Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገርአገር ለምን ያስፈልጋል?

  አገር ለምን ያስፈልጋል?

  ቀን:

  በአንድነት ኃይሉ

  አገር ለሰው ልጅ ለበርካታ ምክንያቶች ያስፈልጋል፡፡ አገር በዋናነት የሚያስፈልገው በነፃነት ለመኖር ብቻ ሳይሆን በነፃነት ለማሰብም ነው፡፡ በነፃነት የትም መኖር ይታይ ይሆናል፡፡ በነፃነት ማሰብ የሚቻለው በአገር ብቻ ነው፡፡ ዓለም የግለሰቦች የሐሳብ ውጤት ነች፣ ሰውም የገዛ ሐሳቡ ውጤት ነው፡፡ በነፃነት እንዲኖር እንጂ  በነፃነት እንዳያስብ ያልተፈቀደለት ወይም የማይችል ሰው ሙሉ ሰው ነው ማለት አይቻልም፡፡ ማንም ሰው ሙሉ የሚሆነው አገር ሲኖረው ነው፡፡

  አገር ማለት ሰውና ምድር፣ ሰውና ሰው ተግባብተውና ተዋህደው የሚያቆሙት የሥራቸው ውጤት ነው፡፡ አንድ ሰው ሙሉ አካል ስላለው ብቻ ሙሉ ነው አንለውም፡፡ ዕውቀቱን የሚገልጽበት፣ መብቱን የሚያስጠብቅበት፣ የጎደለውን የሚያሟላበት፣ ያለውን የሚያካፍልብትና የሚገለገልበት፣ ወዘተ. አገር ያስፈልገዋል፡፡ አገር በሰዎች ውስጥ ያለውን ልዩነት በማጣጣም በሥራ ላይ ማዋል እንዲቻል የሚያስችል ብቸኛው መንገድ ነው፡፡ የሚገርመው የትኛውም ምድር ለሰው ልጅ አገር መሆን ይችላል፡፡ በተቃራኒ ግን ማንኛውም ሰው ራሱንም ምድርንም አገር ማድረግ አይችልም፡፡ ራሱንም ምድርንም አገር ማድረግ የሚችል ሰው በውስጡ ሐሳብ ያለው ነው፡፡ ሐሳብ ያለው ሰው ሥራ አለው፡፡ ለሥራው ደግሞ ግብዓቱ ሰውና ምድር ነው፡፡ ስለዚህ ሰውና ምድርን አጥብቆ ይፈልጋቸዋል፣ አጣጥሞም አገር ያደርጋቸዋል፡፡

  አገር ያለ ምድርና ሰው ዕውን መሆን አይችልም፡፡ አገር የሚሠራው በሰውና በምድር ላይ ነው፡፡ ምድር ሆኖ አገርን ለመሥራት ግብዓት መሆን የማይችል ባይኖርም፣ ሰው ሆኖ ግን አገርን ለመሥራት ግብዓት መሆን የማይችል አለ፡፡ ይህ ሰው ሐሳብ የለውም፡፡ ሐሳብ ስለሌለው ሥራ የለውም፣ ሥራ ስለሌለው አገር አይፈልግም፣ ወይም የአገርን ጥቅም አያውቅም፡፡

  እንኳን አገር ቤት እንኳን ያለ ሐሳብና ግብዓት አይቆምም፡፡ አገርን ለማቆም ልዩነት አንዱ ግብዓት ነው፡፡ ምክንያቱም አገር ለሰው ልጅ የሚያስፈልግበት ምክንያት ልዩነቱን ለማጣጣም ነው፡፡ የሰው ልጅ አገር በሚል ድንቅ ሐሳብ ልዩነቱን አጣጥሞና አቻችሎ ባይኖር ኖሮ ዓለም እዚህ ጋር አትደርስም ነበር፡፡

   የሰው ልጅ ግራና ቀኙ ወይም እጁና እግሩ የተጣጣመው አካል እንደሆኑት ሁሉ፣ የትኛውም የሰው ልጅ ልዩነቱን እንደጠበቀ አገር በሚበል ጥላ ሥር መሰባሰብ ባይችል ኖሮ ልዩነት ያጠፋው ነበር፡፡

   የሰው ልጅ ቀኝና ግራ እግሩን አጣጥሞ ነው የሚኖረው የተለያዩ በመሆናቸው ተጠቃሚ ነው፡፡ ቀኝ እግር ስላለው ግራውን የሚጠላ፣ እጅ ስላለው እግሩን የሚጠላ የለም፡፡ ቀኝና ግራውን እጅና እግሩን በማጣጣሙ ሙሉ ሰው ሆኖ ይኖራል፡፡ ልዩነትን  ይዞ አገር የለም፡፡ አገር የሚኖረው፣ አገር የሚያስፈልገው ወይም የሚወለደው፣ ልዩነትን ለማጣጣም ነው፡፡

  የለየለት ልዩነት ውስጥ ሰላም ሊኖር አይችልም፡፡ የተጣጣመ ልዩነት ውስጥ ግን ሰላም ይኖራል፡፡ ድሮ ዓለም ጥርት ባለ ልዩነት ውስጥ በነበረችበት ጊዜ ምን ያህል ዋጋ ተከፍሎ እንደነበር ታሪክ ይናገራል፡፡ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በምንም ዓይነት ደረጃ ላይ ያለውን መጣጣም መጠበቅ ካልቻልን ዋጋ ሊያስከፍለን እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡

  የሰው ልጅ ሁሉ አንድ ዓይነት ሐሳብና ፍላጎት ሊኖረውም አይችልም፡፡ ነገር ግን አገር በሚል ድንቅ ጥበብ ልዩነቶች ሁሉ ሀብት ይሆናሉ፡፡ በምድር ላይ ያለውን ልዩነት ለማጣጣምና ትክክል ለማድረግ አገርን መሥራት ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ በሰዎች መሀል ያለ ልዩነት በድንበር፣ በባንዲራ፣ በገንዘብ፣ በሕግ፣ በግብይት፣ ወዘተ. ይጣጣማል፡፡

   በአንድ አገር ውስጥ ስንት ድንበር ያስፈልጋል የሚለውን ለባለሙያዎች ብተወውም፣ ልዩነትን ለማጣጣም ግን የጋራ ድንበር አስፈላጊ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡

   ሁሉም አፍሪካዊ የምናውቀውን ድንበር ሠርቶት ሳይሆን፣ ተሠርቶለት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ እናንተ ኢትዮጵያውያን፣ ሱዳናውያን፣ ኬንያውያን፣ ወዘተ. ተባልን እንጂ አገሩን በዕውቀቱና በሐሳቡ ልክ የሠራ አፍሪካዊ ሕዝብ የለም፡፡ በእርግጥ አካለው ከጨረሱ በኋላ በልምራህ ተመራ፣ አትመራኝም ልዩነቶች በአገራችን በርካታ ታሪኮችን አሳልፈናል፡፡ ሁሉንም ታሪኮች ለታሪክ አዋቂዎች ልተወውና በየትኛውም ታሪክ ውስጥ የለፋች አገራችንን ማስቀጠል ግን፣ ማንም ለማንም ሲል የሚያደርገው ሳይሆን ሁሉም ለራሱ ሲል የሚያደርገው ነው፡፡

  ዛሬ ሐሳብ ያለውና ሐሳብ የሌለው ሰው አገርን የተረዳበትና የሚፈልግበት መንገድ እጅግ የተወሳሰበ ነው፡፡ ምክንያቱም ገንዘብ ኃያል ሆኗል፡፡ ገንዘብ ካለ አገር የትም አለ፡፡ ገንዘብ ካለ ፖለቲከኛ መሆን ይቻላል፡፡ ዛሬ ገንዘብ ያለው ሁሉ ፖለቲከኛ መሆንም፣ ማንንም ፖለቲከኛ ማድረግ የተቻለበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ገንዘብ ግብዓቱ የሆነ ፖለቲከኛ ለአገር ያለው ትርጉም ምንም ነው፡፡ የራሱ ሐሳብ ያለው ፖለቲከኛ ደግሞ አገር ማለት ግብዓቱ ነው፡፡

   አገር ግብዓቱ የሆነ ፖለቲከኛ በሰዎች ውስጥ ያለውን የትኛውንም ሀብት ይጠቀማል እንጂ አያባክንም፡፡ ቤት ለመሥራ የተነሳ ገበሬ ጭዱን እንኳን ሊሸጠው ለበሬው ይሰስታል፡፡ ትክክለኛ ፖለቲከኛ አገር የሆነን ምድርንና ሰውን ለመሥራት፣ እንኳን ለወገኑ ጠላት ሊመራበት የተጣመመን ታሪክ እንኳን ለማቃናት ነው የሚተጋው፡፡ ምክንያቱም አገርን ለመሥራት በቀላሉ ግብዓት የሚሆነውን የሰው ልጅ በየትኛውም ምክንያት ሊያባክን አይፈልግም፡፡ ሐሳብ የሌለው ፖለቲከኛ ደግሞ ሥራ ስለሌለው ግብዓት አያስፈልገውም፡፡ ስለዚህ ለወገኑ ጠላት አበጅቶ ይኖርበታል እንጂ፣ አገር የሆነን ሰውና ምድርን አጣጥሞ ሰላሙን አይሰጠውም፡፡

   አገር የሚያስፈልገው ልዩነት ስላለ ነው፡፡ አንዱ ባለው ነገር ተጠቃሚ ሲሆን ሌላው የጎደለውን ነገር በቀላሉ ማግኘት እንዲችል፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያን ምድራዊ ልዩነት ስንመለከት፣ የፈጠራት ፈጣሪ ስለሆነ ልዩነቱ የሚጣፍጥና ሕይወት ያለው ነው፡፡ ሁለት ምሳሌዎችን ብናይ  በአፍዴራ ያለው ጨው የሚጣፍጠው በሌላ ኢትዮጵያዊ ጫፍ አለመኖሩ ነው፡፡ የሆነ ክልል ሙሉ ለሙሉ ለምና እርጥብ ቢሆን፣ የሚያጣፍጠው የሆነ አካላችን ደረቅና በማዕድን ወይም በሰው ሀብት የበለፀገ ሲሆን ነው፡፡ አለበለዚያ ሁሉም ለምና እርጥብ ቢሆን ሀብቱ ሀብት ሳይሆን ጭቃና ዕዳ ይሆንብን ነበር፡፡

   አገር የሚጥመው በልዩነት ሲሠራ፣ ልዩነት ፍትሐዊ የሚሆነው በግብይት ሲደገፍ ነው፡፡ ልዩነት ለግብይት የቀረበ ከሆነ አገር ዜጎቿን የሥራ ባለቤት ማድረግ ትችላለች፡፡ ልዩነት አገርን እንደ አገር ግብይትን እንደ ግብይት መጣጣም ሲፈጥር ዘላቂ ሰላምና ትልቅ አገር ይሰጠናል፡፡ የሰው ልጅ አገርን በትክክለኛ መንገድ ሲረዳና ሲሠራ ብቻ ነው ያለውን ነገር በትክክል መጠቀም የሚችለው፡፡ ተፈጥሮውን፣ ዕውቀቱን፣ ጉልበቱን፣ ገንዘቡን፣ ሰውን፣ ወዘተ. ሳይባክንበት መጠቀም የሚፈልግ ሕዝብ ልዩነቱን ተጠቅሞ አገር ለመሥራት ዋስትና ነው፡፡ ግለሰብ ማኅበረሰብ ወይም ሕዝብ ተስማምቶ አንድ አገር አንድ አካል መሆን የሚችለው አንድ ዓይነት ነገር ስላለው ሳይሆን፣ የተለያዩ ነገር ሲኖረው ነው፡፡

   አገር ለማንም ተብሎ የሚሠራ፣ ማንንም የሚጎዳ፣ በተለየ ማንንም የሚጠቅም አይደለም፡፡ ሰው ስለሆንክ ብቻ አገር ያስፈልግሃል፡፡ አገርን ሠርቶ ሰፊ የሆነ የግብይት ምርጫ መፍጠር ማንንም አይጎዳም፡፡ አገር ሆኖ ሰፊ የሆነ የሥራ ዕድልና በቀላሉ መጠቀም የምንችልበትን ግብይት መፍጠር ማንንም ተጎጂ አያደርግም፡፡ አገር ሆኖ የጋራ የሆነ መገበያያ ገንዘብ፣ የጋራ ድንበር፣ የጋራ ገበያ ባለቤት መሆን ማንንም አይጎዳም፡፡ ምናልባት ተጎጂ ሊሆን የሚችለው ሐሳብ የሌለው ፖለቲከኛ ብቻ ነው፡፡

   በየትኛውም መሥፈርት ተራው ሕዝብ ትልቅ አገር፣ ሰፊ ገበያና ግብይት፣ ባለ ብዙ ምርጫና መደረሻ ሲኖረው ተጎጂ አይደለም፡፡ ለእውነተኛ መሪ አገር ማለት ትርጉሙ ብዙ ነው፡፡ እውነተኛ መሪ ሕዝብን የሚፈልገው አገርን የሚሠራው ሕይወቱ ስለሆነ ነው፡፡ ሕዝብና አገርን ካልሠራ መኖር ስለማይችል አገርን መሥራት ምግብና መጠጡ ነው፣ ከዚህ ውጪ መኖር አይችልም፡፡ ለእውነተኛ መሪ እንኳን የሰው ልጅ ሕይወት የሌለውን ድንጋይ አገርንና ሕዝብን ለመሥራት እንደሚያስፈልገው ያውቃል፡፡  ሰው ሆኖ የሚያበላልጠው ተፈጥሮ ሆኖ የሚንቀው የለም፣ ሁሉም ግብዓቱ ነው፡፡

   በዓለም ላይ ያለ ሰው የሚያመሳስለው የሚሊያየውና ነገር አለ፡፡ በሚያለያየው ተከባብሮ፣ በሚያመሳስለው ተግባብቶ ይኖራል፡፡ የሰው ልጅ በሚያለያየው ነገር ላይ ብቻ ቢያተኩር ኖሮ፣ እንኳን አገር ቤተሰብ አይኖርም ነበር፡፡ ሕይወቱ በሙሉ በግጭት የተሞላ ይሆን ነበር፡፡ ማንም የየትኛውም ቋንቋ ባለቤት ቢሆን፣ ከሰው የተለየ ፍላጎትና አካል የለውም፡፡ እንዲሁም ማንም የትኛውንም ቋንቋ ወይም ልዩነት ቢኖረው ያለ ሥራ፣ ያለ ግብይት፣ ያለ ገንዘብ፣ ያለ ሕግ፣ ወዘተ. ከማንም ጋር ተግባብቶ መኖር አይችልም፡፡

   ማንም ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ ከሁሉም ጋር በዕውቀቱና በፍላጎቱ እኩል ነው፡፡ የሰው ልጅ የትኛውንም ዓይነት ልዩነት ቢኖረው ገንዘብና ግብይትን በሥራ ላይ ማዋል ባይችል ኖሮ፣ ልዩነት ሚዛኑን እንደጠበቀ ከትውልድ ወደ ትውልድ አይሸጋገርም ነበር፡፡ የትኛውም ዓይነት ግብይት ልዩነትን መሠረት ያደረገ ሳይሆን የጋራ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

   የዓለም ሕዝብ በሙሉ እየተገበያየ ዓለምን ለዚህ ያደረሳት ሁሉም ለራሱ ሲል ነው፡፡ አገር የሚያስፈልገን አንድ ዓይነት ቋንቋ ስላለን አይደለም፡፡ የተለያየ ቋንቋ ስላለንም ሁለት አገር አያስፈልገንም፡፡ ምክንያቱም ቋንቋ ዕውቀት አይደለምና፡፡ አገር የሚያስፈልገን  ከሰው ልጅ ሁሉ እኩል የሆነ ዕውቀና ፍላጎት ስላለን ሥራና ግብይት ስለሚያስፈልገን ነው፡፡

   የሰው ልጅ  በባህሪው ትልቅ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ገበሬው እንዲያርስ፣ አምራቹ እንዲያመርት ምክንያት የሚሆነው ሰው ነው፡፡ ይህን ሰው አገር አድርጎ ሀብት ማድረግ፣ አንድ ሰው ለሌላ ሰው ለመኖር ምክንያት ወይም ግብዓት ማድረግ፣ ጤናማ አገር እንዲኖረን ያስችላል፡፡

   የሰው ልጅ በተፈጥሮ ምንም ጠላት የለውም፡፡ የገዛ ራሱም ሆነ ሌሎችን የሚያይበት መንገድ ግን ፍላጎቱን ይወስናል፡፡ ጤናማ ከሆነ ሁሉንም ለመረዳት ብዙ ምክንያቶች ይኖሩታል፡፡ ጤናማ ካልሆነ ሁሉንም ለመጥላት ብዙ ምክንቶች ይኖሩታል፡፡ ዛሬ አገርን የሚጠላ፣ ብሔርን የሚጠላ፣ መሪን የሚጠላ፣ ሃይማኖቱን የሚጠላ፣ ትውልድ ምክንያቱ ዕይታው ነው፡፡ ማንም ሰው እጅ ስላለው እግሩን አይጠላም፣ እግር ስላለው እጁን አይጠላም፡፡ እጅም በእጅነቱ፣ እግርም በእግርነቱ፣ ሁሉንም በአንድ አካልነታቸው እንደ አፈጣጠራቸው ይጠቀምባቸዋል፡፡  

   ሰው በሰው ውስጥ ያለውን ቋንቋ፣ ዕውቀትና ፍላጎት አጣጥሞና አገር አድርጎ፣ ሥራና ገንዘብ ግብይትና ሕይወት አድርጎ ይጠቀምባቸዋል እንጂ እንዴት አንዱ አንዱን  ጠላት ያደርገዋል? አገር የሚያስፈልገው ቋንቋን ተጠቃሚ ለማድረግ ሳይሆን፣  ዕውቀትና ፍላጎትን ተጠቃሚ ለማድረግና ግብይትን ለማስገኘት ነው፡፡ የትኛውም ቋንቋ፣ የትኛውም ተፈጥሮ፣ የትኛውንም ዕውቀት ቢኖረው ግብይት መፍጠር ካልቻለ ጠፊ ነው፡፡  ግብይት ሙሉና አስተማማኝ የሚሆነው አገርን መሥራት ሲቻል ነው፡፡ ቻይና እዚህ የደረሰችው ጠንካራ ሕዝብ ስላላት ብቻ ሳይሆን፣ ከደሃ አገሮች ጋር ጠንካራ ግብይትን መፍጠር ስለቻለች ነው፡፡

   ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው hailuandinet75@gmial.com ማግኘት ይቻላል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...