Tuesday, August 16, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የበላይነት በባህልና በሌሎችም መገለጫዎች ላይ ተፅዕኖ ሊያመጣ ይችላል››

  ወጣት ብርሃኑ ወልደሰንበት፣ የኢንተርናሽናል ትሬድ ሃንድቡክ አዘጋጅ

  ወጣት ብርሃኑ ወልደሰንበት ይባላል፡፡ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ ዲፕሎማ ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ የመጀመሪያ ሥራውን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጀመረው ወጣት ብርሃኑ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በግል ባንኮች በተለያዩ ቅርንጫፎች በተለይ በውጭ ንግድ ዘርፍ (አስመጪና ላኪ) ከአሥር ዓመታት በላይ ሠርቷል፡፡ ወጣቱ በሠራባቸው ዓመታት በአስመጪና ላኪነት ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎች ዘርፉን አጥርቶ ከማወቅ ጋር በተገናኘ ሲቸገሩ በማየቱ፣ መፍትሔ ይሆን ዘንድ International Trade Handbook (ኢንተርናሽናል ትሬድ ሃንድቡክ) የተባለ መጽሐፍ በእንግሊዝኛ አዘጋጅቷል፡፡ በመጽሐፉ ዙሪያ ታምሩ ጽጌ ወጣት ብርሃኑን አነጋግሮታል፡፡

  ሪፖርተር፡- ኢንተርናሽናል ትሬድ ሀንድቡክ በሚል ያሳተምከው መጽሐፍ ለማዘጋጀት ምን አነሳሳህ?

  አቶ ብርሃኑ፡- መጀመሪያ ላይ መጽሐፍ ለመጻፍ አላሰብኩም ነበር፡፡ ወይም የመጽሐፍ ዓላማም አልነበረኝም፡፡ ነገር ግን አንድ ባህሪ አለኝ፡፡ ሁልጊዜ ከምሠራው የሥራ ባህሪ ጋር የሚገናኙ መጻሕፍት ካሉ ማንበብ እወዳለሁ፡፡ ይህ ደግሞ ዝም ብዬ ለማንበብ ሳይሆን፣ አንድ ሥራን ለማሻሻልና ሥራውንም ለማሳደግ ጠቃሚ መንገድ በመሆኑ ነው፡፡ እኔ ሥራ የጀመርኩት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ እንደአጋጣሚ ሆኖ ቀጥታ የሥራ ግንኙነቴ በውጭ ንግድ ማለትም መላክ (ኤክስፖርት) እና ማስመጣት (ኢምፖርት) ላይ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት አንድን የአገር ውስጥ ምርት ወደ ውጪ ለመላክና የውጭ አገሮችን ምርት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ግልጽ የሆነ መመርያ ያስፈልጋል፡፡ በወቅቱ እኔ ያገኘሁት ሁለት ዓይነት መመርያዎችን ብቻ ነው፡፡ አንደኛ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያና ከኢንተርኔት የሚገኙ የተለያዩ ከውጭ ንግድ ጋር የሚገናኙ መጣጥፎችን ብቻ ነው፡፡ ሥራውን የተቀላጠፈ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ለማድረግ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ አሰብኩ፡፡ እሱም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጥናቶችንና መጻሕፍትን መፈለግ፡፡ በዚህም የተነሳ ድረ ገጾችን መፈተሽ ጀመርኩኝ፡፡ በአገራችን የውጭ ንግድን በሚመለከት መንገድ የሚሰጥ ወይም አብራርቶ የሚያስረዳ መጽሐፍ ማግኘት አይቻልም፡፡ በመሆኑም በአማዞን ላይብረሪ በመግባት የውጭ አገር መጻሕፍትን በመፈለግና ከዓለም አቀፍ ንግዱ ጋር ተስማሚ የሚሆኑትን በመውሰድ ለመጽሐፍ ግብዓት ተጠቅሜያለሁ፡፡

  ሪፖርተር፡- መጽሐፉን ለመጻፍ በዋናነት ምክንያት የሆነህ ተመድበህ ትሠራበት የነበረው መላክ (ኤክስፖርት) እና ማስመጣት (ኢምፖርት) የሥራ ዘርፍ ላይ ችግር ገጥሞህ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለህ?

  አቶ ብርሃኑ፡- በሥራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስቸግሩ ነገሮች ነበሩ፡፡ በሥራ ላይ ይገጥሙኝ የነበሩትን ችግሮች መፍታት የሚቻለው ልምድ ካላቸውና በሥራው ላይ ብዙ ጊዜ ካሳለፉ ሰዎች እንጂ በመጻሕፍት ላይ ወይም በሥራ መመርያ ላይ ማግኘት አይቻልም ነበር፡፡ በዘርፉ ላይ ዕውቀት ቢኖርም በተበታተነ ቦታ ላይ ነበር፡፡ ማለትም በዘርፉ ላይ ተሰማርተው ረዥም ዓመታት ካገለገሉ ሰዎች ፈልገህ ወይም በስልክ ንግግር በማድረግ ነበር ያጋጠመህን ችግር መረዳት የምትችለው፡፡ የተዘጋጀና በሥራ ላይ ለሚያጋጥምህ ችግር እንደ መፍቻ ቁልፍ ተደርጎ በመጽሐፍ መልክ የተዘጋጀ ነገር አታገኝም፡፡ ዕውቀቱ ወይም መፍቻ ቁልፉ የሚገኘው በሰዎች አዕምሮ ውስጥ እንጂ፡፡ በሌላ በኩል ሰዎች ልምድ ሊኖራቸው የሚችለው እንደ አጠቃላይ ከተማሩት የትምህርት ዘርፍ በተጨማሪ በሥራ ላይ የሚያገኙት ልምድ ነው፡፡ በውጭ ንግድ ላይ ተሰማርቶ የሚሠራ ሰው ዕውቀቱን የሚያገኘው በሥራ ላይ ከነበሩ ሰዎች ከሆነ፣ የሰው ልጅ ዕውቀት ወይም ልምድ ደግሞ እንደየሰው ሊለያይ ይችላል፡፡ ይህ ማለት ደረጃውን የጠበቀና አንድ መስመር የያዘ ዕውቀት ማግኘት ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት እኔ በሥራ ዘርፉ ላይ እያለሁ የሚያጋጥሙኝን ችግሮች ለመፍታት ‹‹እስከመቼ ነው ሰዎችን እያስቸገርኩ የምኖረው?›› የሚለው ጥያቄ ቀድሞ ከነበረኝ በዘርፉ ያለውን የዕውቀት ችግር ከመፍታት ራዕይ ጋር ተደምሮ በዘርፉ ያሉ መጻሕፍትንና የተለያዩ ግብዓቶች በማንበብ ያገኘኋቸውን ግብዓቶች የመጽሐፌ አካል አድርጌያቸዋለሁ፡፡

  ሪፖርተር፡- በአስመጪና ላኪነት ዘርፍ ላይ የሠሩ ልምድ ያላቸውን ሰዎች ሐሳብና አስተያየት በመጽሐፉ አካተሃል?

  አቶ ብርሃኑ፡- አንዳንድ አስተያየቶችን ለማካተት ሞክሬያለሁ፡፡ የሚገርመው ነገር ልምድ ያላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ስትጠይቃቸው ቁንጽል ነገር ነው የሚሰጡህ፡፡ እኔ ግን ቀን በምሠራበት ወቅት የሚገጥሙኝን የሥራ ላይ ችግሮች ማታ ወደ ቤት ስገባ በማስታወሻ ላይ አሰፍራቸዋለሁ፡፡ አንዳንድ ባለሙያዎች ግን በቅንነት ‹‹ይህ ቢገጥምህ ይህንን አድርግ›› ብለው ዕውቀታቸውን ሳይደብቁ የሚነግሩህና ልምዳቸውን የሚያካፍሉህ አሉ፡፡ እነዚህን ሰዎች እከሌ ከእከሌ ሳልል በጅምላ አመሰግናለሁ፡፡

  ሪፖርተር፡- ሰዎች በአንድ የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው የሚያገኙትን ዕውቀት ወይም ልምድ በቅንነት ለሌላው የማያስተላልፉት ለምን ይመስልሃል?

  አቶ ብርሃኑ፡- እንግዲህ አንዳንዶች ፈቃደኛ የማይሆኑበት ምክንያት ሙሉ ዕውቀት ስለሌላቸው ይመስለኛል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎችም ሆነ በሌላ ቦታዎች ዓለም አቀፍ ንግድ እንደ አንድ ኮርስ የሚሰጥ ቢሆንም፣ በመጻሕፍት የታገዘ አይደለም፡፡ እኔ ይህንን መጽሐፍ ለመጻፍ ያልረገጥኩበት ቦታ የለም፡፡ ምንም ዓይነት የተደራጀ መጽሐፍ ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ከብሔራዊ ባንክ መመርያ ውጪ ለመመርያና ማስተማርያ የሚሆኑ መጻሕፍትን አላገኘሁም፡፡ ይህ ባለመኖሩ በዘርፉ ትንሽ ዕውቀት ያላቸውም ቢሆን ለማስረዳት ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ምናልባት የጻፍኩት መጽሐፍ ይህንን ሁሉ ችግር ይቀርፋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ችግሮች እንዴት መፈታት እንዳለባቸውና አንድ በዘርፉ የተሰማራ ነጋዴ ከጅማሮ እስከ መጨረሻው ምን ማድረግ እንዳለበት መጽሐፉ ምላሽ ይሰጣል፡፡

  ሪፖርተር፡- ዓለም አቀፍ ንግድ ሲካሄድ ዓለም አቀፍ ሕግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሥራ ሲሠራ ችግርም ሊከሰት ስለሚችል፣ ችግሩን መፍቻ መሣሪያ ያስፈልጋል፡፡ መጽሐፍህ እነዚህን ነገሮች አካቷል?

  አቶ ብርሃኑ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ንግድ ሲሠራ ችግር ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ችግሮች ቢገጥሙህ እንዴት ሊፈቱ ይችላሉ? ለሚሉት ጥያቄዎች መፍትሔ የሚሰጡ ዓለም አቀፍ ሕግጋትንም በመጽሐፉ አካትቻለሁ፡፡ እያንዳንዱ በዘርፉ የተሰማራ ምን ዓይነት ፎርማት መከተል እንዳለበት? ችግሮች ቢገጥሙት እንዴትና በምን ሁኔታ መፍታት እንደሚችል በመጽሐፉ ዝርዝር ከመገለጹም በተጨማሪ ምሳሌዎች ተያይዘዋል፡፡ አንድ የውጭ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማራ ሰው አንብቦና ተረድቶ ሊተገብረው በሚችለው ሁኔታ መጽሐፉ በመዘጋጀቱ ጠቀሜታው ሰፋ ያለ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- በዋናነት በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ያጋጥማሉ የሚባሉት ችግሮች ምንድናቸው?

  አቶ ብርሃኑ፡- ችግሩን በሁለት እከፍለዋለሁ፡፡ ገበያን ከማግኘት በፊት የሚያጋጥም ችግርና ገበያው ከተገኘ በኋላ የሚያጋጥም ችግር በሚል፡፡ ከገበያ በፊት የሚያጋጥም ችግር ገበያውን የማፈላለግና የማግኘት ችግር ነው፡፡ እንዴት ገበያውን መፈለግና ማግኘት እንደሚቻል የሚያጋጥም ችግር ነው፡፡ ገበያን በቀላሉ ለማግኘት እንደሚቻል አመላካች ወይም መፈለጊያ ዘዴዎች ባለመኖራቸው የሚያጋጥሙ ችግሮች ናቸው፡፡ የጻፍኩት መጽሐፍ ግን የሚያተኩረው ወደ ገበያው ከተገባ በኋላ ያሉ ሒደቶች ላይ ነው፡፡ አንድ በንግድ ላይ የተሰማራ ሰው ከውጭ አገር ዜጋ ጋር የንግድ ግንኙነት ይፈጥራል፡፡ የኤልሲ፣ የሰነድ ድርድርና የመሳሰሉ ነገሮች ያጋጥሙታል፡፡ እነዚህ የድርድር ዓይነቶች የንግድ ስምምነቶች ምንና ምን ዓይነት እንደሆኑ በመጽሐፉ በደንብ ተገልጿል፡፡ አንድ ሰው በየትኛው በኩል ልደራደር ብሎ ሲያስብ፣ እያንዳንዱን ድርድር የሚያካሂድበት መንገድ በመጽሐፉ ተቀምጧል፡፡ ድርድሮቹ የራሳቸው ጥቅምና ጉዳት አላቸው፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ሒደቶች ችግር እንዳይገጥም በድርድር ወቅት ምን መደረግ እንዳለበት በደንብ የሚያስረዱ ነጥቦች ከመጽሐፉ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፡፡ ከድርድሩ በኋላ በሚደረስ ስምምነት መሠረት በቀጣይ የሚኬደው ወደ ጭነት ስምምነት ነው፡፡ የተጫነው ዕቃ በሚጓጓዝበት ወቅት አደጋ ቢደርስበት የማን ወጪ ነው? የሻጭ ወይስ የገዢ? ይህንንም ችግር እንዴት መፍታት እንደሚቻል፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ መጽሐፉ ምላሽ ይሰጣል፡፡

  ሪፖርተር፡- መጽሐፉ እንደነገርከኝ በተለይ በአስመጭነትና ላኪነት ንግድ ላይ ለተሰማሩ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በሌላው የንግድ ዘርፍ ለተሰማሩትስ?

