Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አባላት ያቀረቡት የደመወዝ ክፍያ ይግባኝ ውድቅ ተደረገ

  የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አባላት ያቀረቡት የደመወዝ ክፍያ ይግባኝ ውድቅ ተደረገ

  ቀን:

  የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስተዳደር ፍርድ ቤት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ውስጥ ሲሠሩ የነበሩ ግለሰቦች፣ የደመወዝ ክፍያን አስመልክቶ ያቀረቡትን የይግባኝ አቤቱታ ውድቅ አደረገ፡፡

  ፍርድ ቤቱ ትናንት ሐምሌ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. በዋለው ችሎቱ ለሁለት ወራት በቆየው ክርክር ላይ ይህንን ብይን ያስተላለፈው፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አባላት ያቀረቡትን ይግባኝ የማየት ሥልጣን የሌለው መሆኑን በመጥቀስ ነው፡፡

  የጊዜያዊ አስተዳደሩ አባላት ጉዳያቸው በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስተዳደር ፍርድ ቤት ከመታየቱ በፊት፣ የመጀመርያ ክሳቸውን የመሠረቱት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነበር፡፡ በከፍተኛው ፍርድ ቤት በመሠረቱት የፍትሐ ብሔር ክስ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳደር ላይ ክስ መሥርተው 23.3 ሚሊዮን ብር እንዲከፈላቸው ጠይቀው ነበር፡፡

  ይሁንና ፍርድ ቤቱ መጋቢት 13 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው ብይን ይህንን ክስ የማየት ሥልጣን እንደሌለው ገልጿል፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አባላት ክሳቸውን የመሠረቱት ለፌዴራል መንግሥቱ ተጠሪ በሆነው ጊዜያዊ አስተዳደር ሥር የነበራቸውን የሥራ ኃላፊነት በማንሳት የመንግሥት ሠራተኛ እንደሆኑ ማስረዳታቸውን በፍርድ ቤቱ ብይን ላይ ተቀምጧል፡፡

  ‹‹የመንግሥት ሠራተኞች መሆናቸውን በማመልከታቸው ሊመሩ የሚችሉት በመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ መሠረት ነው፤›› ያለው ፍርድ ቤቱ፣ አዋጁ ደግሞ ይህ ዓይነት ክርክር በመደበኛው ፍርድ ቤት እንደማይታይ ማስቀመጡን ጠቅሷል፡፡ ይህንን ገልጾም ክሱን የማየት ሥልጣን እንደሌለው አስታውቋል፡፡

  ይህንን ብይን ተከትሎ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አባላት መጋቢት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የማመልከቻ ደብዳቤ በመጻፍ ደመወዛቸው እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል፡፡

  የመከላከያ ሠራዊት ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው በደብዳቤው ላይ የጠቀሱት አባላቱ በተደጋጋሚ ክፍያ እንዲፈጸምላቸው ቢጠይቁም ምላሽ እንዳላገኙ አስረድተዋል፡፡ አባላቱ፣ ‹‹ከሰኔ 2013 ጀምሮ እስከ መጋቢት 2014 ዓ.ም. ያለው ደመወዛችንና ከእነ ሙሉ ጥቅማ ጥቅማችን እንዲከፈለን፤›› ሲሉ በማመልከቻው ጠይቀዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ያለው የኑሮ ሁኔታን ‹‹ስለማንችል›› በማለትም የመኖሪያ ቤት እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡

  ጥያቄው የቀረበለት ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ማመልከቻውን ላስገቡት 88 የጊዜያዊ አስተዳደሩ አባላት በሰጠው ምላሽ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የነበሩ ሠራተኞች ጉዳይ እንደማይመለከተው አስታውቋል፡፡

  ኮሚሽኑ ምላሹን ባሳወቀበት ደብዳቤ ላይ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች የሚመሩበትን ደንብ ቁጥር 455/2011 በመጥቀስ ‹‹ኮሚሽኑ የሚመለከተው በፌዴራል የመንግሥት ተቋማት ተመዝነው ምደባ በተሰጣቸው የሥራ መደቦች ላይ ለተመደቡ ሠራተኞች ብቻ መሆኑን እንገልጻለን፤›› ብሏል፡፡

  ከዚህ ምላሽ በኋላ የጊዜያዊ አስተዳደር አባላቱ ለኮሚሽኑ ያቀረቡት ‹‹የአስተዳደራዊ መፍትሔ›› ጥያቄ አግባብነት እንደሌለው በመግለጽ በኮሚሽኑ የአስተዳደር ፍርድ ቤት ይግባኝ ብለዋል፡፡

