Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበኢጋድ ቀጣና ለመንቀሳቀስ ዕውቅና የተሰጠው የንግድ ማኅበረሰብ ፎረም ሥራ ጀመረ

  በኢጋድ ቀጣና ለመንቀሳቀስ ዕውቅና የተሰጠው የንግድ ማኅበረሰብ ፎረም ሥራ ጀመረ

  ቀን:

  በኢትጵያውያን የንግድ ማኅበረሰብ አባላት የተመሠረተውና በሰላም ጉዳዮች ላይ በኢጋድ ቀጣና ለመንቀሳቀስ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዕውቅና (accreditation) ያገኘው አንትርፕረነሪያል ፎረም ፎር ፒስ ኤንድ ዲቨሎፕመንት (Entrepreneurial Forum for Peace and Development)፣ በይፋ ሥራ መጀመሩን አስታወቀ፡፡

  በቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ቦርድ ሰብሳቢነትና በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ምክትል ሰብሳቢነት የሚመራው ፎረሙ በይፋ ሥራ መጀመሩን ያስታወቀው፣ ሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ባካሄደው ሥነ ሥርዓት ነው፡፡

  መስከረም 2014 ዓ.ም. ፎረሙ መመሥረቱን ያስታወሱት የፎረሙ ዋና ሥራ አስኪያጅ በለጠ በላቸው (ዶ/ር)፣ በኅዳር ወር መንግሥታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት ሆኖ መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢጋድ ቀጣና እንዲንቀሳቀስ አክሬዲቴሽን እንዲያገኝ የተደረገ ተቋም ነው፤›› በማለት፣ ፎረሙ በኢጋድ አገሮች ሕጋዊ ውክልና ለማግኘት እንደሚንቀሳቀስ አስረድተዋል፡፡

  የንግዱ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያና በኢጋድ ቀጣና ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ አስተዋጽኦ የማበርከት ዓላማ እንዳለው ሆኖም፣ ከየትኛውም የፖለቲካና የመንግሥት ተቋም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የማያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

  በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች እየተከሰቱ ያሉ የፀጥታ ችግሮች በእንቅስቃሴያቸው ላይ ተፅዕኖ ባሳደረባቸው የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት እንደተመሠረተ የተነገረለት ይህ ፎረም፣ በአገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚንቀሳቀሱ ከ120 በላይ ባለሀብቶችንና ነጋዴችን ይዟል፡፡ የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ባለቤት አቶ በላይነህ ክንዴ፣ የግራንድ ሆቴል ባለቤት ወ/ሮ ትልቅሰው ገዳሙና ከራይድ መሥራቾች አንዷና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ሳምራዊት ፍቅሩ ከፎረሙ መሥራቾች መካከል መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

  እነዚህ ባለሀብቶች ፎረሙን የማቋቋም ሐሳባቸውን ለኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ ማቅረባቸውን ለሪፖርተር የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በለጠ (ዶ/ር)፣ ኢጋድ ፎረሙ ከኢትዮጵያ አልፎ ወደ ቀጣናው አገሮች ለሚያደርገው መስፋፋት የማመቻቸት ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

  ይሁንና ፎረሙ በቀጣናው የሚታዩት የሰላምና የልማት ችግሮች ‹‹ጊዜ የሚሰጡና የተሟላ ድርጅት እስከሚመሠረት የሚጠብቁ ባለመሆናቸው››፣ ፎረሙን በኢትዮጵያ የማስመዝገብና ዋና ጽሕፈት ቤቱንም በአገሪቱ ለማድረግ እንደተወሰነ በመድረኩ ላይ ተነስቷል፡፡

  ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹ኬንያ፣ ጂቡቲ፣ ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን ያሉ ባለሀብቶች የዚሁ ፎረም አባል ሆነው በየአገራቸው የዚህ ፎረም አካል የሆነና በራሳቸው የሚመራ ቻችተር ያቋቁማሉ፤›› ብለዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሒደትም በተለያዩ የቀጣናው አገሮች ያሉ ታዋቂ የንግዱ ማኅበረሰብ አካላትም ስለፎረሙ ዓላማ ማብራሪያ ተደርጎላቸው ፈቃደኝነታቸውን መግለጻቸው ተገልጿል፡፡  

  በለጠ (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት ፎረሙ በቀጣይ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የንግዱ ማኅበረሰብ ሕጋዊ መብቶችን ለማስከበር የፖሊሲና የአድቮኬሲ ሥራዎችን የመሥራትና የፖሊሲ አማራጭ ምክረ ሐሳቦችን የማቅረብ ዕቅድ አለው፡፡

  በሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ፎረሙ የተመሠረተው የሰላም አማራጮችን ለማየት እየተሞከረ ባለበት ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው ይህም አስፈላጊነቱን እንደሚያጎላው ተናግረዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ለሰላም ድርድሩ ‹‹ከአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ውጭ ሌላው ተቀባይነት የለውም›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

  የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነትና ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው የአፍሪካ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በንብረት ላይ የደረሰው የትራፊክ አደጋ በ494 በመቶ ጨምሯል

  በትራፊክ አደጋ 3,971 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናቀቀው...

  አዲሱን የመንግሥት መዋቅር ዘርግተው ያጠናቀቁ ተቋማት 31 በመቶ ብቻ ናቸው

  በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር ካሉት 160 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ...

  ለተቃርኖ ምክንያት የሚሆኑ ከንቱ ድርጊቶች ይወገዱ!

  ሰሞኑን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት...