አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

‹‹መወደድ ዕዳ ነው››

አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)

በዘጠናዎቹ መጀመሪያ አቡጊዳ የሚለውን የመጀመሪያ አልበሙን ያወጣው ቴዲ አፍሮ (ቴዎድሮስ ካሳሁን) በጊዜው ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ከዚያም በተለያዩ ጊዜዎች ባወጣቸው አልበሞች ተመሳሳይ ተቀባይነት እና ዕውቅናን አግኝቷል፡፡ ከሳምንታት በፊት ያወጣው ኢትዮጵያ የሚለው ዘፈኑ ደግሞ የዝና ማማ ላይ አስቀምጦታል፡፡ የሁለት ልጆች አባት የሆነው ቴዎድሮስ ካሳሁን ከሪፖርተር ጋዜጠኞች ዳዊት እንደሻው እና ሳሙኤል ጌታቸው ጋር ባደረገው አጭር ቆይታ ስለ ሕይወቱ እና ሥራው ተጠይቆ መልስ ሰጥቷል፡፡  

ጥያቄ፡- በመጀመሪያ አትርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን አልበምህን ካወጣህ በኋላ ላገኘኸው ስኬትና ተቀባይነት እንኳን ደስ አለህ፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደ ቤተሰብ ኃላፊ፣ እንደ አባት ሆነህ ያወጣኸው አልበም ከበፊቶቹ ምን የተለየ ነገር አለው?

አርቲስት ቴዎድሮስ፡- የቤተሰብ ኃላፊ መሆን፣ ቤተሰብ መመሥረት፣ ሚስት ማግባት፣ ልጆች መውለድ፣ ይኼ አንድ የሕይወት ምዕራፍ ነው፡፡ በዚሁ ውስጥ ደግሞ የሚጨመሩ ብዙ ፀጋዎች አሉ፡፡ በፍቅርና መከባበር፣ የቤተሰብ ፍቅር ተጨምሮ የሚመጣ ነገር አለ፡፡ ያው ቤተሰብ ማፍራት ደስ ይላል፣ ትልቅ ፀጋም ነው፡፡ ለሥራውም ጨምሮ መምጣት ትልቅ አስተዋፅዎ አለው፡፡   

[በኦሮሚያ ክልል በሙስና የተጠረጠሩ 600 ሰዎች ታስረው ክስ ተመሥርቶባቸዋል]

ጥያቄ፡- አልበምህ ላይ ራዕይ ቴዎድሮስ ካሳሁን ተብሎ ተጽፏልና ራዕይ የሚለው ነገር ምንን ለመግለጽ ነው?

አርቲስት ቴዎድሮስ፡- እዛ አቀማመጡ ላይ እንዳየኸው መታሰቢያነቱ ላይ የአባቴ፣ የእናቴ እንዲሁም የአፄ ቴዎድሮስ ፎቶግራፍ አለ፡፡ ይኼ ፎቶግራፍና የቤተሰብ ፎቶግራፍ ከስሜ አወጣጥ ጀምሮ የራሱ የሆነ ታሪክ አለው፡፡ ከዚህ አንፃር ነው እንዲህ ያልኩት ከዚህ በተረፈ እናቴን ራዕይ ብዬ ነበር የምጠራት፡፡ እናት ማለት ደግሞ አገር ናት፡፡ ለእኔ ራዕይ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ራዕይ ደግሞ የሚወጣው ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ይኼን ለመግለጽ ብዬ ነው፡፡

ጥያቄ፡- አዲሱን አልበምህ ኢትዮጵያ ብለኸዋል ለአንተ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት ነው?

አርቲስት ቴዎድሮስ፡- ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በብዙ መንገድ ሊገለጽ ይቻላል፡፡ እንዲሁ በአጭር ቃላት የሚለገጽ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ነፃነት ነው፣ ትህትና ነው፣ መከባበር ነው፣ መተባበር ነው፣ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፣ . .  ብዙ ብዙ፡፡

ጥያቄ፡- ቴዎድሮስ ሌላው ብዙዎች አንተን ወደ ሙዚቃው እንደገባህና ዕውቅና ካገኘህ በኋላ የዘጠናዎቹ ትውልድ ድምፅ አድርገው ይመለከቱሃል፡፡ አሁን ደግሞ ስለአገሩ የተለየ አተያይ ያለው አዲስ ትውልድ ተፈጥሯል፡፡ አሁን ላይ ሆነህ አሁን ያለውን ትውልድ ተረድተኸዋል ወይ?

አርቲስት ቴዎድሮስ፡- . . . ያው እኔም ከትውልዱ ውጪ መሆን አልችልም፡፡ የትውልዱ አካል እንደ መሆኔ መጠን እኔ የሚሰማኝ ስሜት ትውልዱ ላይ አለ፡፡ አገሩን፣ ኢትዮጵያን የመውደዱ ስሜት ሁሉም ላይ አለ ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔም የትውልዱ አካል እንደመሆኔ መጠን ከእዛ ውጭ ላንፀባርቅ አልችልም፡፡ ስለዚህ ያ ስሜት ነው ያገናኘን፡፡

ጥያቄ፡- ሌላው አዲስ ካወጣኸው አልበም ፍቅር እስከ መቃብር ልብ ወለድ መጽሐፍ ላይ መሠረት አድርገህ የዘፈንከው ዘፈን ይጠቀሳል? ለብዙዎች ከዚህ ትልቅ መጽሐፍ ቀንጭቦ ወደ ዜማ፣ ግጥም መቀየር አስቸጋሪ ቢሆንም አንተ ያንን ማድረግ ችለሃል፡፡ ስለዚህ አንተ መጽሐፉ ላይ ያለውን ነገር በግጥምህ በደንብ መያዝ ችያለሁ ብለህ ታስባለህ ወይ?

አርቲስት ቴዎድሮስ፡- መጽሐፉ በጣም ሰፊ ነው፡፡ ከመጽሐፉ ሰፊው ክፍል ውስጥ ዋና ገጸ ባህሪያት ላይ ያተኮረ ሥራ ነው፡፡ በዛብህ ሰብለ ወንጌልን ሩፋኤል (አዲስ አበባ) መጥቶ ይጠብቃት ነበር፣ ጉዱ ካሣ ከብቶቹን ሸጦ ገንዘብ ሰጥጦት ሲሸኘው፣ ብላታ ቀለም ወርቅ ደግሞ የፀሎት መጽሐፉ ጽፎ ያገኛትን 20 ብር ሲሰጠው መጀመርያ ግን ሲመክረው ነበር . . .  የጌታ ልጅ አግብተህ እንዴት ትሆናለህ ይቅርብህ ብሎ መክሮትም ነበር፡፡ ነገር ግን በዛብህ በፍቅር የቆረጠ ነፍስ ስለነበረው ምክሩንም አሻፈረኝ ብሎ ወደ አዲስ አበባ ሩፋኤል መጣ፡፡ እዛ ሆኖ መልዕክት ሲጠብቅ በመጨረሻ መመንኮሷን ይሰማል፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ዋናው ገጸ ባህሪው በዛብህ ላይ ያተኮረ ዘፈን ነበር፡፡

[ቴዲ አፍሮ ሙታኖቻችንን እየገነዘ ታሪክ መሥራቱን ቀጥሏል]

ጥያቄ፡- እዚሁ ከፍቅር እስከ መቃብር ላይ ከዘፈንከው ዘፈንህ ጋር በተያያዘ በግጥሙ ላይ የተሳተፉ ሰዎች አሉ?

አርቲስት ቴዎድሮስ፡- እኔ ራሴ ነኝ የሠራሁት፡፡ በአንድ ምሽት ነው ግጥሙም ዜማውም ያለቀው፡፡ ከዚያ ጠዋት ላይ ገለበጥኩት፡፡ በእርግጥ ከእዛ በኋላ መጠነኛ ማሻሻል አድርጌአለሁ እንጂ የማንም ተሳትፎ የለበትም፡፡ ከፍቅር እስከ መቃብር ደራሲና ከወጋየሁ ንጋቱ በስተቀር፡፡

ጥያቄ፡- ብዙ ጊዜ ግጥምህንም፣ ዜማውንም የምትሠራው ራስህ ነህ ወጣቶችን ግጥም እንዲጽፉ፣ ዜማ እንዲሠሩ፣ አብረውህ እንዲሠሩ ታበረታታለህ?

አርቲስት ቴዎድሮስ፡- እኔ አንድ ሥራ በምሠራበት ጊዜ ለሥራው የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሁሉ ከመጠቀም ወደኋላ አልልም፡፡ በሥራው ላይ ተሳትፎ የማድረጉ ጉዳይ ደግሞ የተስፅኦ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ ባሉት ውስን ሙዚቀኞች ተጠቅሞ ሙዚቃውን ሠርቶ ለሕዝብ ለማድረስ ከሚደረገው ጥረት ውስጥ ከተለያዩ ሙዚቀኞች ጋር ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ እንደውም ብዙ ጊዜ ለጥረት የማይመቹ የተዘጉ ነገሮች እያሉ ብዙ ተሞክሯል፡፡ ስለዚህ ያለው ሁኔታ ከእዚህ ያለፈ አይደለም፡፡

ጥያቄ፡- ለዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የዘፈንከው ተቀባይነት ማግኘቱ ይጠቀሳል፡፡ እዚህ ሙዚቃ ላይ ድምፅህን ቀየር አድርገኸ የአዝማሪ ቅላፄን ጨምረሃል ይኼ እንዴት መጣልህ፡፡

አርቲስት ቴዎድሮስ፡- እዚህኛው ዘፈን ላይ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት የባህሩ ቃኘንም ዘፈን ተጫውቼ አውቃለሁ፡፡ የድሮ ድምፅ ዓይነቶች ሁሉም ይማርኩኛል፡፡ የዛን ጊዜማ በስሜት ፈንቅሎ የወጣ ነውና ስሜት ያመጣው እንጂ ዕቅድ ያመጣው አካሄድ አይደለም፡፡

ጥያቄ፡- የአፄ ቴዎድሮስ ዘፈን ግጥምን መቼ ጻፍከው?

አርቲስት ቴዎድሮስ፡- አፄ ቴዎድሮስ ከተጀመረ ቆየት ብሏል፡፡ የዘፈኖቹ አማካይ ክፍል በፊት ያለው ንድፍ ያለቀው ቀደም ብሎ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ያለው ደግሞ አጥርቶ ለመጨረስ ስንቀሳቀስ የተደረጉ ለውጦች ናቸው፡፡ በዚህ ዓመት ነው ያለቀው፡፡

ጥያቄ፡- አንዳንድ ሰዎች አፄ ቴዎድሮስ ላይ የዘፈንከውን ዘፈን ጎንደር ላይ ከነበረው የፖለቲካ ትኩሳት ጋር ያያይዙታል፡፡ ዘፈኑ በእርግጥ ከእዛ ጋር ይያያዛል ወይ?

አርቲስት ቴዎድሮስ፡- በመጀመሪያ ወዲያው እንደእዛ ዓይነት ስሜት ሊሰጥ ይችላል፡፡ ዘፈኑ ግን ካለመረጋጋቱ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ቀድመው የነበሩ ናቸው፡፡ እኔ ደግሞ ስለ ነገሥታት መዝፈን የጀመርኩት ዛሬ አይደለም፡፡ መልሴ ይኼ ነው፡፡

ጥያቄ፡- እንግዲህ በዚህ አልበምህ ተቀባይነትን አግኝተሃል፡፡ ይኼን ስሜት እንዴት ትመለከተዋለህ?

