Thursday, August 18, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊለትግራይ ክልል 1.6 ሚሊዮን የኮቪድ-19 ክትባት መላኩን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

  ለትግራይ ክልል 1.6 ሚሊዮን የኮቪድ-19 ክትባት መላኩን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

  ቀን:

  ሦስተኛውን ዙር የኮቪድ-19 ክትባት ዘመቻ እያደረገ ያለው ጤና ሚኒስቴር፣ ዘመቻውን በትግራይ ክልልም ለማከናወን ከሁለት ሳምንት በፊት 1.6 ሚሊዮን የኮቪድ-19 ክትባት መላኩን ገለጸ፡፡

  ሚኒስቴሩ በሦስተኛው ዙር የክትባት ዘመቻ ከዚህ ቀደም ክትባት ያልደረሳቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችና አካባቢዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን፣ በጦርነትና በድርቅ የተጎዱ፣ የተፈናቀሉ፣ እንዲሁም ለጤና ተደራሽነት ቅርበት የሌላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ተካተዋል፡፡

  ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. የመጀመሪያውን ክትባት መስጠት ስትጀምር፣ የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) በትግራይ ክልል ተገኝተው ክትባቱን አስጀምረው ነበር፡፡ ይሁንና የፌዴራሉ መንግሥት ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ፣ እስካሁን ድረስ ክትባት በክልሉ ተቋርጦ ነበር፡፡

  በጤና ሚኒስቴር የክትባት አማካሪ ወ/ሮ ሊያ ወንድወሰን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አሁን ከተላከው የክትባት መጠን ውጪ በክልሉ ተሠራጭቶ የነበረው ክትባት 120 ሺሕ ብቻ ነው፡፡ ‹‹ለሌሎች መድኃኒቶች ቅድሚያ በመሰጠቱ የኮቪድ-19 ክትባት ሥርጭት ዘግይቶ ነበር፤›› ያሉት አማካሪዋ፣ አሁን በአጋር አካላት በኩል በክልሉ ክትባት መሠራጨት መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

  ሚኒስቴሩ ከሁለት ሳምንት በፊት 1.6 ሚሊዮን የኮቪድ-19 ክትባት የላከው በዩኒሴፍ በኩል መሆኑን፣ የጤና ሚኒስትሯ ሊያ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በትግራይ ክልል የክትባት ዘመቻው የሚካሄደውም በክልሉ ባለው የጤና ሥርዓትና በአጋር አካላት በኩል እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

  የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው፣ በኢትዮጵያ ክትባት መስጠት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ 57.8 ሚሊዮን ክትባት በአገር አቀፍ ደረጃ ተሠራጭቶ 47.3 ሚሊዮን ሰዎች ተከትበዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 33.2 ሚሊዮን ክትባቱን ሙሉ ለሙሉ ወስደዋል፡፡

  ሚኒስቴሩ ባዘጋጀው ብሔራዊ የክትባት ሥርጭት ዕቅድ የሰኔ ወር ከመጠናቀቁ በፊት 40 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱ ሕዝብ ለመከተብ አስቧል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ይህንን ቁጥር ወደ 70 በመቶ ለማድረስም አቅዷል፡፡

  ሚኒስቴሩ የኮቪድ-19 ክትባት ማሠራጨትን ጨምሮ ለወረርሽኙ ምላሽ የሚሆኑ ሥራዎቹን ለማከናወን የሚያስችል ሀብት የሚያገኝበት አንዱ መንገድ ከውጭ ተቋማት በሚመጣ ዕርዳታ ነው፡፡ ከውጭ ተቋማቱ መካከል አንዱ የሆነው የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽ እስካሁን ድረስ 690 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጓል፡፡

  የዚህ ድጋፍ አካል የሆነው ሦስተኛ ዙር የገንዘብ ድጋፍ ዓርብ ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. የተካሄደ ሲሆን፣ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴና በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ኦስማን ዲዮን በዕለቱ የድጋፍ ስምምነቱን ፈርመዋል፡፡ ባንኩ በሦስተኛ ዙር ድጋፉ በተለይ ለኮቪድ-19 ክትባት ግዥና ሥርጭት፣ እንዲሁም በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው ጤና ተቋማት ግንባታ የሚውል 195 ሚሊዮን ዶላር (10.1 ቢሊዮን ብር) ድጋፍ አድርጓል፡፡

  ቀጣናዊ ዳይሬክተሩ ኦስማን በፊርማው ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች በአጋር አካላት በኩል የክትባት ዘመቻ እያደረገች መሆኑን በመጥቀስ ለሚኒስቴሩ ምሥጋና ችረዋል፡፡

  ዳይሬክተሩ አክለውም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያለ ምንም ልዩነት የኮቪድ-19 ክትባት የማግኘታቸውን ጉዳይ አስምረው ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት፣ የክልል ቢሮዎችና የዕርዳታ ድርጅቶች ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሕክምና ዕድል የማግኘቱን ጉዳይ ዋና ግባቸው ሊሆን እንደሚገባ ተናግረው፣ ‹‹ጤና መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ በየትኛውም አካባቢ ቢሆን በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሁሉ ተገቢውን ትኩረት የሚሰጠው እንዲሆን ማሳሰብ እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

  የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ በበኩላቸው ዓለም ባንክ የሰጠው ሦስተኛ ዙር ድጋፍ ጠንካራ የድንገተኛ ጊዜ ምላሽ ሥርዓት ለመዘርጋት፣ ኮቪድ-19 ክትባትን ለማካሄድና የጤና ሥርዓቱን ለማጠናከር እንደሚውል ተናግረዋል፡፡ በዚህ ድጋፍ ለኮቪድ-19 ተጋላጭ የሆኑ በተለይም ጦርነት ያለበት አካባቢ የሚገኙና በጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች ትኩረት እንደሚሰጣቸው ገልጸው፣ ‹‹ትግራይን ጨምሮ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን ማዳረስ ላይ ትኩረት አድርገናል፤›› በማለት ወደ ትግራይ ክልል ክትባት መላኩን አስታውሰዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...

  የኬንያ ምርጫ ቀጣናዊ አንድምታው

  በዘመናት ውስጥ ሳይናወጥ መዝለቅ የቻለ ይሉታል አንዳንዶች፡፡ የአገሮቹ መሪዎች...