‹‹ብዙ ገዳዮች አሉ፤ ከኛም ዘንድ ብዙ ገዳዮች አሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ እኛ ነፃ ነን እንዴ?››

 

አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ‹‹ፎክስ ኒውስ›› ከተሰኘ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉ ቃለ ምልልስ የተናገሩት፡፡ እሑድ ጥር 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ከፎክስ ጋር ቆይታ ያደረጉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ጋዜጠኛው ቢል ኦራይሊ የሩሲያ ፕሬዚዳት ቭላድሚር ፑቲን ‹‹ገዳይ አይደሉምን?›› ብሎ ለጠየቃቸው የሰጡት ሰያፍ ምላሻቸው ነበር፡፡ የትራምፕ ቃለ ምልልስን ተከትሎ ሩሲያ በበኩሏ የቴሌቪዥን ጣቢያው ፕሬዚዳንት ፑቲንን ‹‹ተሳድቧል›› በማለት በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ ጠይቃለች፡፡ የአገሪቱ የዜና ምንጭ ታስ የክሬምሊን ቤተ መንግሥት አፈ ቀላጤን ጠቅሶ  ‹‹ጋዜጠኛው አቋሙ ትክክለኛ አይደለም፤ የተናገረውም ስድብ ነበር፤›› በማለት ዘግቧል፡፡ ቭላድሚር ፑቲንን እንደሚያከብሩ ግን በሳቸው ዕርምጃ ሁሉ እስማማለሁ ማለት አይደለም ያሉት ትራምፕ፣ ከፑቲን ጋር ባለፈው ቅዳሜ በስልክ ባደረጉት ቆይታ ዳኢሽን (አይኤስ) በጋራ ለመፋለምና በሌሎች ጉዳዮችም ለመተባበር መወያየታቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