  አቶ ብርሃኑ፡- አንድ ሰው ወደ ንግድ ለመግባት መጀመሪያ የሚያስፈልገው ዕውቀት ነው፡፡ ቢያንስ ይህን መጽሐፍ ካነበበ በኋላ፣ በውጭ ንግድ ዙሪያ ያለውን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ሊያውቅ ይችላል፡፡፡ እኔም ትኩረት ሰጥቼ በመጽሐፉ ላይ ያሰፈርኩት የሥራው እንቅስቃሴ ላይ ነው፡፡ በሥራው ላይ ያሉት ነጋዴዎች በተለያየ ባለሙያ እየታገዙ ቢሆንም የሚመጣውን አደጋም ለመቀበል ወስነው ነው፡፡ ይህንን መጽሐፍ ቢያነቡት ግን ለእነሱ በቀላሉ አደጋን እንዴት እንደሚቀንሱና ሥራውን በተቀላጠፈ ሁኔታ መሥራት እንደሚችሉ ተጨማሪ ግብዓት ይሆንላቸዋል፡፡ ለጀማሪዎች ደግሞ ተጨባጭ ዕውቀት ይዘው በቀጥታ ሥራቸውን መጀመር እንዲችሉ የሚያስችል ትልቅ መሣሪያ ይሆናቸዋል፡፡

  ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ተቋም (WTO) አባል እንድትሆን ግፊት እየተደረገባት ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ እንደ አገር የሚያስበውና መስተካከል አለበት በሚለው ላይ ገና እየሠራ መሆኑን በመግለጽ ምላሽ እየሰጠ ነው፡፡ በዋናነት በዕውቀት የበለፀጉ አገሮች በአገር ውስጡን ንግድ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ የሚል እምነትም ስላለው ነው፡፡ ያንተ ሥራ ለንግዱ ማኅበረሰብ አስተዋጽኦ በማድረግና ነጋዴውን ማኅበረሰብ ከሌላው ዓለም አቀፍ ነጋዴ ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን ምን ሚና ይኖረዋል? በዚህ ዙሪያ የሚሠሩ ባለሙያዎችን አማክረሃል?

  አቶ ብርሃኑ፡- መጽሐፉን ለመጨረስ ስድስት ዓመታት ፈጅቶብኛል፡፡ በዚህ ዙሪያ የሚሠሩ ባለሙያዎችን ለማግኘትና ለማማከር ዕድሉን አላገኘሁም፡፡ ነገር ግን በመጽሐፉ ውስጥ የተቀመጡ ነጥቦች በሙሉ የዓለም አቀፍ ንግድ እንዴት እንደሚሠራ፣ ጥቅሙ፣ ጉዳቱና የሚያስከትለው ችግር ጭምር የተካተቱበት በመሆኑ የአገር ውስጥ ነጋዴው መጽሐፉን አንብቦና ራሱን በደንብ አዘጋጅቶ ወደ ገበያው ከገባ፣ ተወዳዳሪ የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡ የዓለም አቀፍ ንግድ ተቋም አባል መሆን የሚያስፈልገው በዕውቀትና በልምድ ብልጫ ያላቸው የውጭው ዓለም ንግድ ማኅበረሰብ፣ በአገር ውስጥ የንግድ ማኅበረሰብ ላይ ብልጫ በመውሰድ የበላይነትን ይይዛሉ የሚል ነው፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የበላይነት ደግሞ በባህልና በሌሎችም አገራዊ መገለጫዎች ላይ ተፅዕኖ ሊያመጣ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያም ፍርሃት ከዚህ የዘለለ አይደለም፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ጥሩ የሚሆነው በየዘርፉ የሚዘጋጁ መጻሕፍትን በማንበብና ዕውቀትን በማዳበር ብቁና ተወዳዳሪ መሆን ነው፡፡ የእኔ መጽሐፍ በአንዱ ማለትም በአስመጪና ላኪ የሥራ ዘርፍ ለተሰማሩ ዕውቀትና መረጃ ይሰጣል፡፡ በሌላ በኩልም ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

  በኢትዮጵያ ውስጥ ሞጆ ደረቅ ወደብ፣ መቐለ፣ ኮምቦልቻና ድሬዳዋ ደረቅ ወደቦች ትልቅ የውጭ ንግድ አካል የሆኑ መሥሪያ ቤቶችን ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተጨባጭ ለማስተማር እስካልቻልን ድረስ፣ የውጭ ንግድ አካል መሆናቸውን የሚያውቁበት መንገድ የለም፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች በተጨባጭ የአገራችንን ኤክስፖርትና ኢምፖርት አሠራር ማስተማር የሚችሉ መጻሕፍትን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ መጽሐፌ በተቻለ መጠን ይህንን ግንዛቤ በሚያስጨብጥ መልኩ አድርጌ ነው የጻፍኩት፡፡

  ሪፖርተር፡- መጽሐፉን ስትጽፍ በዘርፉ ለተሰማሩ የንግዱ ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን ዩኒቨርሲቲዎችንም ታሳቢ በማድረግ ጭምር መሆኑን ገልጸሃል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ትምህርቱን የሚሰጡ መምህራንን አነጋግረህ እንደ ግብዓት የተጠቀምክበት ነገር አለ?

  አቶ ብርሃኑ፡- መጽሐፉን በሚመለከት ለማነጋገር የሞከርኩት ሁለት ጫፎችን ይዤ ነው፡፡ አንደኛ ጭራሽ ዕውቀቱ የሌለው ሰው ስለመጽሐፉ አስተያየት እንዲሰጥ አድርጌዋለሁ፡፡ የውጭ ንግድ ዕውቀቱ የሌለው ሰው ይህንን መጽሐፍ አንብቦ የመረዳት ችሎታው ምን ይመስላል? የሚለውን አይቻለሁ፡፡ ሁለተኛው ስለ ውጭ ንግድ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች የሰጡኝን ግብዓት በመጽሐፉ አካትቻለሁ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያሉ መምህራንን ለማናገር ብሞክርም ከምፈልገው ጊዜ ጋር ሊራመድልኝ ባለመቻሉ ሊሳካልኝ አልቻለም፡፡ ነገር ግን ይህ መጽሐፍ የመጀመሪያ ከመሆኑ አንፃር በቀጣይ ሌሎች ግብዓቶችንና አዳዲስ አሠራሮችን ጨምሬ መሥራቴ ስለማይቀር፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን የመጀመሪያዎቹ አስተያየትና ግብዓት ሰጪዎቼ እንደሚሆኑ ከወዲሁ መናገር እፈልጋለሁ፡፡

  ሪፖርተር፡- መጽሐፉን በአገር ውስጥ ቋንቋዎች ተርጉሞ ለማቅረብ ዕቅድ አለህ?

  አቶ ብርሃኑ፡- ከተለያዩ ሰዎች ጋር እየተነጋገርኩ ነው፡፡ በአማርኛና ኦሮምኛ ቋንቋዎች መተርጎም እንዳለበት እየተነጋገርን ነው፡፡ 

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  ለኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸጥበት ታሪፍ ማሻሻያ ተደረገበት

  በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያና የኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል...

  አዲስ አበባ እንዳይገቡ በተከለከሉ ዜጎች ጉዳይ የኦሮሚያና አማራ ክልሎች ተወያይተው ችግሩ እንዲፈታ አደረጉ

  ለሳምንታት በርካታ ቅሬታ ሲነሳበት የነበረውና ከአማራ ክልል በደብረ ብርሃን...

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ‹‹በድርቅ ምክንያት የሚቀርብልን የዕርዳታ ጥሪ ተበራክቷል›› አቶ አብዲሳ መሐመድ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ክፍል ስራ አስኪያጅ

  ኢንተርናሽናል ሪስኪዩ ኮሚቴ (አይአርሲ) በኢትዮጵያ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ድንገተኛ ችግሮች ሲከሰቱ አፋጣኝ መሠረታዊ ሰብዓዊ ድጋፍ በመስጠት ይታወቃል፡፡ በተለይ የዜጎች መፈናቀል፣ የጎርፍ አደጋ፣ የመጠጥ ውኃ...

  የውጭ አገር ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን እንግልት ለመቀነስ

  በኢትዮጵያ የሕክምና አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለ ይታመናል፡፡ በተለይም በሕክምና ስህተት ሕሙማን ለሞት ሲጋለጡ አልያም ደግሞ ለሌላ ስቃይ ሲዳረጉም ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዝቅተኛ...

  አሠሪና ሠራተኛ የሚገናኙበት ዓውደ ርዕይ

  በአዲስ አበባ ከተማ 23 ሚሊዮን ወጣቶች እንደሚኖሩ ከዓመት በፊት ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡ ከዚህ ውስጥ መሥራት የሚችሉ ወይም ዕድሜያቸው ለሥራ የደረሱ 75...