  አባላቱ ግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ባቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ የጊዜያዊ አስተዳደሩን አወቃቀር ሥልጣንና ተግባር የሚደነግግ ደንብ ቁጥር 479/2013 በሚኒስትሮች ምክር ቤት መውጣቱን ጠቅሰዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅን አንስተው ደግሞ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ራሱን ችሎ በአዋጅ ወይም በደንብ የተቋቋመና ከመንግሥት በጀት የሚመደብለት የሚተዳደር መሆኑን አስፍረዋል፡፡

  ‹‹በመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ጥያቄያችን ተፈጻሚነት እያለው ኮሚሽኑ አይመለከተኝም በማለት የሰጠው አስተዳደራዊ ውሳኔ አግባብነት የለውም፤›› በማለት 30 የጊዜያዊ አስተዳደሩ አባላት ይግባኝ ብለዋል፡፡

  ፍርድ ቤቱ የአሥር ወራት ደመወዝና 4.8 ሚሊዮን ብር ጥቅማ ጥቅም ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ እንዲመለሱ እንዲወስንላቸው ጠይቀዋል፡፡ 

  በዚህ ይግባኝ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳደር መልስ ሰጪ ተብለው የተጠቀሱ ሲሆን፣ በክስ ሒደቱ የጊዜያዊ መስተዳደሩን ወክሎ የቀረበ አካል የለም፡፡

  የክርክር መዝገቡ እንደሚያስረዳው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ነገረ ፈጅ በፍርድ ቤቱ ቀርበው የጊዜያዊ አስተዳደሩ አባላት የተመደቡት ‹‹በፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች ሕግ መሠረት ሳይሆን ባላቸው ፖለቲካዊ አቋም ነው፤›› በማለት ተከራክረዋል፡፡

  አባላቱ የሠራተኛ አዋጅ በሚያዘው መሠረት በምዘና ያልተመደቡ መሆናቸውን በምሳሌነት አንስተው፣ ይግባኝ ባዮቹ የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅን መሠረት አድርገው ክስ ለመመሥረትና ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል ‹‹የሕግ ድጋፍ የላቸውም›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

  ነገረ ፈጇ አክለውም፣ ‹‹ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ ያለውን ሥራ ባቋረጠ ጊዜ የእነሱም ኃላፊነት ወድያውኑ ይቋረጣል፤›› በማለት የይግባኝ አቤቱታው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

  ይግባኝ ባዮቹ በበኩላቸው ‹‹በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቀጥረን እንጂ በፖለቲካ እምነታችን አልተቀጠርንም፤›› የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ‹‹ፈርሷል ወይም አገልግሎቱን አቋርጧል›› የሚለውን በተመለከተም ‹‹አዋጅ በአዋጅ ስለመፍረሱ ማስረጃ በሌለበት፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራውን ስላቋረጠ ደመወዝ አንከፍልም የሚለው ተቀባይነት የለውም፤›› ብለዋል፡፡

  ይህንን ክርክር የተመለከተው የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ፣ ይህ ፍርድ ቤት ጉዳዩን አከራክሮ የመወሰን የሥረ ነገር ሥልጣን አለው ወይስ የለውም? የሚለውን ጭብጥ መርምሮ ይግባኝ ባዮቹ ‹‹የፌዴራል ሠራተኞች የሚሆኑበት መብት›› እንደሌላቸው መረዳቱን አስታውቋል፡፡

  ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተመሠረተበትና የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት በሚደነግገው አዋጅ መሠረትም፣ ‹‹የክልል መንግሥት አደረጃጀትና ሥልጣን ተጠቃሎ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት እንዲሆን የተደረገበት የሕግ አግባብ፤›› እንዳልሆነ በፍርድ ቤቱ ብይን ላይ ተጠቅሷል፡፡

  ብይኑ በመጨረሻም ይግባኝ ባዮቹ ‹‹ፌዴራል መንግሥት ሠራተኛ የተሰጠውን ትርጉም የሚያሟሉና የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች እንዳልሆኑ ለመገንዘብ አስችሎናል፤›› በማለት አቤቱታውን የመዳኘት ሥልጣን እንደሌለው አስታውቋል፡፡

  ከዚህ ብይን በኋላ ይግባኝ ባዮቹ ሙሉ የክስ መዝገብ እንዲሰጣቸው ማመልከቻ ማስገባታቸውን የጊዜያዊ አስተዳደሩ አባላት ተወካይ አቶ ፅጋቡ ቆባዕ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የክስ መዝገቡን ይዘው ለሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ እንደሚሉ አቶ ፅጋቡ ገልጸዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...

  በዓለም ጂኦ ፖለቲካ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት

  የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪካ አገሮች...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር...

  ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2015 የሒሳብ ዓመት ተቀማጭ ገንዘቡን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለማሳደግ እንደሚሠራ አስታወቀ

  በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በተለያዩ ክንውኖቹ ከዕቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገቡን...