አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

‹‹የከተማ ጤና ራሱን ችሎ እንደ አንድ አጀንዳ ሊሠራበት ይገባል››

አቶ ኅብረት ዓለሙ፣ በጄኤስአይ የከተማ ጤና  ማጠናከሪያ ፕሮግራም ፕሮጀክት ኃላፊ

ጆን ስኖው ኢንኮርፖሬትድ ጄኤስአይ የተቋቋመው ከ20 ዓመታት በፊት በአሜሪካ ቦስተን ከተማ ነው፡፡ የጤና ፕሮግራሞችን ቀርጾ በመተግበር ይታወቃል፡፡ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘው ከአሜሪካ የዕርዳታ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ነው፡፡ በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ አገሮችና የዓለም ክፍሎችም ይሠራል፡፡ ፕሮግራሙ በአገሪቱ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አራት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ አቶ ኅብረት ዓለሙ ጄኤስአይ ከሚያስፈጽማቸው ፕሮግራሞች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ የከተማ ጤና ማጠናሪያ ፕሮግራም ፕሮጀክት ኃላፊ ናቸው፡፡ አብዛኛውን ሥራዎቹን የሚሠራው ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከጤና ቢሮዎችና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በአገሪቱ ምን ዓይነት ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ፣ እንዲሁም በከተማ ጤና ዙሪያ ባሉ ጉዳዮች ላይ ሻሂዳ ሁሴን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡-  ጄኤስአይ በአገሪቱ መስራት የጀመረው በምን ዓይነት ፕሮግራም ነበር? በየትኞቹ የአገሪቱ ክፍሎችስ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ያደርጋል?

አቶ ኅብረት፡- በደቡብ ክልል መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ለኢትዮጵያ የሚል ፕሮጀክት ይዞ ነበር በአገሪቱ መሥራት የጀመረው፡፡ በወቅቱ የተሠራው ሥራ ጥሩ የሚባል ውጤት በማስመዝገቡ የፕሮጀክቱ ሁለተኛው ክፍል ደቡብን ጨምሮ በኦሮሚያና በአማራ ክልል መተግበር ጀመረ፡፡ የሕፃናትን ጤና ማሻሻል፣ የጤና ዘርፉን የገንዘብ አሰባሰብና አጠቃቀም ማሻሻል፣ ማኅበረሰቡ ከጤና ዘርፉ ጋር ተቆራኝቶ መሥራት እንዲችል ለማድረግ የማኅበረሰብ ንቅናቄ ሥራዎችን መሥራት በፕሮጀክቱ  ሲተገበሩ የነበሩ ሥራዎች ናቸው፡፡ ድርጅቱ ከሚተገብራቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶች መካከል የከተማ ጤና ፕሮግራም አንዱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡‑ ፕሮጀክቱ ከከተማ ጤና ጋር በተያያዘ ምን ይሠራል?

አቶ ኅብረት፡‑ በአገሪቱ የተለያዩ ሴክተሮች እያደጉ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከተሜነት ዋናው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ባለው መረጃ መሠረት ከ18 እስከ 20 ሚሊዮን የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ የሚኖረው በከተሞች ነው፡፡ አገሪቱ የያዘቻቸው የኢኮኖሚ ስትራቴጂዎች ከተሜነትን የሚያበረታቱ ናቸው፡፡ ስለዚህም አገሪቱ በያዘችው የዕድገት አቅጣጫ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ሊሄድ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው ጥያቄ ከተማ ውስጥ የሚኖረው ሰው ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ የሚሄድ ከሆነ ለዚያ የሚመጥን የጤና ሥርዓት አለን ወይ? አሁን በከተማ ውስጥ ያለው የጤና አሰጣጥ ያንን መቋቋም ይችላል ወይ? የማይችል ከሆነ ደግሞ እንዴት ነው ከወዲሁ መዘጋጀት የምንችለው? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ካልተዘጋጀን ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ከሆኑ በኋላ መመለስ አስቸጋሪ ነው፡፡ ከሌሎች አገሮችም የምንማረው ይህንኑ ነው፡፡ አገሪቱ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ትሰለፋለች ይባላል፡፡ ለዚያ የሚሆን መሠረታዊ የጤና አገልግሎት በከተሞች እንዲኖር የመንግሥትን ጥረት የመደገፍ ሥራ እንሠራለን፡፡ እኛ ጥገኝነትን መፍጠርም ሆነ ሁሉን ነገር እኛ እያቀረብን በእኛ ላይ ብቻ እንዲቆም አንፈልግም፡፡ ቀዳሚ ተግባራችንም የጤና አሰጣጥ ሥርዓቱ ያሉበትን ጥቃቅን ክፍተቶች በመሙላት ቀጣይነት እንዲኖረው ማስቻል ነው፡፡ ሥራችንንም የምንሠራው በከተማ ጤና ሥርዓቱ ላይ ያሉ ክፍተቶችን እያጠናን ነው፡፡

እገዛ የምናደርገውም በአራት በተለያዩ የጤና ዘርፎች ላይ ነው፡፡ የመጀመሪያው በማኅበረሰብ ደረጃ የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽነት ማሻሻል ነው፡፡ በዚህ ረገድ የከተማ ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች መስጠት የሚገባቸውን አገልግሎት ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲሰጡ፣ ሥልጠና በመስጠትና የተለያዩ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ስራቸውን በተገቢው መልኩ እንዲያከናውኑ እገዛ እናደርጋለን፡፡

ማኅበረሰቡን በማስተማርና የተለያዩ መገናኛ አውታሮችን በመጠቀም መረጃ በመስጠት ሕዝቡን የምናነቃበት ሥራም አለን፡፡ በጤናው ሴክተር ያለውን የሰው ኃይል የአስተዳደርና የመሪነት ሥልጠና በመስጠት የአቅም ግንባታ ሥራ የመሥራት፣ መረጃ ማሰባሰብና መረጃውን ተንተርሶ ክፍተቶችን የመሙላት እንዲሁም በጤናው ላይ ያሉ ጉዳዮችን  ባለድርሻ አካላት በየጊዜው እየተገናኙ እንዲወያዩ፣ ችግሮችን ለይተው መፍትሔ እንዲሰጡ፣ የከተማን የጤና ሥርዓት የማደራጀትና የማጠናከር ሥራም እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡‑ የከተማ ጤና ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው በየትኞቹ የአገሪቱ ክፍሎች ነው?

አቶ ኅብረት፡‑ ፕሮጀክቱ የተጀመረው ለ49 ከተሞች ድጋፍ እንዲያደርግ ነው፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታትም 47 ከተሞችን ስንደግፍ ቆይተናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁለት ከተሞችን ጨምረን የከተሞቹን ቁጥር 49 አድርሰናል፡፡ ጋምቤላ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ሲቀሩ በሌሎቹ በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች እንሠራለን፡፡ ትላልቅ ከተሞች በፕሮግራሙ ታቅፈዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከፍተኛ የጤና ችግር ባለባቸው አምስት ክፍለ ከተሞች ላይ እንሠራለን፡፡ አዲስ አበባ የተለያየ ማኅብረሰብ ክፍል የሚኖርባት ከተማ ነች፡፡ የተሟላ የጤና አገልግሎት ማግኘት የሚችሉ የራሳቸው ሐኪም ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በጣም አስቸጋሪ በሆነ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚኖሩ የተወሳሰበ የጤና ችግር ያለባቸውና ወደ ጤና ተቋም ሄዶ ለመታከም እንኳን የሚፈሩ ሰዎች አሉ፡፡ እኛም ትኩረታችንን አድርገን የምንሠራው በእነዚህ ሰዎች ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡‑ በዋናነት የምትሠሩት በየትኞቹ የጤና ጉዳዮች ዙሪያ ነው?

አቶ ኅብረት፡‑ የከተማ የጤና ችግር ብዙ ቢሆንም የእኛ አብዛኛው ትኩረታችን የእናቶችና ሕፃናት ጤና፣ የሥነ ምግብ ጉዳዮች፣ የቤተሰብ ምጣኔ፣ ኤችአይቪና ቲቢ ላይ ነው፡፡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እየበዙ መምጣታቸውን እናውቃለን፡፡ ግን የእኛ ፕሮግራም ዓላማ በእነዚህ ላይ ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡‑ ከምትሠሩባቸው ከተሞች መካከል ከፍተኛ የሆነ የጤና ችግር ያለበት የትኛው ነው?

አቶ ኅብረት፡‑ የእኛን ከተሞች በሦስት መድበን ልናያቸው እንችላለን፡፡ አዲስ አበባ የክልል ከተሞችና የወረዳ ከተሞች አሉ፡፡ እነዚህ እንደየደረጃቸው ያሉባቸው ችግሮች ይለያያሉ፡፡ ለእኔ አዲስ አበባ የተለየ ከተማ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ችግርና የሌሎች የክልል ከተሞች ችግር የተለያየ ነው፡፡ አዲስ አበባ እንደ ሌሎቹ የክልል ከተሞች ወጥ የሆነ ባህል የላትም፡፡ የህዝቡ ብዛትም ከሌሎቹ የተለየ ነው፡፡ ከተማው ከተለያዩ አካባቢዎችና ክልሎች የሚመጡ ሰዎች የሚኖሩበት ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች አዲስ አበባ ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት ውስብስብ ያደርጉታል፡፡ ለምሳሌ ከፅዳት፣ ከቆሻሻ ማስወገድ ጋር ተያይዞ ያለው ችግር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በቅርቡ ተከስቶ የነበረው የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ክስተትም ያሳየን ይህንኑ ነው፡፡ በከተማይቱ ያለው ቆሻሻ የማስወገድ ሥራ ገና ብዙ ልፋት ይጠይቃል፡፡ ሌሎች ከተሞችም ተመሳሳይ ችግር ቢኖርባቸውም አስፈላጊ የሚባሉ ሴክተሮችን አንድ ላይ አገናኝቶ ሥልጠና መሰጠት ካለበትም ሰጥቶ ማሠራት ይቻላል፡፡ ብዙ አይከብድም፡፡ አዲስ አበባ ላይ ግን ቀላል አይደለም፡፡ አስቸጋሪነቱ እንደ አዲስ አበባ አይደለም፡፡ ትንንሾቹ የወረዳ ከተሞች ላይ ደግሞ ያንን ያህል ከባድ አይደለም፡፡ የከተማ ጤና ፕሮግራሙም ወደፊት አዲስ አበባን፣ ባህርዳርን፣ ሐዋሳን እንደሚያክሉ ታሳቢ በማድረግ ትኩረቱን በእነሱ ላይ አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡ ሪፖርተር፡‑ ድርጅታችሁ በኤችአይቪ ዙሪያ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡ ለመሆኑ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለው የኤችአይቪ ሥርጭት ምን ይመስላል?

አቶ ኅብረት፡‑ አሁንም ድረስ ኤችአይቪ በተወሰኑ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ላይ በስፋት ይታያል፡፡ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ቤት ለቤት እየሄዱ ለኤችአይቪ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን እንዲመረመሩ ያስተምራሉ፡፡ ጤና ጣቢያ ሄደው መመርመር ባይፈልጉ እንኳን እዚያው ቤታቸው ውስጥ ሆነው በጤና ኤክስቴንሽን ሠራኞች እንዲመረመሩ እናደርጋለን፡፡ በአጠቃላይ ግን ኢትዮጵያ የኤችአይቪ ሥርጭትን መቆጣጠር ችላለች፡፡ ከፍተኛ የሆነ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ተሠርቷል፡፡ መከላከል ላይ አተኩሮ መሠራቱም ጥሩ የሚባል ለውጥ እንዲታይ ዕድል ሰጥቷል፡፡ በአገሪቱ የነበረውን የኤችአይቪ ሥርጭትም ወደ 1.14 በመቶ ማውረድ ተችሏል፡፡ በገጠር ያለው የሥርጭት መጠን 0.6 በመቶ ሲሆን በከተማ ደግሞ 4.2 በመቶ ነው፡፡ነገር ግን አሁን ነገሮች ጥሩ ሆነዋል በሚል መዘናጋት እንዳይፈጠር መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ችግሩም ወዲያው የሚታይ ሳይሆን ከጊዜ በኋላ ነው፡፡ ተገቢው ጥንቃቄ ሳይደረግ ቀርቶ አገሪቱ  በኤችአይቪ ወረርሽኝ ዳግም እንዳትመታ ህዝቡን የመቀስቀስና የማስተማሩ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የምንሠራው ሥራም ይህንኑ ነው፡፡ ለኤችአይቪ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰቡ ክፍሎች በተለይም ሴተኛ አዳሪዎች ኮንዶም የሚያገኙበትን ሁኔታ እናመቻቻለን፡፡ የወጣት ማዕከላት ላይም እየተገኙ ስለ ሥነ ተዋልዶ ጤናና ስለኤችአይቪ እንዲያስተምሩ እናደርጋለን፡፡ ትምህርት ቤቶች ላይም ያስተምራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከአምስትና ከስድስት ዓመታት በፊት የነበረውን ንቅናቄ አሁን ላናይ እንችላለን፡፡ ኤችአይቪ በከተሞች ላይ ትልቅ ችግር ነው፡፡ መዘናጋት አያስፈልግም፡፡

ሪፖርተር፡‑ ከሥነ ምግብ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ትልቅ ችግር እንዳለ ይነገራል፡፡ የችግሩ መጠን ምን ያህል ነው? እናንተስ በዚህ ረገድ ምን ትሠራላችሁ?

አቶ ኅብረት፡‑ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት የአመጋገብ ሁኔታን በሦስት መንገዶች እንለካለን፡፡ ሕፃኑ ለዕድሜውና ለቁመቱ የሚመጥን ክብደት እንዲሁም ለዕድሜው የሚስተካከል ቁመት አለው ወይ? የሚሉትን እናያለን፡፡ በዚህ መሰረት በተሰራ ጥናት በአገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ የማግኘት ችግር መኖሩ ተረጋግጧል፡፡ በአገሪቱ ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ ሕፃናት መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘታቸው የቀነጨሩ ናቸው፡፡ 8.7 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከቁመታቸው ጋር የማይመጣጠን ክብደት ያላቸው ናቸው፡፡ 13.4 በመቶዎቹ ከመደበኛው ክብደት በታች ናቸው፡፡ ገጠር ላይ  ፕሮዳክቲቭ ሴፍቲኔት የሚባል የመንግሥት ፕሮግራም አለ፡፡ በዚህ ፕሮግራም በምግብ ራሳቸውን ያልቻሉ አርሶ አደሮች በሴፍቲኔት ታቅፈው ሥራ ይሠራሉ፡፡ ለሠሩበት ሥራ በምግብ ይከፈላቸዋል፡፡ የተወሰኑ ከተሞችም የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተመርጠዋል፡፡ በዚህ ላይ እኛ የሚኖረን ዋናው ሚና ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሕፃን ከተወለደ እስከ ስድስት ወር ድረስ ጡት ብቻ ነው መጥባት ያለበት፡፡ ነገር ግን ከተማ ላይ ያለው ኅብረተሰብ ይህንን ያምናል ወይ የሚለው ነገር አጠያያቂ ነው፡፡ ይህንን በጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች አማካይነት ኅብረተሰቡን እናስተምራለን፡፡ ሠራተኞቹ እናትየው በወለደች በ24 ሰዓት ውስጥ እንዲጎበኟት፣ ድጋፍ እንዲያደርጉላት እናደርጋለን፡፡ ሕፃኑ ከእናት ጡት በተጨማሪ ምግቦችን መመገብ በሚያስፈልገው ጊዜም ምን ዓይነት ምግብ መመገብ አለበት የሚለውን እንዲያስተምሯቸው ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ዕርዳታ ያደርጉላቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ላይ ምን ዓይነት ችግሮች ያጋጥሟችኋል?

