትዮጵያ ረዥም የምሥረታ ዕድሜ ካላቸው ስፖርቶች  ቅርጫት ኳስ አንዱ ተጠቃሽ ነው፡፡ እንደሌሎቹ ስፖርቶች ሁሉ ቅርጫት ኳስም ዕድሜውን ከመቁጠር ባለፈ ይህ ነው የሚባል የቅርፅም ሆነ የይዘት ለውጥ ሳይኖረው አሁን ላይ ይገኛል፡፡ የዘጠኝ ክልሎችና የሁለት ከተማ አስተዳደሮች ውክልና ያለው የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን በአዲስ አበባ በተለምዶ ትንሿ ስታዲየም ተብሎ በሚታወቀው ማዘውተሪያ አጠገብ በቆርቆሮ በተሠራች ሦስት በሦስት ክፍል ውስጥ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሲመራ ቆይቷል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በቅርቡ ባካሄደው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ አዲስ አመራሮች ምርጫ አድርጓል፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት ኃላፊነቱን በጀመሩበት ማግሥት የውክልና ጥያቄ ቀርቦባቸው ጉባኤውን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲጠራ አድርገው የቀረበባቸውን የውክልና ጥያቄ እንዲጠራ አድርገዋል፡፡ የውክልና ጥያቄው እንዴትና በእነማን ቀረበ? ምክንያቱስ? በሚለውና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከዶ/ር አሸብር ጋር ደረጀ ጠገናው ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ በአብዛኛው የሚታወቁት እግር ኳሱ ላይ በነበረዎት እንቅስቃሴ ነው፡፡ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት እንደገና ወደ ስፖርቱ ተመልሰዋል፡፡ እንዴት አገኙት?

ዶ/ር አሸብር፡- ለቅርጫት ኳስ ቅርብ ከሆኑ ሰዎችን አንዱ ነኝ፡፡ አዲስም ስላልሆንኩ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ እውነታ አውቀዋለሁ፡፡ አሁንም በአዲስ ኃላፊነት መጥቻለሁ፡፡ ስፖርቱ ማናችንም እንደምናውቀው ዓለም ላይም ሆነ በአገራችን የሚወደድና የሚዘወተር ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በጣም ብዙ ኃላፊነትና ሥራ ይጠብቀናል፡፡

ሪፖርተር፡- ቅርጫት ኳስ በአገሪቱ የሚሰጠው ትኩረት ትርጉም ያለው ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት የብዙዎቹን ቀልብ በመግዛት የሚታወቁት እግር ኳስና አትሌቲክስ ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ቅርጫት ኳስን ለማሳደግና ለመለወጥ የሚቸገሩ አይመስልዎትም?

ዶ/ር አሸብር፡- በእርግጥ ፈተናው ከባድ ነው፡፡ ሕዝባችን በእግር ኳሱም አልረካም፡፡ ወደ ቅርጫት ኳሱም ስንመጣ ተመሳሳይ ነው፡፡ ኅብረተሰቡን ወደ ስፖርቱ ለማምጣት ቀላል አይሆንም፡፡ ቁርጠኝነት ካለ ግን ችግሩ ከባድ አይሆንም፡፡ ለዚያ ደግሞ መንግሥት ከሕዝባዊ አካሉ ጎን ሆኖ በተለይ በፕሮጀክና በትምህርት ቤቶች ስፖርት፣ በክልሎች ተሳትፎና መሰል ድጋፎች ላይ ኃላፊነቱን በመውሰድ በአገሪቱ የስፖርት ፖሊሲ መሠረት መንግሥታዊ አካሉና ሕዝባዊ አካሉ ተደጋግፈን ከሠራን ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ይኼ ከሆነ በተለይ ቅርጫት ኳስ ማዘውተሪያው ያን ያህል ሰፊ ቦታ አይወሰድም፡፡ ትምህርት ቤቶችን እንኳን ብንወስድ የቅርጫት ኳስ ሜዳ የሌላቸው የሉም፡፡ ያንን ማቀናጀቱና ማጠናከሩ ካልሆነ እንደ እግር ኳስ ትልቅ ስታዲየም መሥራት የግድ አይልም፡፡ ይኼ ታዳጊ ወጣቶች በቀላሉ ስፖርቱን እንዲያዘወትሩ በማድረግ ኤሊቶችን ማፍራት እንዲቻል ያግዛል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ቅርጫት ኳሱን ጨምሮ የብዙዎቹ ስፖርቶች የምሥረታ ዕድሜ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ዕድገታቸው ግን የዕድሜያቸውን ያህል አይደለም፡፡ ምክንያት የሚሉት ይኖርዎታል?

