Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ከ235 ሺሕ ቶን በላይ ጥራጥሬና የቅባት እህል በመደበቅ ታሽገው የነበሩ መጋዘኖች ተከፈቱ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ወደ ውጭ መላክ የነበረበትን ከ235 ሺሕ ቶን በላይ ጥራጥሬና የቅባት እህል አከማችተው በመገኘታቸው ያሸጋቸውን የ26 ላኪዎች መጋዘኖችን መክፈቱን አስታወቀ፡፡ መጋዘኖቹ በዚህ ሳምንት የተከፈቱት ለሦስት ወራት ከእነ ያዙት ምርታቸው ታሽገው ከቆዩ በኋላ ነው፡፡

  ሚኒስቴሩ መጋዘኖቹን የከፈተው ላኪዎቹ ቅጣታቸውን በማጠናቀቃቸው መሆኑን ለሪፖርተር የተናገሩት የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ወ/ሮ ቁምነገር እውነቱ፣ ላኪዎቹ ምርቶቹን በድጋሚ አበጥረው ኤክስፖርት እንዲያደርጉ መታዘዛቸውን ገልጸዋል፡፡

  ሚኒስቴሩ በሚያዝያ ወር ላይ መጋዘኖቹን ያሸገው በአዳማ፣ በቡራዩ፣ በቃሊቲና በገላን ከተሞች በላኪ ድርጅቶች ማከማቻ መጋዘንና በማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ  ፍተሻ ካደረገ በኋላ ነው፡፡

  ከአራቱ ከተሞች ብዛት ያለው ክምችት የተገኘው በገላን ከተማ ሲሆን፣ በገላን ባሉ መጋዘኖች 57,274 ሜትሪክ ቶን የቅባት እህልና 177,514 ሜትሪክ ቶን ጥራጥሬ መገኘቱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ በቡራዩ፣ አዳማና አዲስ አበባ ያሉት መጋዘኖች በክምችት ብዛት በተከታታይ ተቀምጠዋል፡፡

  ሚኒስቴሩ፣ ‹‹ላኪዎቹ ፈቃድ ሲወስዱ የገቡትን ምርትን ሙሉ ለሙሉ ወደ ውጭ የመላክ ግዴታ በመተው፣ ምርቱን እያከማቹ ያሉት የመሸጫ ዋጋ ከፍ ይላል በሚል ግምት ተጨማሪ ትርፍ ለማግኘት ነው›› በሚል ወቀሳውን አቅርቧል፡፡

  ከዚህም ባሻገር ብሔራዊ ባንክ ላኪዎች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ የሚኖራቸውን ድርሻ የሚወስነውን መመርያ ‹‹ሐምሌ ላይ ይሻላላል›› በሚል ግምት ምርት ማከማቸታቸውን ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ካሳሁን ጎፌ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረው ነበር፡፡

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ታኅሳስ 2014 ዓ.ም. ባወጣው መመርያ የውጭ ላኪዎች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ የሚያገኙትን ድርሻ ወደ 20 በመቶ ቀንሶታል፡፡ ላኪዎቹ ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ውስጥ 70 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ መስጠት ያለባቸው ሲሆን፣ ቀሪውን አሥር በመቶ በአገሪቱ ካሉት ባንኮች ለአንዱ የመሸጥ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡

  መንግሥት ይኼንን መመርያ ያወጣው በአገሪቱ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትና አቅርቦትን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ዲኤታው፣ ‹‹ይኼ የሚነሳበት ሒደት የለውም፡፡ የዓለም የወጪ ንግድ ካየነው ብዙ አገሮች ጋር መቶ በመቶ የውጭ ምንዛሪውን የሚጠቀመው መንግሥት ነው፤›› ብለዋል፡፡

  ከዚህም ባሻገር ላኪዎች ምርት ልከው በሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገቡት ምርት ላይ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ እየተንቀሳሱ ነው ሲሉ ላኪዎችን ወቅሰዋል፡፡ አቶ ካሳሁን፣ ‹‹ወደ ውጭ ልኬ በማገኘው ገቢ ብረት አስገብቼ ከብረት አተርፋለሁ የሚል ሰው ትክክለኛ ነጋዴ ሊሆን አይችልም፡፡ አንድ ሰው ሰሊጥ ወደ ውጪ እልካለሁ ሲል ከሰሊጥ የሚያገኘውን ትርፍ ብቻ አስቦ ነው መሥራት ያለበት፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

  ንግድና ቀጣናቂ ትስስር ሚኒስቴር የሚመራና ባለድርሻ አካላትን የያዘ የወጪ ንግድ የዋጋ ጥናት ቦርድ፣ በየሳምንቱ ዓርብ እየተሰበሰበ የተለያዩ የግብርና ምርቶች በዓለም ገበያ ላይ እየተሸጡ ያሉበትን ዋጋ ይገመግማል፡፡ በዚህ ግምገማ መሠረትም ቦርዱ ሰሊጥ፣ ቦሎቄና አኩሪ አተርን ጨምሮ ከ20 በላይ ምርቶች የሚላኩበትን ዋጋ ያስቀምጣል፡፡

  ‹‹ላኪዎች በኤክስፖርት ያጣነውን በኢንፖርት እናካክሳለን በሚል ምርቶችን ቅናሽ እየሸጡ ነው፤›› የሚል ክስ የሚያቀርቡት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ከተቀመጠው የዋጋ ማነፃፀሪያ ባነሰ ዋጋ ምርት ለመላክ የሚዋዋሉ ላኪዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

  ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዙት እነዚህ ምክንያቶችም፣ ላኪዎች ምርት አከማችቶ በመያዝ የላቀ ዋጋ እንዲፈልጉ እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ይህ ችግር በበጀት ዓመቱ ጎልቶ መታየቱንና በአራት ከተሞች ብቻ 26 መጋዘኖች ምርት በማከማቸት ምክንያት መታሸጋቸውን ተናግረው ነበር፡፡ ይህ ዓይነት ምርመራ እንደ ጎንደር ባሉ ሰሊጥ የሚመረትባቸው አካባቢዎች ቢደረግ ከፍ ያለ ቁጥር ያለው ምርት ይገኛል የሚል ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡

  ከዚህ መግለጫ በሳምንቱ ላኪዎቹ ከማስጠንቀቂያ ጋር መጋዘኖቻቸው ተከፍተው ምርቱን እንዲልኩ ታዘዋል፡፡ ምርቶቹን ከመላካቸው በፊት የኤክስፖርት ስታንዳርዱን ማሟላታቸው መረጋገጥ እንዳለበት የገለጹት የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዋ ወ/ሮ ቁም ነገር፣ ‹‹ማበጠሪያ መጋዘን ተለይቶላቸው በየማበጠሪያ ክፍል ገብተው ይበጠራሉ፣ የመላኪያ መሥፈርትን እንዲያሟሉ ተደርገው ይኼዳሉ፣ ሦስት ወር ሙሉ የታሸገው እንዲሁ አይላክም፤›› ብለዋል፡፡

  በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ 4.12 ቢሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ 72 ከመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ከግብርና ምርቶች ውስጥ ደግሞ ቡና 1.4 ቢሊዮን ዶላር በማስገኘት ቀዳሚ ነው፡፡ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ የዕቅዱን 69 በመቶ ብቻ ነው፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች