Sunday, August 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገር‹‹አካባቢያዊነት ለተጫጫናቸው ባንኮቻችን›› ማን ጠያቂ ማንስ ነው ተጠያቂ መሆን ያለበት?

  ‹‹አካባቢያዊነት ለተጫጫናቸው ባንኮቻችን›› ማን ጠያቂ ማንስ ነው ተጠያቂ መሆን ያለበት?

  ቀን:

  በእስጢፋኖስ ስሜ

  ሰሞኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ባንኮችና የበላይ አመራሮች ጠንከር ያለ ትዕዛዝ፣ ማስጠንቀቂያ፣ ወይም ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡ ይህንን የተለያዩ ሚዲያዎች ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ሲዘግቡት ሰለነበር፣ እንደ አዲስ መረጃ አሥር ጊዜ የሰማችሁትን ለአሥራ አንደኛ ጊዜ ልደግምላችሁ አይደለም፡፡

  የገዥው ማስጠንቀቂያ በአጭሩ በጎሳ፣ በብሔር፣ በአካባቢ፣ በሃይማኖት በሚመስል አደረጃጀት ተደራጅቶ የባንክ አገልግሎት መስጠት አይቻልም ነው፡፡ ያስጠይቃል የሚል ነው፡፡ በእውነቱ ማስጠንቀቂያው ተገቢነት ያለው፣ ለጤናማ የንግድ ውድድር፣ ለተሻለ የባንክ አግልግሎት አቅርቦት፣ ለኢንዱስትሪው ዘላቂነት፣ በተለይም የአገሪቱን ሀብት ሁሉም ዜጋ ባለው ችሎታ፣ ተግባርና አቅም መሠረት እንዲጠቀምና ከበይ ተመልካችነት ከፋይናንስ ማዕዱ ተቋዳሽነት ለመሻገር ወሳኝ ነው፡፡

  እኔም በግሌ እንደ ባንክ ባለሙያነቴና በዘርፉም እንደቆየ ከዚህ ቀደም በዚሁ ጋዜጣ ከአንድ ዓመት በፊት፣ ‹‹አካባቢያዊነት የተጫጫናቸው ባንኮቻችን›› በሚል ርዕስ የብሔር፣ የጎሳ፣ የአካባቢ፣ የሃይማኖት ገጽታ ይዘው በሥራ ላይ ስላሉት፣ እንዲሁም አዳዲስ በመደራጀት ላይ ስለነበሩ ባንኮቻችን አግባብነትና ተገቢነት ላይ ገዥ ባንኩን ለመሞገት ሞክሬያለሁ፡፡

  ምንም ጥናት ወይም ጥልቅ ትንተና ሳያስፈልግው በዚህ መልክ የተደራጁና የሚደራጁ ባንኮች በዋናነት በንግድ አዋጪነት ወይም በኢንዱስትሪው ሳቢነት ተስበው ሳይሆን፣ በአገራችን በነበረው አሁንም ባልለቀቀው የብሔር ፖለቲካ ተጎትተው  የተደራጁ ናቸው ማለት ለፍፁምነት የተጠጋ እውነታ ነው፡፡ ‹‹እኛም አለን ባንክ›› የሚል ብሽሽቅና ይህንን በመመለስ እርካታን ለማግኘት፣ እንዲሁም ፖለቲካውን ለመቆጣጠር፣ አሊያም ተገዳዳሪ ለመሆን ፋይናንሱን መቆጣጠር ከሚል ፍፁም ፖለቲካዊ ከሆነ አስተሳሰብ የመነጩ ናቸው፡፡

  በዚህ ጽሑፌ አስረግጬ መሞገት የፈለግኩት ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ማን ነው? ኃለፊነት መውሰድስ ያለበት አካል ማን ነው? ማን ጠያቂ ማንስ ነው ተጠያቂ መሆን ያለበት?

  ለእኔ ተጠያቂው ዓይኑን በጨው አጥቦ ጠያቂ ሆኖ ነው ያገኘሁት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ገዥዎቹ በዚህ ድምፀት ወጥተው የመናገር የሞራል ልዕልና ሊኖራቸው አይችልም፡፡ 

  በብሔር፣ በሃይማኖትና በሌሎችም መሰል አደረጃጀቶች አድልኦ አድርጎ የባንክ አገልግሎት፣ በተለይም የብድርና የውጭ ምንዛሪ አገልገሎቶችን መስጠት አልታገስም ማለት ማን ሆነና ነው ፈቃድ ሰጪው? ፈቃድ ሰጥቶ ካበቁ በኋላ ‹‹ዋ››ን ምን አመጣው? ይቻላልንስ?

  ከፖለቲካ ለውጡ በፊትም ሆነ በኋላ አንዳንዶች በግልጽ የአንድን ብሔርን ስም የባንክ ስያሜ አድርገው፣ አንዳንዶች ደግሞ ስያሜውን ትተው በተግባር በብሔር ሲደራጁ የባንክ አገልግሎት ፈቃድ የሰጠው ገዥው ባንክ አይደለም እንዴ? ምን የሚሉት ሞራል ነው አሁን ደርሶ ከአንገት በላይ ማልቀስ?

  ጠያቂውን መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ ፈቃድ በብሔር ስም ሰጥቶ አክሲዮን እንዲሸጡ ከፈቀዱ በኋላ የፖለቲካ ግለቱ ያጋለው በብሔሬ ስም ባንክ ሊመጣልኝ ነው ብሎ አክሲዮን በብዛት እንደሚገዛ፣ የዚያም ባንክ የአክሲዮን ድርሻ በቁጥርም ሆነ በገንዘብ መጠን በብሔሩ ተወላጆች እንደሚያዝ የታወቀ ነው፡፡ የመደራጀት ሒደቱንም ጨርሶ ወደ ገበያው ሲገባም የባንኩ ደንበኞች በአብዛኛው የዚያ ብሔር ተወላጆች እንደሚሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

  ታዲያ እንደ እነዚህ ያሉ ባንኮችንና አመራሮቻቸውን ለአንድ ብሔር አድልኦ አድርጋችሁ ብድር (የውጭ ምንዛሪ) ሰጥታችኋል ብሎ መጠየቅ እንዴት ይቻላል? ለደንበኞቻቸው ካልሰጡት ለማን ሊሰጡት ነው?

  የዚህ ችግር መነሻ ባንኮቹ ሲዳራጁ በዚያ መልክ እንዲደራጁ ፈቃድ ሲሰጣቸው ነው፡፡ ለዚህም በዋናነት ተጠያቂው አሁን ጠያቂ ሆኖ የሚያስጠነቅቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነው ባይ ነኝ፡፡

  ምነው በጨዋ ደንብ አንዳንድ ባንኮች ሲቋቋሙ በዚህ መልክ እንዲሆኑ ፈቃድ መስጠቴ ከባድ ስህተት ሠርቻለሁ፡፡ አሁን ግን ስህተቴን ለማረም ለመሥራት ተዘጋጅቻለሁ ቢል ጨዋነት ይሆን ነበር፡፡ ነገር ግን አልሰማሁም አለ፡፡ ያውም ‹‹ከደሙ ንፁህ ነኝ›› በሚል እጅ ታጥቦ መቅረቡ ግን ያስተዛዝባል፡፡

  ነገሬን ስቋጭ ገዥው ባንክ የአፍ ወለምታ ሳይሆን የእውነት ይህንን ችግር ለመፍታት ተነስቶ ከሆነ መልካም ነው፣ ተገቢ ነው፣ ኃላፊነቱም ጭምር ነው፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የባንክ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው estifanos.sime@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...