Friday, August 19, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናአራጣ በማበደር ወንጀል ተጠርጥረው በታሰሩት የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት ላይ ተጨማሪ የምርመራ...

  አራጣ በማበደር ወንጀል ተጠርጥረው በታሰሩት የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

  ቀን:

  ‹‹የታሰርኩት ሆን ተብሎ በተቀነባበረ ሴራ ነው››

  አቶ ዓብይ አበራ፣ የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት

  አራጣ በማበደርና በተለያዩ ወንጀሎች መጠርጠራቸው ተገልጾ ከሁለት ሳምንታት በፊት በቁጥጥር ሥር በዋሉት የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት አቶ ዓብይ አበራ ላይ የተጠየቀው ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ፡፡

  የፌዴራል ፖሊስ የምርመራ ቡድን ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ እንዳስረዳው፣ ቀደም ብሎ በተፈቀደለት 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ የተለያዩ ሰነዶችን ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ሰብስቧል፡፡ የተለያዩ ውል የፈጸሙባቸው ሰነዶች ቢኖሩም ከውልና ማስረጃ ተቋም ከመሀል ገጽ ተቆርጠው መጥፋታቸውን፣ በጉምሩክ በኩል ቀረጥ የተከፈለባቸው ተሽከርካሪዎች የገቡ ቢሆንም፣ የሰነድ ማስረጃው በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጽሕፈት ቤቶች ሊገኙ አለመቻላቸውን በማስረዳት፣ ቀሪ ሥራዎች በርካታ በመሆናቸውና ከየተቋማቱ የጠፉ ሰነዶችን ለማፈላለግ ጊዜ ስለሚያስፈልገው፣ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት አመልክቷል፡፡

  የተጠርጣሪው ጠበቆች የመርማሪውን ጥያቄ በመቃወም ለፍርድ ቤቱ እንዳመለከቱት፣ መርማሪ ቡድኑ ተመሳሳይ ጥያቄ ሲያቀርብ ለሦስተኛ ጊዜ እንደሆነ፣ ለፍርድ ቤቱ የሚያቀርበው ምክንያት ሦስት ጊዜም ተመሳሳይ መሆኑን፣ በመሆኑም ተጨማሪ የቀጠሮ ጊዜ ሊፈቀድለት እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡ ኦዲትም ሆነ ሌላው ምርመራ በመጠናቀቁ ደንበኛቸውን ማሰር ተገቢ አለመሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ግብርን በሚመለከት ሁሉም ሰነድ በገቢዎችና ጉምሩክ እንደሚገኝ፣ ብርበራና ምርመራ በማጠናቀቅ መዝገቡን ለዓቃቤ ሕግ መላኩን መግለጹንም ጠበቆቹ አስረድተዋል፡፡

  ተጠርጣሪው ከፍተኛ ሕመም እንዳለባቸውና በሪፈራል ሆስፒታል መታከም እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀደም ባሉት የጊዜ ቀጠሮ ቀናት  ተጠርጣሪው ከቤተሰብ፣ ከጠበቃና ከሃይማኖት አባት ጋር እንዲገናኙ ትዕዛዝ የተሰጠ ቢሆንም፣ ተግባራዊ አለመደረጉን ተናግረዋል፡፡ ከ80 በላይ ሠራተኞች የሚያስተዳድሩበትና ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት መታሸጉን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሊሰጥበት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

  መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪው በዋስ ቢወጡ የገንዘብ አቅም ስላላቸውና ብዙ ሰው ስለሚያውቁ መረጃ ሊያሸሹ፣ ምስክሮች ሊያባብሉና ሊያስፈራሩ እንደሚችሉ በመግለጽ የዋስትና ጥያቄ ውድቅ እንዲደረግለት አመልክቷል፡፡

  የተጠርጣሪው ጠበቃ አቶ ሞላ ዘገዬ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ቢለቀቁ ያስፈራራሉ፣ ያባብላሉ፣ ማስረጃ ያጠፋሉ የሚባለው አባባል ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ በማንኛውም የሕግ አግባብ ሰው አስሮ ማስረጃ መፈለግ እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡ ይኼ አባባልም ሕገ መንግሥታዊ መሆኑን በመጠቆም፣ አንድን ተጠርጣሪ ከመያዝ በፊት ቅድመ ማስረጃ (Prima Facia Evidence) መቅደም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ተጠርጣሪው አቶ ዓብይ ሀብት፣ ድርጅትና ቤተሰብ ያላቸው የአደባባይ ሰው መሆናቸውን የገለጹት አቶ ሞላ፣ ገና ለገና ባላጋራዎቻቸው በሚያቀርቡባቸው መረጃ ሊታሰሩ እንደማይገባና ሕገ መንግሥቱንም የሚጥስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወደ ካንሰርነት ሊቀየር በሚችል ሕመም ምክንያት አስቸኳይ ሕክምና ማድረግ ስላለባቸው፣ ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

  አቶ ዓብይ ለፍርድ ቤቱ የሚያስረዱት ነገር እንዳላቸው ጠይቀው ሲፈቀድላቸው እሳቸው ምንም የፈጸሙት የወንጀል ተግባር እንደሌላ ገልጸው፣ ‹‹በቁጥጥር ሥር የዋልኩት ሆን ተብሎ በተቀነባበረ ሴራ ነው፤›› ብለዋል፡፡

  ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገኖች ክርክር ካዳመጠ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ መርማሪ ቡድኑ ይቀረኛል ያላቸውን የምርመራ ሒደቶችና የሠራቸውን ፍርድ ቤቱ ሲመለከት፣ ቀሪ ሥራዎች እንዳሉት ግንዛቤ መውሰዱን ገልጿል፡፡ ተጠርጣሪው በዋስ ቢወጡ ጣልቃ በመግባት ምርመራ ሊያደናቅፉ ይችላሉ የሚል ግምት በመውሰዱም የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ፣ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜውን መፍቀዱን አስታውቋል፡፡ ነገር ግን መርማሪ ፖሊስ ለተጠርጣሪው በቂ ሕክምና እንዲያገኙ እንደሚያደርግ፣ ቤተሰብ፣ ጠበቃና የሃይማኖት አባት የመጠየቅ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን እንዲያከብር ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የታሸገና የታገደ ንብረትን በሚመለከት በቀረበው አቤቱታ ላይ መርማሪ ፖሊስ ለነሐሴ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ሪፖርት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት፣ ለነሐሴ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡  

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  መንግስት 8 የስኳር ፋብሪካዎችን ለጨረታ አቀረበ

  መንግስት ስኳር ኢንተርፕራይዞችን ወደግል ለማዛወር በወጣው ጨረታ ባለሐብቶች እንዲሳተፉ...

  የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈጸምኩም አለ

  የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ...

  12ኛ ክልል እንዲቋቋም ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተወሰነ

  የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት አቤቱታን ተቀብሎ በመመርመር ሕዝበ...