Monday, August 8, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ምጣኔ ሀብትን በፖለቲካ መነጽር የመቃኘት ውጤት

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት መረጋጋት ከራቀውና በተለይ የደሃው ገቢና ወጪ አራምባና ቆቦ ከሆነ ሰነባበተ፡፡ የሚጋጩ የፊስካልና የሞኒታሪ ፖሊሲዎች ኢሕአዴግ ትቶ ያለፋቸውን የኢኮኖሚ ጠባሳዎች ከማዳን ይልቅ እያባባሱ እንደሆነ፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ዓላማና ውጤታማነትም አጠያያቂ ስለመሆኑ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡

  የዋጋ ግሽበት ከ34 በመቶ በላይ በየወሩ የሚያድገው በዋነኛነት መንግሥት ወደ ኢኮኖሚ የሚያሠራጨው ገንዘብ (Money Supply) በከፍተኛ መጠን እያደገ በመምጣቱ ነው፡፡ የገንዘብ ሥርጭቱ በተመሳሳይ በዚህ ዓመት በ29 እጅ ያደገ ሲሆን፣ ይህም ከዚህ በፊት 15 በመቶ መብለጥ የለበትም ከሚባለው ምክረ ሐሰብ በእጥፍ ከፍ ያለ ያደርገዋል፡፡ የገንዘብ ሥርጭት ከጥቅል አገራዊ ምርት ዕድገቱ ጋር ተመጣጥኖ ካልሄደ በሒደት የሚያስከትለው ውጤት አንድ ዳቦ ለመግዛት ቅርጫት ሙሉ ብር ተሸክሞ መሄድ እንደ ማለት ነው፡፡

  የብርን የመግዛት አቅም ለማዳከም መንግሥት እየተከተለ ያለው ፖሊሲ ሌላው ትልቁ የመንግሥት የስህተት መንገድ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

  ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር የፖሊሲ ትንተና ዳይሬክተር የሆኑት ደግዬ ጉሹ (ዶ/ር)፣ መንግሥት በጭፍን ላለፉት አራት ዓመታት ያስቀጠለው ፖሊሲ የብርን ዋጋ ማውረድ ፖሊሲ ከጥቅሙ ጉዳቱ እያመዘነ በመምጣቱ መንግሥት በጊዜ ማቆም ነበረበት ይላሉ፡፡

  ብር በየወሩ በስድስት እጅ እየወረደ ሄዶ በባንክ 52 የደረሰ ሲሆን፣ በትይዩ ገበያው ደግሞ 80 ተሻግሯል፡፡ ምንም እንኳን የብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎች የብር ዋጋ መውረዱ (Devaluation) ‹‹ኤክስፖርትን እያበረታታ ነው፤›› ቢሉም ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ምርት ግን በእጅጉ አስወድዷል፡፡ 

  ‹‹የወጪ ንግድ ገቢ ለመጀመርያ ጊዜ አራት ቢሊዮን ዶላር ቢደርስም፣ ጭማሪው የዓለም አቀፍ ወርቅ ዋጋ በ700 በመቶ በማደጉና ሌሎች ቡና ላኪ አገሮች በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሲቀንሱ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ስለሆነች ነው፡፡ የብር ዋጋን ማውረድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ብቻ እንደተረፈን አውቆ መንግሥት በጊዜ ማቆም ነበረበት፤›› ይላሉ  ደግዬ (ዶ/ር)፡፡ 

