‹‹በነባር ዝርያዎች ብቻ ሕዝብን መቀለብና ለኢንዱስትሪው ግብዓት ማስገኘት ይቻላል ብዬ አላስብም››

  ዶ/ር ጌታቸው በላይ፣ በኮሜሳ የባዮቴክኖሎጂ ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ

ዶ/ር ጌታቸው በላይ በግብርና ምርምር፣ በአካዴሚና በኃላፊነት መስኮች ከ20 ዓመታት በላይ ልምድ አካብተዋል፡፡ ለሰባት ዓመታት ያህልም በምሥራቃዊና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ሥር በሚገኘው የምሥራቃዊና ደቡባዊ አፍሪካ የሸቀጥ ንግድ ትብብር ተቋምን በከፍተኛ የባዮቴክኖሎጂ ፖሊሲ አማካሪነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ዶ/ር ጌታቸው በዘረ መል ምሕንድስና የታገዘ የዘር አቅርቦት የአፍሪካን የግብርና ምርታማነት ማነቆዎችንና የምግብ ደኅንነት ችግሮችን፣ እንዲሁም የአካባቢና መሰል ጉዳቶችን የሚያስቀር ቴክኖሎጂ እንደሆነ ይሞግታሉ፡፡ በዘረመል እንዲሁም ተክል ማዳቀል ሙያ ዘርፎች  ከማስትሬት እስከ ዶክትሬት ዲግሪያቸውን በስዊድን በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መሥራታቸውን የሚያስረዳው ግለ ታሪካቸው፣ ከ30 በላይ  የራሳቸውንና ከአጋሮቻቸው ጋር በኅብረት የተጻፉ ሳይንሳዊ ጽሑፎችንም በዓለም አቀፍ ጆርናሎች አሳትመዋል፡፡ ኮሜሳን ከመቀላቀላቸው ቀደም ብሎ በነበሩት ዓመታት በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የጥራጥሬ ሰብሎች ምርምር ፕሮግራምን በኃላፊነት መርተዋል፡፡ በስንዴና በጤፍ ላይ ምርምር ማድረጋቸውንም ግለ ታሪካቸው ያወሳል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ፣ ከኪንግደም ኦፍ ስዋዚላንድ፣ ከማላዊ እንዲሁም ከዛምቢያ የተውጣጡ ልዑካንን አስከትለው በህንድ ትምህርታዊ የመስክ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ ህንድ ከ14 ሚሊዮን የዓለም ገበሬዎች ውስጥ ግማሹን በዚህ የዘረመል ጥጥ መስክ እንዳሰማራች የምርምር ተቋማቷ አስታውቀዋል፡፡ ከ11 ሚሊዮን በላይ ሔክታር መሬትም በዘረ መል ጥጥ (በቢቲ ኮተን) ሊሸፈን መቻሉንም ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ጌታቸው በዚህ የጥጥ ዝርያ ላይ የሚነሳውን ትችት የሚሞግቱትም የህንዶችን ተሞክሮ በማንሳት ነው፡፡ ይህን ያህል መሬትና ይህን ያህል አምራች በዘረመል ጥጥ አምራችነት የተሰማራው አገራቸውን ባይወዱ ይሆን? በማለትም ይጠይቃሉ፡፡ በአፍሪካ ከሌሎች የሰብል ዝርያዎች በተለይ የጥጥ ሰብል ለዚህ ቴክኖሎጂ ከታጨ ሰነባብቷል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ጥቂት አገሮች የዘረመል ውጤት የሆነውን ጥጥ ሙከራ ሲያካሂዱበት ቆይተዋል፡፡ ሕጎቻቸውንም እያሻሻሉ እንዲሁም በማሻሻል ላይ የሚገኙ አገሮች ጥጡን ወደ ገበያ ለማውጣት እየተቃረቡ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያ በሁለት ዓመት ወይም ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለአምራቾች እንደምታቀርብ አስታውቃለች፡፡ እንደ ኪንግደም ኦፍ ስዋዚላንድ ያሉ አገሮችም በወራት ጊዜ ውስጥ ለገበያ ለማቅረብ የሚያሰችላቸውን ተግባር ለማከናወን መዘጋጀታቸውን ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ በዘረመል ጥጥ ጠቀሜታ፣ በሚነሱበት ትችቶች፣ በሰዎችና በአካባቢ ላይ ያደርሳል ተብሎ ስለሚቀርቡበት የሥጋት ጥያቄዎችና ሌሎች ነጥቦችን በተመለከተ ብርሃኑ ፈቃደ በህንድ በተደረገው ጉብኝት ወቅት ከዶ/ር ጌታቸው ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ህንድ በባዮቴክኖሎጂ ወይም በዘረመል ምህንድስና መስክ የምትገኝበትን ደረጃ ለማየት ከአፍሪካ የተውጣጣ ልዑክ የሳምንት ቆይታ አድርጓል፡፡ በተለይ በጥጥ መስክ ህንዶች ብዙ እንደሠሩ ታይቷል፡፡ ለመሆኑ የዘረመል ምህንድስና በአፍሪካ እንዲተዋወቅ ማድረግ ለምን አስፈለገ? ይህ ቴክኖሎጂስ ለአፍሪካ ምን ማለት ነው?

ዶ/ር ጌታቸው፡- እንደ አገሩ ይለያያል፡፡ ቢቲ ኮተን ስለሚባለው የጥጥ ዓይነት ለመነጋገር ቀድሞ ጥጥ አብቃይ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ወይም ደግሞ በዚህ ቴክኖሎጂ ታግዞ ለማምረት የሚያስችል የተመቻቸ አካባቢ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው የሚያመርቱና ማምረት የጀመሩ አገሮች አሉ፡፡ ሱዳኖች የቢቲ ኮተን ጥጥ ማምረት ከጀመሩ ሦስት ዓመት ያህል ሆኗቸዋል፡፡ ምንድነው የተጠቀሙት? ብለን የሱዳኖቹን ብናይ፣ አፍሪካን ቦልዎርም የሚባል ፀረ ጥጥ የሆነ ተባይ አጥቅቷቸው ነበር፡፡ ምንም ማምረት የማይችሉበት ደረጃ አድርሷቸው ነበር፡፡ ይህንን ቴክኖሎጂ ሲያዩ ከቻይናውያን ጋር ተነጋግረው ሊያገኙ ችለዋል፡፡ አሁን የሱዳን ገበሬዎች ያለዚህ ቴክኖሎጂ ማምረት አይችሉም፡፡ ስለዚህ ቴክኖሎጂው በዚህ መስክ ያስገኘላቸውን የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ማየት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮችን ብንወስድ ደግሞ ለምሳሌ የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ትኩረት ከተሰጣቸው ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የጨርቃ ጨርቅ 80 በመቶ ግብዓት ጥጥ ነው፡፡ ጥጥ ዋናው የጥሬ ዕቃ ግብዓት ነው፡፡ ይህንን ጥሬ ዕቃ ተወዳዳሪ በሆነ መንገድ አምርተን ፋብሪካዎቻችንን መግበን የተረፈንን ኤክስፖርት ማድረግ እንችላለን፡፡

ቀድሞ ነገር ችግሩ አለ ወይ? የሚለውን ማየት ተገቢ ነው፡፡ በተለይ የተባይና የዓረም ችግሮች በሚበዙበትና የሰው ጉልበት እጥረት ባለበት አካባቢ የቴክኖሎጂ ድርሻ ለእንዲህ ያለው ችግር መፍትሔ መስጠት ይሆናል፡፡ እነዚህ ችግሮች ካሉ አንድ ቴክኖሎጂ ወደ አገር ሲመጣ የግድ ችግሩን መፍታት መቻል አለበት፡፡ ያለውን ችግር መፍታት ያልቻለን ቴክኖሎጂ አርሶ አደሩም አይቀበለውም፡፡ ለኢኮኖሚውም ምንም አይጠቅምም፡፡ እነ ህንድ በዘረመል ምህድንስና የተመረተ ቢቲ ኮተን ጥጥ አምርተው በርካሽ ዋጋ እየሸጡ ነው፡፡ ምርቱን እጥፍ አድርገን፣ ራሳችንን ችለን ለኤክስፖርት እያቀረብን ነው እያሉ ነው፡፡ ምርጫው እንግዲህ እዚህ ላይ ነው፡፡ ጥጡን ገዝተን ለፋብሪካዎቻችን እናቅርብ? ወይስ እዚሁ አምርተን ተወዳዳሪ ሆነን አርሶ አደሮቻችንም፣ ፋብሪካዎቻችንም ሆኑ ሌላውም በእሴት ሰንሰለት ይጠቀም? በሚለው ላይ ትልቅ ተዕፅኖ ያለው ይመስለኛል፡፡ አፍሪካውያንም ወደ ኢንዲስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማምራት በሚያደርጉት ሒደት ላይ እንዲህ ያለ ትልቅ ተፅዕኖ ያለው ይመስለኛል፡፡ 

ሪፖርተር፡- አፍሪካ ከቢቲ ኮተን ሌላ እንዲሁም አሁን ከሚያመርቱት የጥጥ ዝርያ ውጪ ሌላ አማራጭ ይኖራቸዋል?

ዶ/ር ጌታቸው፡- ይኼ የዕድገት ጉዳይ እኮ ነው፡፡ ለምሳሌ ጥጥን የሚያጠቃውን ተባይ በምን ነበር የምንቆጣጠረው ከተባለ በፀረ ተባይ ማጥፊያ ኬሚካል ነበር፡፡ ይኼም የራሱ ችግር አለው፡፡ በአካባቢና በሰዎች ጤና ላይ የራሱን ችግር ያስከትላል፡፡ ይህንን የቢቲ ኮተን ቴክኖሎጂ ተባይ ብቻም ሳይሆን ሌሎችም ለምሳሌ እንሰትን የሚያጠቃው ባክቴሪያን ብናይ በምንም መንገድ ሊወገድ አልቻለም፡፡ ያለን አማራጭ የዘረ መል ቴክኖሎጂን ተጠቅመን ማስወገድ መቻል ካልሆነ በቀር፣ የእንሰት ጉዳይ ችግር ውስጥ ነው፡፡ ሆኖም ቴከኖሎጂው እንሰት ላይ እየተሞከረ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ስኳር ድንች ላይ የቫይረስ በሽታዎች አሉ፡፡ ኡጋንዳ ውስጥ የሙዝ ተክል ላይ፣ ድንች ላይ እንዲሁም ካሳቫ ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ሙከራዎች እየተደረጉ ነው፡፡ ችግሩ ግን እነዚህ ተክሎች ለምግብነት ስለሚውሉ ቴክኖሎጂው ምናልባት የሚያመጣው የጎንዮሽ ጉዳት ይኖር እንደሆነ በማለት ለመተግበር ፍርኃት አለ፡፡ እግርጥ ቴክኖሎጂውን ከማይቀበሉ አካባቢዎችም ግፊት አለ፡፡ አንዳንዴ ሕግ አውጪዎችም የተለያየና የተቃረነ ሐሳብ ስለሚቀርብላቸው ይህ እንዲህ ነው ብለው መወሰን እየከበዳቸው ነው እንጂ ቴክኖሎጂውና ሙከራው አለ፡፡

ሪፖርተር፡- በዘረመል ምህንድስናው የተበዛቱም ይሁኑ በተመሳሳይ መንገድ እየወጡ ያሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ ከሚቀርብባቸው ተቃውሞ ውስጥ ዋነኛ የሚባሉትን ሁለት ወይም ሦስቱን ቢጠቅሷቸው? ሳይንሳዊ ማስረጃዎችን ማስቀመጥ ይቻል ከሆነም ቢገልጹልን?

ዶ/ር ጌታቸው፡- ዋናው አስኳሉ ይኼው ነው፡፡ ተቃውሞውን ስናይ መነሻው ቴክኖሎጂው ጉዳት አለው፣ ምንም አይሠራም የሚል ጽንፍ ያለው ተቃውሞ የሚያነሳ አለ፡፡ አይደለም ይህ ቴክኖሎጂ የዓለምን የረሃብ ችግር ይፈታል ብሎ የሚነሳ ሌላ ጽንፍ አለ፡፡ ነገር ግን ሐሳቦቹን ከርዕዮተ ዓለም ውጪ አድርገን ወደ መሀል አምጥተን ብናያቸው፣ አንዱ የሚባለው የጉዳት ደረጃ ሥነ ምኅዳርን ያጠፋል የሚል መከራከሪያ የሚነሳበት ነው፡፡ ለዚህ ተቃውሞ ግን ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ መረጃ የለም፡፡ እኔ ይከብደኛል፡፡ የዘረመል ምህንድስና ተክል ሲበቅል አፈር ውስጥ ያሉ ነፍሳት ምን ይሆናሉ? የሚለው ሁሉ ታይቷል፡፡ ይጠፋሉ፣ ለጉዳት ይጋለጣሉ የሚለውን የሚደግፍ መረጃ ግን አልተገኝም፡፡ በታወቀ ሳይንሳዊ ጆርናል ላይም አልወጣም፡፡ ዱሮ ግን አሜሪካ ውስጥ አንድ ጽሑፍ ወጥቶ ነበር፡፡ ሞናርክ በተርፍላይ የሚባል የቢራቢሮ ዝርያ በዚህ ቴክኖሎጂ ሰበብ ተክስቷል የሚባል ነገር ነበር፡፡ ከዚህ ጋር እየተያያዘ ነው እንጂ ምንም ማስረጃ እየቀረበ አይደለም፡፡ ህንዶች 11 ሚሊዮን ሔክታር የዘረመል ጥጥ ሲያመርቱ አገራቸውን አይወዱም ማለት ነው? እነዚህ ሰዎች አካባቢውን ያጥፋ ብለው ነው? አይመስለኝም፡፡ በጤና ላይ ጉዳት ያደርሳል የሚለው ሥጋትን መነሻ ያደረገ ቅስቀሳም አለ፡፡ የዘረመል ቴክኖሎጂ ውጤትን መመገብ ስድስት ጆሮ ያወጣል፣ ቀንድ ያበቅላል የሚሉ እውነትነት የሌላቸውና ሳይንሳዊ ማስረጃ የሌላቸው ትችቶች አሉ፡፡ እንዲህ ያለ ማስረጃ ቢገኝ ሳይንቲስቶች የዚህ ቴክኖሎጂ ተባባሪ ይሆናሉ ብዬ አላስብም፡፡

ሌላው ሶሺዮ ኢኮኖሚክ ክፍል ላይ ያተኮረ ሥጋትም አለ፡፡ የዘረመል ቴክኖሎጂ ያላቸው ኩባንያዎች ዘሩን ይቆጣጠሩታል፣ ገበሬው ችግር ላይ ይወድቃል የሚለው ሥጋት ትክክል ቢሆንም በድርድር ወቅት መፈታት የሚችል ነገር ነው፡፡ ኩባንያዎቹም ዘሩን ለማዘጋጀት ብዙ እንደሚደክሙና ገንዘብ እንደሚያወጡ ዕሙን ነው፡፡ ነገር ግን ወደ ብዝበዛ መሄድ የለባቸውም፡፡ እንዲህ ከሆነማ ተጠቃሚውም እኮ አይቀበለውም፡፡ ገበሬው ጥቅም ካላገኘበት አይቀበልም፡፡ ሌላው ሥጋት ልዩ ልዩ ፀረ ተባይም ሆነ ፀረ ዓረሞችን መቋቋም ከለመደ የባሰ ጥፋት ያመጣል የሚል ነው፡፡ ይኼም ትክክልና ሊሆን የሚችል ነገር ነው፡፡ ታይቷልም፡፡ ተባዩ ተክሉን መቋቋም ሊጀምር ይችላል፡፡ ነገር ግን ለዚህም የሚሆኑ የተለያዩ የመከላከያ ዘዴዎች አሉ፡፡ እርግጥ ተባዩ ለቢቲ ኮተን ብቻም አይደለም የመቋቋም ጠባይ ሊያመጣ የሚችለው፡፡ መድኃኒት እንዲሁ በተከታታይ የሚረጭበት ከሆነ የመቋቋም ባህርይ ሊያዳብር ይችላል፡፡ እግዲህ የ20 ዓመታት ልምድ አለ፡፡ በዓለም ላይ 14 ሚሊዮን ገበሬዎች የሚጠቁሙበት ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ግማሹ ህንድ፣ አምስት ሚሊዮኖቹ ደግሞ ቻይናውያን ናቸው፡፡ መጀመርያ አካባቢ የምዕራቡ ዓለም ቴክኖሎጂ ነው እየተባለም ይወገዝ ነበር፡፡ አሁን ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ እነ ባንግላዴሽ፣ እነ ፓኪስታን፣ የላቲን አሜሪካ አገሮች እንዲሁም እኛ ዘንድ እነ ሱዳን እየተጠቀሙ ስለሆነ፣ ማየቱ አይከፋም እንሞክረው፡፡ የሚጠቅም ነገር ካለበት እንወስደዋለን፡፡ የማይጠቅም ከሆነም እንተወዋለን፡፡ የሚነገሩትን ነገሮች በሙሉ ዝም ብሎ እንደመጡ መቀበልም ተገቢ አይሆንም፡፡ 

ሪፖርተር፡- ከዚህ በፊት የግሪን ሪቮሉሽን ወይም አረንጓዴ አብዮት የሚባለው በደቡብ አሜሪካ እንዲሁም በእስያ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን የምግብ ችግር ለመቅረፍ አስችሏል፡፡ በአፍሪካ ግን ፉርሽ ሆኗል፡፡ ይህ አብዮት ሲነሳ በአብዛኛው በተሻሻሉ ዝርያዎችና በግብርና ግብዓቶች ላይ ቢያተኩርም በተወሰነ ደረጃ የዘረመል ቴክኖሎጂን ተጠቅሟል፡፡ ነገር ግን በአፍሪካ ሊሠራ አልቻለም፡፡ አሁን ደግሞ ቴከኖሎጂው አድጎ ‹‹ጂን ኤዲቲንግ›› ወይም የዘረመል አርትኦት ቴክኖሎጂ ተጀምሯል፡፡ ያለፈው አልሠራም፣ ባለው ላይ ጭቅጭቅ አለ፡፡ ታዲያ ወዴት ይሆን የምናመራው?

ዶ/ር ጌታቸው፡- የአረንጓዴው አብዮት ሲነሳ በነገራችን ላይ ትችት ነበረበት፡፡ ህንድ ውስጥ ወደ ስድስት ሚሊዮን በረሃብ ሊረግፍ የነበረ ሕዝብ መዳኑ ሳይታይ ቀርቶ፣ ሕዝቡ ከተረፈ በኋላ ግን ትችት ሲሰነዘርበት ነበር፡፡ ማዳሪያ አመጣ፣ መሬቱን አበላሸ፣ የገበሬውን ዘር አጠፋ የሚሉ ትችቶች ተሰንዝረዋል፡፡ ምርጫው ምን ሊሆን ይችል እንደነበር ማየት የሚገባ ይመስለኛል፡፡ አፍሪካ ከአብዮቱ አልተጠቀመችም የሚለውን ዝም ብዬ ሳስበው ምናልባት በዚያን ወቅት የዚያን ዓይነት ቴክኖሎጂና የእርሻ ዘዴ አልነበረን ሊሆን ይችላል፡፡ ዘሎ አመለጠን የሚለውን እኔ ብዙም አልስማማበትም፡፡ ዝግጁ አልነበርንም እላለሁ፡፡ ተግባቦቱም እንዳሁኑ አላደገም፡፡ ድሮ ውድድሩ እዚያው በአገር ውስጥ ካለው አምራች ጋር ነበር፡፡ አሁን እኮ የኢትዮጵያ ጥጥ አምራች ገበሬ ከህንድ ገበሬ ጋር ነው የሚወዳደረው፡፡ ሁሉም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ይጠቀማል ማለት ሳይሆን፣ የሚጠቅመውን በመለየት መነሻ መሠረት እንዲሆን ካላደረግንና ካልተጠቀምንበት እንዴት ይሆናል የሚለው ለእኔም ግልጽ አይደለም፡፡ ቴክኖሎጂው አያስፈልገን ይሆን እንዴ እላለሁ፡፡ ሌሎችን ስታይ ደግሞ ሄደዋል፡፡ አንድ ማለት የምችለው ነገር ግን መጠቀማችን ላይቀር ካሁኑ መሠረት ካላስቀመጥንና እየሞከርን የሰው ኃይሉን እያዳበርን ካልሄድን፣ የግንኙነትና የተግባቦት ክፍተት እየተጠረ ተመራማሪዎቻችንም በዚህ ቴከኖሎጂ ላይ ላይነጋገሩ ነው ማለት ነው፡፡ አንድ ኢኮኖሚ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ካልተደገፈ ምን ያህል ሊሄድና የት እንደሚደርስ አላውቅም፡፡ በተወራው ሁሉ ዝም ብሎ መሄድም አያስፈልግም፡፡ ስለቴክኖሎጂው ሊነግሩን የሚችሉ የራሳችን ሳይንቲስቶች ስላሉ ሌላ ቦታ ጥቅም ላይ የዋሉ ቴክኖሎጂዎችን አምጥተን በማላመድ፣ እንዴት መጠቀም እንዳለብን በደንብ ሥርዓት ይዞ መታየት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት አቅጣጫም በዚህ በኩል ይመስለኛል፡፡   

ሪፖርተር፡- አንድ የቆየ ክርክር ላንሳ፡፡ ነባር ወይም የገበሬ ዝርያ የሚባለውና የተሻሻለ ዝርያ የሚባለው፣ በተወሰነ ደረጃም የዘረመል ምህንድስና የታከለበት ዘር ላይ የሚነሳው የሁለት ወገን ሥር የሰደደ ክርክር አለ፡፡ ነባር ዝርያ ነው የሚታደገን፣ እሱ ከሌለ የተሻሻለ ዘር የሚባለውም አይገኝም ነበር ይላሉ፡፡ የተሻሻለ ዝርያን የሚደግፉት ደግሞ ሳይንሳዊ ግኝቶችን ተጠቅመን ውጤት ማሻሻል አለብን የሚሉ ናቸው፡፡ በሁለቱ መካከል ስለሚነሳው ክርክር የእርስዎ ዕይታ ምንድነው?

ዶ/ር ጌታቸው፡- ክርክሩ የድሮ ነው፡፡ የዘረመል ምህንድስና ቴክኖሎጂ ከመምጣቱም በፊት እነ ማዳበሪያ፣ ዓረምና ተባይ መቆጣጠሪያ መድኃኒቶች ሲመጡ የለም የእኛ አገር ገበሬዎች ድሆች ስለሆኑ፣ ይኼን ወይም ያንን ስለማይችሉ የተሻሻለ ዝርያ ሊሠራ ስለማይችል በነባሩ መቀጠል አለባቸው ይባል ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ክርክር ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻም ሳይሆን ህንድና ሌሎችም አገሮች ውስጥ ነበር፡፡ በመጀመርያ ግን ነባር ዝርያ ማለት ምን ማለት ነው? አንዳንዴ ነገሩን ሁሉ ድፍንፍን እናደርግና ሰዎችን ግራ እናጋባለን፡፡ ጤፍ ላይ ነባር ዝርያ ሳይሆን የተሻሻለ ዝርያ ነው ያለን፡፡ አሁን መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ለመሆን እየተቃረብን ነው፡፡ ወደ ኋላ ሄደን በነባር ዝርያ ራሱን የቀለበ ሕዝብ ብንፈልግ አናገኝም፡፡ እኔ የሚቻልም አይመስለኝም፡፡ ነባር ዝርያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ በተለይ ወደፊት ለሚመጡና ለማናውቃቸው ነገሮች እንፈልጋቸዋለን፡፡ ነገር ግን በራሳቸው ብቻ ምርት ይሰጡናል ማለት የሚያዋጣ አይመስለኝም፡፡ ስንዴ ላይ ሠርቻለሁ፡፡ ከዚያ ያየሁት ነገር የሚቻል እንደማይሆን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ሁለቱ የሚጠፋፉ ሥርዓቶችም አይደሉም፡፡ የግድ ነባር ዝርያ ብቻ ወይም የተሻሻለ ዝርያ አለያም የዘረመል ምህንድስና ቴክኖሎጂ ብቻ የሚል ነገር የለም እኮ፡፡ በሁሉም ጥምር ውጤት ነው ለውጥ የሚመጣው፡፡ ቴክኖሎጂው መሥራት ባለበት ቦታ ሲውል ነው ጥቅም የሚሰጠው፡፡ አንዳንዴ የዓለም ሕዝብ በሙሉ ኦርጋኒክ ምግብ ቢበላ፣ እኔም ልጆቼም ብንበላ ደስ ይለኛል፡፡ ማን ይጠላል? ነገር ግን ሐሳባዊነት ነው፡፡ አይሆንም፣ አይቻልም፣ መቼም አልሆነም ወደፊትም አይሆንም፡፡ የኦርጋኒክ ገበያ ተገኘ ይባልና ነገሩ ሁሉ ይሞቃል፡፡ የኦርጋኒክ ገበያ ግን ወደ ውጭ ለመሸጥ ነው የሚያስበው፡፡ መታሰብ ያለበት አንዱ አንዱን መደምሰስ ያለበት ቴክኖሎጂ ሳይሆን፣ መሥራት ባለበት ቦታ ላይ የሚሠራው ይሥራ የሚለው የሚያስማማ ነው፡፡ በነባር ዝርያዎች ብቻ ሕዝብን መቀለብና ለኢንዱስትሪው ግብዓት ማስገኘት ይቻላል ብዬ አላስብም፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ዘረመል ምህንድስናው እንምጣ፡፡ በዚህ አኳኋን ለማምረት ያፀደቁ አገሮችን ስናይ የሚያወጧቸው ድንጋጌዎች በጣም ጠንቃቃና ጠንካራ፣ የሚያስቀምጧቸው ቅድመ ሁኔታዎችም ከበድ የሚሉ ናቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ ሥጋት እንዳለ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ይህ መሆኑ ቴክኖሎጂውን ለሚቃወሙ አካላት ተጨማሪ የመከራከሪያ ጉልበት አይሆናቸውም?

ዶ/ር ጌታቸው፡- ልክ ነው ሆኗልም፡፡ ከመጀመርያውም ግፊቱን ያደረገውም ያው ኃይል ይመስለኛል፡፡ ካርታኬኛ የሚባለው ስምምነት ሲፈረም መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳቡ ቴክኖሎጂውን መከልከል ሳይሆን፣ መቆጣጠር ላይ የተመሠረተ ሕግ በዘረመል ምህንድስና ላይ እንዲወጣ ነበር፡፡ ነገር ግን አገሮች ከዚህም በላይ የየራሳቸውን ሕግ ጠበቅ አድርገው አሊያም አላልተው ማውጣት እንደሚችሉ ተጠቅሷል፡፡ በአፍሪካ ኅብረት በኩልም አፍሪካ ሞዴል ሎው የተባለውና በጣም ጠንካራ ሕግ ወጣ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ፣ ታንዛንያ፣ ዛምቢያ የመሳሰሉት አገሮች ያንን ሞዴል ተከትለው ጠንካራ ሕጎችን አውጥተዋል፡፡ የተዘነጋ ነገር ምንድ ነው ካልን፣ እንዲህ ያለ ሕግ ይዘህ ስላለህ ማንም መጥቶ ሊሥራ አይችልም ወይም የላላ ሕግ ስላለህም የሚገባ የለም፡፡ ሊያሠራ የሚያስችል የራሱ ሥርዓት አለው፡፡ አሁን ጊዜው እያለፈ ሲመጣና የ20 ዓመታት ልምድ ሲታይ፣ ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም ዳር ዳር ማለት በጀመርንበት ወቅት ቴክኖሎጂው ያላቸውን ኑና እንሥራ ብትቻለው አይቀበሉህም፡፡ አሳሪ ሕጎችን ማሻሻል ይጠቅብናል፡፡ አሁን ሕጎች እየተሻሻሉ ነው፡፡ በኮሜሳ አገሮች እንኳ ከታየ ኢትዮጵያ አሻሽላለች፡፡ ስዋዚላንዶች እያሻሻሉ ነው፡፡ ዛምቢያዎች ለማሻሻል እየሞከሩ ነው፡፡ ዘግይተው ሕግ ያወጡት አገሮች ቴክኖሎጂውን መጠቀም ባይጀምሩም እንኳ የሚያሠራ ሕግ አውጥተዋል፡፡ ኬንያና ዚምባብዌ የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ሕግ ስለተሻሻለ አገሩ ይጥለቀለቃል ማለትም አይደለም፡፡ ፍርኃት አይፈጥሩም ወይ? የሚለውን ለምን ሕጎቹን ማሻሻል አስፈለገ? ከሚለው ጋር ማየት ተገቢ ነው፡፡ አንድ ነገር ተደጋግሞ ሲነገር እውነት ይመስላል፡፡ ደቡብ አፍሪካን እንውሰድ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ለምንድነው የቴክሎጂው ተጠቃሚ የሆነችው? ሌላው የአፍሪካ አገርስ ለምን አልሆነም? የሚለውን ስናይ እኔ የሳይንሳዊ መሠረት ልዩነት ይመስለኛል፡፡ ደቡብ አፍሪካዊያን የራሳቸው ሳይንሳዊ ደረጃ ላይ በማውጣት ከምዕራቡ እኩል የደረሱ በመሆናቸው ማንም አይቃወማቸውም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ዝም ስለሚሉና በእግርጥም ግፊትና ጫናው በመኖሩ ስለማይናገሩ እንጂ ብቃቱ ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ሰውን ሊያስተምሩ የሚችሉትን ተመራማሪዎች በማውጣት ፍርኃቱ እንዲቀንስም ማድረግ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ አንድን ሰው ‹ጂኤምኦ› ምንድነው? ብዬ ብጠይቀው ምናልባት ትልቅ ፍራፍሬ ሊያሳየኝ ይችላል፡፡ ይህ የአመለካከት ችግር እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡ የሕጎቹ መጥበቅ ፍርኃትን ጨምሯል፡፡ ሆኖም ግን ጊዜ እየገፋና ሰዎችም እየገባቸው ሲመጣ ቀስ በቀስ እየተሻሻለ የሚሄድ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ጉዳይ ኮሜሳ ምን እየሠራ ነው?

ዶ/ር ጌታቸው፡- እንደሚታወቀው ኮሜሳ ኢትዮጵያን ጨምሮ 19 አገሮች አባል የሆኑበት የቀጣና ተቋም ነው፡፡ ከሌሎች የቀጣናው የኢኮኖሚ ኅብረት ድርጅቶች ሁሉ በዘረመል ምህንድስና ረገድ ፖሊሲ ያለው ኮሜሳ ብቻ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2003 አካባቢ ነበር የተጀመረው፡፡ በተለይ በደቡባዊ አፍሪካ አካበቢ ድርቅ ተከስቶ ስለነበር ከውጭ የምግብ ዕርዳታዎች ይመጡ ነበር፡፡ ሆኖም የዘረመል ምህንድስና ውጤቶች ስለሆኑ እንቀበል የለም መቀበል የለብንም የሚለው ጉዳይ ብዙ ጭቅጭቅ አስነስቶ ነበር፡፡ በወቅቱ ስለዚህ ቴክኖሎጂ ብዙም አይታወቅም ነበር፡፡ ስለዚህ በተናጠል ከሚደረግ በጋራ እንዲታይ ፕሮግራም ይውጣ ተባለ፡፡ በመሆኑም ከአሥር ዓመታት በላይ የፈጀ ፖሊሲ ሊወጣ ችሏል፡፡ እያንዳንዱ አገር በመሄድ ከባለድርሻዎች ጋር ውይይት ማድረግ ይጠበቅብን ነበር፡፡ ይሁንና የፖሊሲ ማዕቀፉ አስገዳጅ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቴክኖሎጂው አሁን ባለበት ደረጃ አስገዳጅ ሊሆን አይችልም፡፡ የፖሊሲውን ዋናው ዓላማ ካየን ቴክኖሎጂው ጥቅም እንዳለው ሁሉ ሥጋትም አለው፡፡ በመሆኑም ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ በፖሊሲ ደረጃ መቀበል ይገባል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ በባዮቴክኖሎጂ ደኅንነት ቁጥጥር በምንሠራበት ጊዜ ለምሳሌ ተመሳሳይ ምርት ቢኖርና ኬንያ ውስጥ ተሠርቶ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ቢደረግ፣ ኢትዮጵያ ከኋላ እንደ አዲስ ሒደቶቹን ሁሉ ጠብቃ ከመሥራት ይልቅ፣ የጋራ የሆነ የባዮሴፍቲ የሥጋት ግምገማ ሥርዓት ቢኖረን የሚል የፖሊሲ ምክር ቀርቧል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የአቅም ግንባታ ሥራ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ኮሜሳ ለአገሮች በዚህ ረገድ ድጋፍ ይሰጣል፡፡

ሌላው ቴክኖሎጂውን ተጠቅመን እናብቅል ወይም አናብቅል? እንግዛ ወይም አንግዛ? የሚለው ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ የመወሰን ሥልጣን የአገሮቹ ድርሻ ይሆናል፡፡ የኮሜሳ ሥራ ምክር መስጠት ነው፡፡ የወጣውን ፖሊሲ ወደ ተግባር ለመወለጥ የሚያስችል ስትራቴጂ ለመቀየር የትግበራ ዕቅድ አወጣን፡፡ በዚህ ውስጥ አንዱ ትልቁ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ሰዎች እንዲረዱት የሚሠራበት ሲሆን፣ ሁለተኛው የጋራ የባዮሴፍቲ አደጋ ሥጋት ግምገማ እናቋቁማለን የሚለው በኮሜሳ የሚሠራበት ነው፡፡ ሚዲያውን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ቴክኖሎጂው የሚተገበርባቸው አካባቢዎች በመውሰድ እንዲገነዘቡት የማድረግና የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ለሕግ አውጪዎችም ሕግ ከማውጣታቸው በፊት ስለቴክኖሎጂው ግንዛቤ የሚሰጡ የውይይት መድረኮችና ዓውደ ጥናቶችንም እናዘጋጃለን፡፡ እንዲህ ያሉ ሥራዎችን ነው በኮሜሳ በኩል የምንሠራው፡፡

ሪፖርተር፡- የባዮሴፍቲ ሥጋት ቁጥጥርን ካነሱ አይቀር ዋና ዋና የሚጠቀሱ የባዮሴፍቲ አደጋዎችና ሥጋቶች ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ጌታቸው፡- ዶሴ የሚባል ነገር አለ፡፡ ማመልከቻው ሲገባ አብሮ የሚያያዝ ሰነድ ነው፡፡ ይኼም አንደኛው በጤና ላይ ምን ሊያመጣ ይችላል የሚለው ይጠናል፡፡ ለምሳሌ እንደ አለርጂ ያሉ ጉዳቶችን እንዳያስከትል ጥናቶች ይካሄዳሉ፡፡ ጥናቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ ለተመሳሳይ ምርት ኬንያም የተሠራው ኢትዮጵያም የተሠራው ያው ስለሚሆን የግድ የጥናት ድግግሞሽ ማድረግ አያስፈልግም፡፡ ሁለተኛ በሚዘራበት አካባቢ ያሉትን ተባዮች፣ አፈር ውስጥ ያሉትን ነፍሳትና የመሳሰሉትን ይጎዳል ወይ? ሦስተኛ ዘሩ ሲዘራ በምን ያህል ርቀት መዘራት አለበት? የሚለው ይታያል፡፡ ምክንያቱም አንዱ ጋ የዘረመል ዘር ቢዘራ በአቅራቢያውም ሌላ ዝርያ ቢኖር ሁለቱ እንዳይገናኙ የሚደረገው ማገጃ ምን ያህል መሆን አለበት? የሚለው ይታያል፡፡ የአሠራር ሒደቱም ይታያል፡፡ አጥር ማጠር፣ ተረፈ ምርት ማቃጠልና የመሳሰሉት ሁሉ ጥናት ይደረግባቸዋል፡፡ እርግጥ ጊዜው እየተሻሻለ ሲሄድ አንዳንድ አገሮች ተረፈ ምርት ማቃጠልም ትተዋል፡፡