በቅድመ ሰው ዘር ጥናት ሁነኛ ቦታ ያላትን የሉሲ ቅሪተ አካልን ከአርባ ሰባት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ካገኙት የቅሪተ አካል ተመራማሪዎች አንዱ የነበሩት ፈረንሳዊው ኢቭ ኮፐንስ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ታውቋል፡፡ለ ሞንድ የተባለው የአገሬው ሚዲያ እንደዘገበው የፓሊዮንቶሎጂ ባለሙያው ኢቭ ኮፐንስ በ87 ዓመታቸው ያረፉት ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. መሆኑን ባለፈው ግንቦት ትውስታቸውን ያሳተመው ተቋም ቤተሰቡን ወክሎ አስታውቋል።በሳይንሳዊ ስሟ ‹‹አውስትራሎፒቲከስ አፋራንሲስ›› በመባል የምትታወቀውና የ3.2 ሚሊዮን ዓመት ባለዕድሜዋ ሉሲ ኅዳር 15 ቀን 1967 ዓ.ም. በአፋር አዋሽ ወንዝ አቅራቢያ ሀዳር በተሰኘ ቦታ ቅሪተ አካሏን ያገኙት፣ ኢቭ ኮፐንስን ጨምሮ አሜሪካዊው ዶናልድ ጆሃንሰን እና ሌላኛው ፈረንሳዊ ሞሪስ ታይብ (ባለፈው ሐምሌ ወር አርፈዋል) ናቸው፡፡ሦስቱ ተመራማሪዎች አንድ ሜትር ከ10 ሳንቲ ሜትር ቁመት የነበረውንና 40 በመቶውን አካል የሚሸፍኑ ቁርጥራጭ አብረው የተገኙላትን ቅሪተ አካሏን ካገኙ ከሰዓታት በኋላ ምሽት ላይ አረፍ ብለው ካዳመጡት፣ የ1960ዎቹ የቢትልሶች ዘፈን ‹‹Lucy in the Sky with Diamond›› (በግርድፉ ሲመለስ ሉሲ ባለአልማዛዊው ሰማይ) ለቅሪተ አካሏ መስጠታቸው ይታወቃል፡፡ዜና ዕረፍታቸውን ተከትሎም፣ ‹‹በሞሪስ ታይብ እና ኢቭ ኮፐንስ ሞት ገጸ ታሪካችን ተለወጠ። ኢቭ ኮፐንስን እንደ ካሚል አራምቡርግ ወይም ሉዊስ ሊኪ ካሉ የአፍሪካ ፈር ቀዳጅ ፓሊዮንቶሎጂዎች ጋር አገናኝ ድልድይ ነበር፤›› ሲሉ የተፈጥሮ ታሪክ ብሔራዊ ሙዚየም የፓሊዮአንትሮፖሎጂስት ብሪጊት ሴኑት ለ ለ ሞንድ ተናግረዋል፡፡የሉሲ ቅሪተ አካል አምሳል (ቅጂ) የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ለተባበሩት መንግሥታት የባህል ተቋም ዩኔስኮ ከዓመት በፊት ማበርከቱ ይታወሳል፡፡
በፈረንሣይ መዲና ፓሪስ በሚገኘው የዩኔስኮ መንበር የሉሲን ቅሪተ አካል ለዋና ዳይሬክተር ኦውድሬ አዙላይ ያስረከቡት በፈረንሣይ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አቶ ሔኖክ ተፈራ ሻውል ባስረከቡበት ጊዜ ኢቭ ኩፐንስ ከዶናልድ ጆንሰን ጋር መገኘታቸው ይታወሳል፡፡
አምባሳደር አቶ ሔኖክ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት የሐዘን መግለጫ መልዕክታቸው፡- ‹‹በአገራችን የሉሲ ወይም ድንቅነሽ አጽም ካገኙት ተመራማሪዎች መካከል አንዱ የነበሩት ታዋቂው ፈረንሳዊና የአገራችን ወዳጅ፣ ኢቭ ኮፐንስ፣ ሕልፈተ ሕይወት ትልቅ ሐዘን ተሰምቶናል፤›› ብለዋል፡፡