‹‹በየጊዜው ምርጥ ምርጥ ሆቴሎች አሳድረን አበል እየከፈልን የምናዞራቸው ሰዎች፣ ይኼ ግጭት እንዳይቆም ሌት ተቀን ይሠራሉ፡፡ እነዚህ አደብ መግዛት አለባቸው፡፡››

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ሐሙስ መጋቢት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የግማሽ ዓመት የመንግሥታቸውን ሪፖርት ባሰሙበት ወቅት የተናገሩት፡፡ ‹‹በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ማለትም በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በአማራና በትግራይ ክልሎች አዋሳኝ ድንበሮች ጋር በተገናኘ ያልተመለሱና ለረዥም ዓመታት የሚንከባለሉ የሕዝብ ጥያቄዎች ለግጭት እየዳረጉ ይገኛሉ፡፡ ክልሎቹ ተቀራርበው ችግሮቹን ለመፍታት ሲሞክሩ አይታይም፡፡ የፌዴራል መንግሥት እነዚህን ችግሮች እስከ መቼ ነው የሚያስታምመው?›› የሚል ጥያቄ ከፓርላማ አባላት ቀርቦላቸው ከሰጡት ምላሽ ውስጭ በአጽንዖት ከተናገሩት የተወሰደ፡፡