አርቲስት ቴዎድሮስ፡- ያው የሰው ፍቅር የሚሰጠው እግዚአብሔር ነው፡፡ ፀጋን የሚሰጠው እግዚብሔር ነው፡፡ ይኼ የበረከት ውጤት ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ነገር ግን በእኔ ቦታ ሆኖ ነገሩን ማየት ደግሞ ቀላል አይደለም፡፡ መወደድ ዕዳ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ አጋጣሚ ሰው ላሳየኝ ከፍተኛ ፍቅር ማመስገን እወዳለሁ፡፡

ጥያቄ፡- ከዚህ  ቀደም ባወጣሀቸው ዘፈኖች ላይ ስለ አፄ ኃይለ ሥላሴ በተደጋጋሚ ዘፍነሃል፡፡ ብዙዎች ስለ አፄ ኃይለ ሥላሴ የተለያየ አመለካከት አላቸው፡፡ እንደ አምላክ የሚያዩዋቸው አሉ፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውን ደግሞ እንደ ንጉሥ ያዩዋቸዋልና ለአንተ አፄ ኃይለ ሥላሴ የተለየ ነገር አላቸው ወይ?

አርቲስት ቴዎድሮስ፡- ነገሥታቶችን የነበራቸው ፀጋ እንደዚህ ቀላል አልነበረም፡፡ በዓለም ዙሪያ የታፈሩ ብዙዎች ክብር የሚሰጧቸው ነበሩ፡፡ ይኼ ደግሞ እንደዚህ በቀላሉ የመጣ አይደለም፡፡ በተግባራቸው፣ ባላቸው ፀጋና አቅምም ነበር፡፡ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በእኔ አመለካከት ጥሩ መሪ ነበሩ፣ በፍፁም ቅንነትም አገራቸውን አገልግለዋል፡፡ ይኼን ደግሞ ከእኛ ውጭ ያሉም ሰዎች ይመሰክራሉ፡፡

ጥያቄ፡- ከአድናቂዎችህ ካናዳዊው አቀንቃኝ አቤል ተስፋዬ በመድረክ ስሙ ዘ ዊኬንድ አንዱ እንደሆነ ይገለጻል፡፡ አብሮህ መሥራት እንደሚፈልግም ተናግሮ ነበርና እዚህ ላይ ምን አስተያየት አለህ?

አርቲስት ቴዎድሮስ፡- እኔም አብሬው ብሠራ ደስ ይለኛል፡፡ (ሳቅ) ሌላው ልጁ ጎበዝና ጨዋ ልጅ ነው፡፡ ጥሩ አመለካከትም እንዳለው አውቃለሁ፡፡

ጥያቄ፡- ወደ ሙዚቃው መቀላቀል ለሚፈልጉ ታዳጊና ወጣቶች ምን መልዕክት አለህ?

አርቲስት ቴዎድሮስ፡- በመጀመርያ ወደ ሙዚቃ ሲገባ ትክክለኛ ተሰጥኦ መኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ትጋትና መመሰጥ ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ደግሞ መሠረታዊ ነገር ለኪነ ጥበብ ቅን መሆን ይጠይቃል፡፡ ጥሩ ማሰብ፣ መተባበር፣ ሙዚቃን መሥራት፣ መስማት ከምንም በላይ ደግሞ ውጤት ላይ ሲመጣ ለራስህ የምትሰጠው ግምት ከፍተኛ መሆን የለበትም፡፡ ምክንያቱም ይኼ ብዙ እንዳትሄድ ያደርግሃል፡፡

ጥያቄ፡- ባለቤትህና አንተ ኪነ ጥበብ ላይ እየሠራችሁ ነውና አብራችሁ የመሥራት ሐሳብ አላችሁ ወይ?

አርቲስት ቴዎድሮስ፡- አዎን ሠርተናል፡፡ ማር እስከ ጧፍ ሙዚቃ ክሊፕ ላይ እንደ ዳይሬክተርና እንደ ተዋናይ (ሰብለ ወንጌል) ሆና የሠራችው እሷ ነች፡፡ ክሊፑ በቅርቡ ይለቀቃል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