አቶ ኅብረት፡- እኛ የምንደግፋቸው ወደ 2,200 የሚሆኑ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አሉ፡፡ በሥራ ላይ የሚያስቸግሯቸው ነገሮች እንዳሉ ጠይቀናቸው ከቤት ቤት እየተዘዋወሩ በሚሰሩበት ጊዜ  ፀሐይ እንደሚያስቸግራቸው ነግረውን ለሁሉም ጃንጥላ ገዝተን አከፋፍለናል፡፡ ዕቃ መያዣ ቦርሳዎችም ጠይቀውን በፈለጉት ዲዛይን ቦርሳ ከአሜሪካ ተሠርቶ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ የክብደት መለኪያ፣ ቴርሞ ሜትር፣ የደም ግፊት መለኪያ መሣሪያም ለማቅረብ ግዥ በመፈጸም ላይ ነን፡፡ እንደዚህ ያሉ ቁሳቁሶቹን በበቂ የሚያቀርብ ድርጅት ባለመኖሩ እንቸገራለን፡፡ ቁሳቁሶቹን አገር ውስጥ የሚያቀርቡ ድርጅቶች የሚይዙት ውስን በመሆኑ የምንፈልገውን ያህል መጠን ለማግኘት እንቸገራለን፡፡ የሕክምና ቁሳቁሶችን ለማግኘት ያለው ውጣ ውረድ ደግሞ በጣም ከባድ ነው፡፡ የሕክምና ቁሳቁሶችን ከውጭ ለማስገባት ፈቃድ ሊኖረን ይገባል፡፡ ፈቃዱን ለማግኘት ያለው ሒደት ደግሞ እንደኛ ላለ ድርጅት ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህም ከአገር ውስጥ አቅራቢዎች እንድንገዛ እንገደዳለን፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ጉዳዮች በአገር ውስጥ ያሉ ድርጅቶች አቅርቦት እኛ በምንፈልገው መጠን አይደለም፡፡ ስለዚህም ገበያው ላይ የተገኘውን እየገዛን በሒደት የተፈለገውን ያህል ለማቅረብ አስበናል፡፡ ቦርሳውንም በምንፈልገው መጠን ሠርቶ የሚያቀርብልን ድርጅት ባለመኖሩ ወደ ውጭ ገበያ ለመሄድ ተገደናል፡፡ እንደዚህ ያሉ ችግሮች በሥራችን ላይ እንቅፋት እየሆኑብን ይገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡‑ ፕሮግራሙ ቀጣይነት ይኖረዋል ወይስ በቅርቡ የሚዘጋበት ሁኔታ አለ?

አቶ ኅብረት፡‑ እኛ የምንሠራው ዩኤስኤአይዲ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በሚኖረው የሁለትዮሽ ስምምነት ላይ ተመሥርትን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የእኛን ሥራ ለሁለት ዓመታት ያህል አጠናክረን እንሠራለን፡፡ ከከተሞች መስፋፋትና ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ለመቋቋም የጤናው ሴክተርም መጠናከር አለበት፡፡ በቀጣይ አመታት የከተማ ጤና ራሱን ችሎ እንደ አንድ አጀንዳ ሊሠራበት ይገባል፡፡