ዶ/ር አሸብር፡- ብዙ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዋናነት ግን ድህነታችን ነው፡፡ አገሪቱ በተለይም በአሁኑ ወቅት በዕድገት ጎዳና ላይ ስለምትገኝ ስፖርቱም አብሮ የሚያድግበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም፡፡ አሁን ላይ ሁሉም እንደሚያውቀው መንግሥት ለስፖርቱ መሠረተ ልማት በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ፕሮጀክቶችና ክልሎች ላይ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ግን ስፖርቱ የሚፈለገውን ያህል ትኩረት ስላላገኘ ታዳጊዎችንና ወጣቶችን እያፈራን አይደለም፡፡ በዚህም ስፖርቱ በገበያ ደረጃ  ኩባንያዎችንና ድርጅቶች ለመሳብ አልታደለም፡፡ ስፖርት ያለስፖንሰር በመንግሥት ድጎማ ብቻ የትም መድረስ አይችልም፣ ከባድም ነው፡፡ ሌላው ምክንያት ደግሞ በአገሪቱ በሁሉም ስፖርቶች ከፍተኛ የሆነ የአቅም ችግር አለ፡፡ ይኼ ተቋማቱ ተልዕኮዎቻቸውን እንዳይወጡና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶቻቸውን እንዳያዳብሩ አድርጓል፡፡ በተለይ አሁን አሁን ለስፖርቱ ቁልፍ ሚና ለሚጫወተው ማርኬቲንግ ማነቆ መሆኑ አልቀረም፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የግንዛቤ ችግር አለ፡፡ ለዚህም መንግሥት በአገሪቱ የስፖርት ፖሊሲ አውጥቶ አሰቀምጧል፡፡ በፖሊሲው ከተካተቱት በአንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ 1 እንደሚለው፣ ሕዝባዊ አካሉ ስፖርቱን ይሠራል፡፡ መንግሥታዊ አካሉ ደግሞ ይደግፋል ይላል፡፡ ግን ይህንን ከመንግሥት ተልዕኮ ውጪ በሆነ መንገድ ስፖርቱን በብቸኝነት በመያዝ እነሱ በፈለጉት መንገድ ብቻ እንዲሄድ የሚፈልጉ አካላት አሉ፡፡ እነዚህ አካላት አንድ ምርጫ በመጣ ቁጥር የማጭበርበር፣ የመንግሥት አቋምና አቅጣጫ ነው በሚል እገሌን ምረጡ የሚለው አካሄድ እጅግ እየተለመደ እንዲመጣ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህ የማከናወን ሥራ ላይ የተሰማሩ አንዳንድ የመንግሥት አካላት በፖሊሲው ከተቀመጠው የመንግሥት ተልዕኮ ወጪ የሚሄዱበትን መንገድ በማስቆም ወደ ስፖርቱ መምጣት የሚገባቸው ኃይሎች እንዲመጡ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ የመንግሥት አቋም እኔን ጨምሮ የምናውቀውና እየሆነ ያለው መንግሥት በሚያምንበት አግባብና ደረጃ የተቋቋመ ጠቅላላ ጉባኤ አለ፡፡ በዚያ መሠረት መንግሥት ያመነበት ጠቅላላ ጉባኤ የሚወስነውንና የሚደርስበትን ጭብጥ የመንግሥት አቋምና ፍላጎት ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ውጪ መንግሥት ከከበደ አበበን ብሎ የሚሄድበት አግባብ የለውም፡፡ በቅርቡ ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንትነት ለምርጫ ሲቀርቡ የመንግሥት አቋምና አቅጣጫ ስለሆነ አትምረጡ የተባለበትን ሁኔታ ሰምተናል፡፡ ይኼ ማወናበድ ነው፡፡ ሻለቃ ኃይሌ ተመርጠው ኃላፊነት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለምንድነው ታዲያ የመንግሥት አቅጣጫ ከሆነ መንግሥት የተቀበለው? ሒደቱ በአጠቃላይ የመንግሥት ፍላጎት የሌለበት መሆኑን ነው የሚያሳየው፡፡ መንግሥት ገለልተኛ ሆኖ፣ ግን በሕግና በሥርዓት የጉባኤውን ውሳኔ ሲቀበልና የጉባኤውን አቅጣጫ ሲከተል ነው ያየነው፡፡ ኃይሌ ለምን ተመረጠ? ብሎ ሲቃወም አላየንም፣ አልሰማንም፡፡ ከዚህ አኳያ ወደፊትም መንግሥት ስፖርቱን የሚያግዝ  ከሆነ በስሙ የሚነግዱ አካላትን ትኩረት አድርጎ መስመር ሊያሲዛቸው ይገባል፡፡ ከዚህ ባለፈ  የስፖርቱ ሌላው ትልቅ ችግር የቁርጠኝነት መጥፋት ነው፡፡ አንድ ሰው ኃላፊነቱን ከተቀበለ በኋላ ያንን ኃላፊነት ለመወጣት ያለው ቁርጠኝነት አናሳ ነው፡፡ ከዚህ ባልተናነሰ ስፖርቱ ላይ የዲሲፕሊን ማለትም ስፖርተኞችን ከማነፅ ጀምሮ ለራሱ ለስፖርቱ ሕግና ደንብ ታማኝ አለመሆን ሌላው ቁልፍ ችግር ነው፡፡ ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ ግን አሁን አሁን ትኩረት እያገኘ የመጣ የማዘውተሪያ እጥረትን በመቅረፍ ዘርፉን የልማቱ አካል አድርጎ ማየት የግድ ይላል፡፡

ሪፖርተር፡- በመንግሥት ሽፋን አንዳንድ ኃይሎች በተለይ ስፖርቱ ላይ ያላቸው ጣልቃ ገብነት የሚቀጥል ከሆነ እርስዎ ችግሩን ተቋቁመው ለመቀጠል አይቸገሩም?

ዶ/ር አሸብር፡- በእኔ እምነት መንግሥት ወይም ያለው ሥርዓት በአገራዊ ጉዳዮች አስመሳዮችን የሚታገስበት ጊዜ ላይ አይደለም፡፡ እውነተኛ ከሆንን ለሁላችንም እኩል የቆመ መንግሥት ነው፡፡ ብዙ ነገር እንደሚባል እሰማለሁ፡፡ ዶ/ር አሸብርን መንግሥት አይወደውም፡፡ እሱ ወደ ስፖርቱ እንዳይመጣ የመንግሥት አቋም ነው ብለው የሚያስወሩ አሉ፡፡ በግሌ የምቀበለው አይደለም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነኝ ሕግና ደንቡ እስከፈቀደልኝ ድረስ የምረበሽበትና የምሠጋበት ሁኔታ የለም በሚል በውስጤ ስለማምን እስከመጨረሻው እገፋበታለሁ፡፡ ሁሌም በአሸናፊነት የምወጣው ለዚያ ነው፡፡ ስፖርቱ ላይ የመንግሥት አቋም ነው የሚሉ ሰዎች ብዙ ጊዜ በጊዜያዊ ጥቅማ ጥቅም የታወቁ፣ ኑሯቸውና ሕይወታቸው በዚያው የሆነ፣ በስፖርቱ በሚያገኙት ጥቅማ ጥቅም ኑሯቸውን የለወጡና ለመለወጥ የሚያስቡ፣ የማይገባቸውን ጥቅም ሲያገኙ የኖሩ አሁንም ይቋረጥብናል ብለው የሚሠጉ ካልሆነ በስተቀር መንግሥት በዚህ ጉዳይ ለሁላችንም እኩል ነው፡፡ በእያንዳንዱ ትናንሽ ጉዳይ የሚገባበት ምንም ነገር የለውም፡፡ ምክንያቱም በፖሊሲው የሕዝባዊ አካሉንና የመንግሥታዊ አካሉን ድርሻና የኃላፊነት ገደብ አስቀምጧል፡፡ ይህም በመሆኑና እውነትን ይዤ በምሠራው ሥራ ቅንጣት ታክል አልሠጋም፡፡

ሪፖርተር፡- ከእርስዎ የቅርጫት ኳስ ምርጫ ጋር ተያይዞ የማጭበርበር ሥራ ተሠርቷል በሚል ምርጫው እንዲደገም፣ ጉባኤውም እንደገና የተጠራበት ሁኔታ አለ፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?

ዶ/ር አሸብር፡- አንድ ባለድርሻ አካል ቅሬታ ስላቀረበ ብቻ ድጋሚ ጉባኤ ለምን ጠራችሁ? ብሎ ድጋሚ የተጠራው ጉባኤ ሚዲያው ባለበት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ጠይቋል፣ ወቅሷል፡፡ እውነትነት ያለው ወቀሳ ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሁለት ጊዜ ጉባኤ መጥራት በጣም እንግዳ የሆነ ነገር ነው፡፡ የተለመደም አይደለም፡፡ ወደዚህ ውሳኔ የመጣነው ለስፖርቱ ሲባል በጣም አስበንበት ነው፡፡ በዋናነት ስፖርቱ ላይ የተመደቡት የስፖርቱ መሪዎቻችን እንግዶች በመሆናቸው ከወዲሁ የተለያዩ ችግሮች ተነስተው ከስፖርቱ መሪዎች ጋር ቅሬታ ውስጥ መግባት ስላልፈለግን ነው፡፡ መከፋፈል ውስጥ እንዳንገባና ከምንም በላይ የአገሪቱ ስፖርት ሰላማዊ ጉዞ እንዲኖረው ስለምናምን ነው፡፡ ምክንያቱም ስፖርቱ እንኳን ተከፋፍለን ቀርቶ አንድ ሆነንም በመንገዳገድ ላይ ነው፡፡ ሌላው ለእኔ ድጋፍ የሰጠው የደቡብ ክልል ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ድጋፉን ሰጥቶኝ ሲያበቃ አልሰጠሁም በሚልበት ሁኔታ ለራሴ ሞራልም ጥሩ ስላልሆነ ጉዳዩ ጠርቶ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም እውነታውን እንዲያውቅ ከነበረኝ ፍላጎት ነው፡፡ የደቡብ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽንም የሄደበትን አግባብ ቆም ብሎ እንዲመለከትና ከምንም በላይ ደግሞ እኔ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ገብቶ አገልግሎት ለመስጠት ፍላጎቱ ስላልነበረኝና የጉባኤውን ውሳኔ በፀጋ ለመቀበል እምነቱ ስለነበረኝ ነው፡፡ በግሌ የያዝኩት እውነታ አለ፡፡ በመልካም ፈቃደኝነት ስፖርቱን ከማገልገል ያለፈ ጉባኤው አልፈልግህም ቢለኝ የሚቀርብኝ ምንም ነገር የለም፡፡ እውነቱን ለመናገር ፍላጎቴ ስፖርቱን ለማገልገል እስከሆነ ድረስ የክልል ፌዴሬሽኖችን ድጋፍ አጣለሁ የሚል እምነት አልነበረኝም፡፡ ሲጀመር የደቡብ ክልል ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ቅሬታውን ባቀረበበት መልኩ እኔን የሚገልጽ ሰብዕና የለኝም፡፡ ውሸትንና ማጭበርበርን የምጠላ ሰው ነኝ፡፡ እውነቱ እንዲወጣም ስለምፈልግ ጭምር ነው ጉባኤው እንደገና እንዲጠራ የፈለግኩት፡፡

ሪፖርተር፡- የጉባኤው ምልከታ በምን ውሳኔ ተጠናቀቀ?

ዶ/ር አሸብር፡- ጥንቃቄና ኃላፊነት በተሞላበት ጉዳዩን አዳምጦ ትክክለኛውን አቅጣጫ በማስቀመጥ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ የደቡብ ክልል ቅሬታ ጉባኤው የተጠራው ምርጫ ለማካሄድ መሆኑን የሚገልጽ ደብዳቤ ከፌዴሬሽኑ አልደረሰኝም የሚል ቅሬታ ማቅረቡን የሚገልጽ፣ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ደብዳቤ ደርሶናል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የደቡብ ክልል ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ከግለሰብ ጠቅላላ ጉባኤ መኖሩ ስለተነገረው ብቻ በጉባኤው ሊገኝ መቻሉን በቅሬታው አሰምቷል፡፡ ሦስተኛው ውክልናው የተሰጠበት ማኅተም ትክክለኛው የደቡብ ክልል ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን እንዳልሆነም አመላክቷል፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ለደቡብ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በዚህ ቀንና ቁጥር ደብዳቤ ጽፎልናል፤ ምርጫም እንዳለ ቢያሳውቀንም የእኛ ቢሮ ሠራተኛ በሆኑት አቶ ታምራት ታዬ ደብዳቤውን እንደደበቁባቸው ጭምር የደቡብ ክልል ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ቅሬታውን አቅርቧል፡፡ ጉባኤውም የክልሉ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የተጻፈለትን ደብዳቤ ቀኑንና ቁጥሩን ካወቀ ተደብቆብኛል የሚለውን ቅሬታ እንዴት ሊያቀርብ እንደቻለ፣ ከዚህም በላይ ጉዳዩ በራሳቸው የቢሮ ሠራተኛ የሆነ ነገር መሆኑ እየታወቀ የውስጥ ችግራቸውን በራሳቸው መፍታት ሲገባቸው ለምን ወደ ጉባኤ እንዳመጣው፣ የደቡብ ክልል ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን አንድ ግለሰብ ነግረውን መጣን ካለ ጉባኤው ሲካሄድ ግልጽ ያልሆነልኝ ነገር ስላለ ለመሳተፍ አልችልም ብሎ ለምን በልዩነት አልወጣም? ለምንስ መረጠ? ግለሰብ የተባሉት ሰው የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ቅርጫት ኳስ ላይ በኃላፊነት እንዲሠሩ ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸው ስለመሆናቸው ጭምር ጉባኤው ካረጋገጠ በኋላ የክልሉን ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ ማኅተሙን በተመለከተም የክልሉ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ትክክለኛ ያለው ማኅተም የእንግሊዝኛው ትርጉም ስሕተት እንዳለበትም አረጋግጧል፡፡ ትክክለኛው ማኅተም ውክልና የተሰጠበት ስለመሆኑም እምነት ተወስዷል፡፡ በመጨረሻም ችግሩ የክልሉ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን የውስጥ ችግር በመሆኑ በራሱ እንዲፈታና ምርጫው እንደማይደገም ድምዳሜ ላይ መድረሱን ያረጋገጠበት ሁኔታን አመላክቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ከእርስዎ ቀደም ሲል በነበረው የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን የአመራር ዘመን፣ የዓለም አቀፍ ቅርጫት ኳስ ማኅበር (ፊባ) ኃላፊዎች በአዲስ አበባ ተገኝተው የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ጽሕፈት ቤት ሳይጎበኙ መመለሳቸው ተሰምቷል፡፡ ምክንያቱን ያውቁታል?

ዶ/ር አሸብር፡- ከፌዴሬሽኑ አመራሮች እንደተረዳሁት ከሆነ፣ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት በቆርቆሮ የተሠራ ሦስት በሦስት ክፍል በመሆኑ ምክንያት አዝነውና ተገርመው መሆኑን ነው፡፡ ሰባት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለበት የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ሦስት ሰዎችን እንኳ ማስተናገድ የማይችል በመሆኑ ሰዎች አንገባም ቢሉ ሊገርመን አይገባም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁንስ ምን የታሰበ ነገር አለ?

ዶ/ር አሸብር፡- ከሁሉ በፊት ቀዳሚ ሥራችን አድርገን የወሰድነው የቢሮ ጉዳይ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ከራሳችን ኪስ ቢሆንም ቢሮ ተከራይተናል፡፡ ቢሮ በሌለበት ስለ ቅርጫት ኳስ ዕድገት ማሰብ አይታሰብም፡፡ በቀጣይ መንግሥት ከረዳንና ለግንባታ ቦታ ከሰጠን የራሳችንን ቢሮ ለመገንባት ዕቅድ አለን፡፡ ከዚህ ባለፈ ከፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚዎች መካከል ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ለምናደርገው ግንኙነት ጥሩ አቅምና ዕውቀቱም ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ሁላችንም ያለንን ዕውቀት አቀናጅተን መንቀሳቀስ ከቻልን ውጤታማ የምንሆንበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ቅርጫት ኳስ ዓለም ላይ ትልቅ አቅም ካላቸው ስፖርቶች አንዱ ስለሆነ ድጋፍና እገዛ የምናገኝበትም ዕድል በዚያው መጠን ከፍተኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በስፖርቱ ባለፉባቸው ጊዜያት የሚቆጩባቸው አጋጣሚዎች ካሉ?

ዶ/ር አሸብር፡- በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በቆየሁባቸው የኃላፊነት ጊዜያት ለእግር ኳሱ የሚበጀውን ከማሰብ ባለፈ ህሊናዬን የሚቆረቁር የሠራሁት አንድም ነገር የለም፡፡ አሁንም አቅሜና ዕውቀቴ በፈቀደልኝ መጠን ስፖርቱን ለመርዳት ነው የመጣሁት፡፡ እንደሚሳካልኝ አልጠራጠርም፡፡ ሌላው እኛ ኢትዮጵያውያን ለአገራችን ስፖርት ዕድገት ስንል የግል ጥቅምና አጀንዳችንን ወደ ጎን ትተን በጋራ ለብሔራዊ ጥቅማችን መሥራት ይኖርብናል፡፡ ለወደፊቱም ቢሆን ስፖርቱን ለመምራት ፍላጎቱ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ካሉ መቶና ከዚህም በላይ ዕጩዎችን በማቅረብ የተሻለውን በመምረጥ ስፖርታችንን መታደግ ይኖርብናል፤ ወክያለሁ አልወከልኩም በመባባል የምናጠፋው ጊዜ መኖር የለበትም፡፡ አቅሙና ዕውቀቱ ያላቸውን ሰዎች ልንጠቀምባቸው ይገባል፡፡