Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ከጀግኖቹ አትሌቶቻችን እንማር!

  ሰሞኑን በአሜሪካ ኦሪገን እየተካሄደ ባለው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ጀግኖቹ የኢትዮጵያ አትሌቶች ላስመዘገቡት አንፀባራቂ ድል፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በአንድነት ደስታውን እየገለጸ ነው፡፡ ለበርካታ ዓመታት ኢትዮጵያ በተለያዩ ችግሮችና መከራዎች አንገቷን ስትደፋ፣ በተለያዩ ትውልዶች ውስጥ ያለፉ ጀግኖች አትሌቶች ቀና እንድትል ከፍተኛ መስዋዕትነት ሲከፍሉ ኖረዋል፡፡ ከጀግናው ሻምበል አበበ ቢቂላ እስከ አዲሲቱ የኦሪገን ጀግና ጎቲይቶም ገብረ ሥላሴ ድረስ፣ በርካቶች አገራቸውን ከወርቅ እስከ ነሃስ ሜዳሊያ በማንቆጥቆጥ ታሪክ ሠርተዋል፡፡ ወደፊትም አዳዲስ ጀግኖች በእግራቸው እየተተኩ የጀግንነት ታሪኩን ያስቀጥላሉ፡፡ በቅርቡ በወለጋ ዞኖች ውስጥ በተፈጸሙ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጭፍጨፋዎች ብዙዎች ልባቸው ቢሰበርም፣ ኢትዮጵያ በዓለም የስፖርት አደባባይ በጀግኖች ልጆቿ እንደኮራችው ሁሉ የሰሞነኛውን አሳዛኝ ገጽታም መለወጥ ይቻላል፡፡ ለአገራቸው ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን ብቻ ሳይሆን ሕይወታቸውን ከመስጠት ወደኋላ የማይሉ ጀግኖች እንዳሉ መዘንጋት አይገባም፡፡ ኢትዮጵያን ለታሪካዊ ጠላቶቿ ከሚያጋልጧት እኩይ ድርጊቶች በመታቀብ ለህልውናዋ በጋራ መቆም የሚቻለው፣ በመናኛ ሐሳቦች የተከፋፈሉ ልቦችን ወደ ጠንካራ አንድነት በማምጣት መሆኑን ከጀግኖቹ አትሌቶቻችን መማር ይገባል፡፡ 

  በአገሩ ህልውና የማይደራደረው ኩሩውና አስተዋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ መከበር አለበት፡፡ ይህ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ወንድሞቹ ታላቅ አርዓያ የሆነ ሕዝብ በገዛ አገሩ በክብር መኖር ይገባዋል፡፡ የሚወዳት አገሩ ሰላም ሰፍኖባት በዕድገት ጎዳና መራመድ የምትችለው፣ ትውልድ በነፃነት እየኖረባት ሲቀጥል ነው፡፡ የትውልድ ቅብብሎሹ ውጤታማ ሆኖ ከከፍታው ማማ መድረስ የሚቻለው ደግሞ አገር በሕግ የበላይነት ሥር ስትመራ ነው፡፡ በሕዝብ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ መንግሥት ኃላፊነትም ይህ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ማንም እየተነሳ ጉልበተኛ ሲሆን፣ የአገር ሀብት ሲዘርፍ፣ ሕዝብን እያጋጨ ደም ሲያፈስና አገርን መከራ ውስጥ ሲጥል ዝም ማለት በትውልድም በታሪክም ያስጠይቃል፡፡ ሕዝብ በመንግሥት ውሳኔዎች ላይ ያለው ተሳትፎ ወደ ጎን እየተገፋ፣ ግለሰቦችና ቡድኖች የሚያብጡበት ሥርዓት አገር ያጠፋል፡፡ በሕዝብ ስም እየተነገደ ከፍላጎቱ በተቃራኒ መንጎድ ለበለጠ ትርምስ በር ይከፍታል፡፡ የተበላሸውን የፖለቲካ ምኅዳር አስተካክሎ ለአገር አንድነት በጋራ መሥራት ያስከብራል፡፡ አገርም ትውልድም በዘለቄታዊነት መቀጠል የሚችሉት በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ መንግሥትም ሆነ ተፎካካሪዎቹና የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ፣ አገርን ከሚከፋፍል አስተሳሰብ ለመላቀቅ ከጀግኖቹ አትሌቶቻችን ይማሩ፡፡

  በአሁኑ ጊዜ ከኅብረተሰቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው የመንግሥት መዋቅር በብልሹ አሠራርና በከፋ የሥነ ምግባር ችግር የተጠቃ ሲሆን፣ ከፍተኛ የሆነ የብቃት ችግርም አለበት፡፡ በከተሞች ውስጥም ሆነ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ ደካማ መዋቅሮች ውስጥ የተሰገሰገው ኃይል ፀድቶ፣ በብቃታቸውና በሥነ ምግባራቸው ምሥጉን በሆኑ ዜጎች መተካት ይኖርበታል፡፡ ለዚህም ሲባል አስፈላጊው ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ በፌዴራል ደረጃ፣ በክልሎች፣ በዞኖች፣ በወረዳዎችና በከተማ አስተዳደሮች ውስጥ በፓርቲ አባልነትና ታማኝነት መሥፈርት ተደላድሎ የተቀመጠው ብቃት አልባ ኃይል ለመልካም አስተዳደር መጥፋት፣ ለፍትሕ መጓደል፣ ለሕገወጥ ድርጊቶች መበራከትና በአጠቃላይ ለዜጎች ምሬት ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ ግብር ከፋዩ ሕዝብ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዳያገኝ በማድረግ፣ የወጣቶች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዳይኖር መሰናክል በመፍጠር፣ ብልሹ አሠራሮችን በማስፋፋት፣ ሐሰተኛ ሪፖርቶች በመፈብረክ የተሳሳቱ መረጃዎች በማቅረብ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን በመጣስ፣ የሕግ የበላይነትን በመጋፋትና በመሳሰሉት ሕዝብን በማስመረር ወደር የሌለው ይህ ከንቱ ኃይል ከቢሮክራሲው ውስጥ መውጣት አለበት፡፡ ጀግኖቹ አትሌቶቻችን የሚያኮሩን በብቃታቸው ብቻ እንደሆነ ይታወቅ፡፡

  በቁጭት፣ በእልህ፣ በንዴት፣ በቂም በቀል፣ በጥላቻና በመሳሰሉት ለአገር የማይጠቅሙ አረንቋዎች ውስጥ ሆኖ ስለዴሞክራሲም ሆነ ስለዕድገት መነጋገር አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታጋሽ፣ ጨዋ፣ ኩሩና አርቆ አሳቢ በመሆኑ ይህንን አኩሪ የጋራ እሴት ለሚመጥን ፖለቲካዊ ግንኙነት መዘጋጀት የሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ኃላፊነት ነው፡፡ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ የሚሆንበት ኋላቀር አስተሳሰብና ጀብደኝነት ሳይሆን፣ በመርህ ላይ የተመሠረተ ውይይትና ድርድር ለአገር እንደሚበጅ መቼም ቢሆን መዘንጋት የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ ለሁሉም ልጆቿ እኩል እናት እንድትሆን ከተፈለገ፣ ሁሉም ልጆቿ ያለ ምንም አድልኦ የሚሳተፉበት ዴሞክራሲያዊ ዓውድ መፈጠር አለበት፡፡ ይህ በተግባር ይረጋገጥ ዘንድ ደግሞ መጀመርያ ከጀብደኛ ድርጊቶች መታቀብ፣ ለሕግ የበላይነት መገዛት፣ ከሕገወጥ ድርጊቶች መራቅ፣ የዴሞክራሲን እሴቶች ማክበር፣ ለሥልጣን የሚደረገው ትንቅንቅ ከአገርና ከሕዝብ ህልውና እንደማይበልጥ ማመን፣ ከሴራ ፖለቲካ መላቀቅና ከምንም ነገር በላይ ሕዝብን ማክበር በምንም ዓይነት ሁኔታ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ጀግኖቹ አትሌቶቻችን መስዋዕትነት ከፍለው የሚያሸንፉት አገርና ሕዝብ አክብረው ነው፡፡

  ለኢትዮጵያ ከሰላምና ከዕድገት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ምክንያቱም በአፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥላ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጓታል፡፡ ከአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች በተጨማሪ በርካታ የውጭ ኢንቨስተሮች መምጣት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቅ ገበያ ስለሆነች በርካታ የልማት አጋሮች ያስፈልጋሉ፡፡ ሰፊ ለም መሬቷ መታረስ አለበት፡፡ በርካታ ማዕድናቷ ወጥተው ጥቅም ላይ መዋል አለባቸው፡፡ የኃይድሮ፣ የፀሐይ፣ የንፋስና የጂኦተርማል ሀብቷ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስገኘት አለበት፡፡ የውኃ ሀብቷ ጥቅም ላይ ውሎ ሲሳይ ማስገኘት ይጠበቅበታል፡፡ የቱሪዝም ሀብቷ በአፍሪካ ቀዳሚ ሆኖ በረከት ማምጣት ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያውያን በእነዚህ ሀብቶች ባለፀጋ የመሆን መብት አላቸው፡፡ ጥራቱ የተጠበቀ የመኖሪያ አካባቢ፣ ምግብ፣ ጤና፣ ትምህርትና የመሳሰሉት አገልግሎቶች ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከተመፅዋችነት ተላቀው በምቾት መኖር አለባቸው፡፡ ግጭት፣ ሞት፣ ውድመትና መፈናቀል በፍጥነት ተወግደው በክብር መኖር የኢትዮጵያውያን አዲሱ ገጽታ እንዲሆን፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነት መነሳት አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከጀግኖቹ አትሌቶቻችን አርዓያነት መማር ያስፈልጋል፡፡

  ኢትዮጵያ ድህነት ውስጥ ሆና መዝናናት አይቻልም፡፡ ሚሊዮኖች ዕርዳታ እየተለመነላቸው ሥራ ፈቶ ማስፈታት ነውር ነው፡፡ ባሉት ችግሮች ላይ ተጨማሪ መደረብ አሳፋሪ ነው፡፡ ከአገር ህልውናና ከሕዝብ ጥቅም በላይ የራስንና የቡድንን ብቻ  ለማስጠበቅ መረባረብ ኋላቀርነት ነው፡፡ ግጭት እየቀሰቀሱ በንፁኃን ደም መታጠብ፣ የገዛ ወገንን ማንገላታት፣ አገርን የሥጋት ቀጣና ማድረግ፣ ግብር ማጭበርበርና መሰወር፣ በሰው ሠራሽ እጥረት የዋጋ ግሽበት መፍጠር፣ የሕዝብን ጤና አደጋ ውስጥ የሚከቱ ምግቦችንና መድኃኒቶችን መሸጥ፣ በብሔራዊ ደኅንነት ላይ ማሴርና የአገር ጠላት መሆን የሚወገዙና የሚያስጠይቁ ወንጀሎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በድህነት እየማቀቀ በጎስቋላ ኑሮ አሳሩን ሲበላ፣ በላዩ ላይ ለማትረፍ የሚማስኑ ኃይሎች የሕዝብ ጠላት መባል አለባቸው፡፡ ሀቀኛ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ዓይነቶቹን የማጋለጥ ኃላፊነትም ግዴታም አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ደስተኛ የሚሆኑባት አገር ታስፈልጋቸዋለች፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የሕግ የበላይነት፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት ያስፈልጓታል፡፡ በአምባገነኖችና በከፋፋዮች ደባ ሕዝብ መሰቃየት የለበትም፡፡ በዚህ ጊዜ የሀቀኛ ኢትዮጵያውያን ጥረት ከምንም ነገር በላይ ተፈላጊ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከጀግኖቹ አትሌቶቻችን እንማር!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  የዩኒቨርሲቲ መምህራን ከደመወዝ ጭማሪና ከዕርከን ዕድገት ጋር በተያያዘ መንግሥትን አስጠነቀቁ

  ‹‹የደመወዝ ጉዳይ የትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንም...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ነፃነትም ተምሳሌት ናት፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያለፉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም...

  የማንም ሥልጣንና ጥቅም ከኢትዮጵያ አይበልጥም!

  የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ፣ የኢትዮጵያን የወደፊት ብሩህ ጊዜ አመላካች ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህ የአፍሪካ ታላቅ ግድብ ፕሮጀክት ዕውን...

  የሴራ ፖለቲካ መረብ ይበጣጠስ!

  ኢትዮጵያ አሁንም ከበርካታ ፈተናዎች ጋር እንደ ተፋጠጠች ነው ያለችው፡፡ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት ግብፅ በጎረቤት አገሮች አማካይነት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ፍጥነቷን ጨምራ እየተንቀሳቀሰች...