Tuesday, August 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ለሞጆ የተቀናጀ የቆዳ ኢንዱስትሪ ማዕከል ቃል የተገባ 700 ሚሊዮን ብር በመቅረቱ ፕሮጀክቱ ተስተጓጎለ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ከተጀመረ አሥር ዓመታት ያስቆጠረው የሞጆ የተቀናጀ የቆዳ ኢንዱስትሪ ማዕከል በ2014 ዓ.ም. ወደ ትግበራ ምዕራፍ እንደሚገባ ቢጠበቅም፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ከነበረው ጦርነት ጋር በተገናኘ ከአውሮፓ ኅብረት ቃል ተገብቶ የነበረ የ700 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ሊለቀቅ ባለመቻሉ ፕሮጀክቱን ማጠናቀቅ እንዳልተቻለ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

  ከ30 በላይ የቆዳ ፋብሪካዎችን በውስጡ አካቶ እንደሚይዝ የተነገረለትና በ200 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተገንብቶ የቆዳ ኢንዱስትሪ ማዕከል በመሆን እስከ 30 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል የተባለው ፕሮጀክት፣ ከበርካታ ዓመታት በኋላም ወደ ሥራ ለማስገባት አለመቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናግረዋል፡፡

  በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሸዋ ዞን ከአዲስ አበባ ከተማ 64 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሞጆ ከተማ የሚገኘው የተቀናጀ የቆዳ ኢንዱስትሪ ማዕከል፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) ጋር በመሆን የአዋጭነት ጥናቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማሠራት የተጀመረ ፕሮጀክት ነው፡፡

  ይህ የቆዳ ኢንዱስትሪ ዞን ነባሮቹን የቆዳ ፋብሪካዎችን ጨምሮ ወደ ሥራ የማስገባት ፕሮጀክት፣ በአፍሪካ ደረጃውን የጠበቀና ተምሳሌት የሆነ የቆዳ ኢንዱስትሪን በለጋሾችና በግሉ ጥምረት ትብብር ለመገንባት ያለመ ነበር፡፡

  ይሁን እንጅ አሁን ላይ ብዙዎቹ ፋብሪካዎች ተገንብተው ቢጠናቀቁም፣ የተገነቡትን ፋብሪካዎች ለማጠናቀቅ የቀሩና አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማሟላት ከአውሮፓ ኅብረት የድጋፍ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ቃል ተገብቶ የነበረ 700 ሚሊዮን ብር ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ ባለመለቀቁ ሥራው ወደፊት መሄድ እንዳልቻለ አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡

  አቶ መላኩ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን የአሥር ወራት ሥራ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ሲያቀርቡ፣ የሞጆ የተቀናጀ የቆዳ ኢንዱስትሪ ፕሮጀክት በጣም አስፈላጊና ወሳኝ፣ እንዲሁም የቆዳ ኢንዱስትሪን የበለጠ የሚደግፍ በመሆኑ፣ በቀጣይ ከለጋሾች ድጋፍ ከተገኘ በድጋፉ እንደሚሠራ፣ ካልሆነ ግን በመጪዎቹ ዓመታት በኢትዮጵያ መንግሥት በጀት ተይዞለት እንዲጠናቀቅ ይደረጋል ብለዋል፡፡

  ፕሮጀክቱ በዓይነቱ ልዩና ግዙፍ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ዘመናዊ የተረፈ ምርት አወጋገድ ልማት፣ የቤቶች ግንባታ፣ የቆዳ ኢንስቲትዩቶች፣ የኬሚካልና የጫማ ፋብሪካዎች፣ የመንገድ፣ አሁን በሥራ ያሉትን የቆዳ ልማት ፋብሪካዎችን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶችን ያቀፈ ነው፡፡ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በእንስሳት ሀብት ቀዳሚ የምትባልበትን ሀብት ወደ ተግባር በመቀየር፣ ከዘርፉ በቂ ምርት ማምረት የሚቻልበትን ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እንደሆነ ተገልጿል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች