‹‹እንዲህ ሆነናል!››

በአዲስ አበባ ከተማ መገናኛ ድልድይ አካባቢ፣ በአራት ዓመት ውስጥ የታየ ለውጥ፡፡ በደቡብ አቅጣጫ ወደ ኢምፔሪያል- ቦሌ መንገድ ግራና ቀኝ የቀድሞና ያሁን ገጽታን ልብ ይሏል፡፡

  1. ጥር 2005 ዓ.ም.
  2. የካቲት 2009 ዓ.ም.

(ፎቶ በታምራት ጌታቸው)

* * *

አስመሳይ

አፍሼ ዘግኜ ላይ በላይ ብክበው

እፍኝም ላይሞላ ክንዴን አደቀቀው፡፡

ከ’ኔው መስሎኝ ነበር ሚዛን የጎደለው

ለካስ የቀለለ ገለባ ኾኖ ነው፡፡

መላኩ ደምለው ‹‹ብልጭታ›› (2008)

* * *

የፈስ ነገር

ፈስ፣ ታችኛ ትንፋሽ ግም የዓይነ ምድር ወላፈን፡፡ (ተረት) የጠበኛ ፈስ ዓይን ያፈስ፤ እንዲያውም በመላ ፈስ ዳለቻ ነው፡፡

ፈሰ ከንቱ (ቲ) የፈሱ ሽታ ራስ የሚበጠብጥ ሆድ የሚቆርጥ የሚያም ቁናሳም፡፡

ፈሳም፡፡

ፈረሱን ጠበሰ፣ ሮጠ ሸሸ ጋለበ (የአሮጊት ፈስ) ክረምት አፈራሽ ነገር፣ በበጋ እንደ ፈስ የሚበን የሚተን፣ ክብ እንክብል ዓይን የሚያኽል ፍጥረት፡፡ ልጆች በተሰበሰቡበት ፈስ ተፈስቶ የፈሳው ባይታወቅ፣ የፈስ አፈርሳታ ለማውጣት ‹‹ፈስ ፈሶ ፈስ አራራ፣ ቆርጦ ቆርጦ ደም ያሳራ፣ ደሙ ሲረጋ በለው ባለንጋ፡፡ . . . ያጤ መስቀል ሲንቀለቀል የፈሳውን ልቡን ይንቀል›› ይባላል፡፡

ደስታ ተክለወልድ

‹‹ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት›› (1962)

* * *

    ‹‹ያይብ ልጥልጥ››

በየካቲት መባቻ የተመረጡት አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ በቅጽል ስማቸው፣ ‹‹ፎርማጆ›› በመባል ይታወቃሉ፡፡ በ50ዎቹ አጋማሽ  የሚገኙት ፕሬዚዳንቱ በአማርኛ ‹‹ጅብና›› ማለትም፣ ያይብ ልጥልጥ ወይም ዱቄት የሚባለው ፎርማጆ (ቺዝ) ስለሚወዱ ስያሜውን እንዳገኙ ይነገራል፡፡

የሶማሊያና የአሜሪካ ጥምር ዜግነት ያላቸው ‹‹ያይብ ልጥልጡ›› አብዱላሂ መሐመድ ቡፋሉ ከሚገኘው፣ የኒው ዮርክ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በታሪክ የባችለር ዲግሪ፣ በፖለቲካ ሳይንስ የማስትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡ በአሜሪካ በስደት መኖር ከጀመሩበት ከ1977 ዓ.ም. ወዲህ በተለያዩ ሙያዎች ዲፕሎማት፣ ፕሮፌሰርና ፖለቲከኛ ሆነው ብቻ አላሳለፉም፡፡ የእግር ኳስ ዳኛም ነበሩ፡፡ በቲውተር ገጽ ላይ የተገኘው ፎቶዋቸው በአሜሪካ ኦሃዮ ግዛት በኮሎምቦስ፣ የቤት ውስጥ ግጥሚያን የመሩበትን ያሳያል፡፡