  መንግሥት የብር ዋጋ ማውረዱን የቀጠለበት ለአዲስ የገንዘብ ሥርጭት እንዲያመቸው ሲሆን፣ የገንዘብ ሥርጭቱ ደግሞ በዋናነት የተፈለገው እየሰፋ የመጣውን የበጀት ጉድለት ለመሙላት ነው ሲሉ የኢኮኖሚ ባለሙያው ደግዬ (ዶ/ር) ይተቻሉ፡፡ ‹‹ችግሩን ያባሰው ደግሞ አዲስ የሚሠራጨው ገንዘብ በብዛት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ምርትን መጨመር ለማይችሉ አገልግሎቶች ማለትም ለደመወዝ ክፍያ፣ የአገልግሎት ዘርፉንና የገቢ ንግድን ለሚያበረታቱ ተግባራት ነው፡፡ በእርግጥ የትግራይ ጦርነት የመንግሥትን ካዝና ማራቆቱና ለገንዘብ ሥርጭቱ እያበጠ መምጣት ዋነኛው መንስዔ ነው፡፡ ገንዘብ ያለ ምክንያት ማሠራጨት ልምድ እየሆነ የመጣ ሲሆን፣ ይህም ጊዜያዊ ችግሮችን ለመፍታት ብቻ ተብሎ የረዥም ጊዜ ችግር እየፈጠረ ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

  በአንድ በኩል መንግሥት ግሽበትን እቆጣጠራለሁ ቢልም በጀትን መመጠን፣ የገንዘብ ሥርጭትን መገደብና የብር ዋጋ መውረድን መግታት እየቻለ በቸልታ መመልከቱ ኃላፊነት ከሚሰማው መንግሥት አይጠበቅም ይላሉ ኢኮኖሚስቱ፡፡

  እንደ ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ ያሉ ምሁራን ደግሞ ጉዳዩን ከውጭ ጫና ጋር ያቆራኙታል፡፡ 

  ‹‹የዓለም አቀፉ ገንዘብ ተቋማት የብር ዋጋ እንዲወርድ፣ ድጎማ እንዲነሳ፣ መንግሥት እጁን ከኢኮኖሚው እንዲያወጣ፣ የልማት ድርጅቶች ወደ ግል እንዲዞሩና የንግድና ኢንቨስትመንት ከለላዎች እንዲነሱ እንደ ብድር ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠው እየሠሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች በኢትዮጵያ ላይ በግድ ተጭነው ሳይሆን አሁን ያለው መንግሥት አማካሪዎች አምነውበትና ወደው ስለተቀበሉት ነው፡፡ እነዚህ አማካሪዎች የተማሩት በአብዛኛው በአሜሪካ ሲሆን፣ በነፃ ገበያ መርህ ተጠምቀው የመጡ ናቸው፤›› ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡ ዓለማየሁ እንዲያውም የአንድ ዶላር ዋጋ በብር ከሦስት ዓመት በፊት ወደነበረበት መመለስ አለበት ይላሉ፡፡ 

  ምንም እንኳን መንግሥት ነፃ የኢኮኖሚ አማካሪዎች ምክር ቤት አቋቁሞ የነበረ ቢሆንም፣ ምክር ቤቱ ከመነሻው ገሸሽ በመደረጉ ምንም እንቅስቃሴ ሳያደርግ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ምጣኔ ሀብቱን በፖለቲካ ቅኝት እየመራ ያመቸውን ፖሊሲ ሲያፀድቅ ሃይ የሚል ሳይንሳዊ መርህን የሚከተል ነፃ ተቋም ሳይፈጠር ቆይቷል፡፡

  ችግሩ ከቁጥጥር እየወጣበት የመጣው የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከረፈደ በኋላም ቢሆን ለመፍትሔ ማማተር መጀመሩ የሚደገፍ ነው፡፡ ከሳምንት በፊት በኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር ላይ የተገኙት አቶ አህመድ ሺዴ፣ ማኅበሩ አማራጭ የፖሊሲ መፍትሔ ካለው መንግሥት ተቀብሎ ለመተግበር ዝግጁ መሆኑን መግለጻቸው ‹‹ከቀረው ያረፈደ›› ያስብላል፡፡

  ይሁን እንጂ ከተወሳሰበው የምጣኔ ሀብት ችግር በአጭር ጊዜ መውጣት አሁንም አዳጋች ሆኖ ይታያል፡፡ የተዛባውን የሞኒታሪና የፊስካል ፖሊሲዎች ማስተካከል የዋጋ ግሽበቱን መቀነስ ቢችልም፣ ይህ ግን ለሚቀጥሉት ዓመታት ሳይቋረጥ ከተተገበረ ብቻ ነው ሁሉም ነገር ወደ ነበረበት ሊመለስ የሚችለው፡፡ አስተማማኙ መፍትሔ አቅርቦትን ማሻሻል ሲሆን፣ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግና በሌሎች አምራች ዘርፎች ውስጥ ያሉ ለዓመታት የዘለቁ ተግዳሮቶች በቁርጠኝነት ከተፈቱ የአገር ውስጥ አቅርቦቱ ተሻሽሎ እንዲያውም የገቢ ምርትን ሊተካ ይችላል፡፡ 

  የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር በቅርቡ ለኢኮኖሚው መዛባት ምክንያት ናቸው ካላቸው 50 መንስዔዎች ውስጥ 25ቱ በቶሎ ካልተፈቱ ችግሩ እየተባባሰ እንደሚሄድ ገልጸዋል፡፡ በተለይ እየቀነሰ የመጣውን የመሬት አቅርቦትና አጠቃቀም ማሻሻል ምርታማነትን ለማሻሻል መተኪያ እንደሌለው አስምሮበታል፡፡

  በእርግጥ የፋይናንስ አቅርቦትን ማሻሻልም አምራች ዘርፎች ውስጥ ሕይወት ለመዝራት ወሳኝ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህም ብቻውን ውጤት አያመጣም፡፡ ‹‹በማንኛውም ኢኮኖሚ ውስጥ ዋጋ ሲወደድ አምራቹ ተጠቃሚ ስለሚሆን በደንብ አምርቶ ወደ ገበያ ያቀርባል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጠረ ያለው በተቃራኒ ነው፡፡ ዋጋ ቢያድግም ምርት የለም፤›› ይላሉ ዶ/ር ደግዬ፡፡ 

  ለዚህ ተቃርኖ ዋነኛ ምክንያት ደግሞ እስከ 45 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ አምራች ክፍል በአማራ፣ ከፊል ኦሮሚያና ትግራይ የግጭት ሰለባ በመሆናቸው አምራቹ ተረጂ ሆኗል፡፡ ስለዚህ የዋጋ ግሽበትን ለማስተካከል የሚወሰድ ማንኛውም ዕርምጃ ውጤታማ የሚሆነው በአገሪቱ ያለው ግጭት ቆሞ የአገሪቱ የሰው ኃይልና ሀብት ወደ ምርት ሲመለስ ነው፡፡

  እንዲያም ሆኖ በዜጎች ገቢና ወጪ መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ለማጥበብ መንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡

  ‹‹ዕድገት በራሱ ግብ አይደለም፣ የዜጎችን ሕይወት ካላሻሻለ፡፡ ባለፉት ዓመታት መንግሥት ባወጣቸው ትክክል ያልሆኑ ፖሊሲዎች መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ የሚገኙ ኅብረተሰብ ክፍሎች 14 በመቶ ገቢያቸውን አጥተዋል፡፡ በሌላው ጫፍ ያለው ከፍተኛ ገቢ ማኅበረሰብ ግን 14 ከመቶ ተጨማሪ ገቢ አግኝቷል፡፡ በጥናታችን መሠረት በአጭሩ መንግሥት እየተገበረ ያለው ፖሊሲ ድሆችን የበለጠ ደሃ የሚያደርግ፣ ሀብታሞችን የበለጠ ሀብታም የሚያደርግ ነው፡፡ ይህንን ለማጥበብ ማኅበራዊ ፍትሕን የሚያንፀባርቅ ታክስን ከሀብታም ሰብስቦ ለደሃ ማከፋፈል፣ የማኅበራዊ ዋስትናንና ሴፍቲነት ተደራሽነትን ማስፋት ግድ ይላል፤›› ይላሉ ዶ/ር ደግዬ፡፡ 

     

   

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -spot_img

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች