የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር በሚቀጥለው ዓመት በመስከረም ወር መጨረሻ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀውን፣ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ዕጣ የማውጣት መርሐ ግብር አከናወነ፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ ማክሰኞ ሐምሌ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤቱ ባከናወነው ፕሮግራም እስከ 15ኛው ሳምንት የሚደረጉ ጨዋታዎችን ይፋ አድርጓል፡፡
የ2015 የውድድር ዘመን የዕጣ ማውጣት መርሐ ግብር ከመከናወኑ አስቀድሞ፣ ምንም እንኳ ከሊጉ አክሲዮን ማኅበር የወጣ መረጃ ባይሆንም፣ በሊጉ የሚሳተፉ ቡድኖች ቁጥር ከ16 ወደ 18 ከፍ እንደሚችል ሲነገር የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ማክሰኞ ሐምሌ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ በተደረገው ዕጣ የማውጣት ሥነ ሥርዓት በሚቀጥለው የውድድር ዘመን፣ የሊጉ ቁጥር ይጨምራ የሚለው ያበቃለት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
የሊጉ አክሲዮን ማኅበር የሊጉን ቁጥር ከመጨመር ይልቅ ወደ 14 ዝቅ በማድረግ፣ ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ውድድር ማከናወን ቀጣይ ዕቅዱ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ የአክሲዮን ማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ የሊጉን ቁጥር ከ16 ወደ 14 ዝቅ የሚልበት ሁኔታ ጥናት እየተደረገ መሆኑ መናገራቸው መዘገባችን አይዘነጋም፡፡
ማክሰኞ ሐምሌ 26 ቀን በወጣው ዕጣ መሠረት የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታ፣ ሐዋሳ ከተማ ባለፈው ዓመት ወደ ፕሪሚየር ሊግ ካደገው ለገጣፎ ለገዳዴ ጋር ይጫወታል፡፡ ባህር ዳር ከተማ በተመሳሳይ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ያደገውን ኢትዮ ኤሌክትሪክን የሚያስተናግድ ይሆናል፡፡
የመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ላለፉት ሦስት አሥርታት ‹‹መከላከያ›› በሚል ሲጠራበት የነበረው ስያሜ፣ ከሦስት አሥርታት በፊት በነበረው ስያሜው ‹‹መቻል›› እግር እግር ኳስ ክለብ ተብሎ በ2015 የውድድር ዓመት እንደሚቀጥል የቀድሞ የመከላከያ እግር ኳስ ክለቡ አመራሮች፣ ባለፈው ሳምንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
በዚሁ መሠረት መቻል ከሀድያ ሆሳዕና፣ ኢትዮጵያ መድን ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ፋሲል ከተማ ከአዳማ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ወልቂጤ ከተማ ከአርባ ምንጭ ከተማና ድሬዳዋ ከተማ ከሲዳማ ቡና እንደሚጫወቱ ነው ከመርሐ ግብሩ መረዳት የተቻለው፡፡