(ሔኖክ መደብር)

* * *

ፍሬ ልቡና

ካርቱም ላይ ለአጭር ጊዜ ቆመን ወደ አዲስ በሚበር የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሮፕላን ተሳፈርን፡፡ አይሮፕላኑ ላይ ስወጣ ፓይለቱ ጥቁር መሆኑን ተመለከትሁ፣ በሕይወቴ ጥቁር ፓይለት ዓይቼ አላውቅም፣ እንዳየሁትም የመብረር ፍራቻዬን ከላዬ ላይ ገፈፍሁት፣ እንዴት ጥቁር አይሮፕላን መንዳት ቻለ? ወዲያውኑ አሳቤን ገታሁት፣ በደቡብ አፍሪካ የተቀረፀብኝን የአፓርታይድ አስተሳሰብ አይሮፕላን ማብረር የነጮች ሙያ ብቻ ነው፣ ጥቁሮች ዝቅተኞች ናቸው የሚለውን አስተያየት ከላሁት፡፡ መብረር ስንጀምር ሥጋቴ ጠፋና የኢትዮጵያን መልክዓ ምድር ማጥናት ጀመርኩ፣ ከሥሬ በተንጣለሉት ጫካዎች ውስጥ እየሸመቁ ኢትዮጵያውያን አርበኞች የጣልያንን ኢምፔሪያሊዝም እንዴት እንደተዋጉ በምናቤ አወጣ አወርድ ጀመር፡፡

በቀድሞው ዘመን አቢሲኒያ በመባል የምትታወቀውን ኢትዮጵያ፣ ከክርስቶስ ልደት ረዥም ጊዜ በፊት፣ በሰሎሞን በንግሥተ ሳባ ልጅ የተመሠረተች አገር ናት፡፡ ብዙ ጊዜ የተወረረች ቢሆንም ኢትዮጵያ የአፍሪቃ ብሔረተኝነት ትውልድ ሥፍራ ናት፣ እንደሌሎቹ የአፍሪቃ አገሮች ሳይሆን እንደ አመጣጡ ኮሎኒያሊዝምን ተጋፍጣ ተቋቁማለች፣ ባለፈው ምዕት ዓመት ምኒልክ ኢጣሊያኖችን አሳፍሮ መልሷቸዋል፣ በያዝነው ምዕት ዓመት ግን ሊቋቋማቸው ባይችልም ንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ታሪክ ቀያሽ ሆኗል፡፡ ሙሶሎኒ ኢትዮጵያን ሲወር የአሥራ ሰባት ዓመት ወጣት ነበርኩ፡፡ ለዚያ አምባገነን ደንፊ ብቻ ሳይሆን ለሚያናፍሰው ፋሺዝምም በአጠቃላይ ጥላቻ ያደረብኝ ያኔ ነው፡፡ በ1936 ኃይለ ሥላሴ አገር ለቅቆ ለመውጣት ቢገደድም በ1941 ዓ.ም. የተባበሩት ኃይላት ጣልያኖችን ሲያባርሩ ለመመለስ በቅቶአል፡፡

ኢትዮጵያ በምናቤ ውስጥ ሁልጊዜ ልዩ ሥፍራ ይዛ ቆይታለች፣ ወደ እሷ ያደረግሁት ጉዞ ወደ እንግሊዝ ወደ ፈረንሣይ ወይም ወደ አሜሪካ ተጓዝ ከሚሉኝ እጅግ በጣም ይበልጥብኛል፣ የራሴን ኦሪት ዘፍጥረት የምጎበኝበትና፣ የአፍሪቃዊነት ሥረ መሠረት ቆፍሬ የማወጣበት ቦታ አድርጌ ነው የቆጠርኳት፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ጋር መገናኘት ብቻ እንኳን የታሪክን እጅ እንደጨበጥኩት ያህል ነው የምቆጥረው፡፡

የንጉሠ ነገሥቱ መዲና አዲስ አበባ ስናርፍ እንደ ስሙ ሆኖ አላገኘነውም፣ ጥቂት የአስፋልት መንገዶችና ከመኪኖች ይልቅ ፍየልና በጎች የሚበዙበት ከተማ ነው፡፡ ከቤተ መንግሥቱ፣ ዩኒቨርሲቲውና ካረፍንበት የራስ ሆቴል በቀር፣ በጆሃንስበርግ ከተሠሩት በጣም መለስተኛ ህንፃዎች ጋር የሚወዳደሩ ምንም የለም፡፡ የዛሬይቱ ኢትዮጵያም ለዴሞክራሲ ሞዴል የምትሆን አገር አይደለችም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሉም፣ በመንግሥት ውስጥ ሕዝባዊ ድርጅቶች የሉም፣ የሥልጣን ክፍፍል የሚባል የለም፣ ንጉሰ ነገሥቱ ብቻ በቁንጮው ላይ ቁብ ብሏል፡፡

በኮንፈረንሱ ዋዜማ ልዑካኑ በደብረ ዘይት ከተማ ተሰበሰቡ፡፡ በከተማው መካከል አደባባይ ትልቅ መድረክ ተሠርቶአል፤ እኔና ኦሊቨር ራቅ ብለን ወደ ጎም ቆምን፣ ድንገት የጥሩምባ ድምፅ ከሩቅ ተሰማና በከበሮና በታምቡር የታጀበ የሠልፈኛ ሙዚቃ መጣ፣ እየቀረበ ሲመጣ የሠልፈኞች እግር መሰማት ጀመረ፣ ከአደባባዩ ጥግ ካለ ሕንፃ አንድ መኮንን የሚያብለጨልጭ ሻምላ ይዞ ብቅ አለ፣ እሱን ተከትለው በመቶዎች የሚቆጠሩ ትናንሽ አበሾች ልጆች በአራት ረድፍ ተሠልፈው ጠመንጃቸውን በመለዮዎቻቸው ላይ አንግበው ይራመዳሉ፡፡ ሰገነቱ ጋ ሲደርሱ አንድ መኮንን አንድ ትዕዛዝ ሲሠጥ አምስት መቶ ሠልፈኞቹ ቀጥ አሉ፡፡ እንደ አንድ ሰውም ወደ ሰገነቱ ዞረው ለሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ፣ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ሰላምታ ገጭ አድርገው ሰጡ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕይወቴ በጥቁር ጄኔራሎች የሚመራ የጥቁር ሠራዊት ከልዩ ልዩ አገሮች ለመጡ መሪዎች፣ ለአንድ አገር ጥቁር ርዕሰ ብሔር እየተጨበጨበላቸው ሰላምታ ሲሰጡ አየሁ፡፡ ልብ የሚያነሳሳ ትርኢት ለአገሬም የወደፊት ራዕይ ይኼ እንደሚሆን ተስፋ አደረግሁ፡፡  

ስብሰባችን የተከፈተው በጋባዣችን ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ነበር፡፡ በመዳሊያ ያሸበረቀ የሚሊቴሪ ልብስ ለብሰው ነበር፡፡ ቁመታቸው እንዴት አጭር መሆኑን ያኔ ተገነዘብሁ፣ ነገር ግን ግርማቸውና በራስ መተማመናቸው የአፍሪቃው አንበሳ መሆናቸውን በውኑ ይታያል፡፡ አንድ ርዕሰ ብሔር የአመራሩን ተግባራት ሲያከናውን ስመለከት የመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ እጅግ በጣም አስደነቀኝ፤ ቁመናቸው ፍፁም ቀጥ ያለ፣ አንገታቸውን ሰበር የሚያደርጉት ማዳመጫውን ለማሳየት ብቻ ነው፡፡ ድርጊታቸው ሁሉ ግርማ ሞገስ የተጎናፀፈ ነው፡፡