የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይደር አል አባዲ፣ ላለፉት ዘጠኝ ወራት በተካሄደ ወታደራዊ ዘመቻ ነፃ የወጣችውን ሞሱል ከተማ አስመልክቶ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ፡፡ በአይኤስ ቁጥጥር ሥር የነበረችው ሁለተኛዋ የኢራቅ ከተማ ሞሱል ለዘጠኝ ወራት በተካሄደባት ጦርነት የወደመች ስትሆን፣ አይኤስ በቁጥጥሩ ሥር ካዋላት ጊዜ ጀምሮ ቅርሶቿን ሙሉ በሙሉ አውድሟል፡፡
በጦርነቱ ታግተው የነበሩ የሞሱል ነዋሪዎች አሰቃቂ የሚባል ጊዜ አሳልፈው እንደነበር የከሳና የገረጣ ፊታቸው ይናገራል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አል አባዲ ለዓለም በቀጥታ ሥርጭት ባስተላለፉት መልዕክት የሞሱል ጦርነት በሠራዊታቸው ድል መጠናቀቁን፣ አሸባሪው አይኤስ ደግሞ መንኮታኮቱን ተናግረዋል፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት በከተማዋ ያደረሰውን ውድመት በማውገዝ ድሉ በጭካኔ፣ በአሸባሪነትና ሰብዓዊነት በጎደለው ድቅድቅ ጨለማ ላይ የተገኘ ነው ሲሉ ሁኔታውን ገልጸውታል፡፡፡ በምሥሉ ላይ በሞሱል ከተማ የወደመው ኑሪ መስጊድ አጠገብ ታግተው የነበሩ ኢራቃውያን ይታያሉ፡፡ የወደመችውን የሞሱል ከተማ ያዩ ጋዜጠኞች ከተማዋ እንደገና ስለመገንባቷ ጥርጣሬ አለን ብለዋል፡፡