Wednesday, August 10, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  በቀን ገቢ ግብር ግምት ላይ የተፈጠረው ውዥንብር ይጥራ!

     የቀን ገቢ ግብር ግምት ጥናት ተደርጎ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ወዲህ፣ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት የፍትሐዊነት ጥያቄዎች ተሰምተዋል፡፡ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በየደረጃው ቅሬታዎች ቀርበዋል፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በክልል ከተሞች የንግድ መደብሮች ተዘግተው ነበር፡፡ ገማቾች በየቦታው እየተገኙ የቀን ገቢ ግምት ሲያስታወቁ በብዙዎች ዘንድ የተፈጠረው ድንጋጤ የግንዛቤ ሥርፀቱን ውስንነት፣ በገማቾች ዘንድ የተስተዋለውን ወጥ ያልሆነ አሠራር፣ እንዲሁም የክትትሉንና የቁጥጥሩን ልልነት ያጋለጠ ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ ውዥንብር ተፈጥሯል፡፡ ሌላው በዋናነት የተነሳው ችግር በአዲስ አበባ ከተማ ላለፉት ስድስት ዓመታት ጥናት ተካሂዶ አለማወቁ ነው፡፡ በቅርቡ የተካሄደው ጥናትና እሱን መነሻ አድርጎ የተካሄደው ግምት ጥያቄ ሲነሳበት፣ ለጥያቄው ፈጣን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ መዘግየት መፈጠሩ ሌላው ችግር ነበር፡፡ የቀን ገቢ ግምት ጥናቱ በርካታ ድካም ተደርጎበት ወደ ሥራ ሲገባ ቢያንስ ሊኖሩ የሚችሉ ቅሬታዎችን ታሳቢ በማድረግ፣ የግንዛቤ ማስረፁም ሆነ በፍጥነት ቅሬታዎችን የመፍታት አሠራር ተግባራዊ አለማድረግ ለውዥንብር አጋልጧል፡፡

  የቀን ገቢ ግምቱ የሚመለከታቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ቢሆንም፣ እንደ ማንኛውም ዜጋ ግብር የመክፈል ግዴታ አለባቸው፡፡ ነገር ግን በገማቾች በኩል የተስተዋለው ወጥ ያልሆነ አሠራር ሌላው የቅሬታ ምንጭ ሆኗል፡፡ በተመሳሳይ የንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ የተለያዩ ግምቶች መቅረባቸው አሠራሩን ለኢፍትሐዊነት አጋልጦታል፡፡ የገማቾች በጥቅም በመደለልና በመመሳጠር የተፈጸሙ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች ምሬቶች ፈጥረዋል፡፡ በስህተት ተጋነው የቀረቡ ግምቶችም እንዲሁ፡፡ በልፋቱ ጥሮ ግሮ የሚኖር ዜጋ ካሰበው ውጪ የተጋነነ ግምት ሲቀርብለትና ከግራና ከቀኝ ደግሞ በማስረጃ ያልተረጋገጡ መረጃዎች ሲዘረገፉለት ለውዥንብር ይጋለጣል፡፡ ከዚህ ይልቅ የቀን ገቢ ግብር ግምቱ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር በመቀራረብ፣ አንድ ግብር ከፋይ መንግሥት የሚፈለግበት ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳየውን የተብራራ ሥሌት ማስረዳት ይቀል ነበር፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን ግብር ከፋዮች እዲደናገጡ፣ ሸቀጦቻቸውን እንዲያሸሹና ግብር ሥወራ ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል፡፡ ውዥንብር ሲፈጠር በርካታ ተከታታይ ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡

  የቀን ገቢ ግምቱ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ ለሚነሱ ቅሬታዎች በአግባቡ መልስ ከመስጠት ጀምሮ ችግር የታየባቸውን አሠራሮች ለማስተካከል ባለመቻሉ ብቻ ውዥንብር ተፈጥሯል፡፡ ሕዝብና መንግሥትን እንደገና የሚያናቁሩ አጋጣሚዎች ታይተዋል፡፡ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተስተዋሉ የንግድ መደብሮችን መዝጋት የተፈጠረውም በዚህ ሳቢያ ነው፡፡ በተለይ በደረጃ ‹‹ሐ›› ውስጥ የሚገኙ አነስተኛ የንግድ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ዜጎች ለአሠራሩ አዲስ እንደ መሆናቸው መጠን፣ በግርድፉ የቀን ገቢ ግምቱ ሲነገራቸው ተደናግጠዋል፡፡ ጥናቱ ይፋ ሲደረግ የግንዛቤ ማስጨበጡ ጉዳይ እንዴት ነው ተብሎ ጥያቄ ሲቀርብ የተሟላ ምላሽ አልነበረም፡፡ እንዲህ ዓይነት የኅብረተሰብ ክፍሎች ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ከመግፋት ወጥተው የበለጠ እንዲሠሩ ማበረታታትና የተሻለ ግብር ከፋይ እንዲሆኑ ማብቃት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ይህንን ኃላፊነትን በአግባቡ ለመወጣት ደግሞ በአሠራሮች ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ መሰናክሎችን በትጋት መለየት ያስፈልጋል፡፡ ኃላፊነት የማይሰማቸው ፈጻሚና አስፈጻሚዎችን ደግሞ ሸንቆጥ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ተጠያቂነት እንዳለም ማሳያ ይሆናል፡፡

  ከዚህ ቀደም ሕዝብ በመንግሥት ላይ የነበረው ቅሬታ ተጠራቅሞ አገርን ለሥጋት የዳረገ ክስተት የተፈጠረው፣ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ ባለመሆኑ ነው፡፡ መንግሥት ራሱ በተደጋጋሚ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዳለበት፣ ሕዝብ ፍትሕ ማግኘት መቸገሩን፣ ሙስና የአገር ጠንቅ መሆኑንና ሌሎች ተዛማጅ ችግሮችን አምኗል፡፡ በርካቶች የሞቱበትና የአገር ሀብት የወደመበት ሁከት ሰከን ካለ በኋላ፣ በታችኛው እርከን ያሉ በርካታ ተሿሚዎች ከኃላፊነት መነሳታቸው ተሰምቷል፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግም ችግሮቹን ለማስወገድ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ውስጥ ገብቷል፡፡ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ቅሬታ ሲያቀርብ በወቅቱ አዳምጦ ፈጣን ምላሽ አለመስጠት ምን ያህል አደጋ እንዳለው ክስተቱ ትልቅ ምስክር ነበር፡፡ አገሪቱን አሁን ድረስ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የዳረገው ሁከት ዳግም ተቀስቅሶ ሌላ ችግር መፈጠር የለበትም፡፡ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ መሠረት አሠራሩን ለሕዝብ ግልጽ የማድረግና  የተጠያቂነት ኃላፊነት አለበት፡፡ አስፈጻሚ አካላትም ቢሆኑ በሕግ በተሰጣቸው ኃላፊነትና ተጠያቂነት ሥራቸውን ማከናወን አለባቸው፡፡ አዲስ አሠራር ተግባራዊ በተደረገ ቁጥር አገርን ቋፍ ውስጥ የሚከት ችግር ለምን ይፈጠራል መባል አለበት፡፡

  የሕግ የበላይነት ማሳያ ከሆኑ ተግባሮች መካከል አንዱ ዜጎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ግብር መክፈል እንዳለባቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ለመሆናቸው አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ግብር ፍትሐዊ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ትልቁ ግብር ከፋይ የሚባለው ከተቀጣሪነት ገቢ ግብር የሚከፍለው ዜጋ ነው፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ የግብር ግዴታን የመወጣት አቅም ተቀጥሮ ከሚሠራው ኃይል ጋር ሲነፃፀር በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ግብርን ፍትሐዊ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ከባድና ብዙ ልፋት የሚፈልግ እንደሆነም ግልጽ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ግብር አስገቢው መሥሪያ ቤት ድርጅታዊ መዋቅሩን ማዘመን፣ የዘመኑን ቴክኖሎጂ መታጠቅ፣ በሠለጠነ የሰው ኃይል መጠናከርና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮን ለመፍታት የሚያስችል አሠራር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ የግብር ሥርዓቱ ፍትሐዊ ሆኖ ከሐሜት የፀዳ እንዲሆንና የሕዝቡን አመኔታ እንዲያገኝ ደግሞ አሠራሩ ግልጽና ተጠያቂነት እንዳለበት ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡ በቀን ገቢ ግምት አፈጻጸም ላይ እንደ ክፍተት ከታዩ ችግሮች መካከል፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ዓመታዊ ሽያጩና የቀን ገቢ ግምቱ ሲነገረው በዓመት የሚከፈለው ቁርጥ ግብር ይህንን ይመስላል አለመባሉ ተጠቃሽ ነው፡፡ ውዥንብሩም ከዚህ ነው የጀመረው፡፡

