አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!
አዲሱን ድረ ገጽ ይሞክሩ!

የመታወቅ ዋጋ

በቅርበት የሚያውቃቸው ሰው በማረፋቸው ቤተሰቦቻቸውን ለማፅናናት ወደ ለቅሶ ቤት ሄደ፡፡ ነገር ግን ከድንኳኑ እንደገባ የለቅሶ ቤቱ ድባብ ተቀየረ፡፡ ወዲያው ሰው ማልቀሱን አቆመ፡፡ የታፈነ የሳቅ ድምፅም ይሰማ ጀመረ፡፡ ሁኔታው ግራ ያጋባቸው የሟች ጎረቤቶች አረፍ እንዲልና ምግብ እንዲቀምስ ሰሐን አቀበሉት፡፡ እሱም ማልቀሱን አቁሞ የተሰጠውን ምግብ መመገብ ጀመረ፡፡ አልፎ አልፎ የሚሰማው የታፈነ የሳቅ ድምፅ እንደቀጠለ ነው፡፡ በመጨረሻ ሁኔታው ያስቆጣቸው የሟች ባለቤትም ‹‹ሐዘኔን ልወጣበት እባክህ ለቅሶ ቤቱን ለቀህ ውጣ›› በማለት እንዳባረሩት ያስታውሳል፡፡ መሰል አጋጣሚዎች ጥቂት እንዳልሆኑና ዕውቅና ያተረፈበት የኮሜዲ ሥራ እንደማንኛውም ሰው በማኅበራዊ ጉዳዮች ሲሳተፍ የተለያዩ አሉታዊ ተፅዕኖዎች እንዲደርሱበት ምክንያት እንደሚሆን በረከት ይናገራል፡፡ በተለያየ መንገድ የሚታወቁ ብዙዎች በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴአቸው የበረከትን ዓይነት ገጠመኞች እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡ የትወናውን ዓለም ከተቀላቀለች አሥር ዓመት ሆኗታል፡፡ ውሳኔ በተሰኘው የቤተሰብ ፊልም ላይ የደም ካንሰር ሕመም ያለባት አንዲት እናት ገፀ ባህሪን ወክላ ተጫውታለች፡፡ አብዛኛዎቹ የተጫወተቻቸው ገፀ ባህሪያት መልካም ባህሪ ያላቸው ናቸው፡፡ ይህ ማኅበረሰቡ የጥሩ ስብዕና ባለቤት አድርጎ እንዲመለከታት አድርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ተዋናይት ገነት ንጋቱ የተለያዩ ገፀ ባህሪያትን ወክሎ የመጫወት ፍላጎት ስላላት በሰው ለሰው ተከታታይ የቴሌቪዢን ድራማ ላይ ማሚቱ የተባለች እኩይ ገፀ ባህሪ ያላትን እናት ወክላ ሠርታለች፡፡ በዚህም ብዙዎቹ አድናቂዎቿ ቅር ተሰኝተው ነበር፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ያገኟትም ቅሬታቸውን ገልጸውላታል፡፡ ‹‹ተዋናይ እንደመሆኔ የተለያዩ ገፀ ባህሪያትን ወክዬ መጫወት እፈልጋለሁ ሁሌም በአንድ ባህሪ ተወስኜ መቅረት አልፈልግም›› የምትለው ተዋናይት ገነት በቴሌቪዥን መስኮት የሚያውቋት አድናቂዎቿ በሥራዎቿ አስተያየት ከመሰንዘር ባለፈም ድንገት ሲያይዋት የሚደናገጡና ገፅታቸው ላይ የተለየ ስሜት የምታይባቸው እንዳሉ ትናግራለች፡፡ በተለያዩ ቦታዎች አድናቆት ከማትረፍ ባለፈ የሕዝብ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎች ላይ ቅድሚያ ማግኘት እንደ ገነት ላሉ የተለመደ ነው፡፡ ‹‹ትልቁም ትንሹም ቅድሚያ ይሰጠናል፡፡ በአንዳንድ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትም የሚሰጠን አገልግሎት በጥንቃቄና በልዩ ትኩረት ነው፡፡ በተለይም በመዝናኛና በሆቴሎች አካባቢ ለተጠቀምነው አገልግሎት ሒሳብ የሚቀበለን የለም፡፡ ብዙ ጊዜ ደንበኞችም ይከፍሉልናል፡፡ ታዋቂ ሰዎች አገልግሎታቸውን መጠቀማቸውን የሚያስደስታቸው ባለቤቶችም ሒሳብ ለመቀበል ፈቃደኛ አይሆኑም፤›› በማለት ያየችውን ምላሽ ትገልፃለች፡፡ ምላሹ አወንታዊ ብቻም ሳይሆን በተቃራኒው የሚሆንበት ዕድል እንዳለ ‹‹ሙያው ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ሕዝቡ አንድን ተዋናይ ከወደደ ወደደ ነው፡፡ አርቲስቱን ያከብራል፡፡ ከጠላም እንዲዚያው፡፡ የቀድሞውን የሕዝብ ፍቅር ለመመለስ ከባድ ነው፡፡ ይቅርታ የማያደርጉ አድናቂዎች አሉ›› በማለት አርቲስት ፈቃዱ ተክለማርያም ይናገራል፡፡ ዕውቅና መልካም ምላሽ አስገኝቶላቸዋል ከሚባሉ ከቀዳሚዎቹ መካከል ነው ሊባል ይችላል፡፡ ይሁንና አልፎ አልፎ አዎንታዊ ቢሆንም ከገደብ ያለፈ ምላሽ እንደሚያጋጥመው ይህም ምቾት እንደሚነሳው ገልጿል፡፡ ‹‹ስላወቁኝ የተጋነነ መስተንግዶ መስተናገድ ይከብደኛል›› ሲል ቅድሚያ የመስጠቱ ጉዳይ መልካም ቢሆንም ሌላውን ሰው በማያስከፋ መልኩ ቢሆን እንደሚመርጥ ይናገራል፡፡ እንደ እሱ አተያይ ሁለት ዓይነት ተመልካቾች አሉ፡፡ ገፀ ባህሪያት በሚኖራቸው መልካምና እኩይ ባህሪ ተዋናዩን የሚያደንቁና የሚጠሉ በሌላ በኩል ደግሞ ከገፀ ባህሪያቱ ውጪ በትወና ብቃት አርቲስቱን የሚያደንቁ ናቸው፡፡ አብዛኛው ተመልካችም በትወና ብቃት ሳይሆን ገፀ ባህሪ አርቲስቱን የሚመዝን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሙያው በሚያስገድደው መልኩ ሁለቱንም ባህሪያት ሲጫወቱ አድናቂው ቅር ይሰኛል፡፡ አልፎ አልፎ እኩይ ገፀ ባህሪያትን በመጫወት የሚታወቁ አርቲስቶች ከማኅበረሰቡ ተግሳፅና ቁጣ ሲሰነዘርባቸው ይታያል፡፡ አብዛኛው ሰው ግን በቴሌቪዥን የሚያውቀውን ግለሰብ በአካል ሲያገኘው ተመሳሳይ የመገረምና የመደናገጥ ስሜት ያሳያል፡፡ በተለያዩ ፊልሞችና ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ረዳትና መሪ ተዋናይት ሆና የሠራችው ዕፀ ሕይወት አበበ ተመሳሳይ ገጠመኞች ፈገግ እንደሚያሰኟት ትናገራለች፡፡ ‹‹ሳያስቡት ድንገት ሲያዩን የሚደናገጡ ብዙ ናቸው፡፡ ተደናግጠው በሚሆኑት ነገርም ሳቄ ይመጣል›› ትላለች፡፡ የአድናቂዎቿ አክብሮት በብዙ ቦታዎች ቅድሚያ እንዲሰጣት አስችሏታል፡፡ በዚህም ደስተኛ ነች፡፡ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በዜና አንባቢነት ማገልገል ከጀመረ አሥር ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ጋዜጠኛ መሰለ ገብረ ሕይወት መታወቁ ካተረፈለት ነገሮች አንዱ በብዙ ቦታዎች ቅድሚያ ማግኘት መሆኑን ይናገራል፡፡ ‹‹መታወቃችን በሰዎች ዘንድ እምነት እንዲጣልብን አድርጎናል፡፡ እንደ ቤተሰብ እንድንታይም ረድቶናል፡፡ ሕዝቡ የሚያሳየን አክብሮትና ፍቅርም ያስደስታል›› በማለት ዕውቅናው ያተረፈለትን መልካም አጋጣሚ ያብራራል፡፡ ከታዋቂዎች ጋር ሰላምታ ለመለዋወጥ የግድ መተዋወቅ አያስፈልግም፡፡ አድናቂው ካወቃቸው በቂ ይመስላል፡፡ ‹‹ለሁሉም ሰው ሰላምታ መስጠት ይጠበቅብናል፡፡ አንዳንዴ ግን የተለየ ሁኔታ ያጋጥመናል፡፡ በሆነ አግጣሚ አንዴ ያገኘን ሰውም እንድናስታውሰው የጠበቀ ሰላምታ እንድንሰጠው ይጠብቅብናል፡፡ ይህንን ማድረግ ሳንችል ስንቀር ብዙዎች ይቀየሙናል›› ያለው መሰለ በዚህ ረገድ ጥቂት የማይባሉ ገጠመኞች እንዳሉት ይናገራል፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያገኙት ዕውቅና ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገርም ዋጋ ሲያስከፍላቸው ይታያል፡፡ ከሌላው በተለየ መልኩ ፍጹማዊነት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህም ማኅበረሰቡ ከሰጣቸው ግምት ውጪ ላለመሆን እንዲጨነቁና ከራሳቸው እንዲጣሉ እንደሚያደርጋቸው ብዙዎቹ ይናገራሉ፡፡ እንደማንኛውም ሰው በማኅበራዊ ሕይወት፣ በትዳር ወይም በቢዝነስ ከሚያጋጥማቸው ሁኔታ ጋር በተያያዘ በተለያየ መንገድ ተፅዕኖ እንደሚደርስባቸው የገለጹም አሉ፡፡ ‹‹ማንኛውም ሰው ከሥራው ባሻገር የራሱ የሆነ ስብዕና አለው፡፡ ነገር ግን እኛን ሁሌም ትክክል እንድንሆን ይጠበቅብናል›› የምትለው ዕፀ ሕይወት አጋጣሚው ስሜታቸውን በነፃነት እንዳይገልጹ እንደሚያስገድዳቸው አልሸሸገችም፡፡ ይህ ከመጠን ያለፈ ጭምት እንዲሆን እንዳደረገው፤ ሁኔታው የሰውነት ስሜት እንደሚያሳጣውና አንዳንዴም እንደሚረብሸው አርቲስት ፍቃዱ ገልጿል፡፡ ‹‹ፍጹም ለመሆን መጣር ከሰውነት ባህሪ ውጭ መሆን ነው፡፡ እኛ እንደማንኛውም ሰው እንከፋለን፣ መዝናናት ያምረናል፣ እንናደዳለንም›› በማለት ዕውቅናቸው ግላዊነታቸውን ሲነፍጋቸው ቅር እንደሚያሰኝ ይናገራል፡፡ ‹‹አንዲት ቦታ ደረስ ብሎ ለመመለስ ከቤት ድሪያና ሻሽ ለብሼ ወጣሁኝ፡፡ አንዲት ልጅ ተደናግጣ ‹ብቻ ገነት እንዳትሆኚ ምን ነካሽ› ብላኝ እየተገረመች አለፈች›› በማለት በአለባበስ፣ በመዝናኛ ቦታ ምርጫ ከሌላ ነገር አንፃርም በተወሰነ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ እንደሚጠበቅ ትናገራለች፡፡ ገንዘብ የተረፋቸው ባለፀጎች አድርገው የሚገምቷቸውም ብዙ ናቸው፡፡ በመሆኑም የሚያስፈልጋቸውን ለመሸመት ገበያ ሲወጡ ነጋዴዎች ከፍተኛ ዋጋ እንደሚጠሩላቸው ታዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ ‹‹ዋጋውን ብናውቀውም መከራከር ራስን ላላስፈላጊ ትችት ማጋለጥ ነው፡፡ መልስ መጠየቅም ከንዝንዝ ይቆጠራል፡፡ ነገር ግን እኔ ይህን አልቀበልም›› በማለት መከራከር ካለባት ተከራክራ በመዘዋወር በገበያ ዋጋ እንደምትሸምት ትናገራለች፡፡ ለትችት ላለመጋለጥ ሲሉ ከሥራ ውጪ ቤት ውስጥ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ማሳለፍ የሚመርጡም አሉ፡፡ ‹‹ሁሉም ነገር ይገንብናል፡፡ አንድ ቀን ሥጋ ቤት ብገኝ ሁሌ ሥጋ እንደምበላ ይወራል፡፡ ርቦኝ ደና ጉርሻ ብወስድ ሆዳም ነው ይባላል፡፡ ስለዚህም ቢርበኝ እንኳን ሬስቶራንት ገብቼ መመገብ አልፈልግም›› የሚለው መሰለ፣ አጋጣሚውን ሽሽት ራሱን እንደሚጎዳ ይገልጻል፡፡ ይህንን በዚህ ቢወጣም ድንገት በሚፈጠሩ ስህተቶች አብዛኛው ሰው ‹‹ካንተ አይጠበቅም›› በማለት አፍ አፉን እንደሚሉትና መሰል አጋጣሚዎች እንደሚረብሹት ይናገራል፡፡ ሁኔታውንም ‹‹ዕውቅና ለሀሜትና ለትችት ቅርብ ያደርገናል›› ሲል ገልፆታል፡፡ በማንኛውም ማኅበራዊ ጉዳይ ለመሳተፍ እንደሚቸገር ኮሜዲያን ፍልፍሉ ይናገራል፡፡ በግል ጉዳዩ አልያም በማኅበራዊ ጉዳዮች የሚያደርገውን ተሳትፎ በቀልድ የሚመለከቱና የሚስቁ ብዙ ናቸው፡፡ ከለቅሶ ቤቱ ገጠመኝ ባሻገር በሆስፒታልና በቤተ ክርስቲያን የማይረሳቸው ገጠመኞችም አሉት፡፡ ቢታመም ሕክምና ለማግኘት ይቸገራል፡፡ ከሆስፒታል መግቢያ ጀምሮ የሚከቡት ብዙ ናቸው፡፡ መታመሙን፣ ለሕክምና መምጣቱን ቢናገርም በሳቅ ያጅቡታል፡፡ አጋጣሚው በመደጋገሙ ሌላ አማራጭ መጠቀም ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ምርመራው እስኪቀር ድረስ መሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች የሚያስጨርሰው በጓደኞቹ አልያም በቅርብ ዘመዶቹ ሆኗል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ችግር ገጥሞታል፡፡ ‹‹አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ በሰው ካስጨረስኩ በኋላ ዶክተሩ ጋር ገባሁ፡፡ አቀርቅሮ ይፅፍ ስለነበር ስገባ አላየኝም፡፡ መቀመጫ ከያዝኩ በኋላ ቀና ብሎ ተመልክቶኝ እኔ መሆኔን ሲያውቅ ‹ብዙ ሥራ አለብኝ፡፡ ለቀልድ ጊዜ የለኝም› ብሎ እየተበሳጨ ጥሎኝ ወጣ›› ሲልም ያስታውሳል፡፡ በእምነት ቦታዎችም ተመሳሳይ ሁኔታዎች አጋጥሞታል፡፡ ‹‹ቤተ ክርስቲያን እየተሳለምኩ ነበር፡፡ ከአንድ ጥግ ተቀምጠው ዳዊት ይደግሙ የነበሩ አንድ አባት እንዳዩኝ ዳዊታቸውን ዘግተው እናንተም እዚህ ትመጣላችሁ እንዴ? ሲሉ ጠየቁኝ›› በማለት በእምነት ቦታዎችም ነፃነታቸውን እንደሚያጡ ይናገራል፡፡ ሰዎች በሚያጋጥሟቸው ልዩ ልዩ ችግሮች ሊነጫነጩ እንዲሁም ከሰው ጋር ሊጋጩ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ታዋቂ ሰዎች ጋር ሲደርስ የተለየ ትርጉም ሊሰጠው ይችላል፡፡ ታዋቂ ሰዎች በተሰማሩበትና ዕውቅና ባገኙበት ዘርፍ ልክ፣ በማኅበራዊ ሕይወታቸውም እንዲተገብሩት የሚፈልጉ አሉ፡፡ ሁሌም መልካም እና የተረጋጉ፣ አለዚያ ኩራተኛና ለሰው ክብር የሌላቸው ተደርገው ሊገመቱ ይችላሉ፡፡ ዕውቅናቸው በሚያሳድርባቸው ተፅዕኖ ስሜታቸውን በነፃነት ለመግለጽ ሲቸገሩ ‹‹ምነው ታዋቂ ባልሆንኩ›› የሚል ምኞት እንደሚያድርባቸውም ይናገራሉ፡፡ መሰል አጋጣሚዎችን ያስተናገዱም ገጠመኞቻቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ከዓመታት በፊት ነው፡፡ አርቲስት ፍቃዱ ወርሃዊ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ ለመክፈል በአቅራቢያው ወደሚገኝ የክፍያ ጣቢያ ያመራል፡፡ ከቦታው እንደደረሰም ምንም እንኳ ወረፋው ብዙ ቢሆንም ከፊቱ ከነበሩት አብዛኞቹ ቅድሚያ ይሰጡታል፡፡ ዕድሉን ለመቀበል ቢያንገራግርም በጅ አላሉትም፡፡ ዕድሉን አመስግኖ በመቀበል ወደ መክፈያው መስኮቱ ተጠጋ፡፡ ይሁን እንጂ ከፊት ተሰልፎ የነበረው ግለሰብ ታዋቂ ቢሆንም ተራ መጠበቅ እንዳለበት ነገረው፡፡ ፍቃዱ እንደሚለው፣ ያልተገቡ ቃላቶችም ሰነዘረበት፡፡ ሁኔታው ቢያበሳጨውም በእርጋታ ሊያስረዳው ሞከረ፡፡ ግለሰቡ ግን ለመስማት ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ በሁኔታው ቢበሳጭም ስሜቱን በነፃነት መግለጽ አልቻለም፡፡ አጋጣሚው ታዋቂ መሆኑን የጠላበትም ነበር፡፡ ተመሳሳይ ስሜት ያሳደረበት አጋጣሚ መኖሩን የሚናገረው ኮሜዲያን ፍልፍሉ ነው፡፡ በቅርቡ የመኪና አደጋ ደርሶበት ነበር፡፡ በወቅቱ አደጋውን ያደረሱበት ግለሰቦች ፖሊስ ጣቢያ የተወሰዱ ሲሆን፣ አደጋውን ያደረሱት ፍልፍሉ ላይ እንደነበር ግን አልተገነዘቡም፡፡ እሱም አስፈላጊውን ሕክምና ካገኘ በኋላ በነጋታው ፖሊስ ጣቢያ ሄደ፡፡ ላደረሱበት ጉዳት ቢታሠሩ ፍላጎቱ ቢሆንም ገና ከበር እንዳዩት ‹‹አድናቂህ ነን›› በማለት በፈገግታ ተቀበሉት፡፡ ‹‹አድናቂዬን እንዴት አሳስራለሁኝ ብዬ ክሱን ትቼ ተመለስኩኝ›› በማለት ታዋቂ መሆን የጠላበትን ቅጽበት ያስታውሳል፡፡