‹‹አሁን ሱዳን ከግብፅ ተፅዕኖ ተላቃ በነፃነት ውሳኔዎችን ማሳለፍ ጀምራለች››

ዶ/ር ሳልማን መሐመድ ሳልማን፣ የዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ ተመራማሪና አማካሪ

ዶ/ር ሳልማን መሐመድ ሳልማን ሱዳናዊ የሕግ ባለሙያ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የʻኢንተርናሽናል ዎተር ሎውʼ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ናቸው፡፡ የዓለም አቀፍ የውኃ ሀብቶች ማኅበር (ኢውራ) ፌሎውም ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ ታኅሳስ 2009 ድረስ በዓለም ባንክ የሕግ ምክትል ፕሬዚዳንት ሥር ዋና አማካሪ ሆነውም አገልግለዋል፡፡ በዚህም ባንኩን በውኃ ሕግ፣ በአካባቢ ጥበቃና በማኅበራዊ ዋስትና ፖሊሲዎች ዙሪያ በዋነኛነት ያማክሩ ነበር፡፡ የዓለም ባንክን ከመቀላቀላቸው በፊት ዶ/ር ሳልማን እ.ኤ.አ. ከ1981 እስከ 1983 ጣሊያን ሮም በሚገኘው የተመድ ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ (ኢፋድ) በሕግ ኦፊሰርነት ሠርተዋል፡፡ ዶ/ር ሳልማን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እ.ኤ.አ. በ1972 ከካርቱም ዩኒቨርሲቲ በሕግ አግኝተዋል፡፡ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ አሜሪካ ከሚገኘው ዬል ዩኒቨርሲቲ በሕግ እ.ኤ.አ. በ1974 እና በ1977 አጠናቀዋል፡፡ ዶ/ር ሳልማን በካርቱም ዩኒቨርሲቲ ከአሥር ዓመታት በላይ ሕግ አስተምረዋል፡፡ ለረጅም ዘመናት ከዘለቀው አገልግሎታቸው ጎን ለጎን በብሔራዊና ዓለም አቀፍ የውኃ ሕግና ፖሊሲ ላይ እጅግ በርካታ የምርምር ሥራዎችን አሳትመዋል፡፡ ዶ/ር ሳልማን በቅርቡ በሱዳን ዋድ መዳኒ ከተማ በተዘጋጀ ዓውደ ጥናትና በሩዋንዳ ኪጋሊ ከተማ በተዘጋጀ የጋዜጠኞች ሥልጠና ላይ ተገኝተው በዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ ላይ ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡ ሰለሞን ጎሹ በዓለም አቀፍ የውኃ ሕግና ተዛማጅ የዓባይ ተፋሰስ ጉዳዮች ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ ዕድገት ውስጥ ወሳኝ የሚባሉት ሁነቶች የትኞቹ ናቸው?

ዶ/ር ሳልማን፡- ከ46 ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ. በታኅሳስ ወር 1970 የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ክርክር ካደረገ በኋላ የውሳኔ ሐሳብ ቁጥር 2669ን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡ በዚህም የጉባዔው የሕግ ክንፍ ዓለም አቀፍ የሕግ ኮሚሽን (አይኤልሲ) ዓለም አቀፍ የውኃ ተፋሰሶችን በማጥናት ለዘርፉ ዕድገት የሚበጅ ሐሳብ እንዲያቀርብና የሕግ ረቂቅ እንዲያዘጋጅ ጠይቋል፡፡ የጉባዔው አባላት በወቅቱ እንዳስገነዘቡት ከ300 በላይ ወንዞች፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሐይቆችና የጉድጓድ ውኃዎች በሁለትና ከዚያ በላይ አገሮች የጋራ ባለቤትነት ሥር ናቸው፡፡ እነዚህ ተፋሰሶች ከመሬት ክፍል ውስጥ 45 በመቶ ያህሉን ይሸፍናሉ፡፡ ከ40 በመቶ በላይ ከሚሆነው የዓለም ሕዝብ ሕይወት ጋርም የተቆራኙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ የማውጣት ተግባር ዘግይቷል ከሚባል በስተቀር አስፈላጊነቱ አጠራጣሪ አልነበረም፡፡ እ.ኤ.አ. ግንቦት 21 ቀን 1997 የተመድ ዓለም አቀፍ የውኃ ኮንቬንሽን ፀድቋል፡፡ ይህም ከዚህ በፊት በስቶኮልም፣ ማር ዴል ፕላታ፣ ደብሊን፣ ሪዮና ማራኬሽ ኮንፈረንሶች አማካይነት የተደረጉት ዓለም አቀፍ ጥረቶች መቋጫ ነበር፡፡

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በመጨረሻ ዓለም አቀፍ የውኃ ተፋሰሶችን በአግባቡ ለመጠቀም፣ ለማልማት፣ ለመጠበቅ፣ ለማስተዳደርና ለመጠበቅ እንዲሁም ለአሁኑና ለቀጣዩ ትውልድ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ ለማስቻል በአስቸኳይ የጋራ ውሳኔ እንደሚያስፈልግ ተገንዝቦ ነበር፡፡ አይኤልሲ ረቂቅ ኮንቬንሽን ለማቅረብ 24 ዓመታት ፈጅቶበታል፡፡ በሒደቱ አምስት ራፖርተሮች የነበሩት ሲሆን፣ አሥራ አምስት ሪፖርቶችንም አውጥቷል፡፡ ረቂቁ እ.ኤ.አ. በ1994 የቀረበለት ጠቅላላ ጉባዔ ተከራክሮ ከተስማማ በኋላ ለማፅደቅ ተጨማሪ ሦስት ዓመታት ፈጅተዋል፡፡ ኮንቬንሽኑ ከፀደቀ በኋላ እ.ኤ.አ. በነሐሴ 2014 ወደ ሥራ እስኪገባ ድረስ 17 ዓመታት መጠበቅ ግድ ሆኖበታል፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ ዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ አሁን የያዘውን ቅርፅ ለመያዝ 44 ዓመታት ወስደውበታል፡፡ ይህም ጉዳዩ ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ኮንቬንሽኑ በትብብር ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያለ ትብብር ዓለም አቀፍ የውኃ ተፋሰሶችን በአግባቡ ለመምራት፣ ለመጠበቅና በጋራ ለመጠቀም እንደማይችል ያረጋገጠ መሆኑን የሚያሳይ ስምምነት ነው፡፡      

ሪፖርተር፡- በዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ የፍልስፍና ማዕቀፍ ውስጥ የትኞቹ መርሆዎች የአብዛኛውን አገሮች ይሁንታ አግኝተዋል? የትኞቹስ በአከራካሪነት ዘልቀው ስምምነት የሚጠብቁ ናቸው?

ዶ/ር ሳልማን፡- ዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ እጅግ ውስብስብ ዘርፍ ነው፡፡ የአንድ ወንዝ ምንጭ አንድ አገር ነው የሚሆነው፡፡ ይህ አገር የውኃው ዋነኛ ምንጭ ሊሆንም ይችላል፡፡ ውኃ ሲፈስ ድንበር አያውቅም፡፡ ድንበሮችም ወንዞችን ከግምት ውስጥ በማስገባት አይከለሉም፡፡ አንድ ወንዝ በበርካታ አገሮችን ሊያልፍና የጋራ ንብረታቸው ሊሆን ይችላል፡፡ እያንዳንዱ አገር በወንዙ ላይ ያለው ጥገኝነት፣ አስተዋጽኦና ጥቅም ይኖራል፡፡ እነዚህን ፍላጎቶችና ጥቅሞች ማስታረቅ ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ ከላይ እንደገለጽኩት ይህ ውስብስብ ባህሪ የተመድ የውኃ ኮንቬንሽን በሚዘጋጅበት ወቅት ግልጽ ሆኗል፡፡ አሁን ዓለም አቀፍ ስምምነት አለ፡፡ ድንበር ተሻጋሪ የውኃ ሀብቶችን ለማስተዳደር፣ በጋራ ለመጠቀምና ለመከላከል ያስቀመጣቸው ድንጋጌዎች በስፋት ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡ ይህ ስምምነት የማዕቀፍ ስምምነት ነው፡፡ ምክንያቱም አገሮቹ በመደራደር፣ በመወያየትና በመስማማት ዝርዝር ጉዳዮችን በሌላ ስምምነት በመወሰን ከኮንቬንሽኑ ጋር አጣጥመው እንዲሄዱ ዕድሉን ይሰጣቸዋል፡፡ ስምምነቱ መሠረታዊ መርሆዎችንም ያስቀምጣል፡፡ መሠረታዊ የሚባሉት መርሆዎች አምስት ናቸው፡፡ ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም ቅድሚያ የሚሰጠው መርህ ነው፡፡ የተቀሩት መሠረታዊ ጉዳት ያለማስከተል ግዴታ፣ የታቀዱ ዕርምጃዎችንና ፕሮጀክቶችን ለሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ማስታወቅ፣ አካባቢን መጠበቅና የግጭት አፈታት መርሆዎች ናቸው፡፡ እነዚህ መርሆዎች ከኮንቬንሽኑም በፊት የነበሩ ናቸው፡፡ ላለፉት 200 ዓመታት በሥራ ላይ ነበሩ፡፡ ʻልማዳዊ ዓለም አቀፍ ሕግʼ የምንለውን የሕግ ክፍል የሚወክሉ ናቸው፡፡ ይህም ማለት አገሮች ኮንቬንሽኑን አፀደቁትም አላፀደቁት የማክበር ግዴታ አለባቸው እንደማለት ነው፡፡

ይህ ባህሪ በዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት (አይሲጄይ) ውሳኔዎች ተንፀባርቋል፡፡ አይሲጄይ ኮንቬንሽኑን የተቀበለ ሲሆን፣ ውሳኔዎቹም ስምምነቱን የተመረኮዙ ነበሩ፡፡ ኮንቬንሽኑን በማጣቀስ አይሲጄይ ሁለት ጉዳዮችን ወስኗል፡፡ የመጀመሪያው እ.ኤ.አ. በ1997 በሃንጋሪና በስሎቬኒያ መካከል የነበረው ክርክር ሲሆን፣ ሁለተኛው እ.ኤ.አ. በ2010 በአርጀንቲናና በኡራጓይ መካከል የነበረው ክርክር ነው፡፡ አይሲጄይ እ.ኤ.አ. በመስከረም ወር 1997 ያየው የጋብሲኮቮ ናጋይማሮስ ጉዳይ ሃንጋሪና ስሎቫኪያ በዳኑብ ወንዝ አጠቃቀም ላይ የፈጠሩትን አለመግባባት የተመለከተ ነበር፡፡ አይሲጄይ ይህን ጉዳይ ያየው ስምምነቱ ከፀደቀ ከአራት ወራት በኋላ ሲሆን፣ በወቅቱ አንድም አገር ስምምነቱን በአገር ውስጥ አላፀደቀውም ነበር፡፡ ሃንጋሪና ስሎቫኪያም ፈራሚ አገሮች አልነበሩም፡፡ አይሲጄይ እ.ኤ.አ. በ2010 አርጀንቲናና ኡራጓይ በኦሮጎ ወንዝ አጠቃቀም ላይ የነበራቸውን አለመግባባት ለመቅረፍ ስምምነቱ ላይ ተመሥርቷል፡፡ በተመሳሳይ አርጀንቲናም ሆነ ኡራጓይ የስምምነቱ አካል አልነበሩም፡፡ ስምምነቱ ካለው የልማዳዊ ዓለም አቀፍ ሕግ ባህሪ ባሻገር አገሮቹ ልዩ ተጨባጭ ሁኔታቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ማሻሻያ እያደረጉ እንዲጠቀሙበት ተመቻችቶ የተቀረፀ ነው፡፡                   

ሪፖርተር፡- አገሮቹ እነዚህን መርሆዎች በማቀናጀት ከመጠቀም ይልቅ አንዱን መርጠው መመርኮዝ የሚመርጡት ለምንድነው?

ዶ/ር ሳልማን፡- ባለፉት 200 ዓመታት ዓለም አቀፍ የውኃ ሕግን የገጠመው መሠረታዊ ጉዳይ በፍትሐዊና በምክንያታዊ አጠቃቀምና መሠረታዊ ጉዳት ያለማድረስ ግዴታ መርሆዎች መካከል ያለው ግንኙነት ነው፡፡ የትኛው ይበልጥ ይጠቅማል? ለየትኛው ቅድሚያ ይሰጣል? የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ኢትዮጵያና ግብፅ በናይል ጉዳይ ያላቸውን ጉዳይ ለአብነት ማየት እንችላለን፡፡ ግብፅ በዋነኛነት የምትጠቅሰው መሠረታዊ ጉዳት ያለማስከተል ግዴታን ነው፡፡ ግብፃዊያን እየተጠቀሙ ያለው ውኃ ታሪካዊ መብት እንደሆነና ሌላ ማንም አገር ጣልቃ ሊገባበት እንደማይችል ያስባሉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ መሠረታዊ ጉዳት ያስከትላል የሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ሁሉ ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህን ታስቀድማለች፡፡ ምክንያቱም ግብፅ የምትጠቀመውን መጠን ግምት ውስጥ ሳታስገባ ውኃው ላይ ድርሻ እንዲኖራት ስለሚያደርግ ነው፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ወይም በላይኛውና በታችኛው ተፋሰስ አገሮች መካከል ማን ማንን ይበልጥ ይጎዳል በሚለው ጉዳይ ላይ ውጥረት አለ፡፡ በነገራችን ላይ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ብቻ ናቸው ጉዳት የሚያስከትሉት የሚል የተሳሳተ አመለካከት አለ፡፡ ይኼ ትክክል አይደለም፡፡ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ታሪካዊ መብቶችን በመጥቀስ በሚያቀርቡት የይገባኛል ጥያቄ፣ የላይኞቹን ተፋሰስ አገሮች የወደፊት የውኃ መጠቀም መብት በመገደብ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡            

ሪፖርተር፡- ድንበር ተሻጋሪ የውኃ ሀብቶችን ለመምራት የተመድ የውኃ ተፋሰሶች ኮንቬንሽን ምርጡ መፍትሔ እንደሆነ የሚያምኑ ይመስላሉ፡፡ ታዲያ ለምንድነው ከዓባይ ተፋሰስ አገሮች  ውስጥ አንዱም ይህን ስምምነት ያላፀደቀው?

ዶ/ር ሳልማን፡- ድንበር ተሻጋሪ የውኃ ሀብቶችን በተመለከተ የተመድ ስምምነት ብቸኛው ዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፍ ነው፡፡ ስምምነቱ ወደ ሥራ የገባው ከሁለት ዓመት በፊት ነው፡፡ በስምምነቱ ላይ ተመድ ውስጥ ድምፅ ሲሰጥ የአሥሩ የናይል ተፋሰስ አገሮች ድምፅ የተከፋፈለ ነበር፡፡ በወቅቱ ደቡብ ሱዳን ራሷን የቻለች ነፃ አገር አልነበረችም፡፡ ሱዳንና ኬንያ ኮንቬንሽኑን ደግፈው ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ሩዋንዳና ታንዛኒያ ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል፡፡ ቡሩንዲ በመቃወም ድምፅ ሰጥታለች፡፡ ኤርትራና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በድምፅ መስጠት ሒደቱ ተሳታፊ አልነበሩም፡፡ አራቱ ድምፀ ተአቅቦ ያደረጉ አገሮች የተለያየ ምክንያት ነበራቸው፡፡ ኢትዮጵያ ድምፀ ተአቅቦ ያደረገችው ስምምነቱ አስቀድሞ ስለማሳወቅ ዝርዝር የሆኑ ድንጋጌዎችን ይዟል ብላ በማሰቧ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልነበረችው ለግብፅና ለሱዳን ውሳኔዎቹንና ፕሮጀክቶቹን ቀድማ ብታሳውቅ እ.ኤ.አ. በ1902 ግብፅና ኢትዮጵያ ፈርመውታል በተባለው ስምምነት ለግብፅ ለተሰጠው የቬቶ ሥልጣን ዕውቅና እንደመስጠት ስለወሰደችው ነው፡፡ ግብፅ ደግሞ ድምፀ ተአቅቦ ያደረገችው ስምምነቱ ለፍትሐዊና ለምክንያታዊ አጠቃቀም ያደላና ቅድሚያ የሚሰጥ ነው በማለት ነው፡፡ ግብፅ ቅድሚያ የምትሰጠው ለመሠረታዊ ጉዳት ያለማድረስ ግዴታ ነው፡፡ ነገር ግን የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (ሲኤፍኤ) ከተመድ ኮንቬንሽን የተወሰደ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀምን ለመወሰን ግንዛቤ ውስጥ የሚገቡ መሥፈርቶች ተጨማሪ ሁለት ከመካተታቸው ውጪ ከተመድ ኮንቬንሽን ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በእኔ ዕይታ በናይል ተፋሰስ አገሮች ዘንድ ስለኮንቬንሽኑ ያለው አመለካከት የተሳሳተ ነው፡፡ በአግባቡ የተረዱት አልመሰለኝም፡፡            

ሪፖርተር፡- በሲኤፍኤውና በናይል ላይ ተፈጽመዋል በሚባሉት ሁለትዮሽ ስምምነቶች መካከል ግንኙነት አለ ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ሳልማን፡- በእኔ ዕይታ ሲኤፍኤው ጥሩ የሕግ ሰነድ ነው፡፡ ብቸኛው የዚህ ሰነድ ችግር የናይል ተፋሰስ አገሮችን ሙሉ ድጋፍ ያላገኘ መሆኑ ነው፡፡ በአንድ በኩል ግብፅና ሱዳን በሌላ በኩል የላይኛው ተፋሰስ አገሮች በፍትሐዊና በምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ያላቸው ልዩነት አደራዳሪዎቹ ʻየውኃ ደኅንነትʼ የሚል ጽንሰ ሐሳብ እንዲያመጡ አድርጓቸዋል፡፡ ይኼ የሕግ ጽንሰ ሐሳብ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ጽንሰ ሐሳብ እንጂ፡፡ በዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ ምንም ቦታ የለውም፡፡ ይህ ጽንሰ ሐሳብ ያለውን አለመግባባት ይቀርፋል ተብሎ የመጣ ቢሆንም፣ እውነታው ግን ችግሩን ይበልጥ እንዳባባሰው ነው የሚያሳየው፡፡ ለዓለም አቀፍ የውኃ ሕግም ሆነ ለሲኤፍኤው በርካታ ችግሮች ነው ያመጣው፡፡ ግብፅና ሱዳን የሚሉት እየተጠቀሙ ያሉት መብት ዕውቅና ተሰጥቶት በሲኤፍኤው ተጠቅሶ እንዲቀመጥ ነው፡፡ ሌሎቹ አገሮች ደግሞ ይህን አይቀበሉም፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ይህን ካደረጉ ለእነሱ የሚቀር ነገር የሌለ መሆኑንና ሴኤፍኤው መሠረት ያደረገበትን ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህም የሚንድ መሆኑ ነው፡፡

በተጨማሪም ቀድሞ የማስታወቅ መርህ ላይ ስምምነት አልነበረም፡፡ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ቀድሞ የማሳወቅ መርህን ቢቀበሉ ግብፅና ሱዳን የ1902 እና የ1929 ስምምነቶችን በመጥቀስ የቬቶ ሥልጣን አለን እንዳይሉ ሥጋት አላቸው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የተወሳሰቡ ናቸው፡፡ ነገር ግን መፍትሔ አላቸው፡፡ ግብፅ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. መጋቢት 23 ቀን 2015 በኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የመግባቢያ መርሆዎች ስምምነት ፈርመዋል፡፡ በዚህም ግብፅና ሱዳን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በናይል ውኃ ላይ ሌሎች የተፋሰሱ አገሮች የመጠቀም መብት እንዳላቸው ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡ ይኼ በትክክለኛ አቅጣጫ እየሄደ ያለ ታላቅ እመርታ ነው፡፡ በእኔ ዕይታ ይህ ስምምነት የ1902፣ የ1929 እና የ1959 ስምምነቶችን የሻረ ነው፡፡ በሲኤፍኤው ላይ ሙሉ ስምምነት ለመፍጠር ሊያገለግል ሁሉ የሚችል ነው፡፡ ይህን ስምምነት ለመፍጠር ግብፅና ሱዳን አለን የሚሉት ታሪካዊ መብት በሲኤፍኤው ይካተት የሚሉትን ውትወታ ማቆም አለባቸው፡፡ በተመሳሳይ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ቅድሚያ ማሳወቅ በሲኤፍኤው መካተት የለበትም የሚለውን ውትወታቸውን መተው አለባቸው፡፡             

ሪፖርተር፡- እርስዎ እንዳሉት የላይኛው ተፋሰስ አገሮች በአስቀድሞ ማስታወቅ መርህ አፈጻጸም ላይ ከፍተኛ ሥጋት አላቸው፡፡ እንደ ሁኔታው ሊራዘም የሚችል የስድስት ወራት የማስታወቂያ ጊዜ፣ ተከታታይ ውይይትና ምክክሮች ፕሮጀክቶቻችንን ሊያግቱ ይችላሉ የሚል ፍርኃት አላቸው፡፡ ይኼ ሥጋት በእውነታው ላይ የተመሠረተ አይደለም?

ዶ/ር ሳልማን፡- በሲኤፍኤው ላይ ይደረግ የነበረው ድርድር ከመጨናገፉ በፊት የናይል ቤዚን ኢኒሺየቲቭ መሥፈርትን ተጠቅሞ ለማስታወቅ መድረክነት እንዲያገለግል ለማድረግ የዓለም ባንክ ወስኖ ነበር፡፡ ስድስት ወራትን መጠበቅ የግድ አይደለም፡፡ አገሮች ለማሳጠር ሊስማሙ ይችላሉ፡፡ በሲኤፍኤው ለተቋቋመው ኮሚሽን የትኛውም ፕሮጀክት ሊላክ ይችላል፡፡ ሁሉም አካላት በኮሚሽኑ ተወክለዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹን ያለምንም አድልኦ ሊገመግም ይችላል፡፡ የዓለም ባንክ ስድስት ወራት አይጠይቅም፡፡ ከዚያ ያነሰ ጊዜ ለምሳሌም 45 ቀናትና ሁለት ወራት ነው የሚጠይቀው፡፡ በዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ ዋነኛው ነገር ስለዕርምጃዎችና ፕሮጀክቶች በቅድሚያ እንዲያውቁ የሚደረጉ አገሮች የቬቶ ሥልጣን የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ እነዚህ አገሮች ጥያቄ መጠየቅ ይችላሉ፣ ተጨማሪ መረጃ መጠየቅ ይችላሉ፣ ሊቃወሙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ተቃውሞ ማቅረብ የቬቶ ሥልጣን ሊሆን አይችልም፡፡ ተቃውሞ ለበለጠ ውይይትና ድርድር በር የሚከፍት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ የባሰ ነገር አመጣ እንኳን ቢባል የእውነታ አጣሪ ኮሚሽን ተቋቁሞ ተቃውሞው ታይቶ ሪፖርት ይወጣል፡፡            

ሪፖርተር፡- የመርሆዎች መገለጫ ስምምነቱ የሕግ ደረጃ ላይ ያለዎት አቋም ምንድነው?

ዶ/ር ሳልማን፡- ይህ ስምምነት አስገዳጅ አይደለም በማለት የሚቀርብ ክርክር በእኔ እምነት ትክክል አይደለም፡፡ ይኼ ስምምነት በአገር መሪዎች የተፈረመ ነው፡፡ የዓለም አቀፍ ሕግ መሠረታዊ መርሆዎችን የያዘ ነው፡፡ ስለዚህ አስገዳጅ አይደለም ቢባልም እንኳን ልማዳዊ ዓለም አቀፍ ሕግ ነው፡፡ ይኼ ስምምነት ወደ ትብብርና የጋራ ድርጊት ለማምራት መሠረታዊ ዕርምጃ ነው፡፡ ስምምነቱ የተፋሰሱ አገሮችን እኩልነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀበለ ነው፡፡          

ሪፖርተር፡- ሁሉን አቀፍ ስምምነት በተፋሰሱ እንዲፈጸም የሱዳን ሚና ምን መሆን አለበት ይላሉ?

ዶ/ር ሳልማን፡- እ.ኤ.አ. ከ1910 እስከ 1959 ግብፅና ሱዳን የናይል ውኃ አጠቃቀምና የገዚራ የመስኖ ግብርና ላይ ከፍተኛ አለመግባባት ፈጥረው ነበር፡፡ ከፍተኛ ውጥረት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ሱዳን እ.ኤ.አ. የ1929 ስምምነት ውድቅ አድርጋ ሁሉ ነበር፡፡ ከዚያ የ1959 ስምምነት በመፈራረም የቅርብ አጋርነት ፈጠሩ፡፡ ይህ ግን ሌሎች የተፋሰሱ አገሮችን ያገለለ ነበር፡፡ የናይል ውኃን ለብቻቸው ለመጠቀም መወሰናቸው ትልቅ ስህተት ነበር፡፡ ስምምነቱ ራሱ ሌላ የተፋሰሱ አገር የሌለ ይመስል ‹‹የናይል ውኃን በሙሉ ለመጠቀም›› የሚል ገለጻን ይዟል፡፡ ግብፅና ሱዳን ከውኃው ድርሻ የሚፈልግ ሌላ አገር ለእነሱ ማመልከቻ ማስገባት እንዳለበት ሁሉ ይጠይቃሉ፡፡ ምን ያህል ውኃ ማግኘት እንዳለባቸው የመወሰን ሥልጣንንም ለራሳቸው ይሰጣሉ፡፡ ማመልከቻውንም ውድቅ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ወስነዋል፡፡ ይኼ አንድ አገር ሊፈርም የሚችለው እጅግ መጥፎው ስምምነት ነው፡፡ የዓለም አቀፍ ሕግ መሠረታዊ መርሆዎችን ሁሉ የሚጥስ ነው፡፡

አሁን ሱዳን ከግብፅ ተፅዕኖ ተላቃ በነፃነት ውሳኔዎችን ማሳለፍ ጀምራለች፡፡ ይኼ በእኔ ዕይታ ጤናማ ምልክት ነው፡፡ ይኼ ሱዳንን ብቻ ሳይሆን ግብፅንም የሚጠቅም ነው፡፡ ሁለቱ አንድ ላይ በመሆን የተሳሳተ ውሳኔ መወሰን ብቻ ሳይሆን እንዲፈጸም ይወተውቱ ነበር፡፡ አሁን ግን ሱዳን ትክክለኛ ውሳኔ መወሰን በመጀመሯ ግብፅም አንዳንድ ውሳኔዎች ላይ ጥያቄ ማንሳት ጀምራለች፡፡ ከላይ የገለጽኳቸው ማሻሻያ ሐሳቦች በሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮች ተቀባይነት ካገኙ ሁለቱ አገሮች የሲኤፍኤው አፅዳቂ የማይሆኑበት ምክንያት የለም፡፡ ሱዳን በሁለቱ አገሮች አጋርነት ደካማዋ ክፍል ሆና ነው የቆየችው፡፡ በ1959 ስምምነት መሠረት የሱዳን የውኃ ድርሻ 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ቢሆንም፣ ሱዳን ግን ስትጠየቀም የቆየችው 12 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ብቻ ነው፡፡ 6.5 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ወደ ግብፅ ይሻገር ነበር፡፡ በስምምነቱ መሠረት የተቋቋመው ኮሚሽን በሱዳን ፕሮጀክቶች ላይ ቁጥጥር የሚያደርግ ሲሆን፣ በግብፅ ግን የመከታተል ሥልጣን ብቻ ነው የተሰጠው፡፡ ስለዚህ ሱዳን በርካታ ጥቅሞቿን አሳልፋ በመስጠት ግብፅን የበላይ አድርጋ ብትቆይም፡፡ አሁን ግን ለራሷ ጥቅምና ፍላጎት መቆም ጀምራለች፡፡