  በአጠቃላይ ሁሌም እንደምንለው በአሠራር መዝረክረክም ሆነ በአፈጻጸም ድክመት ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮች አገርንና ሕዝብን መጉዳት የለባቸውም፡፡ ሕግ አክብሮ የሚሠራ ዜጋና በሕገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሰውም በአንድ ዓይን መታየት አይኖርባቸውም፡፡ የሕግ የበላይነት ሲከበር ገማቹም ሆነ ተገማቹ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ይወጣሉ፡፡ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለመፈለግ ሲባል ሕገወጥ ድርጊት ሲፈጸም የሚጎዳው ሕዝብ ነው፡፡ ሕዝብ ሲጎዳ ደግሞ ምሬቱ ይጨምራል፡፡ ምሬት ሌላ ምሬት እየወለደ ለአመፅ በር ይከፍታል፡፡ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ሲሆን ደግሞ ለሌላ ዓላማ የሚጠቀሙበት ኃይሎች አገርን የሚያተራምስ ሁከት ይቀሰቅሱበታል፡፡ በሕጋዊ መንገድ መፈታት የሚችል ቅሬታ የሌሎች አጀንዳ ይሆንና አገርን ለማተራመስ በር ይከፍታል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ ያስከፈለው መስዋዕትነት በቅርቡ ታይቷል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ሕዝብን ያዳምጥ፡፡ ቅሬታዎቹን በአስቸኳይ መፍትሔ ይስጣቸው፡፡ ዜጎች በሕግ የበላይነት ብቻ እንዲተማመኑ ይደረግ፡፡ በቀን ገቢ ግምት ላይ የተፈጠረው ውዥንብር ይጥራ!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

  ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

  የአገር ውስጥ የፍራፍሬ ገበያን ፍላጎት ይሸፍናል የተባለለት የብላቴው እርሻ ልማት

  መንግሥት የግብርና ምርታማነትና የፍራፍሬ ምርትን ለማሳደግ በ‹‹አረንጓዴ አሻራ›› በሚል...

  ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ገለጹ

  ‹‹የኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቀናል›› የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ‹‹ጉዳዩ...

  የአገሪቱ ባንኮች ካፒታል 199.1 ቢሊዮን ብር ደረሰ

  ከታክስ በኋላ 50 ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ የአገሪቱ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የክላስተር አደረጃጀት ፖለቲካዊ ውዝግብ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይባል የነበረውን አደረጃጀት...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

  የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ምሥረታና ተጠባቂ ዕድሎቹ

  ነፃ የንግድ ቀጣናዎች የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣናዎች አካል ሲሆኑ፣ በውስጣቸው...

  የቅጥፈት እንጀራ!

  የዛሬው ጉዞ ከሲኤምሲ ወደ መገናኛ ነው። በዚህ በከባዱ የኑሮ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የሥጋት ደመና ተወግዶ ሰላም ይስፈን!

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ የአገሪቱ ክፍል ክልል ለመሆን የፈለጉ የተለያዩ ዞኖች እየተሰባሰቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ ለብቻችን ክልል መሆን አለብን የሚሉ ዞኖችም...

  በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር መሆኑ ይብቃ!

  ኢትዮጵያ የታፈረችና የተከበረች አፍሪካዊት አገር ናት፡፡ ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ነፃነትም ተምሳሌት ናት፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የሚያኮራ ተግባር ፈጽመው ያለፉት፣ ከአገራቸው በፊት የሚቀድም...

  የማንም ሥልጣንና ጥቅም ከኢትዮጵያ አይበልጥም!

  የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁ፣ የኢትዮጵያን የወደፊት ብሩህ ጊዜ አመላካች ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህ የአፍሪካ ታላቅ ግድብ ፕሮጀክት ዕውን...